‹‹ሞትን አትፍሩ፤ ኃጢአትን ፍሩ›› ቅዱስ ያሬድ

የሰው ዘር በሙሉ ምድራዊ ሕይወቱ የሚፈጸምበት ዕለተ ሞቱ በመሆኑ ከዚህች ዓለም  ይለያል፡፡ ነፍሳችን ከሥጋዋ ስትለይም ሥጋችን ሕይወት አይኖረውምና በድን ይሆናል፤ ሥጋ ፈራሽ እና በስባሽ ስለሆነም ወደ መቃብር ይወርዳል፤ ይህም ሥጋዊ ሞት ነው፡፡ አለቃ ኪዳነ ወልድ ክፍሌ መጽሐፈ ሰዋስው ወግስ ወመዝገበ ቃላት ሐዲስ በሚል መጽሐፋቸው ‹‹መሞት፣ መለየት፣ በነፍስ ከሥጋ፣ በሥጋ ከነፍስ መራቅ፣ እየብቻ መሆን፣ መድረቅ፣ መፍረስ፣ መበስበስ፣ መነቀል፣ መፍለስ፣ መጥፋት፣ መታጣት›› ሲሉ ስለሞት አስረድተዋል፡፡ (ኪዳነ ወልድ፣ገጽ፣፭፻፹፩)

ሆኖም ነፍስ በባሕርይዋ አትሞትም፤ ስንፈጠር ጀምሮ አምላካችን እግዚአብሔር እስትንፋሱን እፍ ብሎ ሕያው እንዳደረገን ነፍስ እስከዘለዓለም ትኖራለች፡፡ ነገር ግን ከቆሸሸችና  ከአደፈች  መጨረሻዋ ከገነት ይልቅ ሲኦል ሊሆን ይችላል፡፡ ይህም ሞተ ነፍስ ነው፤ ‹‹ሞት በቁሙ የሥጋዊና የደማዊ ሕይወት ፍጻሜ በአዳም ኃጢአት የመጣ ጠባይዓዊ ዕዳ ባሕርያዊ ፍዳ›› እንደተባለው የሰው ልጅ ለኃጢአቱ ንስሓ ሳይገባ ከሞተ በነፍሱ ወደ ሲኦል ይወርዳል፡፡  ዝኒ ከማሁ)

አዳም በኃጢአቱ የተነሣ በሞት ቅጣት እንደተቀበለ ሁሉ ማንኛውም ሰው በዚህ ምድር ኖሮ ዕለተ ሞቱ ሲደርስ ነፍሱ ከሥጋው ትለያለች፡፡ ሆኖም የሥጋን ሳይሆን የነፍስን ሞት መፍራት እንደሚገባ ልናውቅ ይገባል፡፡ የነፍስ ሞት ዘለዓለማዊ ቅጣት ወደ ተዘጋጀበት ገሃነም መውረድ ነውና፡፡ ኢትዮጵያዊው ሊቁ ቅዱስ ያሬድ ስለዚህም ‹‹ኢትፍርህዎ ለሞት ፍርህዋ ለኃጢአት እስመ ሞትሰ ኢየኀድገክሙ ዘበላዕሉ ኀልዩ ወአኮ ዘበምድር፤ ሞትን አትፍሩት ኃጢአትን ግን ፍሩ ሞት አይቀርምና ስለሰማያዊው አስቡ እንጂ ስለምድራዊው አይደለም›› ሲል አስተምሯል፡፡

የሰዎች ኃጢአት ሲበዛ እግዚአብሔር አምላካችን ምድር ላይም ቢሆን ይቀጣናል፡፡ ጠቢቡ ሰሎሞን እንደተናገረው ሞት የሰው ልጅ የፈጣሪውን ሕግ በመተላለፉ ምክንያት የመጣበት ቅጣት ነው። «በሕይወታችሁ ስሕተት ለሞት አትቅኑ፤ በእጃችሁም ሥራ ጥፋትን አታምጡ። እግዚአብሔር ሞትን አልፈጠረምና፤ የሕያዋንም ጥፋት ደስ አያሰኘውምና። ነዋሪ ይሆን ዘንድ ፍጥረቱን ፈጥሮአልና፤ የዓለም መፈጠርም ለድኅነት ነውና፤ በእነርሱም ዘንድ የጥፋት መርዝ አልነበረምና፤ ለሲኦልም በምድር ላይ ግዛት አልነበረውምና። ጽድቅ አትሞትምና፡፡ ክፉዎች ግን በእጃቸውና በቃላቸው ጠሩት ባልንጀራም አስመሰሉት። በእርሱም ጠፉ። የእርሱ ወገን መሆን ይገባቸዋልና ከእርሱ ጋር ቃል ኪዳን አደረጉ» በማለትም ነግሮናል። (ጥበ.፩፥፲፪-፲፯)

ድኅነተ ነፍስን እናገኝ ዘንድ በሥጋችን ኃጢአት ሳንሠራ የክብር ሞት ልንሞት ይገባል፡፡ ይህም የጻድቃን ሞት ነው፤ የኃጥኣን ሞት  ግን በሥጋቸው ድሎትን አግኝተው ኃጢአትን ሠርተው በነፍስ ስለሚሞቱ ዘለዓለም በእሳት ውስጥ ይሠቃያሉ፡፡ ምክንያቱም ኃጥኣን ከዚህ ዓለም በሚለዩበት ጊዜ መከራ ወዳለበት እንዲሁም ሥቃይ ወደሚበዛበት ይሄዳሉ እንጂ ነፍሳቸው ዕረፍት አያገኝምና፡፡ ስለዚህም ይህንን ሞት ልንፈራ ያስፈልጋል፡፡

ነቢዩ ዳዊት «ሞቱ ለኃጥእ ጸዋግ፤ የኃጥእ ሰው ሞት ክፉ ነው» በማለት ተናግሯል። ጻድቃን ግን ሞተ ሥጋን እንጂ ሞተ ነፍስን አያዩም። ኃጥኣን ደግሞ በሥጋም ሆነ በነፍስ ይሞታሉ። በዚህም ኃጥእ ሰው ሞተ ሥጋውም ሆነ ሞተ ነፍሱ የከፋ እንጂ መልካም የሚባል አይደለም። (መዝ.፴፫፥፳፩)

ንስሓ ሳይገቡ በድንገተኛ ሞት መሞትም ከነፍስ ሞት መዳን ስለማይቻል «የመዳን ቀን ዛሬ ነው» እንደተባለው በንስሓ ሕይወት ውስጥ መኖር ከእኛ ይጠበቃል፤ ሰብአ ትካት በንፍር ውኃ በጠፉበት ዘመን ኖኅ ከነቤተሰቡ መዳኑን በመጽሐፍ ቅዱስ አንብበን ይሆናል፡፡ እግዚአብሔር አምላክ የሰዶምና የገሞራ ሕዝብ ሲጠፉ ሎጥን ከሁለት ልጆቹ ጋር እንዳዳናቸውም ልናውቅ እንችላለን፡፡ የእነዚህን መጥፎ ሥራ እየሠራን ፈጣሪያችንን በኃጢአት የተነሣ ከራቅን ልክ እንደእነርሱ ሊያጠፋን እንደሚችል እንረዳለን፡፡ ሥጋዊ ሞትን ፈርተን ከበሽታም ሆነ ከመከራ ለመላቀቅ ፈጣሪ ባልፈቀደው መንገድና አስተሳሰብ በመመራት ለጥፋት እንዲሁም ለዘለዓለማዊ ሞት መዳረግ የለብንም፤ ምንም እንኳን ጊዜያዊ መፍትሔ ልናገኝ ብንችልም እኛ ሰዎች ከአፈር ስለተሠራን መልሰን አፈር መሆናችን አይቀርም፡፡ ‹‹አፈር ነህና ወደ አፈርም ትመለሳለህና›› እንዲል፡፡ የሥጋዊ ሞታችን ይቅረብም ይራቅ አይቀሬ ነው፡፡ (ዘፍ.፯፥፩-ፍጻሜ፣፲፱፥፲፪-፳፪፣፪ቆሮ.፮፥፪)

በነፍስ ላለመሞት ግን ኃጢአትን ከመሥራት መታቀብ ይቻላል፡፡ በሚቻል ነገር እንጂ በማይቻል ነገር መታገል ደግሞ አግባብ ስላልሆነ መፈራት ያለበትን ብቻ ፍሩት በማለት ሊቁ አስረድቷል፡፡

በአሁኑ ጊዜ በኃጢአታችን መብዛት የተነሣ መቅሠፍት ከእግዚአብሔር አምላክ እንደተላከብን ከአወቀን በኋላ እንኳን ተጸጽተን ወደ ንስሓ ከመመለስ ይልቅ ሥጋዊ ሞትን ብቻ በመፍራት መድኃኒት ለሌለው ኮሮና በሽታ መፍትሔ ለመፈለግ ስንረባረብ ከርምናል፡፡ ከላይ እንደተገለጸው ግን ሥጋዊ ሞት በምንም መልኩ ሊቀር አይችልም፡፡ ይህ ማለት ሰው በሃይማኖት ጸንቶ ቢኖር በበጎ ምግባርም ፈጣሪውን ቢያስደስተው እንኳን ከሥጋ ሞት አያመልጥም፡፡ ‹‹ሞትስ አይተዋችሁምና›› ብሎ ሊቁ ያሬድ እንደነገረን ሥጋዊ ሞትን ማምለጥ ስለማይቻል‹‹ አትፍሩት›› ተብለናል፡፡

ነገር ግን የንስሓ ዕድሜ ይኖረን ዘንድ አምላካችን እየታገሠን በመሆኑ ጊዜያችንን ለነፍሳችን ድኅነት ልንጠቀምበት ይገባል፤ የነፍስ ሞት አስፈሪና አስከፊ በመሆኑ ምድራዊ ሕይወታችን በክርስቲያናዊ ትጋት የተሞላ መሆን አለበት፡፡ ‹‹ክብር ለሞቱ ለጻድቅ በቅድመ እግዚአብሔር፤ የጻድቅ ሞት በእግዚአብሔር ፊት የከበረ ነው›› እንደተባለው ነፍሳችን ትከብር ዘንድ ሥጋዊ ድሎትን ንቀን ዘለዓለማዊ ሕይወትን እንመኝ፡፡  (መዝ.፻፲፭-፻፲፮፡፲፭)

እግዚአብሔር አምላክ ከሁለተኛው ሞት ይታደገን፣ እንዲሁም ለነፍሳችን ምሕረትን ያበዛልን ዘንድ እንማጸን፡፡