ቅዱስ ሲኖዶስ ችግሮችን በውይይት መፍታት እንዳለበት ተገለጸ

 ጥቅምት 12 ቀን 2006 ዓ.ም. 

በእንዳለ ደምስስ

meglecha 11
ቅዱስ ሲኖዶስ ችግሮችን በውይይትና በውይይት ብቻ በጋራ የመፍታት ባሕልን መደገፍና ማጎልበት እንደሚገባው ተገለጸ፡፡

በዛሬው ዕለት ጥቅምት 12 ቀን 2006 ዓ.ም. ጠዋት የቅዱስ ሲኖዶስ ምልዐተ ጉባኤ ከመጀመሩ በፊት ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም ወእጨጌ ዘመንበረ ተክለ ሃይማኖት በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ በአሁኑ ጊዜ በጥልቀት፣ በማስተዋልና የሓላፊነት መንፈስ በተላበሰ ወኔ፣ አጥብቆ ሊወያይባቸውና ሊወስንባቸው፤ ከውሳኔ በኋላም ለተግባራዊነታቸው ሊረባረብባቸው የሚገቡ በርከት ያሉ ጉዳዮች እንዳሉ አመልክተዋል፡፡

ቤተ ክርስቲያን ልጆቿን ከጉያዋ እየተነጠቁ ወደ ሌላ ካምፕ ሲወሰዱ የወላድ መካን መሆን እንደሌለባት ያወሱት ቅዱስነታቸው የታሪክ ተወቃሽ ከመሆን ለመዳን አስተማማኝና ዘላቂ መፍትሔ ሊፈለግለት እንደሚገባ ገልጸዋል፡፡ ከአስተዳደር ጋር በተያያዘም “ከአድልዎና ከወገንተኝነት ሙሉ በሙሉ ያልተላቀቀው አስተዳደራችን የቤተ ክርስቲያናችን ታላቅነትና ተሰሚነትን ክፉኛ እየጎዳው መሆኑ አሌ ልንለው አይገባም” ብለዋል፡፡

ቤተ ክርስቲያኗ የተማረና የሰለጠነ የሰው ኃይል ከማፍራት አንጻርም የአብነት ትምህርት ቤቶች፤ የማሠለጠኛና የከፍተኛ ትምህርት ተቋሞቿን በብዛትም፤በጥራትና በአደረጃጀት ተማሪውን ለመለወጥና ለመቅረጽ በሚያስችል አዲስ አሠራር ማስተካከልና ማብቃት እንደሚገባም ጠቁመዋል፡፡

የመግለጫው ሙሉ ቃል እንደሚከተለው ይቀርባል፡፡

 

 meglecha 12