ምኵራብ፡- የዐቢይ ጾም ሦስተኛ ሳምንት

ዲያቆን ደረሰ ተሾመ

መጋቢት ፲፫፤፳፻፲፮ ዓ.ም

ቦአ ኢየሱስ ምኵራበ አይሁድ ወመሐረ ቃለ ሃይማኖት፤ ወይቤሎሙ ምጽዋተ አበድር እመሥዋዕት፤ አነ ውእቱ እግዚኣ ለሰንበት ወአቡሃ ለምሕረት፤ እግዚኣ ውእቱ ለሰንበት ወልደ እጓለ እመሕያው፤ ጌታችን ኢየሱስ ወደ አይሁድ ምኵራብ ገባ፤ የሃይማኖት ቃልን አስተማረ፤ ከመሥዋዕት ይልቅ ምሕረትን እወዳለሁ፤ የሰንበት ጌታዋ የምሕረት አባቷም እኔ ነኝ፤ የሰው ልጅም የሰንበት ጌታዋ ነው።(ጾመ ድጓ)

በኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ሦስተኛውን የዐቢይ ጾም ሳምንት “ምኵራብ” ይባላል። ቀጥተኛ ፍቺው “ኮረብታ፣ ተራራ የሚያህል ታላቅ ሕንጻ፣ ሰቀላ መሰል አዳራሽ” ሲሆን፣ የአይሁድ መካነ ጸሎት ወይም ቤተ መቅደስ በመሆን ያገለግል ነበር። በብሉይ ኪዳን አይሁድ ቤተ መቅደስ ነበራቸው፡፡

ናቡከደነጾር ኢየሩሳሌምን በወረረ ጊዜ ግን ቤተ መቅደሱን አፈረሰ፤ ሕዝቡን ወደ ባቢሎን አፈለሰ፤(፪ነገ.፳፬-፳፭፣ኤር.፬፥፯:፣፴፱፥፩-፲፣፶፪፥፩-፴) ከዚህ ጊዜ ጀምሮ አይሁድ በሚኖሩባቸው ሥፍራዎች ሁሉ ለጸሎት ቤት ይሠሩ ነበር፡፡ በዚያን ዘመን ቢያንስ ዐሥር አባ ወራዎች/የቤተ ሰብ ኃላፊዎች/ በቦታው ከተገኙ እነዚህን ምኵራቦችን ለመሥራት ይፈቀድላቸው ነበር፡፡ (Talmud Mishnah, Responsa literature, Jewish Encyclopedia, Academic Scholarly Works.)  ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በኢየሩሳሌም እየተዘዋወረ በሚያስተምርበት ጊዜ ግን ብዙ ምኵራቦች ነበሩ፡፡ በሐዲስ ኪዳንም ለሐዋርያት በብዛት የስብከት ዓውደ ምሕረቶች ሆነው አገልግለዋል።

ምኵራበ አይሁድ በውስጡ የብራና የሕግ እና የነቢያት መጻሐፍት ይገኛሉ፡፡ ምእመኑ እንዲሰማቸው ከፍ ባለ መድረክ ላይ በመሆን መምህራንና ካህናት ቆመው መጻሕፍትን ያነባሉ፤ ቃለ እግዚአብሔርንም  ያስተምሩ ነበር። የምኵራብ ሹማምንት አለቆች ጥፋተኛ ሰው ሊቀጡ ሥልጣን ነበራቸው፡፡ አገልጋይ ወይም የሚራዱ ወጣቶችም ልጆችን በማስተማር፣ በማቅረብ በተጨማሪ የአለቆችን ትእዛዝ በመፈጸም ያገለግላሉ፡፡

በሰንበት ሕዝብ ሁሉ በምኵራብ ተሰብስቦ ከሕግና ከነቢያት ንባብ፣ ስብከትና ቡራኬ በመቀበል አምልኮታቸውን ይፈጽሙ ነበር፡፡ ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በዚህ ምኵራብ ተገኝቶ ሕዝቡን አስተምሯል፡፡ ቅዱስ ሉቃስ በወንጌሉ ”ወዳደገበትም ወደ ናዝሬት መጣ፤ እንደ ልማዱም በሰንበት ቀን  ምኵራብ ገባ ሊያነብም ተነሣ” እንዳለ ቅዱሳት መጻሕፍትን ማንበብ፣ መማር፣ መመርመር፣መተርጎም፣ጉባኤ መሥራት አዘውትረው የሚፈጽሙት ተግባር እንደነበር ያስረዳል።(ሉቃ.፬፡፥፲፮)

ነገር ግን በምኵራብ ሰዎች ለተለያየ ዓላማ ይሰበሰቡ ነበር፡፡

. አማናዊ እረኛ ነው ብለው፦ ወልድ ዋሕድ ብለው ሲጠብቁት የነበረው ተስፋ “ደረሰልን፤ ወረደ፤ ተወለደ፤ የዓለም መድኃኒት እርሱ ነው” ብለው አዳኝነቱን አምነው ይከተሉታል። “ነዋ በግዑ ለእግዚብሔር ዘያአትት ወያሴስል ኃጢአተ ዓለም፤ የዓለሙን ኃጢአት የሚያስተሰርይ የእግዚብሔር በግ መሆኑን አውቀው የሚከተሉት አሉ። ”በጎቹም ድምፁን ያውቃሉና ይከተሉታል” እንዲል። (ዮሐ.፲፥፬)

. የቃሉን ትምህርት የእጁን ተአምራት ሽተው፦ ከደዌ ለመፈወስ ይሰበሰባሉ፤ ልብሱን ዳሰው፣ ወድቀው ሰግደው፣ ጥላውን ተጋርደው፣ በእጁ ተዳሰው የሚፈወሱ ነበሩ። (ማር. ፭፥፳፪ እስከ ፍጻሜ)። ጌታችን በዕለተ ሰንበት ሕዝብ በተሰበሰበበት በምኵራብ እንደሚያስተምር ያስረዳናል፤ ”ሰንበትም በሆነ ጊዜ በምኵራብ ያስተምር ጀመር፤…ወደ ምኩራባቸውም ገብቶ ዝም ይሉ ዘንድ ገሠፃቸው፤ እነርሱም ትምህርቱን፣ የቃሉን ግርማ፣ የአነጋገሩን ጣዕምና፣ የአንደበቱን ቅልጥፍና አደነቁ፡፡”  (ማር.፮፥፩) “ወደ ገዛ አገሩም መጥቶ እስኪገረሙ ድረስ በሚገባቸው ያስተምራቸው ነበር።” (ማቴ.፲፫፥፶፬)

. ምግበሥጋ ፈልገው ደም ግባቱን አይተው:- ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ከምኵራብ ጉባኤ ትምህርት በኋላ ጥቂቱን አበርክቶ እልፉን ይመግብ ስለነበር ጉባኤውን ይታደማሉ። ክርስቲያኖች እግዚአብሔርን የምናመልከው ምግበ ሥጋ ስለሰጠን አይደለም። እርሱንማ ለሕዝብም ለአሕዛብም ሳይሰስት የሚመግብ መጋቤ ዓለማት ነው። ክርስቲያን በመብል አይገመትም። “እንግዲህ በመብልም ቢሆን÷ በመጠጥም ቢሆን÷ በልዩ ልዩ በዓላትም ቢሆን÷ በመባቻም ቢሆን÷ በሰንበትም ቢሆን የሚነቅፋችሁ እንዳይኖር ተጠንቀቁ፡፡” እንዲል፡፡ (ቆላ. ፪፥፲፮ እስከ ፍጻሜ)

. ለክስ የሚቀርቡ አሉ፦ ከቃሉ ግድፈት ከትምህርቱ ስሕተት የሚፈልጉ ሰቃለያን አይሁድ፣ ሊቃነ ካህናት አምላክነቱን የሚጠራጠሩ አይሁድ የሸንጎውን ጌታ ለሸንጎ ፍርድ ሊያቀርቡት ከግር በግር ይከተሉት ነበር። “ወጸቢሖ ተጋብኡ ሊቃነ ካህናት ወጸሐፍት ወሊቃናተ ሕዝብ ወወሰድዎ ውስተ ዐውዶሙ። ወይቤልዎ እመ አንተሁ ክርስቶስ ንግረነ ገሃደ ወይቤሎሙ እመኒ አይዳእኩክሙ ኢተአምኑኒ፡፡ በነጋም ጊዜ፥ የካህናት አለቆች፥ ጻፎችና የሕዝቡ ሽማግሌዎች ተሰብስበው ወደ ሸንጎአቸው ወሰዱት፡፡ “አንተ ክርስቶስ እንደ ሆንህ በግልጥ ንገረን” አሉት፡፡እርሱም እንዲህ አላቸው፥ “ብነግራችሁም አታምኑኝም” እንዲል፡፡ (ሉቃ. ፳፪፥፷፮፣ ማቴ.፳፮፥፶፱)

ዛሬም በአማናዊቷ ቅድስት ቤተ ክርስቲያን ሥጋዊ ነገር ብቻ ገዝፎባቸው ቤተ መቅደሱን ለንግድ፣ ንዋያተ ቅድሳትን ለትርፍ ብቻ አሳልፈው የሚሸጡ፣ የሚለውጡ፣ ለክስ የሚፋጠኑ ከምኵራብ ያልወጡ የበጎችን እረኛ አሳልፈው የሚሰጡ አዋልደ ይሁዳ እንዳሉ ግልጽ ነው። “ወረከበ በምኵራብ እለ ይሠይጡ አልህምተ ወአባግዐ ወአርጋበ …፤ በመቅደስም በሬዎችን፣ ላሞችን፣ በጎችን፣ ርግቦችን፣ የሚሸጡትን አገኘ …፤ “ኢትግበሩ ቤተ አቡየ ቤተ ምስያጥ ቤትየሰ ቤተ ጸሎት ይሰመይ፤ የአባቴን ቤት የንግድ ቦታ አታድርጉት፤ እናንተ ግን የሌቦች ዋሻ አደረጋችሁት፤ ቤቴስ የጸሎት ቤት ይባላል” እያለም የሃይማኖትን ቃል አስተማራቸው፡፡ (ዮሐ.፪፥፲፮፣ማቴ.፳፩፥፲፫)

በምኵራብ ይሸጡ፣ ይለውጡ የነበሩትን የገሠፀበት፣ ቤተ መቅደስን የከብት መንጃ የወርቅ መነገጃ ያደረጉ ሰዎችን ከእነ ሸቀጣቸው ከቤተ መቅደስ ያስወጣበት፣ ቤተ መቅደስ የእግዚአብሔር ማደሪያ፣ የመሥዋዕቱ መክበሪያ፣ የጸሎት ሥፍራ ምስካበ ቅዱሳን መሆኗን ያስተማረበት ዕለት ነው። ቃሉ በዚያን ዘመን ተነግሮ ብቻ ያለፈ አይደለም፤ ለእኛ የተነገረን መሆኑን አውቀን የባለቤቱ ጅራፍ ሳይገርፈን ልንመለስ ይገባል። “የገመድም ጅራፍ አበጅቶ ሁሉን በጎችንም በሬዎችንም ከመቅደስ አወጣቸው፥ የለዋጮችንም ገንዘብ አፈሰሰ ገበታዎቻቸውንም ገለበጠ፡፡” (ዮሐ.፪፥፲፬)

ከሚመጣው ጅራፍ ለመዳን እምነት ከተግባር ይዞ መገኘት ያስፈልጋል።” ወንድሞቻችን ሆይ÷ እምነት አለኝ፤ ምግባር ግን የለኝም የሚል ሰው ቢኖር÷ ምን ይጠቅመዋል? በውኑ እምነቱ ልታድነው ትችላለችን? ከወንድሞቻችን÷ ወይም ከእኅቶቻችን÷ የታረዙ ወይም የዕለት ምግብ ያጡ ቢኖሩ÷ ከእናንተም አንዱ …እንደዚሁም ሥራ የሌለው እምነት ቢኖር በራሱ የሞተ ነው።” እንዳለ። (ያዕ.፪፥፲፬ እስከ ፍጻሜ)

የዕለቱ መዝሙር (ከጾመ ድጓ)፦ ቦአ ኢየሱስ ምኩራበ አይሁድ ወመሐረ ቃለ ሃይማኖት፤ጌታችን ኢየሱስ ወደ አይሁድ ምኩራብ ገባ፤ የሃይማኖት ቃልን አስተማረ፤

መልእክታት፦(ቆላ.፪፥፲፮ እስከ ፍጻሜ) (ያዕ.፪፥፲፬ እስከ ፍጻሜ)

ወንጌል፦ (ዮሐ.፪፥፲፪-እስከ ፍጻሜ)

(የሐዋ.፲፥፩-፰)

ምስባክ፦ “እስመ ቅንዐተ ቤትከ በልዐኒ፡፡ ትዕይርቶሙ ለእለ ይትዔየሩከ ወድቀ ላዕሌየ፡፡ወቀጻዕክዋ በጾም ለነፍስየ፡፡” ትርጉም “የቤትህ ቅንዓት በልቶኛልና፥ የሚሰድቡህም ስድብ በለዬ ወድቆአልና፡፡ ሰውነቴን በጾም አደከምኋት፡፡  (መዝ.፷፰፥፱)

በምሕረቱ ይታደገን፤ ለእግዚአብሔር ምስጋና ይሁን፤ አሜን!!!