ርእሰ ዓውደ ዓመት ዮሐንስ

ክፍል ሁለት

በዓሉ እንዴት ይከበራል?

በማኅበረ ቅዱሳን ዐቢይ ማዕከል መምህር የሆኑት ሊቀጠበብት ሐረገወይን አገዘ «ቤተ ክርስቲያን በዓሉን በመንፈሳዊና ማኅበራዊ ክንውኖች ታከብረዋለች» በማለት እንደሚከተለው ያስረዳሉ፡፡
 

መንፈሳዊ ክንውኖች

የቅዱስ ዮሐንስ መጥምቅ ጽላት ባለባችው አብያተ ክርስቲያናት ከዋዜማው /ጳጉሜን 5/6/ ከሰዓት/ ጀምሮ በሌሎቹ ደግሞ ከምሽት ጀምሮ ማኅሌት ይቆማል፡፡ በዕለቱ ቅዱስ ዮሐንስ መጥምቅን እና የአዲስ ዓመትን መግባት በሚያነሱ ያሬዳዊ ዜማዎች ምስጋና ሲቀርብ ያድራል፡፡

በበዓሉ ዕለት ጠዋት /ረቡዕ እና ዓርብ ከሆነ ከሰዓት/ ቅዳሴ ይቀደሳል፤ ካህናትና ምዕመናንም ሥጋ ወደሙ ይቀበላሉ፤ ቤተ ክርስቲያን በዓላትን የምታከብርበት ዋና ምክንያትም ይኸው ነውና፤ ምዕምናን ሥጋ ወደሙ የሚቀበሉበት የዕረፍት ቀን ያገኙ ዘንድ፡፡

አይሁድ የዘመን መለወጫ በዓላቸው የሆነውን ሮስ ሆሻና /በዓለ መጥቅዕ/ በሚያከብሩበት ዕለት ሊቀ ካህናቱ የአገልግሎት አልባሳቱን ለብሶ ቆሞ የዓመቱ በዓላት የሚውሉበትን ቀን ያውጅ ነበር፡፡ ቤተ ክርስቲያንም ይህንን ትውፊት በመከተል ከቅዳሴ በኋላ /ቅዳሴው ከሰዓት ከሆነ ከቅዳሴው ቀደም ብሎ ሊሆን ይችላል/፡፡ የባሕረ ሀሳብ አዋቂ የሆኑ አባቶች የዓመቱ ተለዋዋጭ በዓላትና አጽዋማት የሚወሉባቸውን ቀናት በባሕረ ሃሳብ ቀመር እያሰሉ ያውጃሉ፡፡ 

በዚህም መሠረት መስከረም አንድ ቀን 2002 . የሚከተለው ይታወጃል፡፡ ዘመኑ ዘመነ ማርቆስ ነው፡፡

 

በዓላት /አጽዋማት

የሚውሉበት ቀን

ጾመ ነነዌ

ጥር 17

ዐቢይ ጾም

የካቲት 1

ደብረ ዘይት

የካቲት 28

ሆሣዕና

መጋቢት 19

ስቅለት

መጋቢት 24

ትንሣኤ

መጋቢት 26

ርክበ ካህናት

ሚያዝያ 20

ዕርገት

ግንቦት 5

ጰራቅሊጦስ

ግንቦት 15

ጾመ ሐዋርያት

ግንቦት 16

ጾመ ድኅነት

ግንቦት 18

 

ከዚህ በኋላ በዓመቱ የሚቀርቡ መስዋዕቶችን ሁሉ ወክለው ስንዴ /መገበሪያ/ ወይን /ዘቢብ/ ዕጣን፤ ጧፍ፣ወዘተ ይቀርቡና ይባረካሉ፡፡ በመጨረሻም ሠርዎተ ሕዝብ ይደረጋል፤ ሕዝቡ ይሰናበታል፡፡

ማኅበራዊ ክንውኖች

«ከዚህ በኋላ ማኅበራዊ ክንውኑ ይቀጥላል» ይላሉ ሊቀ ጠበብት ሐረገ ወይን፡፡ በዓሉን ምክንያት አድርገው ሰዎች ወዳጆቻቸውን፣ ዘመዶቻቸውን እንዲሁም የተቸገሩትና የሚበሉት የሚጠጡት ያጡ ወገኖችን በመጥራት ይጋብዛሉ፡፡ እነርሱም ይጋበዛሉ፡፡

«ይህ በበዓላት ላይ በእምነት ከማይመስሉን ጋር ሳይቀር የሚደረገው መተሳሰብና የፍቅር ግንኙነት ማኅበረሰቡን አንድ አድርጎ ይዞ የኖረ ገመድ ስለሆነ ልንጠብቀው ይገባል፡፡» ይላሉ ሊቀጠበብት፡፡

ከዚህም በተጨማሪ «በዓሉን ስናከብር የተቸገሩ፣ የሚበሉትና የሚጠጡት ያጡ ነዲያን ወገኖቻችንን ልናስብና «ብራብ አብልታችሁኛል» የሚለውን አምላካዊ ምሥጋና ለመስማት የሚያበቃ ሥራ ለመሥራት ልንተጋ ይገባናል» በማለት ያሳስባሉ፡፡

የበዓሉ መንፈሳዊ ትርጉም /ፋይዳ

የአዲስ ዓመት በዓል ለእኛ ለመንፈሳዊያን ሁለት ዋና ዋና መንፈሳዊ ትርጉሞች /ፋይዳዎች/ አሉት፡፡

  1. የምስጋና ዕለት ነው

በእርግጥ እግዚአብሔርን ማመስገን የዘወትር ተግባራችን መሆን አለበት፡፡ እርሱ ኅልፈት የሌለበት ዘመናትን ግን የሚያሳልፍና የሚለዋውጥ እግዚአብሔር ያለፈውን ዓመት አሳልፎ ለአዲስ ዓመት ሲያደርሰን ደግሞ ቢያንስ ለሚከተሉት ሁለት ምክንያቶች ልናመሰግነው ይገባል፡፡

. ቅዱስ ዳዊት «ወትባርክ አክሊለ ዓመተ ምሕረትከ፤ የምህረትህነ ዓመት ትባርካለህ» /መዝ.64.11/ እንዳለው ያለፈውን ዓመት ሙሉ በመግቦቱ ከምንተነፍሰው አየር ጀምሮ የሚያስፈልገንን ነገር ሁሉ ስላዘጋጀልንና በጠብቆቱም እኛ ከምናውቃቸውና ከማናውቃቸው ነገሮች ጠብቆ ወደ አዲሱ ዓመት ስላደረሰን ልናመሰግነው ይገባናል፡፡

. ቅዱስ ዳዊት «አንተ ኃጢአትን ብታስብ፤ አቤቱ በፊትህ ማን ይቆማል» እንዳለው እግዚአብሔር ኃጢአታችንን ቢያስብብን እና እንደ ኃጢአታችን ቢፈርድብን አንዲት ደቂቃ እንኳን መኖር አንችልም ነበር፡፡ እርሱ ግን ኃጢአታችንን እየታገሰ፤ አይቶ እንዳላየ እየሆነ በንስሃ እንድንመለስ ዕድሜ ይጨምርልናል፡፡ ሰዎች ወደ ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ሔደው ጲላጦስ ስለገደላቸውና ደማቸውን በመስዋዕታቸው ጋር ስለቀላቀለው ሰዎች የነገሩት፡፡ እርሱም መልሶ እንዲህ አላቸው «ይህች መከራ ስላገኘቻቸው እነዚህ ገሊላውያን ከገሊላ ሰዎች ይልቅ ተለያይተው ኃጢአተኞች የሆኑ ይመስሉአችኋልን? አይደለም፡፡ እላችኋለሁ፤ እናንተም ንስሓ ካልገባችሁ እንዲሁ ትጠፋላችሁ፡፡» አላቸውና የሚከተለውን ምሳሌ ነገራቸው፡፡

«አንድ ሰው በታወቀች በወይኑ ቦታ ውስጥ በለስ ነበረችው፤ ፍሬዋን ሊወስድ ወደ እርስዋ ሔዶ አላገኘም፡፡ የወይኑን ጠባቂም፡– «የዚችን በለስ ፍሬ ልወስድ ስመላለስ እነሆ ሦስት ዓመት ሆነኝ አላገኘሁም፤ እንግዲህስ ምድራችንን እንዳታቦዝን ቁረጣት» አለው፡፡ እርሱም መልሶ እንዲህ አለው «አቤቱ አፈር ቆፍሬ በሥሯ እስካስታቅፋት ፍግም እስከ አፈስባት ድረስ የዘንድሮን ተዋት፡፡ ምናልባት ለክረምት ታፈራ እንደሆነ ያለዚያ ግን እንቆርጣታለን» /ሉቃ.131-9/

ስለዚህ የዘመን መለወጫን በዓል የምናከብረው እግዚአብሔር በዕድሜያችን ላይ ሌላ ዓመት የጨመረልን በቸርነቱ ኃጢአታችንን ታግሶ የንስሐ ጊዜ ሊሰጠን መሆኑን በማስተዋልና ለዚህም ምስጋና በማቅረብ፤ እንዲሁም ቀጥለን እንደምንመለከተው የተጨመረልንን ዓመት ተጠቅመን ለከርሞ አፍርተን እንድንገኝ ለንስሐ እና ለለውጥ በመነሣት መሆን አለበት፡፡

2. ንስሐ እና ለውጥ

ንስሐ ማለት በኃጢአት መጸጸት፤ ኃጢአትን ለመተውና አዲስ ሕይወት ለመጀመር መወሰን ማለት ነው፡፡

ሐዋርያው ቅዱስ ጴጥሮስ እንዲህ ይላል፤ «የአህዛብን ፈቃድ ያደረጋችሁበት፤ በመዳራትና በሥጋ ምኞትም፣ በስካርም፣ በዘፈንም ያለ ልክም በመጠጣት ነውርም ባለበት በጣዖት ማምለክ የተመላለሳችሁት ያለፈው ዘመን ይበቃል» /1ጴጥ. 4.3/

መንፈሳዊ ሕይወትና የክርስትና ጉዞ ሁል ጊዜ ራስን መመርመርና የቆሙበትን ማወቅ፤ ከዚያም የተሻለ ነገር ለማድረግ መወሰንን ይጠይቃል፡፡ ይህ ሁል ጊዜ መደረግ ያለት ቢሆንም የዘመን መለወጫ ወቅት ደግሞ ይህን ለማድረግ የሚያስችል የተሻለ የሥነ ልቡና ዝግጅት ያለበት መልካም አጋጣሚ ነው፡፡

ስለዚህ የዘመን መለወጫ በዓልን ስናከብር ከበዓሉ አስቀድሞ ወይም በኋላ ባሉት ቀናት ውስጥ ይህንን ለማድረግ ጊዜ መመደብና ቁጭ ብለን በዕርጋታና በጥሙና ያለፈውን ዓመት መገመግም፣ የነበሩትን ደካማ ጎኖች /ችግሮች/ እና ጠንካራ /መልካም/ ነገሮች ነቅሰን ማውጣት ከነበሩት ችግሮች ውስጥ በአዲሱ ዓመት ልንፈታቸው የሚገቡ ችግሮችን ለይተን ማስቀመጥ ይገባናል፡፡ ከዚያም ቅዱስ ያዕቆብ በመልእክቱ «እግዚአብሔር ቢፈቅድና ብንኖር ይህን ወይም ያንን እናደርጋለን ማለት ይገባችኋል» /ያዕ.4.15/ እንዳለው፡፡ እያንዳንዳቸውንም እንዴት አድርገን እንደምንቀርፋቸው አስበን ስልት መቀየስና ዕቅድ ማውጣት ዕቅዳችንን ለመፈጸምም መወሰን ይገባናል፡፡

ሊቀጠበብት ሐረገወይን «የምንቀበለው ዓመትአዲስሊባል የሚችለው እኛ መታደስ ከቻልን ብቻ ነው» ይላሉ፡፡

ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ሐዲስ ኪዳንን ሲመሠርት በብሉይ ኪዳን የነበሩ ነገሮችን አድሷቸዋል፡፡ ደካማ የነበሩትንም ነገሮች አጠንክሯቸዋል አበርትቷቸዋል፡፡ በብሉይ ኪዳን የነበሩትን ክህነት፣ መስዋዕት፣ ሕግ፣ በኃጢአት የተበላሸውን የሰው ልጅ ባሕርይ እና ሌሎቹንም ሁሉ መቅረት ያለባቸውን አስቀርቶ፣ መስተካከል ያለባቸውን አስተካክሎ፣ ሐዲስ ኪዳንን ሠርቷል፡፡ ጌታችን ይህንን ካደረገ በኋላ ያለውን ዘመን «ዘመነ ሐዲስ» ያስባለው የእነዚህ ነገሮች መስተካከል ነው፡፡

«ይህ በእያንዳንዳችን ሕይወት መደረግ አለበት፡፡ መጪው ዓመት አዲስ ዓመት፣ አዲስ ዘመን የሚሆንልን ዓመቱ ችግሮቻችንን ቀርፈን፣ ጥንካሬዎቻችንን አጎልብተን የተሻለ ሕይወት የተሻለ አመለካከት የተሻለ ሥራ የምንጀምርበት ከሆነ ነው፡፡ ይህ ካልሆነና አምና የነበረውን ችግር ሁሉ መልሶ መድገም ካለ ግን ዓመቱ ለእኛ አዲስ ዓመት አይደለም» ይላሉ ሊቀጠበብት፡፡

ይህ ነገር በግለሰብ ብቻ ሳይሆን በቤተሰብም በአገልግሎታችንም ሁሉ መደረግ አለበት፤ ያን ጊዜ እውነትም ወደ አዲሱ ዓመት እንሸጋገራለን፡፡

«የዘመን መለወጫ በዓል የአዲስ ሕይወት መጀመሪያ እንዲሆንልን የአምላካችን ቅዱስ ፈቃድ ይሁንልን፡፡ የእመቤታችን የቅድስት ድንግል ማርያም፣ የጻድቃን፣ የሰማዕታት፣ የመላእክት፣ የቅዱሳን ሁሉ አማላጅነትና ተራዳኢነት ከእኛ ጋር ይሁን፡፡

 ወስብሐት ለእግዚአብሔር