በማኅበረ ቅዱሳን ላይ የተሠሩ የሐሰት ሰነዶችን አስመልክቶ ከማኅበሩ ሕዝብ ግንኙነት አገልግሎት የተሰጠ መግለጫ፡፡

በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን!

በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን በሰንበት ት/ቤቶች ማ/መምሪያ ሥር ተዋቅሮ በርካታ መንፈሳዊና ማኅበራዊ አገልግሎቶችን ለቤተ ክርስቲያን በማበርከት ላይ የሚገኘው ማኅበረ ቅዱሳን በቅዱስ ሲኖዶስ በተሰጠው መተዳደሪያ ደንብ መሠረት በመመራት ሕጋዊ በሆነ መንገድ አገልግሎቱን በመስጠት ላይ የሚገኝ ማኅበር ነው፡፡

ይሁን እንጂ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያንን ዕድገትና ልማት የማይፈልጉ አፅራረ ቤተ ክርስቲያን የማኅበሩን መልካም ስም በማጥፋት አገልግሎቱን ለማሰናከል በየጊዜው ይጥራሉ፡፡ በተለይም ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የማኅበሩን ስም ለማጥፋት አመች ነው ብለው ያሰቡትን የሐሰት ሰነድ የማዘጋጀት ተግባራቸውን አጠናክረው ቀጥለዋል፡፡ ከዚህ በፊት በስምዐ ጽድቅ ጋዜጣ የግንቦት ወር ልዩ ዕትም “የማኅበረ ቅዱሳን የ25 ዓመት ዕቅድ” ብለው ያዘጋጁትን የሐሰት ሰነድ አስመልክተን እንደገለጽነው ሁሉ አሁንም ሁለት የሐሰት ደብዳቤዎች በማኅበሩ የመቀሌ ማዕከል ስም ተዘጋጅተው በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን በሰንበት ት/ቤቶች ማ/መምሪያ መካነ ድር ተለቅቀዋል፡፡

እጅግ በጣም የሚያሳዝነው የሐሰት ሰነዶቹ መዘጋጀት ሳይሆን እነዚህ በከባድ ወንጀል ሊያስጠይቁ የሚችሉ የተጭበረበሩ ሰነዶች የቤተ ክርስቲያኒቱ መምሪያ ነኝ በሚል ተቋም መካነ ድር ላይ መለቀቃቸው ነው፡፡

ከሐሰት ሰነዶቹ መካከል አንዱ የተሐድሶ መናፍቃንን ዝርዝር የሚገልጽ ሲሆን ሁለተኛው ደግሞ የመቀሌ ማዕከል የሒሳብ ሪፖርት አስቸጋሪ መሆኑን ይገልጻል፡፡

ማኅበረ ቅዱሳን ይህንን የሐሰት ሰነድ አስመልክቶ ድርጊቱ እንዲጣራና ሕጋዊ እርምጃ እንዲወሰድ ለቅዱስ ሲኖዶስ፣ ለመንበረ ፓትርያርክና ለሚመለከታቸው ሁሉ የሚያቀርብ ሲሆን በሐሰት ሰነዶቹ ስማቸው የተነሱ አካላትም ድርጊቱ የማኅበሩ አለመሆኑን እንዲያውቁና ምዕመናንንም እውነቱን እንዲረዱ ይህ መግለጫ ተሰጥቷል፡፡

በሰንበት ትምህርት ቤቶች ማደራጃ መምሪያ መካነ ድር የተለቀቁት ሁለቱም የሐሰት ሰነዶች በቁጥር መቀጽቤ 99/2003 ዓ.ም እና መቀጽቤ 100/2003 ዓ.ም “ለማኅበረ ቅዱሳን የሕዝብ ግንኙነት አገልግሎት ክፍል” በሚል አድራሻ የተላኩ ናቸው፡፡

ነገር ግን ከመቀሌ ማዕከል መዝገብ ቤት ቀሪ ሆነው የተገኙት እውነተኞቹ ደብዳቤዎች በማኅበረ ቅዱሳን የመቀሌ ማዕከል በቁጥር መቀጽቤ 99/2003 ዓ.ም እና በቁጥር መቀጽቤ 100/2003 ዓ.ም በቀን 05/09/2003 ዓ.ም በማዕከሉ የሰባኬ ወንጌልነት ተቀጥረው ሲያገለግሉ ለነበሩ /አሁን የIT ምሩቅ ናቸው/ ግለሰብ የሥራ ስንብትና የሥራ ልምድ መስጠትን የሚመለከቱ ናቸው፡፡ መመልከት እንደሚቻለው የሐሰት ሰነዶቹም ሆነ  እውነተኞቹ ደብዳቤዎች ቁጥራቸው ተመሳሳይ ነው።

በቀጣይነትም በሰነዶቹ ላይ ማጭበርበሩ የተደረገው በማዕከሉ መዝገብ ቤት ከተገኙት ደብዳቤዎች ሳይሆን ምን አልባትም ከባለጉዳዩ እጅ ከወጡት ደብዳቤዎች ሊሆን እንደሚችልም አንባቢ ያስተውል፡፡ ምክንያቱም የማኅተሞቹና የፊርማዎቹ አቀማመጥ ተመሳሳይነት የላቸውምና አልተጭበረበሩም ብለን እንዳናስብ ያደርገናልና፡፡

ወደ ዝርዝር ጉዳዮቹ ስንገባ ደግሞ፣

1. በአድራሻው ላይ የተጠቀሰው የማኅበረ ቅዱሳን የሕዝብ ግንኙነት አገልግሎት እንደ ክፍል ያልተዋቀረ እንደሆነ ይታወቃል። በአድራሻው የሚመጡለት ደንዳቤዎችም “ለማኅበረ ቅዱሳን የሕዝብ አገልግሎት” ተብለው ይደርሱታል እንጅ “ለማኅበረ ቅዱሳን የሕዝብ ግንኙነት አገልግሎት ክፍል” ተብሎ በአድራሻ አይጠራም። ከዚህ በፊት በመካነ ድራችን የተለቀቁትንና በአገልግሎቱ እየወጡ የሚታተሙትን የመጽሔተ ተልዕኮ መጽሔቶችንም መመልከት ይቻላል።

2. በቁጥር መቀጽቤ 99/2003 ዓ.ም የተጻፈው የሐሰት ሰነድ “በቀን 17/07/2003 ዓ.ም በቁጥር አአ/ልዩ/05/2003 ዓ.ም 11 ገጽ አባሪ አድርጋችሁ በጻፋችሁልን ደብዳቤ ተንተርሰን የሰራነው ሥራ…” ብሎ ከማኅበረ ቅዱሳን ዋናው ማዕከል ጽ/ቤት ለመቀሌ ማዕከል የተላከ ለማስመሰል ይሞክራል፡፡ ነገር ግን በማኅበረ ቅዱሳን ስም የሚወጡት ማናቸውም ደብዳቤዎች ቁጥራቸው ማቅ በማለት የሚጀመሩ ናቸው። በተጨማሪም የማኅበሩ ዋናው ማዕከል ጽ/ቤት ለመቀሌ ማዕከል ልኮታል ተብሎ የተጠቀሰው ደብዳቤ የተጻፈበትን ቀን ስንመለከት፤ 17/07/2003 ዓ.ም የዋለው ቅዳሜ ዕለት ሲሆን በዚህ ቀን የማኅበረ ቅዱሳን መደበኛ አገልግሎት የማይኖርበት ዕለት መሆኑ ይታወቃል፡፡ ምን አልባት ካላንደር ሳይዙ ጽፈውት ይሆን? የሰንበት ት/ቤቶች ማደራጃ መምሪያው በየጊዜው ከማኅበሩ ደብዳቤዎች ይደርሱታል። አአ/ልዩ/05/2003 ዓ.ም የሚለው ቁጥር አስተውሎት ውስጥ ሳይገባ በመካነ ድሩ በችኮላ መለቀቁ ማኅበሩን ለመክሰስ ካለው የግለሰቦች ጉጉት የተነሣ ይሆን?

3. በቁጥር መቀጽቤ 99/2003 ዓ.ም በተጻፈው የሐሰት ሰነድ ሒሳብ ክፍልንና ትምህርትና ሐዋርያዊ አገልግሎት ክፍልን የሚመለከት ምንም ጉዳይ ሳይኖረው ወደ ሒሳብ ክፍልና የትምህርትና ሐዋርያዊ አገልግሎት ክፍል ግልባጭ መደረጉ ለምን ይሆን? ለዚያውም በማደራጃ መምሪያው መካነ-ድር እንደተገለጠው የተደበቀ የስለላ ሥራ ከሆነ እንዴት ለእነዚህ ክፍሎች ግልባጭ ሊደረግ ይችላል? ሒሳብ ክፍልስ ከሕዝብ ግንኘነት አገልግሎቱ ጋር ምን ግንኙነት ይኖረው ይሆን? እነዚህ ጥያቄዎች በጥብቅ ሊመለሱ የሚገባቸው ናቸው።

ምን አልባት ለማጭበርበር በሚደረገው ሙከራ የአንዱ ደብዳቤ ሐሳብ ከሌላው ደብዳቤ ላይ ተቀያይሮባቸው ይሆን? የየትኛው ደብዳቤ ሃሳብ ለየትኛው ክፍል ግልባጭ መደረግ እንዳለበት ፊደል የቆጠረ የሚያስተውለው ነው።

4. በማኅበሩ የአገልግሎት ክፍሎች የሚመደቡት አባላት በሰበካ ጉባኤ ወይም በሰንበት ትምህርት ቤት የታቀፉ መሆን እንዳለባቸው በመተዳደሪያ ደንቡ አንቀጽ 6/ለ ተጠቅሶ ሳለ “የሰ/ት/ቤቶችን በተመለከተ፣ የማኅበሩ አባላት በሙሉ በየሰንበት ትምህርት ቤቱ በአባልነት እንዲያገለግሉ ተደርጓል፤ እየተሰራበት ይገኛል።” የሚለው ዓረፍተ ነገር የማኅበሩ አባላት የሰ/ት/ቤትና የሰበካ ጉባኤ አባላት አይደሉም የሚለውን የአባ ሠረቀን የሐሰት የክስ ሐሳብ ለማጽናት ይሆን?

ማኅበረ ቅዱሳን በሰ/ት/ቤቶች ማደራጃ መምሪያ ስር የሆነው በራሱ ጥያቄ አቅራቢነት ነው፡፡ ይኸውም አባላቱ በሰ/ት/ቤቶች ታቅፈው እንዲያገለግሉለት ካለው ጽኑ ፍላጎት የተነሣ እንደሆነ ግንዛቤ ውስጥ ሊገባ ያስፈልጋል፡፡

የሐሰት ሰነዶቹን አጠቃላይ ሐሳብ ለመረዳት ለሚሞክር ሰው፥ አጭበርብሮ ማኅበረ ቅዱሳንን ለመክሰስ እንዲሁም የፀረ ተሐድሶ መናፍቃንን ዘመቻ ለማጨናገፍ የሚደረግ ሴራ መሆኑን ማኅበሩ አያጣውም፡፡

ማኅበረ ቅዱሳንና ሌሎች ማኅበራትም በሚያደርጉት የፀረ ተሐድሶ መናፍቃን እንቅስቃሴ በቅዱስ ሲኖዶስ ተወግዘው ከተለዩት ግለሰቦች ውጭ የማንም ስም በግልጽ ተጠቅሶ አያውቅም፡፡ የተሐድሶ መናፍቃንን ምልክቶች ግን ይጠቁማል፡፡ ከተሰጡት መረጃዎች እንዲሁም ከምልክቶቹ ምእመኑ እየተረዳው እንደመጣ ይታመናል፡፡

የተሐድሶ መናፍቃኑ እንቅስቃሴ ዘርፈ ብዙ የሆነ፣ በብዙ ሚሊዮኖች በጀት ተመድቦለት፣ በዓላማ የቤተ ክርስቲያንን ትምህርት ለመበርዝና ለማጥፋት እጅግ ተምረዋል ተብለው በሚገመቱ ሰዎችና በግዙፍ ድርጀቶች የሚመራና የሚታገዝ ቤተ ክርስትያኗን የሚያናጋ ነው።

ነገር ግን ትግሉ ከተጀመረ ጀምሮ አንዳንድ ግለሰቦች እንቅስቃሴውን ከግለሰቦች ጋር እያያዙት ይገኛሉ፤ የተሐድሶ ኑፋቄ ዘመቻንም እያፋጠኑት ይገኛሉ።

ይህንን ለመከላከል የሚደረገውን ጥረት ለማስተጓጐል ብሎም የምእመኑን ትክክለኛ ትኩረት ለማሳጣት የሚደረግ እንቅስቃሴ እንደሆነ እናምናለን፡፡

ምን አልባት ማኅበረ ቅዱሳን ስም አጥፊ ነው፣ የአባቶችና የሊቃውንት ከሳሽ ነው የሚለውን የአንዳንዶችን ክስ ለማጠናከር ይሆን? አንባቢ ይመርምር።

እግዚአብሔር ሀገራችን ኢትዮጵያን እና ቅድስት ኦርቶዶክሳዊት ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያንን ይጠብቅልን፡፡

ወስብሐት ለእግዚአብሔር