ምኞት

ሰው አንድን ነገር የራስ ለማድረግ በብርቱ ፍላጎት ወይንም ምኞት ይነሣሣል፤ በመልካም ምኞቱ የነፍስ ፍላጎትን ሲፈጽም የሥጋዊው ግን ወደ ጥፋት ይመራዋል፡፡ ሥጋዊ ምኞት በመጀመሪያ ጊዜያዊ ደስታን ቢሰጥም ፍጻሜው ግን መራራ ኅዘንን የሚያስከትል ነው፡፡ ጠቢቡ ሰሎሞንም ይህን በምሳሌው እንዲህ ሲል ገልጾታል፤ ‹‹የጻድቃን ምኞት መልካም ነው፤ የኃጥአን ተስፋ ግን መቅሠፍት ነው›› (ምሳሌ. ፲፩፥፳፫)

መልካም /በጎ/ ምኞት

ጻድቃን እግዚአብሔር አምላካቸውን ያገለግሉ እንዲሁም በእርሱ ፊት ክብርና ሞገስን ይጎናጸፉ ዘንድ በብርቱ ምኞት ዘወትር ፈጣሪያቸውን አገልግለው እና በመንፈሳዊ ተጋደሎ ኖረው ወደ እርሱ ይጓዘሉ፡፡ ምኞታቸው መልካም ወይንም በጎ ስለሆነ ምግባራቸው ሠናይ እንዲሁም መንገዳቸው ሁሉ ቀና ይሆንላቸዋል፤ ‹‹የጻድቅ ምኞቱ ግን በእግዚአብሔር ዘንድ የተወደደች ናት›› እንዲል፡፡  (ምሳሌ. ፲፥፳፬)

ሶርያዊው ቅዱስ ኤፍሬም ሕይወቱን በብሕትውና የመራ የትርጓሜ መጻሕፍትን፣ የቅኔ፣ የግጥምና የወግ ጽሑፍ በማዘጋጀት የኖረ ባለ በጎ ገድል አባት ነው፡፡ በመጽሐፈ ስንክሳርም እንደተመዘገበው እጅግም ብዙ የሆኑ ዐሥራ አራት ሺህ ድርሳናትንና ተግሣጻትን ደርሷል፤ ከእርሳቸውም ውስጥ አምላክን የወለደች የእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ውዳሴዋን ነው፡፡  (ስንክሳር ዘሐምሌ ፲፭)

ይህ ቅዱስ አባት የእመቤታችን ፍቅር ቢጠናበት ‹‹ምነው ምስጋናዋ እንደ ሰማይ ከዋክብት እንደ ምድር አሸዋ በዝቶልኝ እንደምግብ ተመግቤው›› እያለ ይመኝ ነበር፡፡ እግዚአብሔርም ለቅዱሳኑ የወደዱትን ያደርጋልና እመቤታችን ተገልጣለት፣ ውዳሴዋም በዝቶለት ‹‹አኅዝ እግዚኦ መዋግደ ጸጋከ፤ ጌታ ሆይ የጸጋህን ሞገድ ያዝልኝ›› እስኪል ድረስ አመስግኗል፡፡ (ውዳሴ ማርያም አንድምታ)

ክፉ /መጥፎ/ ምኞት

በምድራዊ ሕይወት ሰዎች ብዙ ነገር ይመኛሉ፡፡ ገንዘብ፣ ሀብት፣ ሥልጣን፣ ዕውቀት እንዲሁም የተለያዩ ጥቅማ ጥቅሞችን የራሳቸው ብቻ ለማድረግም ይጥራሉ፡፡ የእነርሱ ያልሆነ ነገርን በተመኙ እና የፈለጉትን ለማግኘት በማይችሉበት ጊዜ ግን በሌሎች ሰዎች ላይ ክፋት ማሰብና ማድረግን ይለምዳሉ፤ ኃጢአትንም አብዝተው ይሠራሉ፤ ክፉ ምኞት የኃጢአት ምንጭ ነውና፡፡ ‹‹ነገር ግን እያንዳንዱ በራሱ ምኞት ሲሳብና ሲታለል ይፈተናል፡፡ ምኞትም ከፀነሰች ኃጢአትን ትወልዳለች፤ ኃጢአትም ከተፈጸመች ሞትን ትወልዳለች›› እንዲል፡፡ (ያዕ. ፩፥፲፬-፲፭)

ለዚህም እንደ ምሳሌ ይህን ታሪክ እናውሳ፤ በአንድ ወቅት አንድ አረጋዊ ከአንድ አባት ጋር ሆነው አባታችን አባ መቃርስን ጎበኙት።  እነርሱም ‹‹አባታችን ሆይ፤ እንደ አንድ ሰው ሆነን መኖር እንፈልጋለን›› አሉት። እርሱም አረጋዊውን እንዲህ አለው። ‹‹መጀመሪያ እንደ እረኛ ሁን ክፉ ትል ተሸካሚ (አስተላላፊ) የሆነች ወፍ በበጎች መካከል ትሎችን ብትዘራባቸው ትሎችን እስከሚገድላቸው ድረስ ለታመመችው በግ መድኃኒት ይሰጣታል። አንድ በግ ተላላፊ የሆነ በሽታ የሚዘራ ከሆነ ግን በሽታውን እስከሚያስወግደው ድረስ መድኃኒት ይጠቀማል›› አላቸው። አረጋዊውም ‹‹የዚህን አባባል ትርጉም ንገረኝ››  አለው። ‹‹ትል የሚዘራው ወፍ እንደ ዲያቢሎስ ነው። በጉ ደግሞ ከአንተ ጋር እንደሚኖረው ወንድም ያለ ነው። ትሎቹ ደግሞ በነፍስ የሚኖሩና በልብ የሚራቡ የአጋንንት ፍትወታትና ክፉ ምኞቶች ናቸው። ትሎች በሰውነት ቁስል ላይ እንደሚኖሩት ማለት ነው። በሽታውን እንደሚያስወግደው መድኃኒት ደግሞ በመንፈስ ማደግ ትምህርትና መድኃኒት የሆነው የእግዚአብሔር ቃል ትምህርት ነው።  ነፍስን የሚያንጿት ነገሮች እነዚህ ናቸው። አጋንንት በእኛ ላይ ክፉ ከሚያሠሯቸው ጠላቶቻችን ከእኩያት ፍትወታትና ከክፋቶች ሁሉ የሚጠሯት እነዚህ ናቸው።››

ከአረጋዊው ጋር አብሮ የመጣውን አባት ደግሞ እንዲህ ብሎ ተናገረው፤ ‹‹ልጄ ሆይ በእግዚአብሔር ፊት የተወደደ መሥዋዕትና መባእ አድርጎ እስኪያቀርበው ድረስ አባቱን እንደታዘዘው እንደ ይስሐቅ ሁን።  እርሱ ለአባቱ በመታዘዙ በቤተ ክርስቲያን መዝገብ ውስጥ እስከ ዓለም ፍጻሜ ድረስ ተጽፏልና። (ገድለ አባ መቃርስ)

ክፉ ሀሳብ፣ ተግባርና ምኞት እራስን ወደ ዝሙት፣ ሐሰተኝነት፣ ዘረኝነት፣  ንፉግነት፣ እና ስግብግብነት ይመራል፤ ፍቅረ ንዋይ እና ጥቅም እንዲገዛን ያደርጋል፤ ለአላስፈላጊ ደስታ፣ ኩራት እንዲሁም ትምክሕትም ይዳርጋል፡፡

ያሰብነው ሳይሳካ ሲቀር እና የፈለግንበት ደረጃ ያልደረስን ከሆነ ደግሞ ተስፋ ወደ መቁረጡ እንደርሳለን፡፡ እምነት ከማጣትም የተነሣ ኀዘን፣ ቁጣ፣ ንዴት፣ ብስጭት፣ ምቀኝነት እና  ግብዝነት ያጠቃናል፡፡

ቅዱስ ጳውሎስ ወደ ሮሜ ሰዎች በላው መልእክቱ ክፉ ምኞት ስላለባቸው ሰዎች ሲገልጽ ይህን አለ፤ ‹‹እግዚአብሔርን ለማወቅ ባልወደዱት መጠን እግዚአብሔር ይህን የማይገባውን ይሠሩ ዘንድ ሰነፍ አእምሮ ሰጣቸው፡፡ እነርሱም ዐመፅን ሁሉ፥ ክፋትንም፣ ምኞትንም፣ ቅሚያንም፣ ቅናትንም፣ ነፍስ ገዳዮች፣ ከዳተኞች፣ ተንኰለኞች፣ ኩሩዎች፣ ጠባያቸውንና ግብራቸውንም ያከፉ ናቸው፡፡ሐሜተኞች፣ እግዚአብሔርን የሚጠሉ፣ ተሳዳቢዎች፣ ትዕቢተኞች፣ ትምክሕተኞች፣ ክፋትን የሚፈላለጉ፣ ለወላጆቻቸው የማይታዘዙ ናቸው፡፡ የማያስተውሉ፣ ዝንጉዎች፣ ፍቅርም፣ ምሕረትም የሌላቸው ናቸው፡፡ ይህን እንዲህ ላደረገ ሞት እንደሚገባው እነርሱ ራሳቸው የእግዚአብሔርን ፍርድ እያወቁ፥ እነርሱ ብቻ የሚያደርጉት አይደለም፤ ነገር ግን ሌላውን ያነሣሡታል፤ ያሠሩታልም።›› (ሮሜ.፩፥፳፰፥፴፪)

በአሁኑ ጊዜም ሰዎች በክፉ ምኞት ተነሣስተው የራሳቻው ያልሆነ ነገርን ጭምር ለማግኘት እና ሥጋዊ ድሎትን እንዲሁም ምድራዊ ደስታን ለማግኘት ይለፋሉ፤ ከራሳቸውም አልፎ በሌሎች ላይ ክፉ ምኞት እንዲፈጥር መንሥኤም ይሆናሉ፡፡

ነገር ግን ከክፉ ምኞት እራስን በመጠበቅ ሕይወታችንን በመልካም ምግባራት መምራት  ያስፈልጋል፤ በእርግጥ አንዳንድ ሰዎች መልካም እና ክፉ ምኞትን ለይተው ላያውቁ ወይንም ኃጢአት መሆኑን ላይገነዘቡ ይችላሉ፤ ስለዚህም ልዩነቱን ማወቅን መረዳት ያስፈልጋል፡፡ ‹‹በኋላኛው ዘመን እንደ ራሳቸው ምኞት የሚመላለሱ ዘባቾች በመዘበት እንደሚመጡ ይህን በፊት ዕወቁ›› ተብሏልና፡፡ (፪ ጴጥ. ፫፥፫)

ሁሉንም መመኘት ወይንም ምኞት ሁሉ በጎ አይደለም፤ የምንመኘውን ነገር ለይተን ማወቅ አለብን፤ የራሳችን ያልሆነውን መመኘት ኃጢአት ነው፤ አንድ ሰው የራሱ ያልሆነን ቤት ወይንም ትዳር አይቶ ‹‹እንደዚህ ዓይነት ትዳር ወይንም ቤት በኖረኝ ብሎ መመኘት እንጂ ቤቱም ወይንም ትዳሩ የእኔ በሆነ ብሎ ቢመኝ ኃጢአት ነው፡፡ የእርሱ ያልሆነውን ከመመኘቱ ብዛትም በውስጡ ክፉ ሀሳብን ከመፈጠሩ የተነሣ የቤቱ ባለቤት ለመሆን ወንጀለኛ እና የተባረከውን ትዳር ለማፍረስም ዝሙተኛ ያደርገዋልና፡፡ ‹‹ሴትን አይቶ የተመኛትም ሁሉ ፈጽሞ በልቡ አመነዘረባት›› ይላልና ቃሉ፤ (ማቴ. ፭፥፳፰)

ሰዎች በዕለት ከዕለት ኑሮአችን ውስጥ በተለያዩ አጋጣሚዎች የምንመኘው ነገር ሊኖር ይችላል፤ ነገር ግን ልንጠነቀቅ ይገባል፤ ምክንያቱም ከመልካም ምኞት በስተቀር የራስ ያልሆነን ነገር ሁሉ መመኘት ኃጢአት እንድንሠራም ይገፋፋናልና፤ ክፉ ምኞት እንኳን በውስጣችን ከተፈጠረ ሳንውል ሳናድር ንስሓ መግባት ያስፈልጋል፡፡

እግዚአብሔር አምላክ በመልካም ምኞት እንድንኖር ይርዳን፤ አሜን፡፡

ምንጭ፤ ውዳሴ ማርያም አንድምታ፣ ገድለ አባ መቃርስ፣ መጽሐፈ ስንክሳር ዘሐምሌ ፲፭