ሶርያዊው ቅዱስ ኤፍሬም

ጥዑመ ልሳንመምህረ ዓለምዓምደ ቤተ ክርስቲያን

ሐምሌ ፲፬ ቀን ፳፻፲፬ ዓ.ም

ሜሶፖታሚያ በምትገኝ ንጽቢን ከተማ ከዋክብትን ከሚያመልኩ ሰዎች መካከል በ፫፻፮ ዓ.ም ገደማ የተወለደው ሶርያዊው ቅዱስ ኤፍሬም አባቱ ክርስትናን የሚጠላ ሰው እንደነበር ይነገራል፡፡ እንዲያውም ካህነ ጣዖት ስለመሆኑ መጽሐፈ ስንክሳር ይጠቅሳል፡፡ (ስንክሳር ሐምሌ ፲፭)

ቅዱስ ኤፍሬም ከወላጆቹ ጋር የኖረው እስከ ፲፭ ዓመት ድርስ ብቻ ነው፡፡ መንፈስ ቅዱስ እንዳመለከተውም ወደ ንጽቢን ጳጳስ ቅዱስ ያዕቆብ በመሄድ የእግዚአብሔርን ቃል በመማር የክርስትና ጥቅምትን ተጠምቋል፡፡ በጸሎት እንዲሁም በጾም እየተጋደለ ለበርካታ ዓመት በእርሱ ዘንድ ከተቀመጠ በኋላም በብሕትውና ሕይወት በመወሰን ብዙዎችን አስተምሯል፡፡ ንጽቢን በሚገኘው መንፈሳዊ ትምህርት ቤትም ኃላፊ ሆኖ አገልግሏል፡፡

በ፫፻፳፭ ዓ.ም በተደረገው የኒቅያው ጉባኤም ከተገኙት አባቶች መካከል አንዱም ነው፤ ከመምህሩ ቅዱስ ያዕቆብ ጋር በመሆን የ፫፻፲፰ቱ ሊቃውንት ስብሰባንና ውግዘተ አርዮስን መመልከት ችሏል፡፡ ከጉባኤውም በተመለሰ ጊዜ ዓምደ ብርሃን ከምድር እስከ ሰማይ ተተክሎ ሌሊት በሕልሙ ራእይ አየ፡፡ ‹‹ራእዩን እንደገጽክልኝ ባለቤቱንም ግለጥልኝ›› ብሎም ወደ እግዚአብሔር ቢያመለክት የታዘዘ መልአክ መጥቶ ‹‹ባስሌዮስ ዘቂሳርያ ነው፡፡ ለቤተ ክርስቲያን ዓምድ ጽንዕ ነውና፤ በትምህርቱ የሰውን ልቡና ብሩህ ያደርጋልና እንዲህ ባለ አርአያ አየኸው›› አለው፡፡ ቅዱስ ኤፍሬምም ወደ ቂሣርያ ከሄደ በኋላ ቅዱስ ባስልዮስን አገኘው፤ ቅዱስ ያዕቆብም  ዲቁና ሾሞ በሀገረ ስብከቱ ውስጥ እንዲያስተምር አደረገው፤ ቅዱሱም በዚያም ሥፋራ ብዙ ተአምራትን አደረገ፤ መጻሕፍትንም ደረሰ፡፡

በ፫፻፺፫ ዓ.ም የንጽቢን ከተማ በጠላት እጅ ወድቃ ስትወረር ቅዱስ ኤፍሬም ሮም፣ ኤዴሳ ከተማ ለመሰደድ ተገዶ ነበር፡፡ አብረውትም ሌሎች ክርስቲያኖች ተሰደዋል፡፡ በከተማዋም መናፍቃን ይገኙባት ስለነበር ይህ ቅዱስ የክህደት እምነታቸውን ለማጥፋት ከእነርሱ ጋር በእጅጉ ተጋደለባት፤ የተሳሳተ ትምህርታቸውና አመለካከታቸውንም በመቃወም ያለ መታከት ሞግቷቸዋል፡፡ ከዚህም በኋላ በርካታ ትምህርቶችን አዘጋጀ፤ መጻሕፍትንም ጻፈ፡፡ ድርሰቶቹም ዐሥራ አራት ሽህ ድርሳናትንና ተግሣጻት ናቸው፡፡ በመጽሐፈ ስንክሳር እንደተጻፈው ‹‹አቤቱ የጸጋህን ማዕበል ግታልኝ›› እስከሚል ድረስ ድርሳናትን ደርሷል፡፡ (ስንክሳር ሐምሌ ፲፭)   እርሱ የደረሳቸው አብዛኛዎቹ መጻሕፍት ወደ ግእዝ ተተርጉመዋል፡፡ ከእነዚህ ውስጥ በተለይም የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የምትጠቅሳቸውና የምትጠቀምባቸው የጸሎት ድርሰቱ የእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ውዳሴ ማርያም ነው፡፡

ቅዱስ ኤፍሬም በእመቤታችን ስም ይመጸውትና ለእርሷም በነበረው ፍቅር የተነሣ  ‹‹የእመቤቴ ምስጋናዋ እንደ ሰማይ ኮከብ እንደ ባሕር አሸዋ በዝቶልኝ እንደ ልብስ ለብሼው እንደ ምግብ ተመግቤው ጠግቤው›› እያለ  ሲመኝ ይኖር ስለነበር የተመኙትን መስጠት ልማዱ ነውና እግዚአብሔር የልቡን መሻት ፈጸመለት፡፡ እመቤታችንም ተለገልጻለት እርሷን ለማወደስ በቅቷል፡፡ ከዕለታት በአንዱ ቀን ሰኞ ነግህ በሆነ ጊዜ ተግባሩን አድርሶ ከመካነ ግብሩ ተቀምጦ ሳለ እመቤታችን መጣች፤ የብርሃን ምንጣፍ ተነጠፈ፤ የብርሃን ድባብ  ተዘረጋ፡፡ ከዚያም ላይ ሁና ‹‹ሰላም ለከ  ኦ ፍቅርየ ኤፍሬም፤ ወዳጄ ኤፍሬም  ሰላም ለአንተ ይሁን›› አለችው፤ እርሱም ታጥቆ እጅ ነሥቶ ቆመ፡፡ ‹‹ወድሰኒ›› አለችው፤ ‹‹እፎ እክል ወድሶተኪ ዘኢይክሉ፤ ሰማያውያን ወምድራውያን ምድራውያን ጻድቃን ሰማያውያን መላእክት አንችን ማመስገን የማይቻላቸው ለእኔ እንደምን ይቻለኛል?›› አላት፤ ‹‹በከመ አለበወ፤ በመንፈስ ቅዱስ ተናገር›› አለችው። ከዚህ በኋላ ‹‹ባርኪኝ›› አላት፤ ‹‹በረከተ ወልድየ ወአቡሁ ወመንፈስቅዱስ ይኅድር በላዕሌከ፤ የልጄና የአባቱ እና የመንፈስ ቅዱስ በረከት በላይህ ላይ ይደርብህ›› አለችው፤ ተባርኮም ምስጋናዋን ጀምሯል፡፡ በእንደዚህም ሁኔታ የሰባቱን ዕለታት ውዳሴ ማርያም መድረስ ችሏል፡፡ (ውዳሴ ማርያም ትርጓሜ)

አባታችን ቅዱስ ኤፍሬም የደረሰው የሰባቱ ሰዓታት ክርስቲያን ለተባለን ሰዎች በሙሉ የክርስቲያናዊ ሕይወታችን ስንቅ በመሆኑ እያንዳንዱን የጸሎት ሰዓት ልናውቅና ልንጸልይ ይገባል፡፡ በርግጥ ዓለም ላይ ሆነን ካለንበት የአናናር ዘይቤ የተነሣ ለኑሯችን ዘወትር እሩጫ ላይ በመሆናችን ሰባቱንም ሰዓት ጠብቆ መጸለይ ሊከብደን ይችላል፡፡ ሆኖም ግን ሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያን በየዕለቱ ቢያንስ የሦስት ጊዜያቱን የጸሎት ሰዓት መጠበቅ እንደሚገባን ያስተምራሉ፡፡ ያለበለዚያ መንፈሳዊ ሕይወታችን ሙሉ እንደማይሆን ልናውቅ ይገባል፡፡ በነግህ፣ በሠለስት (በሦስት ሰዓት)፣ በቀትር፣ በተሰዓት፣ (ዘጠኝ ሰዓት)፣ በሠርክ፣ በንዋም (በመኝታ ሰዓት) እንዲሁም በመንፈቀ ሌሊት ከዘወትር ጸሎት ጋር ውዳሴ ማርያምን እንዳርሳለን፡፡

በእግዚአብሔር ረድኤት በእነዚህ የጸሎት ሰዓቶች ውስጥ በጸሎት ልንተጋ ይገባል፡፡ በተለያየ አስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ ሆነን መጸለይ ቢያቅተን እንኳን ጠዋት ከመኝታችን ስንነሣና ማታ ወደ መኝታችን ስናመራ መጸለይ ይገባናል፡፡ በገዳማት ተወስነው፣ ዳዋ ጥሰው፣ ጤዛ ልሰው፣ ቁርበት ለብሰውስ፣ ድንጋይ ተንተርሰው፣ ድምጸ አራዊቱን፣ ግርማ ሌሊቱን፣ ጸብና አጋንንቱን ታግሰው የሚኖሩ ገዳማውያን መነኰሳት አባቶቻችን እና እናቶቻችን ሰባቱን የጸሎት ሰዓታት ለዓይን ጥቅሻ ለምታክል ጊዜ እንኳን ሳያስታጉሉ እስካሁን ጸንተው ኖረዋል፡፡  ቅዱስ ኤፍሬምም ምንኩስናን በገቢር የገለጣት አባት ነው፡፡ በተጋድሎውም እስከ መሠረሻው ጸንቶ በሐምሌ ፲፭ ቀን ዐርፏል፡፡ ቅዱሱ ለሰዎች ሁሉ የሕይወት ስንቅ የሚሆነውን ይህንን የጸሎት ሥርዓት ደርሶ ለእኛ አበርክቶልናልና እስከ ሕይወታችን መሠረሻ ድረስ እንጠብቀው!

የአባታችን ቅዱስ ኤፍሬም በረከት ይደርብን፤ አሜን፡፡