ሥርዓተ አምልኮ

ክፍል ሦስት

ጥር ፰፤፳፻፲፭ ዓመተ ምሕረት

ሥርዓተ ክብረ በዓላት

በዓላት ከማንኛውም ቀናት የበለጠ አምላካችን እግዚአብሔርን የምናመሰገንባቸውና የምናወድስባቸው፣ የተቀደሱትን ዕለታት በማሰብና በመዘከር በዝማሬ፣ በሽብሻቦና በእልልታ የምናከብርባቸው ናቸው፡፡ ታቦታት ከመንበረ ክብራቸው የሚወጡባቸውና ሕዝበ ክርስቲያኑን የሚባርኩባቸው ስለሆኑም በክብርና በድምቀት ይከበራሉ፡፡   

በዓል

በዓል አብዐለ፣አከበረ›› ከሚለው የግእዝ ግሥ የተገኘ ነው፡፡ የቃሉ ትርጕም ደግሞ ‹‹መታሰቢያ ማድረግ፣ ማክበር፣ ማሰብ፣ መዘከር፣ ማስታወስ›› ማለት ነው፡፡ ከዚህም ባሻገር በዓል በቁሙ ‹‹የደስታ እንዲሁም የዕረፍት ቀን እንደሆነ አለቃ ኪዳነ ወልድ ክፍሌም በመዝገበ ቃላታቸው ላይ ገልጸዋል፡፡ (ገጽ ፪፸፱)

በቤተ ክርስቲያን አስተምህሮና በምእመናን ዘንድ የተለመደው አስተሳስብና አመለካከት ደግሞ በዓል “በዓመትና በወር የሚከበር፣ ያለፈ ነገር የሚታሰብበት፣ ሕዝብ የበዓሉን ምሥጢር እያሰበ ደስ ብሎት እና በአማረ ነጭ ልብስ አጊጦ የሚዘምርበት፣ እልል የሚልበት፣ ሽብሸባና ጭብጨባ የሚያደርግበት (የሚያበዛበት) ቀን››  ነው፡፡

የበዓላት ዓይነት

በቤተ ክርስቲያን አስተምህሮ በዓላት ሁለት ዓይነት ናቸው፡፡ በቤተ ክርስቲያን የሚከበሩ እና በዐደባባይ የሚከበሩ በዓላት ተብለውም ይጠራሉ፡፡

በቤተ ክርስቲያን የሚከበሩ በዓላት

ቅድስት ቤተ ክርስቲያናችን በየወሩም ሆነ በየዓመቱ በቀዳሚነት በአምላካችን ስም የሚታሰቡ በዓላትን ማለትም ‹‹በአጋዝእተ ዓለም ሥላሴ፣ በቅዱስ አማኑኤል፣ በጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ››  እና በእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ስም ማለትም ‹‹ልደታ ለማርያም፣ በዓታ ለማርያም፣ ኪዳነ ምሕረት፣ ብዙኃኗ ማርያም፣ በዓለ አስተርእዩ ለማርያም እና ፍልሠታ ለማርያምን›› ታከብራለች፡፡ ከዚህ በተጨማሪ ደግሞ የሊቃነ መላእክትን፣ የቅዱሳንን፣ የጻድቃንና የሰማዕታትን የመታሰቢያ በዓል ታከብራለች፡፡

በቤተ ክርስቲያን የሚከበሩ ዓመታዊ በዓላት አከባበር ሥርዓት ከዋዜማ ጀምሮ እስከ ዕለቱ ሠርክ ጉባኤ ድረስ ይዘልቃል፤ በቅዱስ ያሬድ ዝማሬ ማኅሌተ ጽጌ ታጅቦ የሚከበረው የበዓሉ ዋዜማ ከምሽት ጀምሮ በሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያን ማኅሌትና በምእመናን እልልታና ጭብጨባ ደምቆ ያድራል፡፡

ከጸሎተ ኪዳንና ቅዳሴ በኋላም ታቦተ ክብሩ ከመንበሩ ወርዶ በቤተ ክርስቲያን የተሰበሰበውን ሕዝብ ለመባረክ ዑደት በሚያደርግበት ጊዜ የደብሩ ሰንበት ትምህርት ቤቶች ዕለቱን በተመለከተ የተማሯቸውንና ያጠኗቸውን መዝሙራት በቅደም ተከተል ያቀርባሉ፡፡ ታቦቱም ሦስት ጊዜ ዑደት አድርጎ በዐውደ ምሕረቱ ሲቆም ሊቃውንቱ እንዲሁም የአባቶቻቸውን ፈለግ በመከተል የሰንበት ተማሪዎች ወረብ ያቀርባሉ፡፡

በመቀጠል ደግሞ ለክብረ በዓሉ የተመረጡ ብቁ መምህራን ለዕለቱ በሚመጥን መልኩ ቃለ እግዚአብሔርን ካስተማሩ በኋላ በሰዎች ዘንድ የሚደረጉ ምስክሮችና ሥዕለቶች በዐውደ ምሕረቱ ይነገራሉ፡፡ አልፎ አልፎም ከቤተ ክርስቲያን ልማት ጋር የተያያዙ ሥራዎች፣ ርእሰ ጉዳዮች፣ ገለጻዎች እንዲሁም በምእመኑ የሚደረጉ መዋጮዎች ይከናወናሉ፡፡

የደብሩ አስተዳዳሪ የሆኑ የቤተ ክርስቲያን አባቶች ቃለ ምዕዳን ከሰጡ በኋላም ታቦተ ክብሩ በዝመሬ፣ በእልልታና በጭብጨባ ታጅቦ ወደ መንበረ ክብሩ ይመለሳል፡፡ ሕዝቡም የቀረውን ጊዜ በተገቢው መንገድ ለማክበርና ለመዘከር ወደ ቤቱ ይሄዳል፡፡ ለበዓል ባዘጋጁት መዐድም ከቤተሰቦቻቸው ጋር እንዲሁም ከነዳያን ጋር በማቋደስ ያከብራሉ፡፡

ከዚያም ተመልሰው በሠርክ ጉባኤ ጸሎት ካደረሱ በኋላ ለዕለቱ ከሚመደቡ ዘማርያን ጋር በመሆን በዓሉን ያከብራሉ፡፡ በተጋባዥ መምህራንም ከቀኑ የቀጠለ ትምህርት በመማር እስከ ምሽት ድረስ ከካህናቱ ጋር ይቆያሉ፡፡ በመጨረሻም በዓሉን አባቶች በጸሎት ያሳርጉታል፡፡

የዐደባባይ በዓላት አከባበር

በኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ሃይማኖት አስተምህሮ መሠረት የዐደባባይ በዓላት ሁለት ናቸው፡፡ እነርሱም የመስቀልና የጥምቀት በዓላት ናቸው፡፡ እነዚህም የጌታችን የመድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ግማደ መስቀል በቅድስት ዕሌኒ መጋቢት ፲ ከመገኘቱ በፊት መስከረም ፲፯ ቁፋሮ ያስጀመረችበት  እና መስከረም ፲፮ ለመስቀሉ ቤተ መቅደስ የሠራችለት ቀን እንዲሁም ጌታችን ኢየሱስ በመጥምቀ መለኮት ቅዱስ ዮሐንስ እጅ በጥር ፲፩ የተጠመቀበት ቀን ታቦተ ክብሩ ከመንበሩ ወርዶና ከየአጥቢያ ቤተ ክርስቲያኑ በሚወጡ ካህናትና አገልጋዮች ታጅቦ ወደ መስቀል ዐደባባይ እንዲሁም ወደ ባሕረ ጥምቀቱ ስፍራ የሚወርድበት ሂደት በመሆኑ እነዚህ ሁለት በዓላት የሚከበሩት በዐዳባባይ ነው፡፡ በመቀጠልም የበዓላቱን አከባበር ነጣጥለን በአጭሩ እንመለከታለን፡፡

 የመስቀል በዓል አከባበር   

በሀገራችን ኢትዮጵያ የመስቀልን በዓል የምናከብረው ከመስከርም ፲፮ ቀን ደመራ በመደመርና ችቦ በማብራት ነው፡፡ ይህም ንግሥት ዕሌኒ መስቀሉን ለማግኘት ፍለጋ ስትሰማራ ያደረገችውን ክንውን የሚያወሳና የሚዘክር ነው፡፡

በመስከረም ፲፯ ቀን ደግሞ በተለይም መስቀሉ የተገኘበትን ቀን በማውሳት ሌሊቱን በማኅሌተ  ጽጌ ዝማሬ ነግህኑን በጸሎተ ኪዳንና በቅዳሴ እንዲሁም ዕለቱን ደግሞ ታቦቱን በማጀብ በዓሉ ተከብሮ ይውላል::

በየዓመቱ በመስቀል ዐደባባይ በመገኘት በዓሉን በሽዎች የሚቆጠሩ ሰዎች በመስቀል ዐደባባይ ተግኝተው ያከብራሉ፡፡ በዚህም ሥርዓት ውስጥ ጌታችን አምላካችን  መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ለእኛ ያደረገልንን ሁሉ በማሰብና ቀኑንን በመዘከር እርሱን እያመሰገንን እንውላለን፡፡ ሆኖም ግን በቅርብ ጊዜ በመስቀል ዐደባባይ መከበር ከጀመረ ዘመናት ያስቆጠረውን የመስቀል በዓል ‹‹እኛም አንድ ሃይማኖታዊ ሁነት ፈጥረን ማክበር አለብን›› በሚል ሰበብ በእስልምና ሃይማኖት ታሪክ ውስጥ የሌለ ‹‹የዐደባባይ አፍጥር መርሐ ግብርን›› ምክንያት አድርጎ ቦታውን ዒላማ በማድረግ በመነሣት ክብረ በዓሉ እንዳይከበር ለማገት የተሞከረ ቢሆንም አለመግባባቶች ተፈትተውና ችግሮቹ ተቀርፈው የመስቀል በዓል እንደ ቀድሞ መከበር ቀጥሏል፡፡

ከዚህም ባሻገር ምእመናን በየአጥቢያ ቤተ ክርስቲያናቸውም በመገኘት የመስቀል በዓልን ደመራ በመለኮስ፣ ችቦ በማብራትና ሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያንን በማጀብ ያከብራሉ፡፡

የጥምቀት በዓል አከባበር

የጥምቀት በዓል በሀገራችን የሚከበረው ከዋዜማው ከከተራ ጀምሮ ታቦታቱ ከየአብያተ ክርስቲያናቱ በክብር ወጥተው በሕዝቡ እልልታ፣ ሽብሽባ እና በካህናቱ ያሬዳዊ ዜማ ወደ ወንዝ አልያም ወደተዘጋጀ የውኃ ቦታ በመውረድ ሕዝቡን በሰፊው የሚያሳተፍበት የጥምቀት ሥነ ሥርዓቱን በማከናወን ነው።

በዓሉ በተለይ በጎንደር ከተማ በድምቀት ይከበራል፡፡ የበርካታ ታቦታት መገኛ የሆነችው ከተማዋ ሕዝቡን ለማጥመቅ የምትጠመቅበት የቅዱስ ፋሲለደስ ቤተ ክርስቲያን ያለበት የሚዋኝበት የጥምቀት ስፍራ ነው፡፡ በባሕረ ጥምቀቱ አካባቢ መቀመጫ መድረክ እንዲሁም እስከ ፶ ሜትር የሚረጭ የውኃ ማስተላለፍያም በማዘጋጀት በጥር ፲፩ ቀን ሊቀ ጳጳሳቱ ሕዝበ ክርስቲያኑን ያጠምቃሉ!

ከበዓሉ ረድኤት ያሳትፈን፤ አሜን!

ይቆየን!