‹‹በልቅሶ የሚዘሩ በደስታ ይሰበስባሉ›› (መዝ.፻፳፭፥፭)

ዲያቆን ዳዊት አየለ
ሰኔ ፳፮፤፳፻፲፭ ዓመተ ምሕረት

የሰው ልጅ በዚህ ምድር ከሚፈራረቁበት የስሜት ነጸብራቆች ዋነኞቹ ኀዘን (ልቅሶ)ና ደስታ ናቸው። እርግጥ ነው እግዚአብሔር የሰውን ልጅ የፈጠረው እያመሰገነው በደስታ ይኖር ዘንድ ነበር፡። ስለዚህም እግዚአብሔር ሰውን የሚያስፈልገውን ሁሉ ካዘጋጀለት በኋላ በአትክልት ሥፍራ ኤደን ገነት በደስታ እንዲኖር አስቀመጠው፡፡ ነገር ግን የሰው ልጅ በገዛ ፈቃዱ ደስታ የሚሰጠውን ሕግ አፍርሶ የደስታ ምንጭ የሆነውን እግዚአብሔርን አጣ፤ በማጣት ብቻም አልቀረም ‹‹…ስለዚህ የተገኘባትን መሬት ያርስ ዘንድ እግዚአብሔር አምላክ ደስታ ከሚገኝባት ገነት አስወጣው…›› (ዘፍ. ፫÷፳፫)። የሰው ልጅ በድሎ ከኤደን ገነት ወደ ምድር (ዓለመ መሬት) ከመጣ በኋላ እግዚአብሔርን አሳዝኖ ጸጋውን አጥቷልና በሕይወቱ ኀዘን (ልቅሶ) ሰፊውን ጊዜ የሚወስድበት ፍጡር ሆነ። ለ፭ሺ ፭መቶ ዘመን የሰው ልጅ ፍጹም በሆነ ኀዘን ውስጥ ከኖረ በኋላ እግዚአብሔር ወልድ በተለየ አካሉ ሥጋን ተዋሕዶ በመገለጥ ለአዳም (ለሰው ልጅ) ካሣ በመሆን ወደ ፍጹም ደስታ መልሶታል።

ኀዘን (ልቅሶ) ማለት ትካዜ፣ ቁዘማ፣ ሙሾ፣ የእንባ መመንጨት መፍሰስ መውረድ ማለት ሲሆን እንደ ቤተ ክርስቲያናችን አስተምህሮ የሚገባና የማይገባ ኀዘን ብለን በሁለት ወገን መድበን መመልከት እንችላለን። (መዝገበ ቃላት ደስታ ተክለ ወልድ ገጽ ፯፻፴፱) የተገባ ኀዘን (ልቅሶ) የምንለው ጌታችን በወንጌሉ ‹‹….ዛሬ የሚያዝኑ ብፁዓን ናቸው፤ መጽናናትን ያገኛሉና…›› ብሎ እንዳስተማረን ዛሬ ላይ የራስን በደል ኃጢአትን አስቦ ማልቀስ እንዲሁም የወንድምን ኃጢአትና ግፍዐ ሰማዕታትን ሞተ ወልደ እግዚአብሔርን አስቦ ማልቀስ በአጠቃላይ በክርስትና ሕይወታችን የሚያጋጥሙንን ፈተናዎች በትዕግሥት መቀበልና መከራውን መታገሥ የሚገባ ኀዘን ተብሎ ከሚታወቁት መካከል ናቸው። የማይገባ ልቅሶ (ኀዘን) ተብለው ከሚታወቁት መካከል “እናት አባት ሞቱብኝ፣ ወንድም እኅት ዘመድ አጣሁ፣ ርስት ጉልት ሄደብኝ” በማለት አብዝቶ ከመጠን ያለፈና ከሥርዓት የወጣ ኀዘን ይጠቀሳሉ። (ማቴ.፭፥፬ አንድምታ) በዚህ መልኩ ማዘን ተገቢ እንዳልሆነ ባስተማረበት ወቅት ለተጠየቀው ጥያቄ አባታችን ሊቁ ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ ‹‹እንግዲያውሳ? ሰው ሆነን ተፈጥረን ሳለ ለሞተው ሰው አለማልቀስ ይቻለናልን? ያለ ሰው አለ። አይደለም እኔም ለሞተ ሰው አታልቅሱ አላልኩም። እኔ እየከለከልኩ ያለሁት ደረት መድቃትንና ሥርዓት የለሽ የሆነ ኀዘንን ነው›› በማለት ምላሽ ሰጥቷል። (የክርስቲያን መከራና ሌሎችም በቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ ገብረ እግዚአብሔር ኪደ እንደተረጎሙት)

አንድ ሰው ራሱን እየመረመረና በኃጢአቱ እግዚአብሔርን መበደሉን እያሰበ ዕለት ዕለት የሚያዝንና የሚያነባ ከሆነ፣ ከልቡ እውነተኛ ንስሓን የሚገባ ከሆነ ይህ ኀዘን ለመንግሥተ ሰማያት በር መክፈቻ ቁልፍ ይሆነዋል፤ ዘለዓለማዊ ደስታንም ያገኛል። አቡነ ሺኖዳ ‹‹የሕይወት ዘመኑን ሙሉ ለዘለዓለም ሕይወት ትኩረት ሳይሰጥና ኃጢአቱን ሳይተው በምድራዊ ተድላና ሳቅ የሚያሳልፍ ሰው በኋላ በእውነተኛው አምላክ የፍርድ ዙፋን ፊት ሲቆም ይህ የውሸትና ኃላፊ የሆነው ደስታ አይጠቅመውም። ስለዚህ እያነቡ መኖር ከኃጢአታቸው በንስሓ የተመለሱ ሰዎች ባሕርይ ብቻ ሳይሆን የእግዚአብሔር ልጆች የሆኑ ሁሉ ባሕርይ መሆኑን እንረዳለን። እንዲያውም ማልቀስ የታላላቅ ቅዱሳን አባቶች ልዩ ባሕርይ ነው›› በማለት እውነተኛ ኀዘን ወደ እግዚአብሔር አባታችን የምንቀርብበትና የምንደርስበት ድልድይ መሆኑን ያስረዳሉ። (የተራራው ስብከት በአቡነ ሺኖዳ አያሌው ዘኢየሱስ እንደተረጎሙት) ብርሃነ ዓለም ቅዱስ ጳውሎስም ስለሚገባ ኀዘን እንዲህ ይላል፤ ‹‹አሁን ግን እኔ ስለ እርሷ በብዙ ደስ ይለኛል፤ ደስታዬም ስለ ኀዘናችሁ አይደለም፤ ንስሓ ልትገቡ ስለ አዘናችሁ እንጂ፤ ከእናንተ አንዱ ስንኳ እንዳይጠፋ፥ ስለ እግዚአብሔር ብላችሁ አዝናችኋልና። ስለ እግዚአብሔር ተብሎ የሚደረግ ኀዘን የዘለዓለም ሕይወትን የሚያሰጥ ንስሓ ነው።›› (፪ኛቆሮ.፯÷፱-፲)

አብዛኛውን ሕይወታቸውን በማልቀስ ያሳለፉና ክብር ያገኙ ቅዱሳን በብሉይም በሐዲስም እጅግ ብዙ ናቸው፤ እንደ አርአያ ከሚጠቀሱ ቅዱሳን መካከል ቅዱስ ዳዊት፣ ቅዱስ አርሳንዮስና ቅዱስ ዮሐንስ ሐፂር ይገኙበታል። ቅዱስ ዳዊት ንጉሥ፣ ዙፋን ላይ ተቀምጦ መፍረድ የሚችል ፈራጅ፣ የጦር መሪ፣ ደስታን ሊሰጡት የሚችሉ ብዙ ነገሮች በእጁ የሆኑለት፣ የሕዝብ መሪ ባለ ሥልጣንና እጅግ ብዙ ጸጋ እግዚአብሔር ያሉት ሆኖ ሳለ ‹‹…ሌሊቱን ሁሉ አልጋዬን አጥባለሁ፥ በዕንባዬም መኝታዬን አርሳለው›› በማለት ስለበደሉ ዘወትር የሚያነባ እንደነበር ተናግሯል። (መዝ.፮÷፮) ቅዱስ ዮሐንስ ዘሰዋስው ደግሞ ‹‹እንደ እግዚአብሔር ፈቃድ የሆነ ኀዘን ምንጊዜም ፈጥኖ ጓግቶ የተጠማባቸውን ነገሮች የሚፈልግ የነፍስ ትካዝና የኅዙን ልብ ጠባይ ነው፤ በፍለጋው ሲደናቀፍም ተግቶ ይፈልገዋል፤ ነቅቶም እያዘነ በልቅሶ ይከተለዋል። ወይም እንዲህ ነው፦ ኀዘን ከቁራኛዎችና ከማዕሠሮች ሁሉ የሚያላቅቅ በነፍስ ውስጥ ያለ ወርቃማ መኮርኮሪያ ነው፤ ልብህን ትጠብቀው ዘንድ በቅዱስ ኀዘን ጽና›› እያለ ከልብ ሆኖ በእግዚአብሔር ፊት ስለኃጢአት ጉስቁልና የሚቀርብ እውነተኛ ኀዘን ከማዕሠረ ኃጢአት የሚያላቅቅ እንደሆነ ያስተምረናል። (ቅዱስ ዮሐንስ ዘሰዋሰው ምዕራግ እና ድርሳን በሳሙኤል ፍቃዱ)

በሌላ መልኩ እንዲሁ እኛ ክርስቲያኖች በዚህ ዓለም ሳለን ለመከራና ለፈተና የተጋለጥን ነን፤ ጌታችን አምላካችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በቅዱስ ወንጌሉ ‹‹…በዓለም ሳላችሁ መከራ ትቀበላላችሁ፤ ነገር ግን ጽኑ፤ እኔ ዓለሙን ድል ነሥቼዋለሁና›› በማለት የክርስትና ሕይወትና ዓለም የማይጣጣሙ ነገሮች መሆናቸውንና ዓለም ክርስቲያኖችን ለማስጨነቅ እንደሚደሰት ነግሮናል። (የሐ.፲፮÷፳) ለክርስቲያኖች በዓለም ሳሉ የሚገጥማቸው መከራ የሚጠቅማቸው ነው፤ መከራን በትዕግሥት መቀበል ማለት ከሰማያዊ ክብር መሳተፍ ነውና። የክርስቲያን መከራ ነፍስን የሚረዳ፣ በክብር ላይ ክብርን የሚያስገኝ ስለሆነ ኀዘኑም ሆነ መከራው ለጥቅማችን ነው። ጌታችን ‹‹እውነት እላችኋለሁ፤ እናንተ ታለቅሳላችሁ፤ ታዝኑማላችሁ፤ ዓለምም ደስ ይለዋል፤ እናንተ ግን ኀዘናችሁ ወደ ደስታ ይለወጣል›› እንዳለን ዛሬ በምድር በተለያዩ ፈተናዎችና መከራዎች ብናዝንም በመጨረሻው ሰዓት ግን ዘለዓለማዊ ደስታ የምናገኝበት መንገድ ነው። (የሐ.፲፮ ፥ ፴፫) ‹‹…ዛሬ የምታለቅሱ፥ ብፁዓን ናችሁ፤ ትስቃላችሁና።›› (ሉቃ.፮ ፥ ፳፩) እንዲሁም በማቴዎስ ወንጌል ‹‹ወደ ሕይወት የምትወስደው በር እጅግ ጠባብ፥ መንገድዋም ቀጭን ናትና፤ የሚገቡባትም ጥቂቶች ናቸው›› ተብሎ እንደተጻፈው ጠባብ የተባለች የዘለዓለም የሕይወት መንገድ ክርስትና በፈተና ውስጥ ጸንተው ለሚያልፉ ዘለዓለማዊ አክሊልን የምታሰጥ ፍሬዋ እጅግ ጣፋጭ የሆነ መንገድ ናት።(ማቴ.፯÷፲፬)

ስለዚህም በክርስትናችን ምክንያት የሚገጥሙ ኀዘኖችና መከራዎች ነቢዩ ዳዊት ‹‹በልቅሶ የሚዘሩ በደስታ ይሰበስባሉ›› እንዳለው በኋላ ላይ በደስታ የምንሰበስበው ፍሬ ያላቸው ናቸው።(መዝ.፻፳፭፥፭) ዘር የሚዘራ ገበሬ የክረምት ጭቃውን፣ ዝናሙንና ብርዱን ሳይሰቀቅ በትዕግሥት ለሥራና ለዘር እንደሚሰማራና በበጋው የእጁን ፍሬ በደስታ እንደሚሰበስብ ሁሉ እኛ ምእመናንም በሰማያዊው ዓለም የምናገኘውን ተድላና ደስታ በማሰብ በምድር ቆይታችን የሚደርስብንን ልዩ ልዩ መከራ በትዕግሥት ማሳለፍ እንደሚገባን እንገነዘባለን።

በዚህ ኀላፊና ጠፊ በሆነው ዓለም የማያልፍና የማይጠፋ ነገር የለም፤ ኀዘኑም፣ መከራውም፣ ልቅሶውም፣ ጊዜያዊ ደስታውም ቢሆን ሁሉም ኀላፊና ጠፊ ነው፤ የማያልፉት በክርስትና ሃይማኖታችን ጸንተን ለእግዚአብሔር ታምነን የምንሠራቸው የትሩፋቶች ሥራዎች ናቸው፤ በመከራዎች ውስጥ ሁሉ እርሱን ዘወትር ማመስገናችን እና ለእርሱ መታመናችን እስከ ወዲያኛው ዓለም አብሮን የሚሸጋገር ሀብታችን ነውና ዘወትር ፈተናዎችን ታግሠን በስሙ ልንታመን ይገባል። ሊቁ ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ እንዲህ ይላል፤ ‹‹መንፈሳዊ ሰው፥ ስፍር ቁጥር የሌላቸው መከራዎች ቢያጋጥሙትም እንኳን አይጠራጠርም፤ ከእነርሱ በአንዳቸውም አይሸነፍም። ምናልባት ድህነት ሊያገኘው ይችላል፤ በሽታ ሊያገኘው ይችላል፤ ሰዎች ሊንቁት ይችላሉ፤ ሰዎች ሊሰድቡት ይችላሉ፤ ሊያዋርዱት ይችላሉ፤ ደዌያት ሊይዙት ይችላሉ፤ ሌሎች እነዚህን የመሰሉ መከራዎች ሊያገኙት ይችላሉ። ሰዎች ሊሳለቁበት፣ ሊዘባበቱበትና ሊያፌዙበት ይችላሉ። ዳሩ ግን እርሱ የሚኖረው ከዚህ ዓለም ውጭ ስለ ሆነና ከሥጋዊ መሻቶች ነጻ ስለ ሆነ በእነዚህ ሁሉ ላይ ይስቅባቸዋል። እኛ ክርስቲያኖች በሰውነታችን ላይ የሚደርሱ መከራዎች፣ ሕመሞች፣ ደዌያትና ኀዘናት ለበደልናቸው በደሎች ሥርየት የምንቀበልባቸው ናቸው። እንደ ወርቅ የምንጠራባቸው እቶኖች ናቸው…ተወዳጆች ሆይ! መከራ እጅግ በዝቶ ስትመለከቱ ተስፋ አትቁረጡ፤ ደስ ሊላችሁ ይገባል እንጂ። እግዚአብሔር እነዚህን መከራዎች ያመጣው የእናንተን ግድየለሽነት ለማራቅና ከእንቅልፋችሁ እንድትነቁ ብሎ ነውና።›› (የክርስቲያን መከራና ሌሎችም በቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ ገበረ እግዚአብሔር ኪደ እንደተረጎሙት)

አምላካችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በእርሱ አምነን፣ በስሙ ታምነን፣ ስለ ኃጢአታችን እውነተኛ ንስሓን ከልባችን በሆነ ኀዘን ገብተን እንዲሁም በሃይማኖታችን የሚመጡብንን መከራዎችና ፈተናዎች ታግሠንና ጸንተን የመንግሥቱ ወራሽ፣ የስሙ ቀዳሽ እንድንሆን እንዲሁም በመጨረሻው ሰዓት ‹‹…ወደ ጌታህ ደስታ ግባ…›› እንደተባለው ታማኝ አገልጋይ እኛም ወደ ዘለዓለማዊው ደስታ እንገባ ዘንድ በቸርነቱ ይርዳን! (ማቴ.፳፭÷፳፩)

ወስብሐት ለእግዚአብሔር!