‹‹ሱላማጢስ ሆይ ተመለሽ ተመለሽ›› (መሓ.፩)

ክፍል ሦስት

ዲያቆን ይትባረክ መለሰ

ጥቅምት ፲፬፤፳፻፲፮ ዓመተ ምሕረት

‹‹ወቆመ ውእቱ አርዌ አንጻረ ይእቲ ብእሲት ከመ ሶበ ወለደት ይብላዕ ሕፃና ወወለደት ወልደ ተባዕተ ዘውእቱ ይርዕዮሙ ለኩሉ አሕዛብ በበትረ ኀጺን….ወጎየት ይእቲ ብሲት ውስተ ገዳም ወውስተ መካን ዘአስተዳለወ ላቲ እግዚአብሔር፤ ዘንዶውም ሴቲቱ በወለደች ጊዜ ሕፃንዋን እንዲበላ ልትወልድ ባላት ሴት ፊት ቆመ፡፡ አሕዛብንም ሁሉ በብረት በትር ይገዛቸውም ዘንድ ያለውን ወንድ ልጅ ወለደች፡፡……..ሴቲቱም ሺህ ከሁለት መቶ ስድሳ ቀን በዚያ እንዲመግቧት በእግዚአብሔር ተዘጋጅቶላት ወደ ነበረው ስፍራ ወደ በረሃ ሸሸች፡፡ (ራእ.፲፪፥፬-፮) የነገረ ማርያም ሊቃውንት ሴቲቱ የተባለች እመቤታችን፣ አሕዛብን በብረት በትር የሚገዛቸው ወንድ ልጅ የተባለው ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ነው ብለው ተርጉመዋል፡፡ ‹‹ሕፃን ተወልዶልናልና ወንድ ልጅም ተሰጥቶናልና አለቅነትም በጫንቃው  ላይ ይሆናል›› (ኢሳ.፱፥፮) እንዳለ ኢሳይያስ፡፡

ዘንዶ የተባለ ዲያብሎስ በጨካኙ ሄሮድስ ላይ አድሮ ያለ አባት በድንግልና የወለደችውን ልጇን ይገድልባት ዘንድ ተነሥቶባታልና፤ በረሃ ወደ ተባለ ግብጽ ተሰደደች፡፡ በዚያም ብዙ መከራን ተቀበለች፡፡ እስከ ምድረ ግብጽ ባደረገችው ስደት ለ ሦስት ዓመት ከስድስት ወር  ያህል በረሃ ለበረሃ፣ ጫካ ለጫካ፣ እሾህ እየወጋት፥ እንቅፋት እየመታት፣ ረኃቡና ጥሙ እያሠቃያት ሽፍቶች እና ጨካኞች አራዊት ባገኟት ቁጥር በድንጋጤ፣ በጭንቀት ብዙ መከራ እየተቀበለች ተንከራታለች፡፡

ልጇ በስደቷ ወቅት ያደረጋቸውን ተአምራትና ስለደረሰባት መከራም ስትናገር ‹‹…ሁሉን ብነግርህ ኖሮ ወረቀት ባልቻለውም ነበር›› ትላለች፡፡ (ድርሳነ ማርያም ገጽ ፪፻፰) በስደቷ ወቅት ከደረሱባት መከራዎች ጥቂቶቹን እንኳን ስንናገራቸው ስናስባቸው እንዴት አስጨናቂ እንደሆኑ እንረዳለን፡፡ ‹‹ኵሉ እኁዝ ውስተ እዴሁ›› የተባለ ልጇን ይዛ ግን ተሰደደች፤ በስደትም ትበላው ዘንድ ምግብ፣ ትጠጣው ዘንድ ውኃ አጥታ ፍለጋ ልመና ወደ ሰዎች ቤት ሄደች፤ ወደ መንደር ገብታ ስመ እግዚአብሔር ጠርታ ስትለምን ሰይጣን እየተከታተለ የሰዎችን ልብ ያስጨክንባት ነበርና አንድ ስንኳ የሚዘክራት ሰው አጣች፡፡ በዚህም እያዘነች ስትመለስ ሰብአ ሰገል ለልጇ ያመጡለትን የወርቅ ጫማ በሽፍታ ተወስዶ ጠበቃት፡፡ ‹‹ሄጄም ላላገኝ የልጀንም ጫማ አስወሰደኩት›› ብላ አምርራ አለቀሰች፡፡

እመቤታችን ራስዋ ይህንን ስትተርከው እንዲህ ትላለች፤ ‹‹ውኃ ፈለግሁ የሰጠኝ ግን አልነበረም፡፡ የልጄን ጫማ ከማጥፋት በቀር የተጠቀምኩት የለም፡፡ ይህን ብዬም አለቀስሁ፡፡ የተወደደው ልጄም እንባዬን ተመልክቶ በጣቶቹ ጠረገልኝ፡፡ ትንሽ ጣቱንም ወደ መሬት አወረደ፤ እንደ ማር የሚጣፍጥ እንደ ወተት የነጣ ውኃ አፈለቀ፡፡ ይህንንም ውኃ ከዚያች ሀገር ሰዎች በቀር ለሚጠጣው ለሚያልፈው ለሚያገድመው ሁሉ ፈውስ፣ ጤና ይሁን! ብሎ ባረከው፡፡›› (ድርሳነ ማርያም)

‹‹ሰሚዖ ሕፃን ለእሙ ገዓራ፤ ባረከ ኰኩሐ ወአንቅዐ ማየ እምታሕተ እግራ፤ ወእምኔሃ ለጽምኣ ትስተይ አመራ፤ ሕፃን ልጇ ክርስቶስ የእናቱን ጭንቀት ሰምቶ ዓለቱን ባረከው፤ ከእግሯ ሥርም ውኃን አፈለቀ፤ ከዚያችም ለጥሟ ትጠጣ ዘንድ አመለከታት›› እንዳለ ደራሲ ከዐለት ላይ ውኃ አፍልቆ፣ በእሳት ዓምድ መርቶ፣ በደመና መሶብ መና አዘግኖ እስራኤልን የመራ የስደተኞች ተስፋ፣ የራብተኞች ምግብ ልጇ ለእናቱ አዘነላት፡፡ (ሰቆቃወ ድንግል) እንባዋንም በእጆቹ ጠረገላት፤ ተጠምታለችና ውኃ ፍለጋ ሄዳ አንድም ሰው ስላላዘነላት አዝናለችና አዘነላት፤ እንደ መዓር ጣፋጭ እንደ ወተት ነጭ ለሚጠጡት ሁሉ ፈውስና ጤና የሚሆን ውኃ ከቆመችበት ምድር ከእግሯ ሥር አፈለቀላት፡፡ እስከ ዛሬ ድረስ ያ ምንጭ ‹‹የማርያም ምንጭ›› እየተባለ ይጠራል፡፡ እመቤታችንም በዚያ ውኃ የልጇን ልብስ አጥባ በደፋችበት ቦታ ቅብዓ ሜሮን የሚዘጋጅበት ዕፅ በቅሎበታል፡፡

በዚህ ታሪክ ውስጥ አንድ የሚያሳዝን ነገር ተከስቷል፡፡ ከእናቱ አግር የፈለቀው ለሕሙማን ፈውስ የሆነው ውኃ ለሀገሩ ሰዎች ግን እንደ እሬት መራራ ሆኖባቸዋል፡፡ ለነጋድያን ለፈላስያን ግን እንደ ማር የሚጣፍጥ ፈውሰ ሥጋ የሚያሰጥ አድርጎታል፡፡ ‹‹ከሀገሩ ሰዎች አንዳቸው እንኳን አይዳን›› ብሎ ረግሞታል፡፡ ያሳዝናል! መራራውን የሚያጠፍጠውን፣ ለተጠሙት ሁሉ የሕይወት ውኃ የሚሰጠውን፣ ለሕሙማን ፈውስ፣ ለስዱዳን ሞገስ የሆነውን ክርስቶስን እና እናቱን አልተቀበሉምና ትንሽም አልራሩላቸውምና ርግማን ሆነባቸው፡፡

ያጋጠማቸውን መከራ፣ የተደረገውን ተአምራት ሁሉ መዘርዘር እመቤታችን እንዳለችው ምን ወረቀት ሊበቃ ይችላል? ጦጣና ዝንጀሮ ስለሆኑት እነ ትእማን ዘመዶች ወይስ መሬት ተክፍታ ስለዋጠቻቸው ትእማንና ኮቲባ ታሪክ እንተርክ? ተራሮችና ኮረብቶች የሰገዱለትን ወይስ ግመሎቹ ሐውልት የሆኑበትን ታሪክ እንጻፍ? የግብጽን ጣዖታት ስለመሰባበሩ ወይስ ዕረፍት እስኪያጣ ስለፈወሳቸው ሕሙማን እንተርክ? በዚያች መንገድ ለማለፉ ምልክት ትሆን ዘንድ ተክሎ ስላጸደቃት የዮሴፍ የወይራ በትር ወይስ የተጠለሉበትን ጨለማ ቤት እንዴት በብርሃን እንደሞላው እንናገር? የቱ ተነሥቶ የቱ ይቀራል? እንዲያው አድንቆ ማለፍ እንጂ፡፡

ውድ አንባብያን! አንድ ግን ሳንተርክላችሁ የማናልፈው ታሪክ አለና እርሱን ብቻ በጥቂቱ እንተርከው፡፡ ታሪኩም እንዲህ ነው፤ እመቤታችንን ካስጨነቁ ገጠመኞች መካከል የሁለቱ ሽፍቶች ነገር ዋነኛው ነው፡፡ አንድ ግብጻዊና አንድ ዕብራዊ ሽፍቶች በጋራ ነፍስ እየገደሉ፣ ቋንጃ እየቆረጡ፣ ሀብት ንብረት እየዘረፉ ይኖሩ ነበር፡፡ እነዚህ ሽፍቶች እመቤታቸንን በስደቷ ገጥመዋታል፡፡ ስለ እነዚህ ሽፍቶች እንዲህ ትላለች፤ ‹‹…ግብጽ እንደገባን ከበጋው ፀሐይ እናርፍ ዘንድ ከከተማው ውጭ ከዛፍ ጥላ ሥር ተቀመጥን፤ ይህም ግንቦት ፳፬ ቀን ነው፡፡ ሁለት ሽፍቶችም በመንገድ አለፉ፤ አንዱ ግብጻዊ አንዱ ዕብራዊ ነው፡፡ ዕብራዊው ግብጻዊውን “የዚህችን ሴት ልብስ፣ የልጇንም ልብስ ልወስደው እሻለሁ፤ የነገሥታቱን ልብስ ይመስላልና” አለው፡፡ ግብጻዊውም ከተፈጠርኩ ጀምሮ እንደዚህ ያለ ሕፃን አላየሁምና ተው” አለው፡፡ ውኃ ፍለጋ ሄጄ ስመለስ የልጄን ጫማ ወስደውት አገኘሁ፡፡ እነ ዮሴፍንም ቀስቅሼ የልጄን ጫማ ወስደውታል፤ የልጄን ጫማ ከማጥፋት በቀር የተጠቀምኩት ነገር የለም ብዬ አለቀስኩ›› ትላለች፡፡

ከዚህ በኋላ ዮሴፍ ከተማ፥ ከተማውን እንሂድ ሲል እመቤታችን ግን የሰውን ክፋት ተረድታለችና ልጄን ይገሉብኛል፤ ጫካ ጫካውን እንሂድ ትላለች፡፡ የሆነውንም እንዲህ ስትል ትቀጥላለች፡፡ ‹‹ፀሐይ ሲገባ ወደ ተራራው ሄድን፤ ስንጓዝም ለመንጋት ትንሽ ቀረው፡፡ በሌላኛይቱ ሀገር ቀደም ሲል ያየናቸው ሁለቱ ሽፍታዎች እስከዚህች ቦታ ድረስ ተከተሉን፡፡ በዚያ ቦታ በተመለከቱን ጊዜ ዕርቃናቸውን ወደ እኛ እየሮጡ መጡ፡፡ በእጆቻቸውም የተመዘዙ ሰይፎች ነበሩ፡፡ ስንከተላችሁ ብዙ ጊዜ ደከምን፤ ነገር ግን ከዛሬ በቀር የምንይዛችሁን ቀን አላገኘንም፤ አሁን ግን በእጃችን ወድቃችኋልና እንበቀላችኋለን አሉን›› (ድርሳነ ማርያም)፡፡

ከዚህ በኋላ ዘለው የተወደደ ልጇን ከእቅፏ ወሰዱባት፡፡ ልብሶቹንም ገፈፉት፤ የእርሷንም መጎናጸፊያ ከላይዋ ላየ ገፈፏት፤ አረጋዊ ዮሴፍም እንደ በግ ሆነላቸው፤ ልብሱንም ከላዩ ላይ ቀደዱት፤ ሰሎሜም ይህንን በተመለከተች ጊዜ በድንጋጤ መጎናጸፊዋን ጣለች፡፡ በዚህ አላበቁም፤ ልብሶቻቸውን ከወሰዱ በኋላ እርስ በርስ ቆመው ሲነጋገሩ እንዳልሄዱ ባየች ጊዜ ጽኑ ፍርሃትን ፈራች፤ ልጄን ሊገድሉብኝ ነው እንጅ ሌባ ቀማኛ ከቀማ በኋላ አዩኝ አላዩኝ ብሎ ይሄዳል ብላ እጅግ አለቀሰች፡፡ እንዲህም አለች፤ ‹‹ተወዳጅ ልጄ ሆይ፥ ወዮልኝ! በዚህች ሰዓት የት እሄዳለሁ? ወደየትስ እሸሻለሁ? እንዳይገድልህ ርጉም ሄሮድስን በመፍራት ከኢየሩሳሌም ሸሸሁ፤ ከሀገሬ ብቀመጥ ኖሮ ይህንን ሁሉ ድካም ባላወቅሁም ነበር፡፡ የዐይኖቼ ብርሃን ሆይ፥ ከዚህ ሀገር ማንን አውቃለሁ? ያለሁት በምድረ በዳ ነው፤ ዛሬ ከእኔ ጋር ያለቅሱ ዘንድ የሚያውቁኝ የት አሉ? ተወዳጅ ልጄ ሆይ፥ ከአንተ ጋር በመሸሽ አንድ ቀን እንኳ ባልደከምሁ ነበር፤ በዚህ ቦታ አንተን ሲገድሉህ ከማያቸው ቀድመው ቢገድሉኝ በተሻለኝ ነበር፤ ሄሮድስ ልጆቻቸውን የገደለባቸውን ሴቶች ባያቸው ኖሮ ከእኔ ጋር ያለቅሱ ዘንድ በወደድሁ ነበር….፡፡›› ይህንና የመሳሰለውን በዙ ነገር እየተናገረች ምርር ብላ አለቀሰች፡፡

እነዚያ ወንበዴዎች ግን ይጨቃጨቁ የነበረው ግብጻዊው ለዕብራዊው “እባክህ ልብሳቸውን እንመልስላቸው” እያለው ስለነበር ነው፡፡ ‹‹እለምንሃለሁ፤ በፊታቸው ከሰው ሁሉ ይልቅ ታላቅ ብርሃንን እመለከታለሁና፤ ሕፃኑም የንጉሥ ልጅ ይመስላል፤ የሚመስለውም አላየሁምና› አለው፡፡ አይሁዳዊውም “አልሰማህም? የነገሥታት ልብሶች ናቸውና›› አለው፡፡ ግብጻዊውም ማሳመን እንዳልቻለ ባየ ጊዜ ከቤተ ልሔም ጀምሮ የዘረፉትን ብዙ ሀብት እንደሚለቅለት ለመነው፤ በዚህም ተስማምቷል፤ ያ ግብጻዊ አዝኖላቸው ልብሳቸውን መልሶላቸው ጌታንም በትከሻው ተሸክሞ ሸኛቸው፡፡

ጌታም ለተወዳጅ እናቱ እንዲህ አላት፤ ‹‹እነዚህን ሁለት ወንበዴዎች ታያለሽን? በኢየሩሳሌም አይሁድ አንዱን በቀኜ አንዱን በግራዬ አድርገው ይሰቅሏቸዋል፡፡ ይህ በልቡናው ቸርነት ያለውም የቸር አባቴ ነው፤ እርሱ በመስቀል እያለሁ ያምንብኛል፤ አዳምና ዘሮቹን ቀድሞም መንግሥተ ሰማያት ይገባል›› አላት፡፡ እነዚህ ሽፍቶች ጥጦስና ዳክርስ ናቸው፡፡ (ማቴ፳፯፥፴፰) ፈያታዊ ዘየማንና ፈያታዊ ዘጸጋም ተብለው በኋላ ከክርስቶስ ጋር በግራና በቀኝ የተሰቀሉት እነዚህ ሽፍቶች ናቸው፡፡

እንደ እውነቱ ቢሆን ከግብጻዊው ይልቅ ዕብራዊው ሊያዝንላቸው በተገባ ነበር፡፡ ነገር ግን ጨከነባቸው፤ ግብጻዊው ግን ቸርነት አሳይቷልና ቸርነት ተደረገለት፡፡ በመንግሥተ ሰማያትም አዳምን በመቅደም የገነት ጠባቂዋ ሱራፊን አስደመመው፡፡ ከባለ ተስፋው አዳም ቀድሞ ገነት ገብቷልና፡፡ ተወዳጆች ሆይ! መቼም የስደቷን ነገር ተናግሮ መጨረስ፣ ተመራምሮ መድረስ የሚቻለን ሆኖ አይደለም፤ እንዲያው ለመዘከር ያህል እንጂ፡፡ ለመሆኑ የስደቷ ዓላማ ምን ይሆን? እንመለስበታለን፤ ቸር እንሰንብት!

ይቆየን!