በኢትየጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ላይ እየደረሰ ያለውን ወቅታዊ ችግር አስመልክቶ ከቅዱስ ሲኖዶስ የተሰጠ መግለጫ

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ቅዱስ ሲኖዶስ በቤተ ክርሰቲያኒቱና በምእመናን ላይ እየደረሰ ያለውን ችግር አስመልክቶ ከየካቲት 9-11 2012 ዓ.ም. ድረስ ለሦስት ተከታታይ ቀናት ባደረገው አስቸኳይ ስብሰባ በቤተ ክርስቲያናችን፣ በተለያዩ ገደማትና አብያተ ክርስቲያናት እንዲሁም የቤተ ክርስቲያንናችን ተከታይ የሆኑ ምእመናን ላይ እየደረሰ ያለውን ችግር አስመልክቶ በመነጋገር እና ውሳኔ በማሳለፍ የሚከተለውን መግለጫ አውጥቷል፡፡

 1. በቦሌ ክፍለ ከተማ ወረዳ 4 እና 5 በቀድሞው ቀበሌ 24/18/16 እና 15 ነዋሪዎች ለቅዱስ ሲኖዶስ ባቀረቡት አቤቱታ እንደተገለጸው በ24/5/2012 ዓ.ም. ለ25 አጥቢያ በውድቅት ሌሊት በቦሌ ቅዱስ ገብርኤል እና ቅድስት አርሴማ ቤተ ክርስቲያን በርካታ የሆኑ ምእመናን በምሕላና በጸሎት ላይ እያሉ በተኩስና አስለቃሽ የመርዝ ጋዝ ጭስ በመጠቀም በጥይትና በዱላ በርካታ ሰዎች ላይ የአካል ጉዳት መድረሱ ሁለት የቤተ ክርስቲያናችን አማንያን ወጣቶች መገደላቸውን ቤተ ክርስቲያኑ ፈርሶ ክቡር የሆነውን በአባቶች ተባርኮ የነበረው የቃል ኪዳን ጽላት መወሰዱ፣ የቤተ ክርስቲያኑ ንዋያተ ቅዱሳት መዘረፋቸውን የሰማው የቅዱስ ሲኖዶስ ምልዓተ ጉባኤ በድርጊቱ እጅግ ከማዘኑም በላይ ይህን ክፉና ጭካኔ የተመላበት ድርጊት አውግዘዋል፡፡ በቤተ ክርስቲያናችንም ላይ እንዲህ ዓይነት ክፉ ድርጊት የፈጸሙ አካላት ላይ መንግሥት ጥብቅ ምርመራ በማድረግ ወንጀለኞችን ለፍርድ እንዲቀርቡና ውጤቱ ለምእመናኖቻችን እንዲገለጽ እንጠይቃለን፡፡

 1. የቤተ ክርስቲያኒቱን ቦታ በተመለከተ ቤተ ክርስቲያናችን ከአራት ዓመታት በፊት ጀምሮ ቦታው ለአካባቢው ምእመናን ማምለኪያ እንዲሆን ከመንግሥት በመነጋገርና በመጻጻፍ የቆየችበት ከታቦት ሕጉ ጀምሮ ንዋያተ ቅዱሳት የከበሩት ከመሆኑም ባሻገር ሁለቱ የቤተ ክርስቲያናችን አማንያን ወጣቶች በግፍ ጨለማን ተገን ባደረጉ የመንግሥት ፀጥታ አስከባሪዎች ደማቸው የፈሰሰበትና ሕይወታቸው ያለፈበት ቅዱስ ቦታ እንደመሆኑ መጠን ወደ ቀደመ ክብሩ ተመልሶ ሕንጻ ቤተ ክርስቲያን ተሠርቶ ምእመናን በሰላም በመንገድ አምልኮአቸውን እንዲፈጽሙ የሚመለከተው የመንግሥት አካል የበኩልን መመሪያ እንዲሰጥልን ቅዱስ ሲኖዶስ ይጠይቃል፡፡

 1. ይህ ደም የማፍሰስና ሕይወትን የማጥፋት ተልዕኮ አልበቃ ብሎ በየምክንያቱ የታሠሩ ካህናትና ምእመናን ወጣቶች ጭምር በእስር ላይ መሆናቸን ስለሚታወቅ ያለምንም ቅድመ ሁኔታ ከእስራት እንዲፈቱ እንዲደረግ ቅዱስ ሲኖዶስ አጥብቆ ይጠይቃል፡፡

 1. ሀ. ከቤተ ክርስቲያኒቱ ሕግና ደንብ ውጭ በመነሳሳት የኦሮሚያ ቤተ ክህነት ጽሕፈት ቤት እናቋቁማለን በማለት በሕገወጥ መንገድ የሚንቀሳሰቀሱ እንዲሁም በቅዱስ ሲኖዶስ ተባርኮ ጽላት ተሰጥቶናል በሚል በምድረ አሜሪካ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ስም ቤተ ክርስቲያን አቋቁመናል የሚሉት፡-

 1. ሊቀ አእላፍ ቀሲስ በላይ መኮንን
 2. አባ ገብረ ማርያም ነጋሳ
 3. መምህር ኃይለ ሚካኤል
 4. ቄስ በዳሳ ቶላ

እነዚህ ግለሰቦች ቤተ ክርስቲያናችን በማታውቀው መንገድ በአመጽ በመነሳሳት ምእመናንን ግራ እያገቡና እያሳሳቱ መሆኑን እንዲሁም ከኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን አስተምሮ ውጭ የክህደት ትምህርት ማስተማራቸው በመረጃ ተደግፎ ለቅዱስ ሲኖዶስ ጉባኤ የቀረበ በመሆኑ እነዚሁ ከላይ ስማቸው የተጠቀሰ የኦሮሚያ ቤተ ክህነት አደራጆች ነን የሚሉ ከድርጊታቸው ተቆጥበው በንስሐ እስኪመለሱ ድረስ ከየካቲት 11 ቀን 2012 ዓ.ም. ጀምሮ ከቤተ ክርስቲያናችን የተሰጣቸው ክህነት ተይዟል፡፡ በቤተ ክርስቲያናችን ስም ምንም ዓይነት እንቅስቃሴ እንዳያዳረጉና መንፈሳዊ አገልግሎት እንዳይሰጡ ታግደዋል፡፡ ግለሰቦች ከጥፋት ድርጊታቸው ተጸጽተው ለመመለስ ከፈቀዱ ጉዳያቸው በድጋሚ እንዲታይ ቅዱስ ሲኖዶስ ወስኗል፡፡

  ለ. እነዚሁ ካህናት ነን የሚሉ ግለሰቦች ቅዱስ ሲኖዶስ ተባርኮ የተሰጠን ጽላት አለ በሚል ምእመናን እያደናረጉ ቢሆንም እንደ ቤተ ክርስቲያናችን  ሥርዓትና ደንብ መሠረት ጽላት እንዲሰጣቸው ያልጠየቁ ከቤተ ክርስቲያናችንም የሰጣቸውም አካል አለመኖሩ በጉባኤው የተረጋገጠ በመሆኑ ምእመናን ከእንደዚህ ዓይነት ተሳስተው ከሚያስስቱ ግለሰቦች ራሳቸውን ሃይማኖታቸውንና የቤተ ክርስቲያን ሥርዓታቸውን ከምንጊዜውም በላይ እንዲጠብቁ ጉባኤው አሳስቧል፡፡

 1. በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያናችን በርካታ ቅዱሳንና መናንያን ለአገርና ለወገን የሚጸልዮባቸው ታላላቅ ገዳማት እንዳሏት ይታወቃል፡፡ ሆኖም ከጥቂት ዓመታት ወዲህ በአንዳንዱ ገዳማት ላይ ግለሰቦች እየደረሰ ያለው ፈተናና ችግር ያለ መሆኑን ሲታወቅ በተለይም በአሁኑ ጊዜ፡-

ሀ. በምሥራቅ ሸዋ ሀገረ ስብከት በሊበን ዝቋላ ወረዳ የሚገኘው የዝቋላ ደብረ ከዋክብት አቡነ ገብረ መንፈስ ቅዱስ ገዳም፤

ለ. በሰላሌ ሀገረ ስብከት በታላቁ ደብረ ሊባኖስ ገዳም ሆን ተብሎ በአንዳንድ ግለሰቦችና ቡድኖች አማካኝነት እየደረሰ ያለው ችግር እና ታሪክን የማጠልሸት ሂደታቸው በአስቸኳይ እንዲቆም የሚመለከተውም መንግሥት አካል ለጉዳዩ ትኩረት ሰጥቶ ችግር ፈጣሪዎችን እንዲያስቆም ለገዳማቱም አገር ቅርስ እንደመሆናቸው ሁሉ አስፈላጊውን ጥበቃ እንዲያደርግ ቅዱስ ሲኖዶስ የወሰነውን ውሳኔ መንግሥት እንዲያስፈጽምልን እንጠይቃለን፡፡

 1. በአረብ ኤምሬቶችና በዱባይ በስደት የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ክርስቲያን ወገኖቻችን ከፈጣሪያቸው ጋር የሚገናኙበት እግዚአብሔርን የሚያመልኩበት ቤተ ክርስቲያን ለመስራት የአገሪቱ መንግሥት ከቤተ ክርስቲያናችን የቦታ ጥያቄ እየቀረበለት ምላሽ ሳናገኝ እስከአሁን ቆይተን ነበር፡፡

በአሁኑ ጊዜ ግን የአገራችን ጠቅላይ ሚኒስቴር ዶ/ዐቢይ አህመድ በአረብ ኤምሬቶች ባደረጉት የሥራ ጉብኝት በዚያ የሚገኙ ኢትዮጵያውያን ዜጎቻቸውን ከማነጋገርና ከማጽናናት ባሻገር ከአገሩቱ መንግሥት ጋር በመነጋገር ለክርስቲያን ወገኖቻቸውን የማምለኪያ ቤተ ክርስቲያን ቦታ በማስፈቀዳቸው ከዚህም ጋር በዐረቡ ዓለም በስደት ይኖሩ የነበሩ ኢትዮጵያውያን ወገኖቻችን ከስደት እንዲመለሱና ለአገራቸው እንዲበቁ በማድረጋቸው ስደተኛ የሆኑ ክርስቲያን ወገኖቻችን በእጅጉ ያስደሰተና ቤተ ክርስቲያናችንም ሐዋርያዊ ተልዕኮዋን እንድታስፋፋ የሚያግዝ በመሆኑ የቅዱስ ሲኖዶስ ምልዓተ ጉባኤ በእጅጉ ከመደሰቱም በላይ ጠቅላይ ሚኒስቴር ዶ/ዐቢይ አህመድ ወደዚህ አገራዊ መንበር ሥልጣን ከተጠሩበት ጊዜ ጀምሮ የቤተ ክርስቲያናችንን ጉዳይ ጉዳያቸው አድረገው እየፈጸሙት ያለ አኩሪ መንፈሰዊ ተግባር ሁኖ ስላገኘው የቅዱስ ሲኖዶስ ምልዓተ ጉባኤ የከበረ ምስጋናውን አቅርቧል፡፡

 1. በኢትዮጵያ ብሮድካስት ባለሥልጣን፡-

በ OMN

በ LTV

በ OBS

ቴሌቭዥን ጣቢያዎች ከጥቂት ጊዜያት ወዲህ በጥንታዊትና ሐዋርያዊት በሆነችው ለአገርና ለወገን ባላውለታና ባለታሪክ በሆነቸው ቤተ ክርስቲያናችን የከፈቱት የስም ማጥፋት ዘመቻ ማካሄዳቸውን ታሪክን እያበለሻ የተሳሳተ መረጃ ለሕዝብ ማስተላለፋቸው ከዚህም ከ60 ሚሊዮን ያላነሰ ተከታይ ያላትን ቤተ ክርስቲያን ክብሯንና ልዕልናዋን ዝቅ ባደረገ መልኩ የሚያስተላልፉት የተሳሳተ መረጃ   ቤተ ክርስቲያኒቱ ላይ ብቻ ሳይሆን አገራዊ ቀውስ ለማምጣት እየተደረገ ያለ ጥረት በመሆኑ የሚመለከተው የመንግሥት አካል አስፈላጊውን ማጣራት በማድረግ የጣቢያዎቹ ኃላፊዎች ከብዙኃን መገናኛ ሕግ እና ደንብ አኳያ በሕግ እንዲጠየቁ ለወደፊቱም ከእንዲህ ዓይነት ሕገወጥ ድርጊት እንዲታቀቡ መንግሥትም በዚሁ ላይ አስፈላጊውን ውሳኔ እንዲያሳልፍልን ቅዱስ ሲኖዶስ ጠይቋል፡፡

የቅዱስ ሲኖዶስ ምልዓተ ጉባኤ ከየካቲት 9-11 ቀን 2012 ዓ.ም. ድረስ ከ3 ተከታታይ ቀናት ባደረገው አስቸኳይ ስብሰባ ከዚህ በላይ በተለገፁት ነጥቦች ላይ ከመከረና ውሳኔ ካሳለፈ በኋላ በኢትዮጵያ አገራችን በመንግሥታና በሕዝቡ ጭምር እየተከናወኑ ያሉ ተግባራት ማለትም ሕዝባዊ አንድነት እንዲጎለብት፣ ማኅበራዊና ልማታዊ ተግባራት እንዲፋጠኑ፣ በአጠቃላይ በአገራችን ሰላምና አንድነት ሰፍኖ አገራችን ኢትዮጵያ መላው ዜጋ ከሚመኝላት የእድገት ጫፍ እንድትደርስ እንደ አንድ ልብ መካሪና እንደ አንድ ቃል ተናጋሪ ሆኖ ለአገሩና ለሕዝባዊ አንድነቱ ፀንቶ እንዲቆም የቅዱስ ሲኖዶስ ምልዓተ ጉባኤ ጥሪውን በማስተላለፍ ጉባኤውን በዛሬው ዕለት በጸሎት ዘግቷል፡፡

እግዚአብሔርን አገራችንን ኢትዮጵያን ይባርክ

ቤተ ክርስቲያናችን ይጠብቅ

ለሕዝባችንም አንድነቱንና ሰላሙን ይስጥልን

አሜን

አባ ማትያስ ቀዳማዊ

ቀዳማዊ ፓትርያርክ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ

ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም ወእጨጌ ዘመንበረ ተክለ ሃይማኖት

የካቲት 11 ቀን 2012 ዓ.ም.

አዲስ አበባ ኢትዮጵያ