‹‹ሰላምን እተውላችኋለሁ፤ ሰላሜን እሰጣችኋለሁ›› (ዮሐ. ፲፬፥፳፯)

ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በወንጌል ለሕዝቡ ‹‹ሰላምን እተውላችኋለሁ፤ ሰላሜን እሰጣችኋለሁ…›› ብሎ በነገራቸው ቃሉ ሰላምን የሚሰጠው እርሱ እንደሆነ እንረዳለን፤  ይህም የተወልን ሰላም መንፍሰ ቅዱስ በመሆኑ መንፈስ ቅዱስ በአንድ ሰው ውስጥ ሲያድር የልብ ሰላምን ይጎናጸፋል፡፡ ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ ስለዚህ ሰላም ሲጽፍ እንዲህ ብሏል፤‹‹አእምሮውንም ሁሉ የሚያልፍ የእግዚአብሔር ሰላም ልባችሁንና ሀሳባችሁን በክርስቶስ ኢየሱስ ይጠብቃል፤›› (ዮሐ. ፲፬፥፳፯፤ ፊል. ፬፥፯)

ማንኛውም ዓይነት ውጫዊ ተጽእኖ ቢገጥመው ሰላም ያለው ሰው አይታወክም፤ አይጨነቅም ወይም አይረበሽም፡፡ የእርሱ ሰላም የሚመሠረተውም በእግዚአብሔር ጥበቃና እንክብካቤ፣ በሰው መተማመንና በእርሱ ቃል ኪዳኖች ላይ ባለው እምነት እንጂ ከውጪ ባሉ ሁኔታዎች ላይ አይደለም፡፡

እግዚአብሔር እስከ አለ እና እስከ ጠበቀን ድረስ ምንም ዓይነት ፍራቻ በውስጣችን ሊኖር አይገባም፤ ይህ በመሆኑም ነቢዩ ዳዊት እንዲህ በማለት ተናግሯል፤ ‹‹በሞት ጥላ መካከል እንኳ ብሄድ፤ አንተ ከእኔ ጋር በነህና ክፉን አልፈራም፤ በትርህና ምርኩዝህ እነርሱ ያጽናኑኛል፡፡›› የዳዊት ሰላም ምንጭ እግዚአብሔር ከእርሱ ጋር የመሆኑ እውነት ነው፡፡ (መዝ. ፳፪፥፬)

ሐዋርያት በታንኳ ሲጓዙ ጌታ ያንቀላፉ ስለመሰላቸው ሞገዱ ሲያናውጣቸው በጣም ተጨንቀው፤ ሰላማቸውን አጥተው ነበር፡፡ በእነርሱ ላይ የበረታው ውጪያዊው ሁኔታና የጌታ ሥራ ከእነርሱ ጋር ያለ መስሎ ስላልታያቸው ነው፡፡ ስለሆነም ጌታ ተነሥቶ ነፋሱን በመገሠጽ ሰላማቸውን መልሶላቸዋል፡፡

ውስጣቸው ጥብቅ ከሆነና በእምነታቸውም የጸናኑ ከሆኑ ከውጪ ያለ ምንም ዓይነት ነገር እንደማያናውጣቸው ነገራቸው፤ ነፋስና ጎርፍ እንዳልጣለውና በዓለት ላይ እንደተገነባው ቤተ እንዲሆኑም አዘዛቸው፤ ያም ቤት ውስጡ ጥብቅ ነበረና፡፡

ጠንካራ መርከብ በሚመታው ብርቱ ማዕበል ጉዳት ሊደርስበት አይችልም፡፡ መርከብ የሚጎዳው ወደ ውስጡ ውኃ የሚያስገባ ቀዳዳ ሲኖር ነው፡፡

ቅዱስ እንጦንስ ለልብ ሰላም ምሳሌ የሚሆን ሰው ነው፡፡ ሐዋርያው ቅዱስ አትናቴዎስ ስለ  እርሱ ሲናገር፤  ‹‹መሪር ነፍስና የታወከ ሀሳብ ያላቸው ሰዎች ሁሉ የቅዱስ እንጦንስን መልክ ሲመለከቱ ልባቸው በሰላም ይሞላል›› ብሏል፡፡ (ፍኖተ አትናቴዎስ)

ሰላሙ የበዛለት ሰው ለሌሎች ሰላም መስፈን ምክንያት ይሆናል፤  ሰላም ስናገኝ  በሥጋዊ ሆነ በመንፈሳዊ መንገድ ውስጥ በመልካም ጤንነት እንኖራለን፡፡ የክርስቲያኖች በሰላም በአንድነት ለመኖር ደግሞ የቤተክርስቲያን ሰላም ሊጠበቅ ይገባል፡፡

‹‹አቤቱ  ጌታችን ሆይ፤ አንዲት ቅድስት ዓለማቀፋዊትና ሐዋርያዊት የሆነች ቤተ ክርስቲያንህን አስባት፤ በሰላምም ጠብቃት›› የሚለው ጸሎት ስለ ቤተክርስቲያን በየዕለቱ የሚጸለየውም ለዚህ ነው፡፡ ይህን ጸሎት ከሌሎች የንስሓ ጸሎቶች ሁሉ በፊት እንጸልየዋለን፡፡ በመሆኑም በሰርክ ጸሎት ማዕጠንት፤ በነግህ ጸሎት ማዕጠንት፤ ካህኑ በመሠቂያው ዙሪያ እየዞረ ዘወትር ሲጸለይም ይህን ጸሎት ይጸልያል፡፡

ቅዳሴ ከመጀመሩ በፊትና መባ ከመቅረቡ በፊት ደግሞ እንዲህ ብለን እንጸልያለን፤ ‹‹አንዲት፤ ቅድስት፤ ዓለማቀፋዊትና ሐዋርያዊት ለሆነችው የእግዚአብሔር ቤተ ክርስቲያን ሰላምና ቅድስና አድላት፤››  ካህናት ሲሾሙም ይህን የዘወትር ጸሎት እንጸልያለን፡፡

ለንጉሥ በሚደረግ የዘወትር ጸሎት ውስጥም ‹‹አንዲት፤ ቅድስት፤ ዓለማቀፋዊትና ሐዋርያዊት ለሆነችው ቤተ ክርስቲያንህ ሰላም ልቡን ዳስሰው›› በማለት ስለ ቤተክርስቲያን እንጸልያለን፡፡

የቤተክርስቲያን ሰላም የአባቶቻችን ሐዋርያትና የቅዱሳን ሁሉ አንዱና ዋነኛው ጠቃሚ ጉዳያቸው ነበር፡፡ ለእነዚህ ሁሉ አባቶች ይህች ቤተክርስቲያን እስከ ሰማያዊው መንግሥት ድረስ የምትዘረጋ በምድር ያለች የእግዚአብሔር መንግሥት ምሳሌ ናት፡፡ የምትወክለውም የእምነትን ምንጭና እግዚአብሔር ከሕዝቡ ጋር የመኖሩን እውነት ነው፡፡ አንድ ሰው በጸሎቱ ውስጥ ለራሱ ከሚያቀርበው ጥያቄ ይልቅ ለእርሷ ስለሚጠይቅ ሰላሟና ደኅንነቷ የእያንዳንዱ ሰው የጸሎት መሠረት ነው፡፡ ይህ ጥያቄ መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ባስተማረን ጸሎት ውስጥ የተመስጦአችን ማዕከል ስለሆነ ‹‹ስምህ ይቀደስ፤ መንግሥትህ ትምጣ፤ ፈቃድህ በሰማይ እንደሆነች እንዲሁም በምድር ትሁን…›› እያልን እንጸልያለን፡፡

ስለ ቤተክርስቲያን መጸለይ በምእመናን፣ በእረኞቹና በመጋቢዎቹ አንደበት ውስጥ ለብዙ መቶ ዓመታት የቆየ ታላቅ ጸሎት ነው፡፡ ራሳቸውን ከዓለም ለለዩ መነኮሳት በሚደረግ የቅዳሴ ጸሎት ውስጥ እንኳ ለቤተክርስቲያን ሰላም አንጸልያለን፡፡

የመናኞች ሁሉ ታላቅ አባት የሆነው የመጀመሪያው ባሕታዊ አባ ጳውሊ ቅዱሱን አባ እንጦንስን ስለ ቤተክርስቲያን ሰላም መጠየቁ እንደምን ያለ ድንቅ ነገር ነው፡፡ ይህን ጸሎት የምንጸልየው ከልባችን ነው፡፡ የምንጸልየው የቅዳሴ አንድ ክፍል አድርገን ሳይሆን እንደ ሕያውና እንደሚያቃጥል ስሜት እየሆነብን ነው፡፡ እያንዳንዱ ሰው ስሜቶቹን ሁሉ በዚህ ጸሎት ውስጥ በማደረግ ለቤተክርስቲያን መጸለይ ይገባል፤ እግዚአብሔር አምላካችን ሰላሙን ይስጠን፤ አሜን፡፡

ምንጭ፤ ‹‹መንፈሳዊ ቃላትና ጥቅማቸው- ክፍል አንድ፤›› በግብጽ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ፓትርያርክ አቡነ ሺኖዳ ሣልሳዊ፤ ትርጉም አያሌው ዘኢየሱስ