ስንክሳር፡- መስከረም አምስት

መስከረም 5 ቀን 2008 ዓ.ም

አንድ አምላክ በሆነ በአብ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ ስም መስከረም አምስት በዚች ቀን የከበረች ሶፊያ ከሁለት ልጆቿ አክሶስና በርናባ ከሚባሉት ጋር በሰማዕትንት ሞተች፡፡

ይችም ቅደስት አስቀድማ አረማዊ ነበረች፣ ወላጆቿም ጣዖታትን የሚያመልኩ ናቸው፡፡ እርሷም በልቧ አስተዋለች፣ መረመረችም፣ የወላጆቿ ሃይማኖት ከንቱ እንደሆነ ተረዳች፡፡ ከዚህም በኋላ ወደ መኖፌ ኤጲስ ቆጶስ ሔዳ ክብር ይግባውና በክርስቶስ ታመነች፡፡ እንዲህም አለችው፤ በሕያው አምላክህ አምኛለሁና አጥምቀኝ እርሱም ሃይማኖትን፣ የቤተ ክርስቲያንም ሕግ አስተማራት፡፡ ከዚህም በኋላ ከልጆቿ ጋር በአብ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ ስም አጠመቃት፡፡

ከዚህም በኋላ የሀገር ሰዎች ለአማልእክት መስገድን ትታ ክርስቲያን እንደሆነች በገዢው በክላድያኖስ ዘንድ ወነጀሏት፡፡ ገዢውም ወደ እርሱ አስቀርቦ መረመራት፡፡ እርሷም ክብር ይግባውና በክርስቶስ አመነች እንጂ አልካደችም፣ ከልጆቿም ጋር ብዙ ሥቃይን አሠቃያት፡፡

በሥቃይም ውስጥ ላሉ ልጆቿ ታስታግሳቸውና ታጽናናቸው ነበር፣ እንዲህም ትላቸው ነበር፡፡ ልጆቼ ጠንክሩ፣ ጨክኑ የአንጌቤንዋን እመቤት ሶፍያን እመስላታለሁ፤ እናንተም ጲስጢስ፤ አላጲስ አጋጲስ የተባሉ ልጆቿን ምሰሉ፣ እነርሱም እንዲህ ብለው መለሱላት፣ እናት ሆይ እኛ ፍለጋሽን እንከተላለንና ስለእኛ አትፈሪ ይህንንም በሚባባሉ ጊዜ ከእናታቸው ጋር ተሳሳሙ፡፡

ገዢውም ሲሳሳሙ አይቶ ደናግል ልጆቿ እንዲፈሩ እናታቸውን በጅራፍ ይገርፏት ዘንድ አዘዘ፡፡ ያን ጊዜም የእግዚአብሔር መልአክ ከሰማይ ወርዶ እናታቸውን ከግርፋት ሲሠውራት አዩ፡፡

ዝንጉዎችም ይገርፏት ዘንድ ባራቆቷት ጊዜ በዚያን ሰዓት እንዲህ በማለት ትጮህ ነበር፡፡ ዓለሙን ሁሉ በፈጠረ በእውነተኛ አምላክ በእግዚአብሔር የማምን ክርስቲያናዊት ነኝ፣ ያን ጊዜም ገዢው ምላሷን ከሥሩ እንዲቆርጡ አዘዘ፡፡ እርሷ ግን መጮህንና መናገርን አላቋረጠችም፡፡

ከዚህም በኋላ ገዢው ወደ እሥር ቤት እንዲወስዷት አዘዘ፤ ትሸነግላትም ዘንድ ሚስቱን ወደእርሰዋ ላከ፡፡ እርሰዋ ግን ምንም አልመለሰችላትም፡፡ ራሷንም በሰይፍ ይቆርጧት ዘንድ አዘዘ፤ የድል አክሊልም ተቀበለች፡፡ አንዲት ሴትም መጥታ ሥጋዋን በጭልታ ወሰደች፣ ወደ ቤቷም አስገብታ በፊቷ መብራትን አኖረች፡፡

ከዚህም በኋላ ልጆቿን ጠርቶ እሺ ይሉት ዘንድ አስፈራራቸው፣ እምቢ ባሉትም ጊዜ እያከታተለ ራሳቸውን አስቆረጠ፣ ምሥክርነታቸውንና ተጋድሏቸውንም ፈጸሙ፡፡ ከመቃብራቸውም በሽታውንና ደዌውን ሁሉ የሚፈውሱ ብዙ የሆኑ ድንቆች ተአምራቶች ተገለጡ፡፡

ደግ ንጉሥ ቆስጠንጢኖስም ዜናቸውን በሰማ ጊዜ የቅዱሳት ሰማዕታትን ሥጋቸውን ወደ ቁስጥንጥንያ አፍልሶ ወሰደ፡፡

የሶፍያንና የልጆቿን ዜና ከመስማቱ በፊት ታላላቅና ሰፊ የሆኑ ቤቶች እንዲሠሩ በላይዋም ይቺ ቤት የንጉሥ ቆስጠንጢኖስ ናት ብለው ጽሑፍ እንዲቀርጹበት አዘዘ፡፡ እነርሱም ንጉሡ እንዳዘዘ ወደ ማታ ሲሆን ይጽፋሉ፣ የእግዚአብሔርም መልአክ ወርዶ ያንን ደምስሶ ይቺ ቤት የሶፍያ ናት ብሎ ይጽፋል፡፡ የሕንፃውም ባለሙያዎች የሚያደርጉትን አጡ፣ መጻፋቸውንም ተዉ፡፡

በአንዲት ቀንም የንጉሥ ልጅ ብቻውን ሲጫወት መልአክ ተገለጸለትና የዚች ቤት ስሟ ማነው አለው፡፡ ሕፃኑም አላወቅሁም አለው፣ መልአኩም ሁለተኛ እንዲህ አለው አባትህን የሶፍያ ቤት ብለህ ሰይማት ብለህ ንገረው ሕፃኑም ተመልሼ እስክመጣ ትጠብቀኛለህን አለው፣ መልአኩ አዎን እጠብቅሃለሁ አለው፡፡

አባቱም ይህን ሰምቶ መልአክ እንደሆነ ዐወቀ፡፡ ሕፃኑንም በመጠበቅ ምክንያት ያ መልአክ ከዚያች ቦታ እንዳይሄድ ብሎ ንጉሡ ልጁን ገደለው፡፡ መልአኩም ሕፃኑን እየጠበቀ እስከዛሬ ድረስ አለ፡፡

የዚያች ቤተ ክርስቲያም ርዝመቷ ሰባት መቶ ዘጠኝ ክንድ ሆነ፣ አግድመቷም ሦስት መቶ ሰባት ክንድ፣ ምሰሶዎቿም ዐራት መቶ፣ ጠረጴዛዎቿም ስምንት፣ የሚያበሩ ዕንቁቿ ዐራት ናቸው፣ ከአጎበሩ በላይ የተቀረጹ ኪሩቤልም በየሁለት ክንፎቻቸው የእግዚአብሔር ሕግ የተጻፈበትን ታቦት ይጋርዳሉ፡፡

ሥጋቸው በውስጡ ያለበትን የቅድስት ሶፍያንና የልጆቿን ሳጥን በታላቅ ምስጋናና ክብር ወደዚያ አስገብተው አኖሩ፡፡

በድኖቻቸውን የሰበሰበች ያቺንም ሴት ከእርሳቸው ጋር ቀበሯት፡፡

ለእግዚአብሔርም ምስጋና ይሁን እኛንም በከበሩ ሰማዕታት ጸሎት ይማረን በረከታቸውም ከእኛ ጋር ትኑር ለዘለዓለሙ አሜን፡፡

ምንጭ፡- መጽሐፈ ስንክሳር፣ ከመስከረም እስከ የካቲት፣ አዲስ አበባ፤ ትንሣኤ ማሳተሚያ ደርጅት፣ 1994 ዓ.ም፣ ገጽ 20-21፡፡