ሰንበት ትምህርት ቤቶቹ የልምድ ልውውጥ አደረጉ

በይብረሁ ይጥና

ከሲዳማ ሀገረ ስብከት ሀዋሳ ከተማና አካባቢዋ የተውጣጡ የስድስት ሰንበት ትምህርት ቤቶች ተወካዮች በአዲስ አበባ የአምስት ሰንበት ትምህርት ቤቶችን እንቅስቃሴ በመጎብኘት የልምድ ልውውጥ አደረጉ፡፡

ሃያ ዘጠኝ አባላትን ያቀፈው የልኡካን ቡድን፤ በሰንበት ትምህርት ቤቶች መዋቅር አደረጃጀትና አሠራር፣ መዝሙራት፣ የአባላት ክትትልና አያያዝ፣ ሥነ ምግባርና የልማት ጉዳዮች ላይ ውይይት በማድረግም የጋራ ግንዛቤ አግኝቷል፡፡

የልኡካን ቡድኑ አስተባባሪና የሀዋሳ ደብረ ምሕረት ቅዱስ ገብርኤል ገዳም ሰንበት ትምህርት ቤት አባል ወጣት ብስራት ጌታቸው ለስምዐ ጽድቅ ጋዜጣ እንዳስታወቀው፤ «ከየካቲት 19 እስከ 21 ቀን 2002 ዓ.ም ድረስ ከመንበረ መንግሥት ቅዱስ ገብርኤል ገዳም ዓምደ ሃይማኖት፣ መናገሻ ገነተ ጽጌ ቅዱስ ጊዮርጊስ፣ ደብረ ኃይል ቅዱስ ራጉኤል፣ ጽርሐ ጽዮን ሐዋርያት ጎላ ቅዱስ ሚካኤል ቤተክርስቲያን ፍኖተ ብርሃን እና ከልደታ ለማርያም ቤተ ክርስቲያን ተክለ ሳዊሮስ ሰንበት ትምህርት ቤቶች ጋር የልምድ ልውውጥና ውይይት በማድረግ ሰፊ ትምህርት ቀስመናል፡፡» ብሏል፡፡ እንዲሁም፤ «በተለይ የቤተክርስቲያንን ሥርዓት ለማስጠበቅና የሚታዩ ክፍተቶችን ለመሙላት ሰንበት ትምህርት ቤቶች በኅብረት ሆነው መሥራት ጠቃሚ መሆኑን ተረድተናል» በማለት አመልክቷል፡፡

ከአባላቱ መካከል የሀዋሳ ቅዱስ ሩፋኤል ቤተክርስቲያን ሰንበት ትምህርት ቤት ዋና ጸሐፊ ወጣት ሥላስ አዲስ በሰጠችው አስተያየት፤ «ለሦስት ቀናት ባደረግነው ውይይት ጠቃሚና መሠረታዊ የሆነ ነገር አግኝተናል፡፡ ካገኘነውም ተሞክሮ ከተኛንበት እንድንነቃና ሥራዎቻችንን እንደገና እንድንፈትሽ አድርጎናል» ስትል ተናግራለች፡፡

ሌላው በሀዋሳ ደብረ ሰላም ቅድስት ሥላሴ ቤተክርስቲያን ሰንበት ትምህርት ቤት ምክትል ሰብሳቢ ወጣት ይድነቃቸው ጥላሁንም፤ «በአንድ ቤተክርስቲያን ውስጥ ብዙ የአሠራር ልዩነትና ክፍተቶች መኖራቸውን ተረድቻለሁ፡፡ ከዚህ አንፃር እኛ ብዙ መሥራት እንዳለብን ተገንዝቤያለሁ፡፡ በይበልጥ መዝሙራትን በሚመለከት ችግሮች ስላሉ ከጉብኝታትን ባገኘነው ትምህርት ካለፈው በተሻለ ሁኔታ ትኩረት ሰጥተን እንድንሠራ ያደርገናል፡፡ በጠቅላይ ቤተክህነትም አንድ ወጥ በሆነ አሠራር አፈጻጸሙን ለመከታተል ጥረት ቢደረግ በመላው ሀገሪቱ የሚገኙ ሰንበት ትምህርት ቤቶችን ለመቆጣጠር ይመቻል፡፡» ሲል አስተያየቱን ሰጥቷል፡፡

በአዲስ አበባ የመንበረ መንግሥት ግቢ ገብርኤል ገዳም ዓምደ ሃይማኖት ሰንበት ትምህርት ቤት አባል ደነቀ ማሞ በበኩሉ ውይይቱን አስመልክቶ በሰጠው አስተያየት፤ «ከሀዋሳ ከመጡ ስድስት ሰንበት ትምህርት ቤቶች ጋር የልምድ ልውውጥ መደረጉ በሰንበት ትምህርት ቤቶች መካከል የጋራ ግንዛቤ እንዲኖር ያስችላል፡፡ ስለሆነም ሌሎች ሰንበት ትምህርት ቤቶችም ይህን አርአያ ቢከተሉ ጠቀሜታው የጎላ ነው» ሲል ተናግሯል፡፡

ሰንበት ትምህርት ቤቶች በአንድነት ሆነው መወያየታቸው የቤተ ክርስቲያንን ሥርዓትና ትውፊት ለመጠበቅ ትልቅ ድርሻ እንዳለው ይታመናል፡፡