ቅድስት

መጋቢት ፫ ቀን ፳፻፲፫ ዓ.ም

ቅድስት የሚለው ቃል ትርጉሙ ‹‹የተለየች፣ የተመረጠች፣ የከበረች›› ማለት ነው። ሥርወ ቃሉም ‹‹ተቀደሰ›› ሲሆን ፍቺው ደግም ‹‹ክቡር፣ ምስጉን፣ ምርጥ›› ማለት ነው፡፡ ሊቁ ቅዱስ ያሬድ ለዐቢይ ጾም ሁለተኛው እሑድ በአዘጋጀው ምስጋና አማካኝነት ዕለቱ ‹‹ቅድስት›› የሚል ስያሜ ተሰጥቶታል፡፡ (መጽሐፈ ሰዋስው ወግስ ወመዝገበ ቃላት ገጽ ፯፻፹፬)

ዕለቱ ‹‹ቅድስት›› ተብሎ የተሰየመበት ምክንያት ስለ ዕለተ ሰንበት እንዲሁም ስለ እግዚአብሔር አምላክ ፍጹም ቅድስና የሚያወሳ በመሆኑ ነው፡፡ እግዚአብሔር አምላክ በባሕርይው ቅዱስ ነው፤ ዓለም ሳይፈጠር አንድነቱ ሦስትነቱን ሳይጠቀልለው ሦስትነቱ አንድነቱን ሳይከፍለው እግዚአብሔር በአንድነት በሦስትነቱ ሲቀደስ ሲሠለስ ይኖር ነበር፡፡ እግዚአብሔር አምላክም ፍጥረታቱ የእርሱን ስም በማመስገን ይኖሩ ዘንድ ለቅድስና ሕይወት ፈጥሯቸዋልና በሰንበት እሑድ ክርስቲያኖች የቅድስና ተግባራቸውን ከሌላው ቀን አብዝተው ይፈጽማሉ፡፡ ‹‹እኔ እግዚአብሔር አምላካችሁ ቅዱስ ነኝና እናንተ ቅዱሳን ሁኑ›› እንዲል፤ (ዘፍ.፪፥፫፣ ዘሌ.፲፱፥፪)

እግዚአብሔር አምላክ ቅዱስ በመሆኑ በአርአያውና በአምሳሉ የፈጠረን እኛ ሰዎች እንደርሱ ቅዱስ ልንሆን ይገባል፤ ሰው ለኃጢአት ርቆ በጽድቅ እንዲኖር የድኅነት መንገድ ስለተመሠረተለት ምንም እንኳን ችግር መከራ ቢበዛበት እና ፈተና ቢጠናበት በምድር እስከ ኖረ ድረስ በቅድስና ሕይወት መኖር አለበት፡፡ ፈጣሪያችን እግዚአብሔር ኃጢአት እንደማይስማማው ሁሉ ቅዱስ ወይም ቅድስት የሆነ ሰው ኃጢአትን ይጠላል፤ ሰዎች ቅዱሳን ናቸው ስንል ቅድስናቸው የጸጋ መሆኑን፣ ከእግዚአብሔር ዘንድ የተሰጣቸው፣ ለቅድስናቸው ማዕረግ ደረጃ የሚወጣለት እንደ ገድል ትሩፋታቸው መጠን ሊጨምርም ሊጎድልም የሚችል መሆኑን በመረዳት ነው። መላእክት፣ ሰዎች፣ መካናት፣ ዕለታት ሁሉ ለእግዚአብሔር እስከተለዩ ድረስ ከቅድስናው በረከት ይሳተፋሉ፤ የቅድስና ስምም ይሰጣቸዋል ።

በዘመናት የተነሡ ቅዱሳን አባቶችም ሆኑ ቅዱሳት አንስት ሕይወታቸውን ይመሩ የነበረው በሕገ እግዚአብሔር እንዲሁም ትእዛዛቱን በመፈጸም ነበር፡፡ ይህን በፍጹም ትሕትናና ትጋት ይተገብሩ እንደነበር ቅዱሳት መጻሕፍት ይገልጻሉ፡፡ የእነርሱ የተቀደሰ ሕይወትም ለሌሎች ምሳሌ በመሆኑ ዓለም ሲዘክራቸውና ሲያከብራቸው ይኖራል፡፡ በመጽሐፍ ቅዱስ ታሪካቸው ተጽፎ ከምናውቃቸው ቅዱሳን አባቶች በተጨማሪ በዘመናት የነበሩ አበው የሃይማኖት አባቶች፣ ሊቃውንት፣ ካህናት እንዲሁም ሰማዕታት ሁሉ በቅድስና ሕይወት ኖረው መንግሥተ ሰማያትን እንደወረሱ ቅዱሳት መጻሕፍት ይመሰክራሉ፡፡

በየዘመናቱ ተነሥተው ድንቅ ተጋድሎን በመፈጸም በክርስቶስ ክርስቲያን ተብለው በቅድስና ሕይወት ከኖሩት መካከል ፴፮ቱ ቅዱሳት አንስት ማለትም ኤልሳቤጥ፣ ሐና፣ ቤርዜዳን ወይም ቤርስት፣ መልቲዳን ወይም ማርና፣ ሰሎሜ፣ ማርያም መግደላዊት፣ ማርያም እንተ ዕፍረት እኅተ አልዓዛር፣ ሐና ነቢይት፣ ማርያም እሞሙ ለደቂቀ ዘብዴዎስ፣ ሶፍያ (በርበራ)፣ ዮልያና (ዮና)፣ ሶፍያ (መርኬዛ)፣ አውጋንያን (ጲላግያ)፣ አርሴማ፣ ዮስቲና፣ ጤግላ፣ አርኒ (ሶፍያ)፣ እሌኒ፣ ኢዮጰራቅሊያ፣ ቴዎክላ (ቴኦድራ)፣ ክርስቲያና (አጥሩኒስ)፣ ጥቅሞላ (አሞና)፣ ጲስጢስ፣ አላጲስ፣ አጋጲስ፣ እርሶንያ (አርኒ)፣ ጲላግያ፣ አንጦልያ (ሉክያ)፣ አሞን (ሶፍያ)፣ ኢየሉጣ፣ መሪና፣ ማርታ እህተ አልዓዛር፣ ማርያም የማርቆስ እናት፣ ሣራ (ሶፍያ) የይሁዳ እናት፣ ዮሐና (ዮላና) የኩዛ ሚስት እና ሶስና ምሳሌዎች ናቸው፡፡ (መጽሐሰ ስንክሳር)

በክርስቶስ ክርስቲያን የተባልን እኛ የእግዚአብሔር ሕዝቦች በሙሉ ዘወትር በተለይም በሰንበት የተቀደሰ ተግባር መፈጸም እንዳለብን እሙን ነው፤ ይህም መጸለይ፣ ማስቀደስ፣ ስግደት፣ ምጽዋት እና መባ ለቤተ ክርስቲያን ማስገባት፣ ለተራበ ማብላት እና ማጠጣት፣ የተራቆተን ማልበስ፣ የታመመን እና በእስር ያሉትን መጠየቅ እንዲሁም ለሰዎች በጎ ሥራ መሥራትን ያካትታል፡፡ ምንም እንኳን ሰዎች የዕለተ ጒርሻቸውን ለማግኘት እና ኑሮአቸውን ለመሙላት በሥራ ደፋ ቀና ማለት ቢጠበቅባቸውም ግን ለጸሎትና ለጾም እንዲሁም ለምጽዋት ጊዜ ሊኖራቸው ይገባል፡፡ ከዚህም አልፎ ተርፎ በዕለተ ሰንበት ሙሉ ለሙሉ ሥራን ባለመሥራትና ወደ ቤተ ክርስቲያን በመሄድ ሥርዓተ ቤተ ክርስቲያንን መፈጸም፣ እንዲሁም በጎ ምግባራትን አብዝቶ መተግበር ያስፈልጋል፤ ‹‹የሰንበትን ቀን ትቀድሰው ዘንድ አስብ፡፡ ስድስት ቀን ሥራህን ሥራ፤ ተግባርህንም ሁሉ አድርግ፤ ሰባተኛዋ ቀን ግን እግዚአብሔር ለአምላክህ ሰንበት ናት›› እንዲል፤ (ዘፀ. ፳፥፰-፲)

በዚህ በጀመርነው የዐቢይ ጾም በሁለተኛው ሳምንት እሑድ ቅድስት የተቀደሰ ተግባርን እንድንፈጽም ሥርዓቱ ተመሥርቶልናልና ወደ ቤተ ክርስቲያን በመሄድ በዕለቱ በሚሰበከው ስብከት በመሳተፍ እና በመዝሙራትም እግዚአብሔርን ማመስገን ይጠበቅብናል፡፡ ለዚህም ዕለትም ቅዱስ ያሬድ ያዘጋጀው ምስጋና ‹‹ግነዩ ለእግዚአብሔር ወጸውዑ ስሞ ወንግርዎሙ ለአሕዛብ ምግባሮ ሀቡ ስብሐተ ለስሙ አክብሩ ሰንበተ ተገበሩ ጽድቀ ዝግቡ ለክሙ መዝገበ ዘበሰማያት ኀበ ፃፄ ኢያማስኖ ወኢይረክቦ ሰራቂ ድልዋኒክሙ ንበሩ ዘበላዕሉ ጸልዩ ኀበ ሀሎ ክርስቶስ፤ ለእግዚአብሔር ተገዙ፤ ስሙንም ጥሩ፤ ሥራውንም ለአሕዛብ ንገሯቸው፤ ለስሙም ምስጋናን አቅርቡ፤ ሰንበትን አክብሩ፤ እውነትንም አድርጉ፤ ብል የማያበላሸው ሌባም የማያገኘው በሰማያት ያለ መዝገብን ለእናንተ ሰብስቡ፤ ተዘጋጅታችሁም ተቀመጡ፤ ክርስቶስ ወዳለበት ወደላይ አስቡ›› የሚል ነው፡፡ (መዝሙር ዘቅድስት)

በመሆኑም በዚህ ዕለት ሁላችንም የፈጣሪን ቅዱስ ተግባር የምናደንቅበት ከማንኛውም የሥጋ ሥራ ተለይተን የነፍስ ሥራን እየሠራን እርሱን የምናመሰግንበት ዕለት ነው።

እግዚአብሔር አምላክ ቅዱሳን እንሆን ዘንድ እርዳታው አይለይን፤ አሜን፡፡