በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን፡፡

በኦሮምያ ክልላዊ መንግሥት በክርስቲያኖች ላይ የተፈጸመውን ጥቃት አስመልክቶ ከማኅበረ ቅዱሳን የተሰጠ ማሳሰቢያ

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ሰሞኑን በኦሮምያ ክልላዊ መንግሥት በሚኖሩ በክርስቲያኖች ላይ የደረሰውን ጥቃት አስመልክቶ ላወጣችው መግለጫ የክልሉ መንግሥት ኮሚኒኬሽን ቢሮ የሰጠውን ማስተባበያ መንግሥት በድጋሚ እንዲያጤነው ለማሳሰብና የማኅበሩን አቋም ማሳወቅ አስፈላጊ ሆኖ በመገኘቱ ማኅበረ ቅዱሳን ይህን ማሳሰቢያ መስጠቱ አስፈላጊ ሆኗል፡፡

ቅድስት ቤተክርስቲያን  በኦርቶዶክሳዊያኑ ላይ ስለደረሰው ጥቃት በመግለጫዋ፡-

‹‹በኦርቶዶክሳዊነታቸው ብቻ በአሠቃቂ መልኩ በገጀራ ተቀሉ፤ በቆንጨራ ተቆራረጡ፤ በጦር ተወግተው በጩቤ ተዘከዘኩ፤ በሜንጫ ተተለተሉ፤ በዱላ ተቀጥቅጠው እና በደንጊያ ተወግረው ተገደሉ፤ አስከሬናቸው በጎዳና እየተጎተተ ሲንገላታ ዋለ፤ ለቀናት በየቦታው ወድቆ የቆየው የሰውነት ክፍላቸው ለከርሠ አራዊት ሲሳይ ሆነ፤ ሴቶች፥ በልጆቻቸው፣ በአባቶቻቸው እና በባሎቻቸው ፊት ተደፈሩ፤ ለዘመናት የደከሙበት ቤት ንብረታቸው፣ በጥናት እና በጥቆማ እየተለየ ከተዘረፈ በኋላ ቀሪው ጋዝ እየተርከፈከፈበት በእሳት እየጋየ ወደመ፤ ብዙዎች ከሞቀ ቀዬአቸው ተፈናቅለው የክረምቱን ጨለማ በቅጽረ ቤተ ክርስቲያን በሚገኙ መቃብር ቤቶች እና አዳራሾች፣ በልዩ ልዩ መንግሥታዊ ተቋማት እንዲሁም፣ በግሰለቦች ቤቶች ተጠልለው ለማሳለፍ ተገደዱ፤ ለአስከፊ ማኅበራዊ እና ሥነ ልቡናዊ ቀውሶች ተዳረጉ›› በማለት እዉነታዉን አቅርባለች::

ሕግና መንግሥት ባለበት አገር የተፈጸመውና የዜጎችን የመኖር ህልውና ለአደጋ ያጋለጠ እኩይ ተግባር  በጆሮ የተሰማ ብቻ ሳይሆን ከቦታው ድረስ በመሔድ የተረጋገጠ  ነው፡፡ እውነቱ ይህ ሆኖ ሳለ በክልሉ ኮሚኒኬሽን ቢሮ በኩል የተሰጠው መግለጫ በጣም አሳዛኝና የደረሰውን ጉዳት ያላገናዘበ ሆኖ አግኝተነዋል፡፡ ማኅበረ ቅዱሳን የአደጋውን መጠን ከተመለከተና በየመጠለያው የሚገኙት ክርስቲያኖች ለከፋ ረሀብ  መጋለጣቸውን ከተገነዘበ በኋላ ለጠቅላይ ሚንስትር ጽ/ቤት፣ ለጸጥታ አካላትና ለየክልሉ ርእሳነ መስተዳድሮች ጉዳት ለደረሰባቸው ወገኖች አስቸኳይ የምግብ እርዳታ ከማድረግ በተጨማሪ ለወደፊቱ ተመሳሳይ ጥቃት እንዳይፈጸምባቸው የሚያሳስቡ ደብዳቤዎችን ጽፏል፡፡ ማኅበረ ቅዱሳን ይህን ያደረገው በወቅቱ የዕለት ምግብ እንኳ ለማድረስ ከመንግሥት መዋቅር የተሻለ አማራጭ አለመኖሩን በመረዳት ነው፡፡ ሆኖም መንግሥት ከቀረቡለት ጥያቄዎች ለአንዱም መልስ አለመሥጠቱ አስገራሚ ሆኖብናል፡፡  እጅግ ከዘገየና አንዳንዶችም ቀየዎቻቸውን እየለቀቁ ወደተለያዩ ቦታዎች ከተሰደዱ በኋላ በክልሉ ርእሰ መስተዳድር የሚመራ ልዑክ ጥቃት ወደ ተፈጸመባቸው አካባቢዎች መጓዙን ከመገናኛ ብዙኃን ተረድተናል፡፡ ቢሆን ግን መንግሥት ዘግይቶም ቢሆን ችግራቸውን በመስማት መልሶ ለማቋቋም የሚያደርገውን ጥረት ዳር የሚያደርስ ከሆነ እናደንቃለን፣ እንደግፋለንም፡፡

ሆኖም የቤተ ክርስቲያናችን አስተዳደር የበላይ አካል የሆነው የመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ቤተ ክህነት ጽ/ቤት ለሰጠው መግለጫ ከኦሮምያ ክልላዊ መንግሥት ኮሚዩኒኬሽን ቢሮ የተሰጠው ምላሽ ችግሩን በአግባቡ ተረድቶ ዘላቂ መፍትሔ ለመስጠት  ያለዉ ቁርጠኝነት አሳስቦናል፡፡  ምክንያቱም የመንግሥት የታችኛው አካል በየጊዜው የሚፈጽማቸው ተግባራት ከበላዩ ካለው የሚያያቸውንና የሚሰማቸውን በመሆኑ ነው፡፡ የመንግሥት ከፍተኛ ባለሥልጣናት ስለተጎዱት ወገኖቻቸው ምንም ዓይነት መግለጫ አለመስጠታቸው፣ የኀዘናቸው ተካፋይ መሆናቸውን አለማሳየታቸው የሚያመለክተው ነገር እንዳለ ሆኖ፤ ኃላፊነት ባለው አካል እንዲህ ዓይነት መግለጫ መስጠቱ አሁንም መንግሥታዊ መዋቅሩ ለወገኖቹ ያላለው አረዳድ እና ለችግሮች የሚሰጠውን መፍትሔ በተወሰነ ደረጃም ቢሆን አመላካች ተደርጎ ሊወሰድ የሚችል በመሆኑ ነው፡፡ እንዲህ ዓይነቱ እውነታውን የመሸፋፈን ድርጊት ወደፊት ተጨማሪ ጥቃት እንዳይከሠት በቁርጠኝነት ሊሠራ መቻሉ ላይ ስጋት አሳድሮብናል፡፡ በሕዝብ ላይ እየደረሰ ያለው ሰቆቃ እንዲቆምና  ሕዝበ ክርስቲያኑን ከአደጋዎች ለመታደግ መንግሥት ተገቢውን ትኩረት ይሰጥ ዘንድ በድጋሜ ጥያቄዎቻችንን  ለማሰማት ተገደናል፡፡

ችግሩ የገዘፈና ጥልቀት ያለው፣ ጥቃቱ የተጠናና የተቀናጀ መሆኑን የሚያሳየው ባለፉት ሁለት ዓመታት ብቻ በየክልሉ በሚኖሩ ክርስቲያኖች ላይ በተለይም በኦሮምያ ክልላዊ መንግሥት ሥር በሚገኙ ክርስቲያኖች ላይ  ሲፈጸም የቆየው ግፍና መከራ ከመቼውም ጊዜ በላይ እየጨመረ መምጣቱ ነዉ፡፡ ጥቃቱ ድርብ መልክ ሊኖረው ቢችልም፤ በክርስቲያኖች ላይ ያነጣጠረና ክርስትናን ከአካባቢው የማጽዳት ዘመቻ አካል መሆኑን ግን ከታሪካዊ ሒደቱና ጥቃቱን ለመፈጸም ከሚመረጡት ስልታዊ ወቅቶችና ሁኔታዎች መረዳት ይቻላል፡፡

ባለፉት ሠላሳ ዓመታት ክርስቲያኖች ለአሰቃቂ ግፍና መከራ የተዳረጉባቸውን ምክንያቶች ስንመረምር የለውጥ እንቅስቃሴን መሠረት ያደረጉ ሆነው እናገኛቸዋለን፡፡ በ1983 የተከሠተውን የመንግሥት ለውጥ የፖለቲካ ትርክት ተከትሎ በ1983 እና 84 ዓ.ም. በሐረርጌና በአሩሲ እጅግ በርካታ ክርስቲያኖች በአሰቃቂ ሁኔታ ተገድለዋል፤ ሀብት ንብረታቸውን ተቀምተዋል፤ እንዲፈናቀሉና እንዲሰደዱ ተደርገዋል፡፡

ከዚያ ጊዜ ጀምሮ በክርስቲያኖች ላይ ተጽዕኖዎች የቀጠሉ ቢሆንም በ1997ዓ.ም. የተካሔደውን ምርጫ ተከትሎ በሀገሪቱ የተፈጠረውን የፖለቲካ ውጥረት ሰበብ አድርጎ ከ1998 – 1999 ዓ.ም. ድረስ በሐረር፣ በአሩሲ፣ በጂማ፣ በኢሉባቦርና በወለጋ በክርስቲያኖች ላይ አሰቃቂ ግድያ፣ መፈናቀል፣ የንብረት ውድመት እንዲሁም የቤተ ክርስቲያን ቃጠሎ ተፈጽሟል፡፡ በ2002 እና 2003 በድጋሜ የምርጫ ወቅትን ጠብቆ በክርስቲያኖች ላይ ጥቃት ተፈጽሞባቸዋል፡፡ ከዚህ በኋላም የጥፋቱ መጠንና ሽፋን ቢለያይም በክርስቲያኖቹ ላይ ያልተቋረጠ ሰቆቃና በደል በተለይ በሐረርጌ፣ በአርሲና በባሌ ሲፈጽም ቆይቷል፡፡

ባለፉት ሁለት ዓመታት የደረሰው ግን እስካሁን ከተፈጸሙት ጥቃቶች በዓይነትም፣ በቦታ ስፋትም የተለየና አሰቃቂ መሆኑን ለመረዳት አያስቸግርም፡፡ ሐምሌ 28 ቀን 2010 ዓ.ም. በሶማሌ ክልል ከተፈጸመው ጥቃት አንሥቶ በተለያዩ የኦሮምያ አካባቢዎች፣ በተወሰኑት የደቡብ ክልል ቦታዎች እጅግ አሰቃቂ ጥቃቶች ሲፈጸሙ ቆይተዋል፡፡ ሐምሌ 11 ቀን 2011 ዓ.ም በሲዳማ ዞን  እንዲሁም በስልጤ ዞን በተከታታይ ከተፈጸሙት ጥቃቶች ውጭ አሰቃቂ ጥቃት የሚደርሰው በኦሮምያ ክልላዊ መንግሥት ውስጥ ነው፡፡ በአዲስ አበባ ዙሪያ በቡራዩና በለገጣፎ ከደረሱት አንሥቶ በዚህ ዓመት ጥቅምት፣ ጥር እና ሰኔ ወር የተፈጸሙት እጅግ አሳዛኝና መጠነ ሰፊ ጥቃቶች በዋናነት ሊጠቀሱ የሚገባቸው ናቸው፡፡

የጥቃቶቹን ተመሳሳይነት ለመረዳት ባለፉት 29 ዓመታት የተፈጸሙትን ጥቃቶች ስንመለከት፡-

 1. ፖለቲካዊ ትኩሳቶችንና የሥልጣን ሽግግሮችን እንደ ሽፋን መጠቀማቸው አንዱ ማሳያ ነው፡፡ ከ1983ቱ የመንግሥት ለውጥ እስከ 1997ዓ.ም ምርጫ፣ ከዚያም በኋላ ምርጫን ተከትሎ ከሚከሠቱ አለመረጋጋቶች አንሥቶ የአርቲስት ሀጫሉን ግድያ ምክንያት በማድረግ እስከተፈጸሙት ጥቃቶች ድረስ እያንዳንዷን ክሥተት እንደ መልካም አጋጣሚ በመውሰድ ክርስቲያኖችን በመግደልና በማፈናቀል አካባቢውን ከክርስቲያኖች የማጽዳት ተግባሮች ሲፈጸሙ ቆይተዋል፡፡ ይህም ለጥቃቱ በቂ ሽፋን ለመስጠት በጥንቃቄ የሚሠራ፣ አስቦበትና አቅዶ የሚፈያስፈጽም አካል መኖሩን የሚጠቁም ነው፡፡
 2. በጥቃቶች ሁሉ የሁሉም ቋንቋ ተናጋሪ ክርስቲያኖች ዒላማ ተደርገዋል፡፡ በድንገት ተቀላቅለው ወይም ክርስቲያኖችን ከሞት ለማትረፍ ገብተው ካልሆነ በስተቀር በሁሉም ጥቃቶች ማለት በሚያስችል መልኩ ከየትኛውም ቋንቋ ተናጋሪ ቢሆኑ ሙስሊሞችና ከኦርቶዶክስ ውጪ የሆኑ ኢትዮጵያውያን ጥቃት አልተፈጸመባቸውም፡፡ ሌሎቹ ጉዳት የደረሰባቸው በሁለት ምክንያት ነው፡፡ አንደኛው በመከላከል ሒደት ወይም የጸጥታ አካላት ችግሩን ለማስቆም ሲሞክሩ ሲሆን፣ ሁለተኛው ተቀላቅለው ተገኝተው ወይም በሻሸመኔ እንደሆነው የክርስቲያኖችን ሕንፃ ሲያቃጥሉ በሕንፃው ተከራይተው ይሠሩ የነበሩ ሲኖሩ ብቻ ነው፡፡ ከዚህ በቀር ዒላማ ተደርገው የተጠቁበት ጥቃት አላጋጠመንም፡፡ ይህም ለዘመናት በፍቅርና በመተጋገዝ የኖረውን ሙስሊምና ክርስቲያን የማይወክል፣ ክርስቲያኖችን የጥቃት ዒላማ አድርጎ የሚንቀሳቀስ አክራሪ ኃይል ሁለቱን ለማጋጨት እየሞከረ መሆኑን ያሳያል፡፡
 3. በብዙዎቹ ጥቃቶች ክርስቲያን ሴቶች ይደፈራሉ፤ በ1983 እና 1984 እና በጂማ አካባቢ በተፈጸሙ ጥቃቶች ሴቶች ተገድደው የደፋሪዎች ሚስት ተደርገዋል፡፡
 4. በአንዳንድ ቦታዎች በደረሱ ጥቃቶች በስም የተጠቀሱ የአክራሪ እስልምና ቡድኖች መኖራቸውን ታዝበናል፡፡ ለምሳሌ በ1983/4 በአሩሲ በደረሰው ጥቃት ጃራ የተባለው እስላማዊ አክራሪ ቡድን እንዳጠቃቸው ክርስቲያኖቹ ተናግረዋል፡፡
 5. በብዙ አካባቢዎች ጥቃት አድራሾች የመንግሥትን መዋቅር ተገን ያደረጉ ተባባሪዎች ስላሏቸው እራሳቸውን ለመከላከል ብቻ ሳይሆን ክርስቲያኖችን በሐሰት ከስሰው በማሳሰር   ተጠቅመውባቸዋል፡፡
 6. በኦሮምያ ክልላዊ መንግሥት የተፈጸመውን ጥቃት የብሔር መልክ ለመስጠት የሞከሩ ቢኖሩም ኦሮምኛ ቋንቋ ተናጋሪ ክርስቲያኖችም ከ1983 ጀምሮ የጥቃቱ ሰለባዎች መሆናቸውን መረዳት ይቻላል፡፡ በጥቅምትና በሰኔ 2012 ዓ.ም. የተፈጸሙ ጥቃቶች ልዩ መገለጫዎች፡-
 • በሁሉም ቦታዎች ጠንካራ ክርስቲያኖችን ዒላማ ያደረጉ ጥቃቶች መሆናቸው፣
 • በክርስቲያኖች ላይ ጥቃት ሲፈጸም የመንግሥት የጸጥታ ኃይሎች ጥቃቱን ለመከላከል አለመሞከራቸው፣
 • በሥልጣን ላይ የሚገኙ አካላት በጥቃቱ ተሳታፊ መሆናቸው የመንግሥትን ሀብትና ንብረት ለጥቃት መጠቀሚያ ለማድረጋቸው፣
 • በብዙዎቹ አካባቢዎች በመንግሥት ላይ የተቀመጡ አካላት የጥፋቱ ተባባሪዎች መሆናቸው፣
 • ጥቃቱ ከተፈጸመ በኋላ ሰበብ እየፈለጉ ከሞተ የተረፉ ክርስቲያኖችን መክሰስ ማሳሰራቸው፣
 • ራሳቸውን ከጥቃት ለመከላከልም ሆነ ሌሎቹን ለማዳን ጥረት ያደርጉ የነበሩትን ሁሉ ለእስር መዳረጋቸው፣

በየአካባቢው የተደጋገሙ እነዚህ ጥቃቶች የሚያመለክቱት ታቅዶባቸውና ታስቦባቸው መፈጸማቸን ቢሆንም አደጋው ከደረሰ በኋላ ደግሞ፡-

 • ለተጎዱት የዕለት ምግብ እንኳ የሚያደርስ ምንም ዓይነት መንግሥታዊ መዋቅር አለመኖሩ፤
 • ተፈናቃዮችን መልሶ ለማቋቋም የሚደረገው መንግሥታዊ ጥረት አጥጋቢ አለመሆኑ፤
 • በተፈጸመው ጥቃት መንግሥት ኀዘኔታውን ያላሳየ፣ የሚሰጣቸው መግለጫዎች ችግሩን ሊያባብሱና ተበዳዩ ክርስቲያን በመንግሥት ላይ የሚኖረውን መተማመን የሚቀንስና ለተጨማሪ ስጋት የሚዳርግ መሆኑ፤ ድርጊቱን ለዓለም ኅብረተሰብ የሚያሳውቁ አካላትን ለማሸማቀቅ መሞከሩ መንግሥትን የጥቃቱ ተባባሪ አስመስሎታል፡፡

ስለዚህም መንግሥት የችግሩን አሳሳቢነትእና ክብደት ተገንዝቦ የዜጎቹን የሕይወት ዋስትና የማስጠበቅ ኃላፊነቱን ሊወጣ ይገባዋል፡፡  የሚከተሉትን ጥያቄዎች በአፋጣኝ በመመለስም በሰቆቃ ውስጥ ለሚገኙ ዜጎቹ አለኝታነቱን ማረጋገጥ እንደሚኖርበት ለማሳሰብ እንፈልጋለን፡፡

በመሆኑም መንግሥት፡-

 1. ከሁሉ አስቀድሞ ድርጊቱን በይፋ እዲያወግዝና ከተጎጂዎች ጎን እንዲቆም፤
 2. በጉዳት ላይ የሚገኙ አካላትን በተገቢው ደረጃ በመጎብኘት የማጽናናት፣ የማረጋጋት እና ተስፋ የመስጠት ተግባር  በመፈጸም የሕይወት ዋስትና እንዲሰጣቸው፤
 3. በረሀብና በችግር ውስጥ ለሚገኙ ወገኖች ጊዜያዊ ርዳታ እንዲያደርግላቸው፤
 4. በጥቃቱ በመንግሥት መዋቅር ላይ የሚገኘ አካላት ተሳታፊ በመሆናቸው ለደረሰው የሕይወትና የንብረት ጥፋት  ተገቢ የሆነ የማስተካከያ ሥራ እንዲሠራ፤
 5. በጥቃቱ እጃቸው ያለበትን አካላት ሁሉ ለሕግ አቅርቦ ለሌሎች አስተማሪ የሚሆን ተመጣጣኝ ቅጣት በማስተላለፍ ፍትሕን እንዲያሰፍን፤
 6. የመንግሥት ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች ከተጎጂ ወገናቸው ይልቅ ለጉዳት አድራሹና ኃላፊነታቸውንን በአግባቡ ላልተወጡ አካላት ጥብቅና የቆሙ ከሚያስመስል ድርጊታቸው እንዲታቀቡትና ጉዳት የደረሰባቸውን ክርስቲያኖች ኀዘን የሚጨምሩና ተስፋ የሚያስቆርጡ መግለጫዎችን ከመስጠት እንዲታቀቡ እናሳስባለን፡፡

ባጠቃላይም ማኅበረ ቅዱሳን ጥፋቱ ቀጣይነት ይኖረዋል የሚል ስጋት ስላለው በመንግሥት በኩል ጠንካራ አቋምና ዝግጅት ሊኖር እንደሚገባ ያሳስባል። በመሆኑም ካሁን በኋላ ተጨማሪ ጥፋት እንዳይደርስ መንግሥት ችግሩን በመገንዘብ የተጀመሩ በጎ ተግባራትን በማጠናከር መልሶ የማቋቋም፣ የጥበቃና የሕይወት ዋስትና የመስጠት ተግባሩን እንዲያጠናክር በአክብሮት እየጠየቅን። ወገኖቻችንን መልሶ ለማቋቋምም ሆነ በሚያስፈልገው ሁሉ ድጋፋችንን  ለመስጠት ዝግጁ መሆናችንን እንገልጣለን፡፡

ነገር ግን መንግሥት እንደእስካሁኑ ሁሉ ችግሩን በቸልታ የሚያልፈውና የዜጎቹን መብት ለማስከበር የሚጠበቅበትን ኃላፊነት የማይወጣ ከሆነ ኦርቶዶክሳውያን  ክርስቲያኖችን በዓላማ ለመጉዳት አሳልፎ እንደሰጠን፣ ኦርቶዶክሳውያን ሁሉ ራሳችንን ከአደጋ ለመከላከል ሌላ አማራጭ እንድንጠቀም መንግሥታዊ ግፊት እየተደረገብን መሆኑን እንድናምን ሊያደረገን እንደሚችል  ለመግለጽ እንወዳለን፡፡

ረድኤተ እግዚአብሔር አይለየን

ጳጉሜን ፪ ቀን ፳፻፲፪ ዓ.ም.