ቅዱስ ወንጌል

ዲያቆን ተስፋዬ ቻይ

ሰኔ ፲፭፤፳፻፲፭ ዓመተ ምሕረት

ውድ የእግዚአብሔር ልጆች! እንደምን አላችሁ? ጾመ ሐዋርያትን እንዴት እያሳለፋችሁት ነው? ልጆች! ጾም ማለት ከምግብና ከውኃ መከልከል ብቻ ሳይሆን ከክፉ ሥራም መታቀብ (መከልከል) ነው፤ ጾም የጽድቅ በር ናት፤ ጾም ለመልካም ነገር የምታነሣሣን ናት፡፡

ውድ የእግዚአብሔር ልጆች! ስንጾም ከጸሎትና ከስግደት ጋር ወደ ቤተ ክርስቲያን በመሄድ በማስቀደስና ታዛዦች በመሆን የጾሙን ጊዜ ልናሳልፍ ይገባል፡፡ ሌላው ልጆች መዘንጋት የሌለብን ነገር በሰንበት ትምህርት ቤት በመሳተፍ በመንፈሳዊ እውቃችን ጎበዞች ልንሆን ይገባል፤ በአቅራቢያችን ወደ ሚገኘው ቤተ ክርስቲያን በመሄድ በሰንበት ትምህርት ቤት ቃለ እግዚአብሔርን፣ ሥርዓተ ቤተ ክርስቲያንን፣ ነገረ ክርስቶስን፣ ነገረ ማርያምን፣ ነገረ መላእክትን እና ወዘተ ልንማር ይገባል፤ መልካም! ውድ የእግዚአብሔር ልጆች! ዛሬ ስለ ቅዱስ ወንጌል እንማራለን፤ መልካም ንባብ!!!

ልጆች! ቅዱስ ወንጌል በመጽሐፍ ቅዱስ የተጻፈ የአምላካችን የእግዚአብሔር ቅዱስ ቃል ነው፤ ስለ ወንጌል ከማየታችን አስቀድመን ግን ስለ መጽሐፍ ቅዱስ ትንሽ እንንገራችሁ! መጽሐፍ ቅዱስ የምንለው በብሉይ ኪዳንና በሐዲስ ኪዳን የተጻፉትን ነው፤ ይህ ቅዱስ መጽሐፍ እግዚአብሔር ለቅዱሳን ጥበብን ማስተዋልን ሰጥቶ እንዲጽፉ አድርጓል፡፡

ልጆች! በቅዱሱ መጽሐፍ እግዚአብሔር ዓለምንና በውስጧ ያለውን ሁሉ እንደፈጠረ፣ ሰዎችንና ቅዱሳን መላእክትም እንደፈጠረ፣ በቸርነቱ እኛን ሰዎችን ከክፉ ነገር እየጠበቀ የሚያስፈልገንን እየሰጠ እንደሚያኖረን ይነግረናል (ያስተምረናል)፡፡

ውድ የእግዚአብሔር ልጆች! በዓለማችን በርካታ መጻሕፍት ተጽፈዋል፤ ነገር ግን የተረሱ ብዙዎች አሉ፤ ትውልድ አልፎ ትውልድ ሲተካ የቀደመው ይረሳና ሌላ ደግሞ ይጻፈል፤ መጽሐፍ ቅዱስ ግን ለብዙ ዘመናት ኖሯል፤ ወደ ፊትም ይኖራል፤ ምክንያቱም ነገረ እግዚአብሔር ያለበት ስለሆነ፣ ያጻፈውም እርሱ እግዚአብሔር ስለሆነ ዘመናትን ተሻግሮ ይኖራል፡፡

ውድ የእግዚአብሔር ልጆች! መጽሐፍ ቅዱስ የተለየ፣ የተከበረ፣ የተመረጠ መጽሐፍ ነው፤ በእግዚአብሔር ገላጭነት እርሱ እኛን ለማዳን እንደሚመጣ፣ ከሰማያት ወርዶ ከእመቤታችን ከቅድስት ድንግል ማርያም እንደተወለደ በመስቀል ላይ ተሰቅሎልን እንዳዳነን ቅዱስ መጽሐፍ ይነግረናል፡፡ እግዚአብሔር መርጧቸው ቅዱሳን ሰዎች ስለጻፏቸው መጽሐፉን የሚያነቡትንና የሚሰሙትን የሚቀድስ ነውና ቅዱስ ተብሏል፤ ስለ መጽሐፍ ቅዱስ በአጭሩ ይህን ካልናችሁ ከመጽሐፍ ቅዱስ የወንጌል ክፍል የሚባሉትን በጥቂቱ እንመልከት፡፡

ወንጌል ማለት ‹የምሥራች፣ ብሥራት፣ አዲስ ዜና፣ መልካም ወሬ፣ ደስ የሚያሰኝ፣ ስብከት፣ አምላካዊ ሰማያዊ ነገር› ማለት ነው፤ በዚህ ቅዱስ መጽሐፍ ክፍል ደስ የሚል የምሥራች ተጽፎበታል፤ በአዲስ ኪዳን ጌታችን አምላካችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የምሥራቹን ወንጌል ለሕዝቡ ይሰብክ ነበር፤ ከዚያም ደግሞ ለዓለም ሁሉ እንደሚነገር ለቅዱሳን አባቶቻችንን ሐዋርያት ‹‹…ምስክር እንዲሆን ይህ የመንግሥት ወንጌል ለዓለም ሁሉ ይሰበካል…›› በማለት ነግሯቸዋል፡፡ (ማቴ.፳፬፥፲፬)

ውድ የእግዚአብሔር ልጆች! ወንጌል የምንለው በተለየ መልኩ በሐዲስ ኪዳን ቅዱሳን አበው ሐዋርያት የጻፉትን ነው፡፡ ይህ የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል በተለየ መልኩ የሚነግረን አዳምና ሔዋን ያኔ በገነት ዕፀ በለስ በበሉ ጊዜ መከራ ደርሶባቸው ከእግዚአብሔር ልጅነት ተለይተው ነበር፤ ‹ታዲያ ይቅር በለን አጥፍተናል› ብለው በንስሓ ሲመለሱ እግዚአብሔር እንደሚያድናቸው ቃል ኪዳን ገባላቸው፤ ታዲያ የሰጣቸው ተስፋ ተፈጽሞ እኛን ለማዳን ከሰማያት ወርዶ አዳነን፤ ይህንን ውለታ ፍቅሩን ለዓለም ዞረው እንዲያስተምሩ ጌታችንን አዘዛቸው፤ አባቶቻችን ቅዱሳን ሐዋርያትም የሰው ልጆች ከሰይጣን ባርነት ነጻ መውጣቱን፣ ዳግመኛ የእግዚአብሔር ልጅ መባሉን፣ ወንጌልን የምሥራችን ለዓለም ዞረው አስተማሩ፡፡ ጌታችን ያስተማረውን ትምህርት ፣ ያደረገልንን ውለታና ፍቅሩን ለትውልድ ይተላለፍ ዘንድ ቅዱሱን መጽሐፍ ጻፉልን፤ ሰዎችን ወደ ቅድስና የሚመራንና የቅዱስ እግዚአብሔርን ድንቅ ሥራ የሚነግረንን ቅዱስ ወንጌል (የምሥራች) ጻፉልን፡፡

ውድ የእግዚአብሔር ልጆች! መጽሐፍ ቅዱስን ስናነብ ሕይወታችን ይቀደሳል፤ የአምላካችንን ውለታ እንዘክራለን፤ ከክፉ ምግባር እንድንጠበቅ፣ ለሰዎች መልካም እንድናደርግ፣ ከክፉ ነገር እንድንለይ፣ እርስ በእርሳችን እንድንዋደድ ያስተምረናል፡፡ ሌሎች መጻሕፍትን ብናነብ ስለምድራዊ ነገር ብቻ ይነግሩናል፡፡ መጽሐፍ ቅዱስ ግን በምድር ላይ ስንኖር ምን ማድረግ እና በሕይወተ ሥጋ ስንለይ (በሞት ከምድር ስንለይ) መልካም ከሠራን የክብር ሕይወት እንደሚሰጠን ያስተምረናል፤ አያችሁ ልጆች! በሥጋም በነፍስ በረከትን የሚያሰጥ መጽሐፍ ቅዱስ ነው፤ ይህ ቅዱስ መጽሐፍ በክርስቲያኖች ቤት ሁሉ ሊኖር ይገባል፡፡

ውድ የእግዚአብሔር ልጆች! እስኪ ጥያቄ እንጠይቃችሁ! መጽሐፍ ቅዱስን ምን ያህል ጊዜ አነበብን! ቤታችን ውስጥ መጽሐፍ ቅዱስ አለ?! እንዴትስ ነው የምናስቀምጠው? የተለየ፣ የተከበረና የተቀደሰ መጽሐፍ ስለሆነ በክብር ልንይዘው፣ በልዩ ሥፍራ ልናስቀምጠው ይገባል፤ መጽሐፍ ቅዱስን ስናነብ ለማወቅ ብቻ ሳይሆን በተግባርም ፈጽመነው መልካም ሰዎች ለመሆን ይረዳናል፤ ከዚያም እግዚአብሔር ለቅዱሳኑ ያዘጋጃትን መንግሥተ ሰማያትን እንወርሳለን፡፡

አምላካችን እግዚአብሔር ቅዱሳን መጻሕፍትን አንብበን ሕይወታችን ይቀደስ ዘንድ ማስተዋልን ጥበቡን ያድለን፤ አሜን!

ስብሐት ለእግዚአብሔር
ወለወላዲቱ ድንግል
ወለመስቀሉ ክቡር አሜን!!!