በቤተ ክርስቲያን ውስጥ የሚታየውን የአሠራር ብልሹነት ማሰወገድ እንደሚገባ ተገለጸ

ሰኔ 6 ቀን 2005 ዓ.ም.

በትዕግሥት ታፈረ

በቤተ ክርስቲያን አስተዳደር ውስጥ የሚታየውን የአሠራር ብልሹነት ማሰወገድ እንደሚገባ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ቀዳማዊ ፓትርያርክ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም ወእጨጌ ዘመንበረ ተክለ ሃይማኖትና ብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት ገለጹ፡፡

ቅዱስነታቸው ይህንን የገለጹት በግንቦቱ ርክበ ካህናት የቅዱስ ሲኖዶስ ምልዓተ ጉባኤ ባስተላለፈው ውሳኔ መሠረት የጠቅላይ ቤተ ክህነት ዋና ሥራ አስኪያጅ፤ የቅዱስ ሲኖዶስ ዋና ጸሐፊ፤ እንዲሁም የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ሆነው የተመረጡት ብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት ከጠቅላይ ቤተ ክህነት ሓላፊዎችና ሠራተኞች ጋር ሰኔ 4 ቀን 2005 ዓ.ም. የትውውቅ መርሐ ግብር በተካሄደበት ወቅት ነው፡፡

የጠቅላይ ቤተ ክህነት ዋና ሥራ አስኪያጅ ሆነው የተመረጡት ብፁዕ አቡነ ማቴዎስ የወላይታና ዳውሮ አህጉረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ በትውውቅ መርሐ ግብሩ ላይ ቤተ ክርስቲያንን ለማገልገል የሁሉም እገዛ እንደሚያስፈልግ የገለጹ ሲሆን “ለቤተ ክርስቲያናችን ተልእኮ ከተመረጥንና እንድናገለግል ከተጠራን አገልግሎታችን የተሻለ መሆን አለበት፡፡ የሚያዘን ሥርዓታችን፤ ፍቅራችንና ሕጋችን እንጂ ሥልጣናችን ሊሆን አይገባም፡፡ ሥልጣናችን የሚያዘን ከሆነ ሥራችን ሙሉ ሊሆን አይችልም፡፡ ትክክለኛ መሪን ማንም አይጠላም፤ መሪዎችን ተመሪዎች የሚጠሏቸው ከቆሙለት ዓላማና ተግባር ውጪ በአምባገነንነት፤ በጉቦኝነት፤ በዘረኝነት፤ በአድሏዊነት ሱስ ሲጠመዱ ተመሪዎች ያኮርፋሉ፤ ይጨነቃሉ፤ ማንንም ስለማያምኑ እንደ ቃየል ጥላቸው ያስደነግጣቸዋል፡፡  ስለዚህ ሀሰትን የምትጠየፉ፤ አሉባልታን የምትንቁ፤ ሥራን የምትወዱ፤ ሰላምን የምትናፍቁ፤ ፍቅር የምትላበሱ መሆን አለባችሁ፡፡ ወደፊት አብረን ስለምንጓዝ  እግዚአብሔር እንዲረዳን ቅድሰት ቤተ ክርስቲያናችንን አሳድገን እኛም ተረድተን ሌሎችን እንድንረዳ ያስፈልጋል” ብለዋል፡፡

በቅዱስ ሲኖዶስ ምልዓተ ጉባኤ የቅዱስ ሲኖዶስ ጸሓፊ ሆነው የተመረጡት ብፁዕ አቡነ ሉቃስ የሰቲት ሑመራ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ በበኩላቸው ባደረጉት ንግግር “መሰባሰባችን መልካም ነው፡፡ ሁላችንም ግዴታችንን ከተወጣን ያለው ችግር ይወገዳል፡፡ በእውነተኞች ሰዎች ቸርነትና በጎነት አገር ትቀናለች፡፡ አገር ስትቀና ሰው ሁሉ በሰላም ይኖራል፡፡በኅብረት ሆነን ዘመኑን በመዋጀትና በመገምገም በትክክል ሥራችንን ከሠራን ይቃናልናል፡፡” በማለት ተናግረዋል፡፡

የጠቅላይ ቤተ ክህነት አስተዳደርና ሠራተኞች እንዲሁም የተለያዩ የቤተ ክርስቲያኒቱ አካላት ሠራተኞች ችግሮች ናቸው ያሏቸውን አሳቦች ያቀረቡ ሲሆን በቤተ ክርስቲያን ውስጥ ወጥ የሆነ የአሠራር ዘዴ ያለመኖር፤ አለቆች በተለዋወጡ ቁጥር በሚመጣው ሰው ላይ ሠራተኛው ለመንጠልጠል የራሱን ዘዴ መቀየስ፤ በአሠራር ሥርዓቱ ሁሉም ሠራተኛ እኩል መመራት ያለመቻል፤ ሹማምንትን በመፍራት፤ በመስገድና በመሽቆጥቆጥ አማላጅ በመላክ የተሻለ ሥራ ለማግኘት ጥረት ማድረግ፤ ወዘተ. . . የሚሉት በሠራተኞቹ የተጠቀሱ ሲሆን ይህ አካሄድ በአስተዳደርና በስብከተ ወንጌል ተልእኮ ስኬታማ ጉዞ ላይ አሉታዊ ተጽእኖ እንደሚፈጥር በመግለጽ የአሠራር ዘዴ /System/ መዘርጋት እንዳለበት ጠቁመዋል፡፡

ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ቀዳማዊ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም ወእጨጌ ዘመንበረ ተክለ ሃይማኖት በሰጡት ቃለ ምእዳን “ቤተ ክርስቲያናችን ከጥንታዊያንና ከታሪካዊያን የዓለም አብያተ ክርስቲያናት አንዷና አንጋፋዋ መሆኗ የተረጋገጠላት ናት፡፡ ይህ ሊሆን የቻለው አባቶቻችን ከጌታችን መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ፤ ከሐዋርያትና  ከሊቃውንቱ ተረክበው ሕልውናዋንና ክብሯን ጠብቀው ስላስተላለፉልን ነው፡፡ እኛም ለሚቀጥለው ትውልድ ለማስተላለፍ ትልቅ ሓላፊነት ይጠብቀናል፡፡ ስለዚህ ጥንተ ቅድስናዋን፤ ንጽሕናዋንና ታሪኳን መመለስ አለብን፡፡ ቤተ ክርስቲያናችን በሃይማኖት እንከን የላትም፡፡ በአሁኑ ወቅት በአስተዳደር ጤነኛ አይደለችም፤ ብዙ ብልሹነት ይታያል፡፡ ለቤተ ክርስቲያናችን የማይስማሙ ነገሮች ወደ ቤተ ክርስቲያናችን ገብተው መንገዳችንን እያበላሹብን ነው፡፡ ሙስና፤ ዘረኝነትና ሌሎችም ክፉ ነገሮች ይታያሉ፡፡ ቤተ ክርስቲያናችን የመልካም ሥራ መሪ እንድትሆን እንፈልጋለን፡፡ አስተማሪ እንጂ ተማሪ መሆን የለባትም፡፡ ሓላፊነት፤ ተጠያቂነት፤ እውነተኛነት፤ ሃቀኝነትና የሕግ የበላይነት የሰፈነባት መሆን ይገባታል፡፡” ብለዋል፡፡