‹‹ሱላማጢስ ሆይ፥ ተመለሽ፥ ተመለሽ›› (መሓ.፩)

ክፍል አምስት (መጨረሻ ክፍል)

ዲያቆን ይትባረክ መለሰ

ኅዳር ፬፤፳፻፲፮ ዓመተ ምሕረት

‹‹ወጎየ እግዚእ ኢየሱስ ውስተ ደብረ ሊባኖስ ወውስተ ምድረ ግብጽ ወብሔረ አግዓዚ ምስለ ማርያም እሙ፤ ጌታችን ከእናቱ ማርያም ጋር ወደ ሊባኖስ ተራራ ወደ ግብጽና ወደ ኢትዮጵያ መልአኩ እንደነገረው ሳያመነታ ተሰደደ፡፡›› (ትርጓሜ ማቴ. ፪፥፲፫)

እመቤታችን ወደ ኢትዮጵያም ጭምር እንደ ተሰደደች፣ በኢትዮጵያ ውስጥም በተለያዩ ስፍራዎች እንደ ተመላለሰች፣ ሀገራችንንም፣ ሕዝባችንንም እንደ ባረከች፣ ተወዳጅ ልጇ ስለ ኢትዮጵያና ኢትዮጵያውያን ብዙ እንደ ነገራት፣ በቃል ኪዳኗ እንድትጠብቃቸው፣ በምልጃዋ እንድታስምራቸው፣ ዐሥራት አድርጎ እንደ ሰጣት፣ በዚህም የእመቤታችንና የኢትዮጵያውያን ጥልቅ ፍቅር የጸና መሆኑን ሊቃውንትም መዛግብትም ያስረዳሉ፡፡ (ድርሳነ ዑራኤል መቅድም)

ይህን የሚያረጋግጥልን ‹‹ወጎየ እግዚእ ኢየሱስ ውስተ ደብረ ሊባኖስ ወውስተ ምድረ ግብጽ ወብሔረ አግዓዚ ምስለ ማርያም እሙ፤ ጌታ ከእናቱ ከማርያም ጋር ወደ ሊባኖስ ተራራ ወደ ግብጽና ወደ ኢትዮጵያ መልአኩ እንደ ነገረው ሳያመነታ ተሰደደ የሚለው ነው፡፡ (ትርጓሜ ማቴ. ፪፥፲፫)

መምህራነ ቤተ ክርስቲያንም ዕንባቆም ‹‹የኢትዮጵያ ድንኳኖች ሲጨነቁ አየሁ የምድያም አገር መጋረጃዎች ተንቀጠቀጡ›› ሲል የተናገረውን ጌታችን እና ከእናቱ ወደ ኢትዮጵያ መሰደድ ጋር አገናኝተው ይተረጉሙታል፡፡ (ዕንባ. ፫፥፮)

በድርሳነ ዑራኤል ተጽፎ እንደምናገኘው እመቤታችን ወደ ኢትዮጵያ የመጣችው በሀገረ ናግራን በኩል አልፋ በደብረ ዳሞ፥ በአክሱም፣ በደብረ ዓባይ ከዚያም በታላቁ ገዳም ዋልድባ አድርጋ መላው ኢትዮጵያን በደመና ተጭና በመልአኩ ዑራኤል መሪነት ሲሆን በብዙ ቦታዎች በኪደተ እግሯ ተመላልሳ ጎብኝታታለች፤ ባርካታለች፡፡ ‹‹ሰላም ለምጽአትክሙ ጥንተ ዜና ነገር አእመነ፤ በዓለ ደመና ዑራኤል ወድንግለ ሲና እምነ፡፡ ሰሎሜ ወዮሴፍ በኢትዮጵያ ምድርነ፡፡..፤ ከጥንት ጀምሮ የተነገረውን ዜና ለማሳመን የደመናው ባለቤት ዑራኤል ዮሴፍና ሰሎሜ፤ የሲናዋ ድንግል እናታችን ሰላምታ ይገባችኋል፤ ለአደረጋችሁት አመጣጥ በኢትዮጵያ ምድራችን›› እንዲል፡፡

እመቤታችን ለተወዳጁ ሐዋርያ ቅዱስ ዮሐንስ እንደ ነገረችው ጌታችን በተወዳጅ እናቱ ጀርባ ላይ ሆኖ አብዝቶ ወደ ምዕራብ ይባርክ ስለ ነበረ እንዲህ ስትል ጠይቃው ነበር፡፡ ‹‹ለምንት ኩለሄ ትባርክ ነቢረከ ኅዙለከ ዲበ ዘባን ምድረ አዜብ…፤በጀርባዬ ላይ ሆነህ ሁል ጊዜ ወደ ምዕራብ የምትባርከው ስለምን ነው ብዬ ጠየቅሁት፡፡›› (የኅዳር ድርሳን) ልጇም እንዲህ ሲል መለሰላት፤ ‹‹ኦ እምየ ይእተ ሀገረ ዘእባርክ ወሀብኩኪ ዐሥራተ ወይኩኑ ለኪ ሰብአ ኢትዮጵያ ክፍለ ለርስትኪ እስከ ኅልቀተ ዓለም….፤ እናቴ ሆይ በዚች በምባርካት አገር በኢትዮጵያ የሚኖሩ ሰዎችን እስከ ዓለም ፍጻሜ ድረስ ዐሥራት አድርጌ ሰጥቸሻለሁ፤ እናቴ ሆይ አሁንም ወደዚያች ሀገር እንሄድ ዘንደ ተነሽ..›› ይላታል፡፡ እናቱን እንዲህ ባለ ቃል ከነገራት በኋላ ብሩህ ደመና ጭናቸው ወደ ኢትዮጵያ ገብተዋል፡፡

በዚህም በሃማሴን በኩል አድርገው በደብረ ዳሞ፣ በአክሱም ጽዮን፣ በደብረ ዓባይ በተለይም በዋልድባ ወደ ጣና ደሴት ከመግባታቸው በፊት ቆይታ አድርገዋል፤ በአክሱም ጽዮን ገብታ ሕዝቡንም ካህናቱንም ንጉሡንም ባረካቸዋለች፡፡ ደራሲው ይህንንም በውብ ቃል እንዲህ ሲል ይገጸዋል፤ ‹‹…ተፈስሐት ዓውደ ጽዮን ወተሰርገወት ብርሃነ፡፡ እስመ ጽዮን እንዘ ጽዮን አብዓለት ጽዮነ፤ እርሷ ጽዮን ስትሆን የጽዮንን በዓል አከበረች ጽዮን፡፡ የጽዮንንም አደባባይ ደስ እያላት አከበረች በብርሃን ይላል፡፡ እመቤታችን በገዳመ ዋሊ (ዋልድባ) በዋሻዎቿ ሁሉ ተቀምጣ፣ የሚበላ ሳይኖር ልጇ መራራ የዕፀዋት ሥሮችን ቆፍሮ ሰጥቷት ቀምሳ ስለ እርሷ ፍቅር መራራውን ቀምሰው፣ መከራውን ታግሠው፣ በስሟ ተማጽነው፣ በውዳሴዋና በቅዳሴዋ ተጽናንተው፣ ሥጋን እስከ ክፉ መሻቱ አሸንፈው ሰማያዊ ሰው ምድራዊ መልአክ ሆነው የሚኖሩ መነኮሳት መናንያን የሚኖሩበት ታላቅ የቅድስና ስፍራ እንዲሆን ያደረገችው በዚሁ በስደቷ ወቅት ነው፡፡

ኢትዮጵያውያን ደጎች እንደ ነበሩ፤ እንግዳ ተቀባይነታቸውም በቃላት የማይገለጽ እንደ ሆነ እመቤታችን ምስክርነት ሰጥታለች፡፡ ከዋልድባ ተነሥታ ጣናንና አካባቢውን በጎበኘችበት ጊዜ በደስታ እንደ ተቀበሏት እንዲህ ትላለች፤ ‹‹በብርሃን ሠረገላ ተጭነን ተነሣንና ከጣና ባሕር ወደብ ደረስን በዚያች የባሕር ደሴት ውስጥ የሚኖሩ ሰዎች ሁሉ እነዚህ የነገሥታት ልጆች የሚመስሉ እንግዶች ከወዴት መጡ እያሉ በመደነቅ በደስታ ተቀበሉን፤….እነዚያ ደጋግ ሰዎች መምጣታችንን ለጌታቸው ነገሩት፡፡ እርሱም ፈጥኖ ተነሣና ወደ እኛ መጥቶ በሰላም፣ በደስታ ተቀበለን፤  ማረፊያ ቦታም ሰጠን›› በማለት ለቅዱስ ዮሐንስ ስትተርክለት ጽፎታል፡፡

እመቤታችን በጣና ውስጥ ሦስት ወር ከዐሥር ቀን ተቀምጣለች፡፡ በዚህም ምክንያት የጣናን ባሕር የብርሃን መላእክት መጥተው በእሳት ሰይፍ ስለ ከበቧት አጋንንት እንደ ሸሹ፣ መባርቅትም ሊያጠፏቸው እንደ ተከታተሏቸው፣ በዚያም በባሕር እንዳሰጠሟቸውና ወደ ሲኦልም እንደ ጣሏቸው በድርሳነ ዑራኤል ላይ ተጽፏል፡፡ (ደርሳን ዘታኅሣሥ)

እመቤታችን እና ተወዳጅ ልጇ በስደት የቆዩበት ዘመን የተፈጸመውም በኢትዮጵያ ነው፡፡ ‹‹ወመዊቶ ሄሮድስ፤ ናሁ መላከ እግዚአብሔር አስተርዮ በሕልም ለዮሴፍ በምድረ ግብጽ እንዘ ይብል ተንሥእ ወንሣእ ሕፃነ ወእሞ ወሑር ውስተ ምድረ እስራኤል፤ ሄሮድስ ከሞተ በኋላ በግብጽና በኢትዮጵያ ሳለ ከእግዚአብሔር የታዘዘ መልአክ ለዮሴፍ በሕልም ነገረው፤ ብላቴናውንና እናቱን ይዘህ ወደ ምድረ እስራኤል ተመለስ፤ ሕፃኑን የሚፈልጉት ሞተዋልና›› እንዲል፡፡ (ማቴ.፪፥፲፱)  የሄሮድስ መሞት የምሥራቹን የሰሙት በጣና ደሴት ለሦስት ወር ከዐሥር ቀን ያክል ከተቀመጡ በኋላ ነው፡፡ በዚህ ጊዜ መልአኩ እንዲህ አላት፤ ‹‹ተንሥኢ እግዝእትየ ከመ ንሁር ሀገረኪ ናዝሬተ ወተጸዓኒ ዲበ ሠረገላ ብርሃን መልዕልተ ደመና ዘሀሎ፤ ተነሽ ወደ ሀገርሽ ናዝሬት እንሂድ አላትና ሊሄዱ ተነሡ፡፡ ያ ደግ እንግዳ ተቀባይ ሀገረ ገዥ ምነው ምን በደልኩ ለምን ትሔዳላችሁ›› እያለ እያለቀሰ ለመናቸው፡፡

በዚህ ጊዜ መልአኩ ‹‹ምንም አልበደልክም፤ አንዳችም ክፉ ሥራ አልሠራህባቸውም፤ ሄሮድስ ስለ ሞተ ወደ ገሊላ ስለሚመለሱ ነው›› አለው፡፡ ያ መኮንንም ይህን በሰማ ጊዜ ጮሆ አለቀሰ፤ የደሴቱና አካባቢው ሰዎችም እስኪሰበሰቡ ድረስ ጮኸ፡፡ ከዚህ በኋላ ከደመናው በላይ ባለው የብርሃን ሠረገላ ላይ ወጥታ ቆመችና በኢትዮጵያ ውስጥ የሚገኙ ተራሮችን ሁሉ እያሳየ ‹‹ለስምሽ መታሰቢያ ይሁኑሽ›› አላት፤ ባረከቻቸውም፡፡

በዚህ የተደሰቱ የመላእክት ማኅበር በሙሉ ተሰብስበው ‹‹በእንቲአኪ ተራከባ ሣህል ወርትዕ ጽድቅ ወሰላም ተሰዓማ ለዛቲ ሀገረ ኢትዮጵያ ምሕረትኒ ወጽድቅ ይነብር ላይሌሃ..፤ በአንቺም ይቅርታና ቅንነት እውነትና ሰላም ተገናኙ፤ በዚችም በኢትየጵያ ምድር ላይ ምሕረትና እውነት ይኖራሉ›› ሲሉ አመስግነዋታል፡፡ ይህን ሁሉ ከስደቷ መልስ ለዮሐንስ ወልደ ነጎድጓድ የተረከችለት ነው፡፡

ተወዳጆች ሆይ!  እመቤታችንና ኢትዮጵያውያንን ያቆራኛቸው ቃል ኪዳን እስከ ዓለም መጨረሻ መሆኑን እንደተገነዘባችሁ ተስፋ እናደርጋለን፡፡ የማንዘልቀውን ጀምረናልና በዚሁ ይበቃናል፤ ብቻ ዝም ብለን በጠቢቡ ቃል እኛም ‹‹ተመየጢ፥ ተመየጢ፥ ሰላመ ሰጣዊት ወንርአይ ብኪ ሰላመ›› አንቺ የሰላም መፍሰሻ፣ አንቺ የደስታ መገኛ ሆይ፥ ተመለሽ!››  እንበላት፡፡ (መቅድመ ኪዳን)

አሁን ኢትዮጵያውያን ስደተኛ መቀበል አትችልም ስደተኛ ሆናለችና፤ ሱላማጢስ ሆይ አሁን እነዚያ ደጋግ ሰዎች ለእንግዳ ማረፊያ አይሰጡም፤ እነርሱም ማረፊያ መጠለያ አጥተዋልና፤ አሁን የተራበን ለማብላት አቅም የላቸውም፤ እነርሱም ረኃብተኞች ናቸውና፡፡ እናታችን ሆይ ተመለሽ! ሰላማችን ሆይ ነይ! ወደ ዐሥራት ሀገርሽ ተመለሽ! ቃል ኪዳንሽንም አድሽ! የአዲስ ኪዳን ስደተኞች በኩር ሆይ ተመለሽ! መከራችን ያበቃ ዘንድ፣ እንባችን ይታበስ ዘንድ ተመለሽ!

ጨለማው ይገፈፍ ዘንድ፥ ብርሃናችን ሆይ ተገጭ! መላእክት እንደ ተናገሩት ለኢትዮጵያ ምድር ምሕረትና እውነት ይኖሩ ዘንድ ተመለሽ! ሱላማጢስ ሆይ፥ ተመለሽ! ተመለሽ! እናይሽ ዘንድ ተመለሽ! እንበላት፤ ሰላማችን ሆይ ተመለሽ!

ወስብሐት ለእግዚአብሔር!