ቀለማትና ትርጉማቸው

ዲያቆን ተስፋዬ ቻይ

የካቲት ፭፤፳፻፲፮ ዓመተ ምሕረት

ቀለም የሚለውን ቃል ሊቁ አለቃ ኪዳነ ወልድ ክፍሌ የቃላትን ፍቺ (ምሥጢር) በተረጎሙበት መጽሐፋቸው ቀለም በቁሙ “ኅብር፣ ፈሳሽ፣ ዓይነት፣ መጣፊያ፣ ማቅለሚያ” ብለው አብራርተውታል፡፡ (ኪዳነ ወልድ መዝገበ ቃላት፣ ገጽ ፯፻፺፫) ሰዎች ቀለማትን ነገሮችን ለመለየትና ለአንድ ነገር (ክስተት) መለያ ምልክት አድርገው ሲጠቀሙበት ይስተዋላል፤ በዓለም አቀፍ ስምምነት ቀለማትን ለነገሮች በመወከል ያ የቀለም ዓይነት ሲታይ ሰዎች ያንን እንዲያስታውሱ አልያም ሰዎች ኀዘናቸውንና ደስታቸውን ለመግለጽ ያሉበትን ሁኔታ የሚያንጸባርቀውን (የሚገልጠውን) የሚወክል ቀለም ያለውን አልባሳት በመልበስ ሲገልጡ እንመለከታለን፡፡

ቀለማት በቤተ ክርስቲያንም አስተምህሮ የራሳቸው የሆነ ትርጉም አላቸው፡፡ እግዚአብሔር በኖኅ ዘመን ዓለም ከትእዛዙ በመውጣት በበደለና በኃጢአት ባሕር በሰጠመ ጊዜ ከበደላቸው ይመለሱና ይጸጸቱ ዘንድ ቢነግራቸውም በክፋታቸው በመጽናታቸው ዓለም በንፍር ውኃ ስትቀጣ (ስትጠፋ) ቃሉን አድምጠው ትእዛዙን የፈጸሙ ኖኅና ቤተ ሰቡ ኖኅ ታዞ በሠራው መርከብ ገብተው ከጥፋት ውኃ ድነዋል፡፡ የቁጣው ጊዜ አልፎና መዓት ርቆ በምድር ሰላም በሆነ ጊዜ ኖኅ መርከብ ከእነ ቤተ ሰቡና ይዟቸው ወደ መርከብ ከገቡት እንስሳት አራዊት አእዋፋት ጋር ወደ ምድር ወረዱ፡፡

እግዚአብሔርም ለኖኅ ቃል ኪዳን እንዲህ ሲል ገባለት፤ ‹‹በእኔና በአንተ መካከል ሕያው ነፍስ ባለውም ሥጋ ሁሉ መካከል ያለውን ቃል ኪዳን አስባለሁ፤ ሥጋ ያለውንም ሁሉ ያጠፋ ዘንድ ዳግመኛ የጥፋት ውኃ አይሆንም፤ ቀስቲቱም በደመና ትሆናለች፤ በእኔና በአንተ መካከል ያለውን የዘለዓለም ቃል ኪዳን ለማሰብ አያታለሁ፤ እግዚአብሔርም ኖኅን በእኔና በምድር ላይ በሚኖር ሥጋ ባለው ሁሉ መካከል ያቆምሁት የቃል ኪዳን ምልክት ይህ ነው አለው፡፡›› (ዘፍ.፱፥፲፭)

እግዚአብሔር በቀስት ምልክት ደጋኑን ወደ ላይ በማድረግ ሰባት ኅብረ ቀለማት ባሉት በደመና በቀስት ደጋን ምልክት አሳየው፡፡ በሰማይ ቀስተ ደመና ሲታይ እነዚያን ቀለማት ስንመለከት ሁል ጊዜ የእግዚአብሔርን፣ ምሕረትና ቃል ኪዳን እናስታውሳለን፡፡ በሰማይ ሰሌዳ ከደመናው በላይ ቀስተ ደመና ባየን ቁጥር የምሕረትና ይቅርታ ቃል ኪዳን የመጠበቅ ምልክትን እናስባለን፡፡

ቀለማቱ ኅብር ደጋን ሠርተው ዓይናችን ሲመለከት ውሳጣዊ ዓይናችን ዘመናትን ወደ ኋላ ተጉዞ የኖኅ ዘመንን የጥፋት ውኃ ታሪክ ያስታውሰናል (ያሳየናል)፡፡ አያይዞም እግዚአብሔር በቃሉ የታመነ ምሕረቱ የበዛ እንደሆነና ዛሬም ከእኛ ጋር እንዳለ ያስገነዝበናል፡፡ እንግዲህ ቀለማት በሰዎች ሕይወት ታሪክ ውስጥ የሚያጋጥሙ ኩነቶችን ማለትም ደስታም ሆነ ኀዘንን እንድናስታውስ የሚያደርጉ ናቸው፡፡

እግዚአብሔር ከጥፋት ውኃ በኋላ በቀስት ደጋን አምሳል ለአባታችን ያሳየው የቃል ኪዳን ምልክት ቀስተ ደመና የቀለሙ ኅብር ብዙ ቢሆንም መተርጉማነ ቤተ ክርስቲያን በአንድምታ አጉልተው ምሥጢራቸውን የሚተነትኑት የሦስቱን ነው፡፡ ከቀለማቱ ፍቺ ቅድሚያ ግን እግዚአብሔር በቀስት ደጋን አምሳል ለዚያውም የደጋኑን ቀስት ማስወንጨፊያ አቅጣጫውን ወደ ራሱ አድርጎ አሳየው የሚለውን እንመልከት፡፡

ቀስተኛ በቀስቱ አስወንጭፎ ሊወጋ ባሰበ ጊዜ አውታን ወደ እርሱ፣ የቀስቱን ደጋን ጠላቴ ወደሚለው አቅጣጫ ያደርጋል፤ ከዚያም ያስወነጭፋል፤ ሰላም ከሆነ ጠብ ከበረደ ደግሞ ደጋኑን ወደ ራሱ አቅጣጫ አውታን ወደ ሌላኛው አቅጣጫ ያደርጋል፤ አልወጋህም ሲል፤ እንግዲህ በሰው ልጆች የጠብና የሰላም ምልክት በሆነው የቀስት አያያዝ ምሳሌነት ከአሁን በኋላ ዓለምን በንፍር ውኃ አላጠፋም፤ ሰላም ሆኗል ሲል የቀስቱን ደጋን አቅጣጫ ወደ ላይ አድርጎ ቃል ኪዳኑን አጸናለት፡፡

የቀስተ ደመናው ኅብሩ ብዙ መሆኑ ሰው በብዙ ኃጢአት ቢበድለኝ ይቅር እለዋለው ሲል ነው፤ጎልተው የሚታዩት ቀለማት ግን አራት ነው፤ እነርሱም ጥቁር፣ ነጭ፣ ቢጫ እና ቀይ አራት መሆናቸው ከአራቱ ባሕርያተ ሥጋ የፈጠርኩት ሰው ቢበድለኝም ሥጋውን ተዋሕጄ አድነዋለው ሲል ቀይ የእሳት ባሕርይ የመንፈስ ቅዱስ ምሳሌ፣ ነጭ የውኃ ባሕርይ የጥምቀት ምሳሌ ፣ ቢጫ የመሬት ባሕርይ የቅዱስ ሥጋው ምሳሌ፣ ጥቁር የነፋስ ባሕርይ የቅዱስ ደሙ ምሳሌ፣ ደመናው የእመቤታችን ምሳሌ ናቸው፡፡ በጥምቀት በሥጋና ደሜ አድንሃለው ሲለው እነዚህን አሳይቶታል፤ ከጥፋት ውኃ ቃል ኪዳንና ባሻገር ለአዳም በገባው ቃል ኪዳን በሰጠው ተስፋ መሠረት ከሰማየ ሰማያት ወርዶ ከእመቤታችን ከቅድስት ድንግል ማርያም በኅቱም ድንግልና ተፀንሶ በኅቱም ድንግልና እንደሚወለድና ዓለምን እንደሚያድን ሲገልጥለትም ነው፡፡ (ኦሪት ዘፍጥረት ምዕ ፱ ቁጥር ፲፯-፲፱ አንድምታ)

በቅድስት ቤተ ክርስቲያን አስተምህሮ ቀለማት በቅዱሳት ሥዕላት ውስጥ  የሚያስተላልፉት መልእክትም አሉ፤ የፈጣሬ ዓለማት የቅድስት ሥላሴ እና የእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያምን ሥዕላት ሲሣሉ የሚቀባው ቀለም ዓይነት የራሱ የሆነ ትርጉምና የሚያስተላልፈው ነገር አለው፡፡ የቅዱሳን መላእክትን፣ የቅዱሳን አበውን፣ የቅዱሳት እናቶችን ሥዕልም በሚሳልበት ጊዜ የተጋድሏቸውን ጽናት፣ የክብራቸውን ዓይነትና የመጠሪያ ስያሜአቸውን ለመለያነትም ያገለግላል፡፡

የቅዱሳን ሥዕላት ሲሣሉ በሥዕሉ ባለቤት ዙሪያ የምንመለከተው ፀዳለ ብርሃን (አክሊለ ብርሃን) ቅዱሳን በቤተ ክርስትያን የቅድስና ማዕረግ እንደተሰጣቸው ያሳያል፡፡ ነገር ግን በቅድስት ሥላሴና በጌታችን በመድኃኒታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ላይ የሚደረገው ፀዳለ ብርሃን የእግዚአብሔር ቅድስና የባሕርይው መሆኑን እንደሚገልጽ መረዳት ያስፈልጋል፡፡

ለቅዱሳት ሥዕላት በቤተ ክርስቲያናችን ቀኖና መሠረት አብዛኛውን ጊዜ የምንጠቀማቸው ቀለማት ሰማያዊ፣ ቀይ፣ አረንጓዴ፣ ቢጫና ነጭ ሲሆኑ ቀለማቱ ራሱን የቻለ ምሥጢር ወይም ትርጉም አላቸው፡፡

ሰማያዊ፡- ሰማያዊውን ሀብት ገንዘብ ለማድረግ በፈቃደ ነፍስ መመራትን ለማመልከት እንዲሁም በመንፈስ ፍሬዎች ፈቃደ ሥጋን በፈቃደ ነፍስ ድል ማድረጋቸውን ለማመልከት ለቅዱሳን ሥዕላት ይህንን ቀለም እንጠቀመዋለን፡፡ በትሕትና ለመኖራቸውም ምሳሌ ነው።

ቀይ፡- ሰማዕትነትን ያሳያል፤ ቅዱሳን ነፍሳቸውን ለመከራና ለሞት አሳልፈው ስለ ክርስቶስና ስለ ቤተ ክርስቲያን ብለው መስጠታቸውን ለማመልከት ይህንን ቀለም እንጠቀመዋለን፤ እንዲሁም የነጻ አውጪዎችም ምልክት ተደርጎ ይወሰዳል፡፡

ቢጫ፡- ይህ ቀለም እውነተኛነትንና ብርሃንነትን ይገልጻል፡፡ “እናንተ የዓለም ብርሃን ናችሁ” እንዲል፡፡ (ማቴ.፭፥፲፬) ከዚህም በመነሣት ቤተ ክርስቲያን የቅድስና ማዕረግ ላይ የደረሱትን ቅዱሳን “እውነተኞችና የዓለም ብርሃን ናችሁ” ስትል በራሳቸው የብርሃን አክሊል በቢጫ አድርጋ ትሥላለች፡፡

አረንጓዴ፡- ከልምላሜና ከፀዳል ጋር ስለሚያያዝ መንፈሳዊ ትርጉሙ መታደስን፣ አዲስ ሕይወት፣ ደኀንነትና ተስፋን ያሳያል፡፡ በዚህ መሠረት አረንጓዴነትና ሕይወት ተወራራሽ ይሆናሉ፡፡

ነጭ፡- የድል አድራጊነት፣ የንጽሕና እና የፍጹምነት ምሳሌ ነው፡፡ ቅዱሳን ዓለምንና ምኞቱን ድል ያደረጉ ልበ ንጹሐን በመሆናቸው ነጭ ልብስ ለብሰው ይሣላሉ፡፡ መለኮታዊ ክብርንም ያሳያል፡፡ ለምሳሌ በደብረ ታቦርና በትንሣኤ ሥዕሎች ላይ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ነጭ ልብስ ለብሶ ይሣላል፡፡ (ኦርዶቶክሳዊ ቅዱሳት ሥዕላት፣ ገጽ ፸፬)

ቀለማት በመንፈሳዊ እይታ ይህን ዓይነት ውክልና ትርጉም ሲኖራቸው እነዚህ ቀለማት በሌላ ስፍራ ደግሞ ሌላ ትርጉምና ውክልና አላቸው፤ በፍልስፍናው ዓለም ግን ሰዎች ሐሳባቸውን፣ ስሜታቸውንና አስተሳሰባቸውን ለመግለጽ ሲጠቀሙባቸው ይስተዋላል፡፡ ሰዎች ራሳቸው ተስማምተው ስያሜ ሰጧቸው እንጂ አሁን ያላቸውን ትርጓሜና ውክልና ይዘው አልተፈጠሩም፡፡ የሰው ልጆች በጋራ ስምምነት ለራሳቸው መግባቢያነትና ለነገሮች መግለጫነት የወከሏቸው መሆናቸውን ልብ ማለት ያሻል፡፡

ቀለማት እንደ የአገራቱ ደግሞ የራሳቸው የሆነ ትርጉም ተሰጥቶአቸው ለጥቀም ይውላሉ፡፡ አንደኛው አገር ለአንደኛው ቀለም የሚሰጠውን ትርጉምና የሚሰጠውን ውክልና አንደኛው ላይቀበለው ይችላል፡፡ እንደ ምሳሌ ብንወስድ በመንፈሳዊ ዓለም ቢጫ ቀለም ያለው የተስፋ ምልክት ነው፤ በፍልስፍናው ዓለም ደግሞ ቢጫ አበባ የማስጠንቀቂያ እንደሆነ ይገለጻል፤ ሕንጻን አልያም የቤትን ክፍል በቀለም የሚያስውቡ ባለሙያዎች ለቀለማት ከሙያቸው አንጻር የራሳቸውን ትርጉም ይሰጡታል፤ ሁሉም በፈርጁ ሐሳቡን ያንጸባርቅበታል፡፡ ሰዎች ለነገሮች መግለጪያነት፣ ለውክልና በራሳቸው ስያሜን የሰጡት የቀለማት ዓይነት የመግባቢያነት፣ የመፋቀር፣ የአንድነት፣ ምልክት እንጂ የመለያየትና የጥላቻ ምንጭ ሊሆን አይገባም፡፡ ለዚህም እንደ መፍትሔ ሊሆነን የሚችለው ቅድስት ቤተ ክርስቲያን ስለ ቀለማት ትርጉም የምትሰጠውን ትምህርት ማወቅና መረዳት ነው፡፡

ስብሐት ለእግዚአብሔር
ወለወላዲቱ ድንግል
ወለመስቀሉ ክቡር አሜን!!!