‹‹ምን እናድርግ?›› (ግብ.ሐዋ.፪፥፴፯)

ዲያቆን ተስፋዬ ቻይ 

ጥቅምት ፳፤፳፻፲፮ ዓመተ ምሕረት

ከብዙ ሀገራት በጽርሐ ጽዮን ተሰብስበው የነበሩ ሰዎች ይህን ጥያቄ ያቀረቡት ለቅዱሳን ሐዋርያት ነበር፡፡ የመንፈስ ቅዱስ ጸጋን ተቀብለው፣ የረቀቀው የጎላላቸው፣ የራቀው የቀረበላቸው፣ የተሠወረው የተገለጠላቸው፣ ፍርሃት ርቋቸው፣ ጥብዐት (ድፍረት) አግኝተው፣ እምነት ጸንቶላቸው የነበሩት የክርስቶስ ደቀ መዛሙርት በበዓለ ኀምሳ በሕዝቡ እንዲህ ተጠይቀዋል፡፡

ወንጌላዊው ቅዱስ ሉቃስ የቅዱሳን ሐዋርያትን ገድል በጻፈበት በሐዋርያት ሥራ ፪፥፬ ላይ ‹‹በሁሉ መንፈስ ቅዱስ ሞላባቸው፤ መንፈስም ይናገሩ ዘንድ እንደ ሰጣቸው በሌላ ልሳኖች ይናገሩ ጀመር›› በማለት እንደገለጸው ቅዱሳን ሐዋርያት የምሥራቹን ወንጌል በመስበክ ሕዝቡን ከጨለማ ወደ ብርሃን ሊያወጡ፣ ካለማመን ወደ ማመን ያመጡ ዘንድ ማስተማር ጀመሩ፡፡

ቅዱስ ጴጥሮስ በሥፍራው ለተሰበሰበው ሕዝብ ሲሰብክ እውነቱ የገባቸው የክርስቶስ አምላክነት፣ የመስቀሉ ፍቅር የተረዳቸው፣ ሕይወትን የናፈቁ፣ መዳንን የፈለጉ፣ ልባቸው ሲነካ፣ ማስተዋል ሲቸራቸው ቅዱሳን ሐዋርያትን ‹‹ምን እናድርግ?›› አሉ!  ቅዱስ ጴጥሮስም ንስሓ እንዲገቡ፣ እንዲያምኑ፣ እንዲጠመቁ፣ የመንፈስ ቅዱስ ጸጋን እንዲቀበሉና ከጠማማ ትውልድ እንዲለዩ መከራቸው፤ በዚያችም ሰዓት ሦስት ሺህ ምእመናን አምነው ተጠመቁ፡፡

‹‹ምን እናድርግ?›› ይህ በዘመናችን ያለ የሁላችን ጥያቄ ነው! ዘመኑ ከፍቶ፤ ማስተዋል ተስኖናል ነቢየ እግዚአብሔር ክቡር ዳዊት ተግሣፅን ባዘለ ዝማሬው ‹‹ሰው ግን ክቡር ሆኖ ሳለ አላወቀም፤ ልብ እንደሌላቸው እንስሶች ሆነ፤ መሰላቸውም›› በማለት እንደገለጸው ነው፡፡ (መዝ.፵፰፥፲፪) ክብራችንን ዘንግተን፣ በቀና ምግባራችን፣ በበጎ አስተሳሰባችን፣ በቅድስና ሕይወታችን ወደ መልአካዊ ባሕርይ ማደግ (ከፍ ማለት) ሲገባን ከሰባዊነትም ዝቅ ብለን፣ ከእንስሳትም ወርደን፣ አውሬያዊ ጠባይ ተጠናውቶን ከፋን! ‹‹እያንዳንዱ ለራሱ የሚጠቅመውን አይመልከት፤ ለባልንጀራው ደግሞ እንጂ›› የሚለውን የቅዱስ ጳውሎስን አባታዊ ምክር ዘንግተን ለእኛ፣ እኛ ከሚለው ይልቅ እኔ ለእኔ በሚል በራስ ወዳድነት ተይዘን፣ አንዳችን አንዳችንን በመግፋት እርስ በእርስ እስከ መጨካከን ደርሰናል! (ፊሊ.፪፥፬)

‹‹ምን እናድርግ?››  የበደላችን ጽዋ ሞልቶ መከራ ጠርቶብን፣ በግል ሕይወታችን፣ እንደ ቤተ ክርስቲያን፣ እንደ አገር ግራ ያጋቡን፣ ምላሽ የሚያሻቸው በርካታ ጥያቄዎች ገጥመውናል፤ ለፈጠረን አምላክ አንገዛ ስንል ተፈጥሮ እንኳን ጨክኖብን ሕይወታችን የስጋት፣ የሰቀቀን ከሆነ ቀናት ሳምንታትን ተክተው፣ ሳምንታት ወራትን አስገኝተው፣ ወራት ዓመታትን ወልደው፣ ከትናንት ዛሬ ከዛሬ ደግሞ ነገ ይሻላል ስንል የሚጨምር እንጂ የሚቀንስ ችግር ጠፋ! የሚርቅ እንጂ የሚቀርብ ፍቅር አጣን፤ እየደፈረሰ የሚሄድ እንጂ የሚጠራ ሰላም ጠፋ!

 ‹‹ምን እናድርግ?›› የምንኖርባት ምድር በጥፋታችን ተሰደን የመጣንባት ጊዜያዊ መኖሪያችን ምድረ ፋይድ መሆኑን ልብ እንበል! ‹‹እግዚአብሔር አምላክ ከዔደን ገነት አስወጣው፤ የተገኘባትን መሬት ያርስ ዘንድ…››  እንዲል፤ (ዘፍ.፫፥፳፫) በቅዱስ መጽሐፍ የዐሥራ ሁለቱ ነገደ እስራኤል አባት የሆነው ያዕቆብ የግብጹ ፈርዖን ‹‹ዕድሜህ ስንት ነው?›› ብሎ በጠየቀው ጊዜ ‹‹የእንግድነቴ ዘመን መቶ ሠላሳ ዓመት ነው፤ የሕይወቴ ዘመኖች ጥቂትም ክፉም ሆኑብኝ…›› በማለት የገለጸለት ለዚህ ነው፡፡ (ዘፍ.፵፯፥፯) ታዲያ በምድር የእንግድነት ዘመናችን ስንኖር  እንዴት መሆን እንዳለበት ደግሞ ሊቀ ሐዋርያት ብርሃነ ዓለም ቅዱስ ጴጥሮስ እንዲህ ይለናል፤  ‹‹ለሰው ፊትም ሳያዳላ በእያንዳንዱ ላይ እንደ ሥራው የሚፈርደውን አባት ብላችሁ ብትጠሩ በእንግድነት ዘመን በፍርሃት ኑሩ፡፡›› (፩ጴጥ.፩፥፲፯)

በፍርሃት እንድንኖር የነገረን መፍራት ያለብንን ሰው እንዳንበድል፣ በበደል ሥራ እንዳንገኝ፣ ራስ ወዳድ ሆነን ሌላውን እንዳንጎዳ እና ከቅድስና ሕይወት የሚያርቀንን እኩይ ተግባር እንዳንፈጽም ነው፡፡ ዛሬ ግን ፍርሃታችን ተስፋ መቁረጣችን እየሆነ ያለው በክፋታችን ምክንያት ከመጣብን መከራ የተነሣ ሆኗል፤ ታዲያ ‹‹ምን እናድርግ?›› አበው በብሒላቸው ‹‹አምላክ ሲቆጣ በትር አይቆርጥም፤ ያደርጋል እንጂ ነገር እንዳይጥም›› ይላሉ፤ ነገራችን መሮ የአንዳችን ክፋት ለአንዳችን በትር ሆኖ እየቀጣን ነው፤ ፀሐይ ብርሃኗን በምትሰጥበት የመዓልት ጉዟችን የጨለማ ጉዞ እስኪመስል በፍርሃት ተሸብበናል፤ ከቦታ ቦታ ተንቀሳቅሶ የመኖር ተስፋችን፣ እምነትን በወደድነውም ሆነ በፈለግነው ሥፍራ የመግለጽ ነጻነታችን ሲመነምን፣ ነገን በብሩህ ተስፋ የምንመለከትበት የእምነት መነጽራችን በጥርጥር ደመና ሲደበዝዝብን፣ ከአቀበቱ ጀርባ ሜዳ፣ ከጨለማው ማዶ ብርሃን እንዳለን ማስተዋል ተሳነን፡፡

‹‹ምን እናድርግ?›› ሊቀ ሐዋርያት ብርሃነ ዓለም ቅዱስ ጴጥሮስ በጽርሐ ጽዮን ለነበሩት ምእመንን ከገቡበት ጨለማ ወጥተው ወደ ብርሃን ይመጡ፣ ከሰጠሙበት ጭንቀት አዘቅት ይወጡ  ዘንድ ከነገራቸው የሕይወት ቃል አንዱ ‹‹ከዚህ ጠማማ ትውልድ ዳኑ›› የሚል ነበር፡፡ ከጠማማው ትውልድ ለመዳን ወደ እግዚአብሔር እንቅረብ፤ ወደ እግዚአብሔር ለመቅረብ ደግሞ አንዱ መንገድ ንስሓ ነው፤ (የሐ. ሥራ ፪፥፵) ሐዋርያው ቅዱስ ያዕቆብ በአባታዊ ምክሩ የፈለግነውን እናገኝ ዘንድ ጠብና ሙግት ከእኛ እንዲወገዱና የለመንነው ይፈጸምልን ዘንድ እንዲህ ይለናል፤ ‹‹ወደ እግዚአብሔር ቅረቡ፤ ወደ እናንተም ይቀርባል፡፡ እናንተ ኃጢአተኞች እጆቻችሁን አንጹ፤ ሁለት ሐሳብም ያላችሁ እናንተ ልባችሁን አጥሩ፤ ተጨነቁና እዘኑ፤ አልቅሱም፤ ሳቃችሁ ወደ ኀዘን ደስታችሁም ወደ ትካዜ ይለወጥ፡፡›› (ያዕ.፬፥፰) እጆቻችን ከኃጢአት ይንጹ ልባችን ከቂም በቀል ይራቅ!

በቅዱስ መጽሐፍ ሰዎች ከእግዚአብሔር ሲርቁ ተፈጥሮ እንኳን ትጨክነባቸው እንደነበረ፣ ሲመለሱና ሲጸጸቱ ደግሞ እግዚአብሔር በረድኤት ሲጎበኛቸው የመረረው ጣፍቶ፣ የጨለመው ነግቶ፣ የራቀው ቀርቦላቸው ደስተኛና ሰላማዊ ኑሮን በእንግድነት መኖራያቸው በምድር ሲኖሩ ተመልከተናል፤ አንብበናል፤ በነቢዩ ኤልያስ ዘመን ሕዝቡ የፈጠረውን እግዚአብሔርን ዘንግቶ ጣዖት ሲያመልክ በነቢዩ ኤልያስ ጸሎት የተፈጥሮ ችሮታዋን ዝናም ሰማይ እንዳትሰጥ ተገዝታ ነበር፤ (፩ነገ.፲፯፥፩) እግዚአብሔር መሳፍንት እየሾመ ሕዝቡን ያስተዳድርበት በነበረበት ዘመን ውለታውን ዘንግተው፣ ለአባቶቻቸው ድንቅ ያደረገ እግዚአብሔርን የማያውቅ ትውልድ ተነሥቶ ጣኦት በሚያመልኩበት ጊዜ ለመከራ ተዳርገውና በጠላት ተማርከው ነበር፤ ‹‹እግዚአብሔር ለእስራኤልም ያደረገውን ሥራ ያላወቀ ሌላ ትውልድ ተነሣ፡፡››  (መሳ.፪፥፲-፲፬)

ዛሬ በዘመናችን እግዚአብሔር ለኢትዮጵያውያን ያደረገውን የማያውቅ ትውልድ ተነሥቷል ለማለት በሚያስደፍር መልኩ የኃጢአት ተግባራት በቅድስቲቱ አገር ተስፋፍቷል፤ ‹‹ይህ ሕዝብ በአፉ ወደ እኔ ይቀርባልና በከንፈሮቹም ያከብረኛልና ልቡ ግን ከእኔ ራቀ ነውና›› እንዲል አምላካችን! (ኢሳ.፳፱፥፲፫) የልብ ሳይሆን የአፍ አምልኮ በዝቷል፤ የበደላችን ጅራፍ ረዝሞና ወፍሮ ራሳችንን እየቀጣን ነውና እንመለስ! ‹‹እሺ ብትሉ ለእኔም ብትታዘዙ የምድርን በረከት ትበላላችሁ፤ እምቢ ብትሉ ግን ብታምፁም ሰይፍ ይበላችኋል፤ የእግዚአብሔር ቃል ይህን ተናግሯል፡፡›› (ኢሳ.፩፥፳)

‹‹ምን እናድርግ?›› ከገጠመን ቀውስ ለመላቀቅ፣ ከራቀንን ሰላም ለማቅረብ፣ ያጣነውን ፍቅር ለማግኘት፣ የምድርን በረከት ለመብላት ወደ እግዚአብሔር እንመለስ! እሺ ብለን እንታዘዘው! ተስፋችን በእርሱ ይሁን! እምነታችን ይጽና! የፍቅር ሐዋርያው ቅዱስ ዮሐንስ በመልእክቱ ‹‹ዓለምንም የሚያሸንፈው እምነታችን ነው›› እንዳለን የገጠመንን የዓለም ውጣ ውረድ በእምነት ድል እናደርግ ዘንድ እምነታችን ጽኑ ይሁን! (፩ዮሐ.፭፥፬) ጌታችን ዳግም ለፍርድ ከመምጣቱ በፊት የሚከሰተውን ምልክት ለቅዱሳን ሐዋርያት ሲገልጥላቸው ‹‹ጦርንም የጦርንም ወሬ ትሰሙ ዘንድ አላችሁ፤ ይህ ሊሆን ግድ ነውና ተጠበቁ፤ አትደንግጡ›› ብሏቸው ነበር፡፡ (ማቴ.፳፬፥፮)

ዛሬ ዓለማችን በጦር ወሬ የተሸበረችበት ወቅት ነው፤ ሰው በግሉ በውስጡ ጦርነት አለበት፤ ሥጋው በመንፈሱ መንፈሱ በሥጋው ላይ ሲቃወሙ ይኖራሉ፤ ‹‹ሥጋ በመንፈስ ላይ መንፈስም በሥጋ ላይ ይመኛልና፤›› (ገላ.፭፥፲፯) በውጭ ኑሮው ወንድም ከወንድሙ፣ አንዱ አገር ከአንዱ አገር ጦር ሲማዘዝ፣ ቃታ ስቦ ሲታኮስ መስማቱና ማየቱ የተለመደ ከሆነ ከመሰንበትም አልፎ ከረመ፤ የዘመኑን ፍጻሜ መቃረብ የሚያሳውቁን የበደል ዓይነቶች ለዓይናችን እስኪቀፈን ተመለከትን፤ ለጆሯአችን  እስኪሰለቸን ሰማን! ከዚህ ጠማማ ትውልድ ለመዳን ከክፋት ሥራችን እንመለስ! ለራሳችን ስለ አገር መጸለይን አንዘንጋ! ግፉ በዝቶ መከራው መከሰቱ፣ ቅጣቱ መምጣቱ ግድ የሆነ እንደሆነ እኛን ከመከራ ይሰውረን ዘንድ ‹‹የአገርን፣ የሕዝቦቿን፣ የቤተ ክርስቲያንን ጥፋት አታሳየን›› እንበለው፤ እንደ ኢትዮጵያዊው አቤሜሌክ ‹‹የኢየሩሳሌምን ጥፋት አታሳየኝ..›› በማለት እንደ ጸለየውና እስራኤል ሲማረኩና ከተማዋ ስትጠፋ እርሱ ይህን እንዳይመለከት ስልሳ ስድስት ዘመን እንዲተኛ እንደተደረገው እኛንም ከዘመኑ ክፋት ይታደገን ዘንድ እንጸልይ! ከበደላችን እንመለስ! በእግዚአብሔር ያለን እምነታችን ጽኑ ተስፋችን ሙሉ ይሁን፤ እንደ ንጉሥ ነቢዩ ዳዊት ‹‹አምላካችን መጠጊያችን ባገኘን በታላቅ መከራም ረዳታችን ነው፤ ስለዚህ ምድር ብትነዋወጥ ተራሮችም ወደ ባሕር ልብ ቢወሰዱ አንፈራም››  እንበል፤ (መዝ.፵፭፥፩) ‹‹ወላጆች እንደ ሌላቸው ልጆች አልተዋችሁም›› ያለን በቃሉ የታመነ ጌታ አይተወንም፤ እኛ ግን ወደ እርሱ እንመለስ! ምክንያቱም እርሱ የሚሰጠን ሰላም ዓለም እንደሚሰጠን ሰላም አይደለምና፡፡  (ዮሐ.፲፬፥፲፰)

 ‹‹ምን እናድርግ?›› ሁላችንም ራሳችንን እንመልከት! የቆምንበትን እናስተውል! ለገጠመን ቀውስ፣ ለገጠመን መከራ፣ ለመጨካከናችን ምክንያቱ ምንድነው እንበል! ልባችን ከማስተዋል ከማመን አይዘናጋ! ተስፋ ከመቁረጥ ሕይወት እንውጣ! ንግግራችን በጨው እንደተቀመመ ይሁን! ከአንደበታችን የሚደመጡ ንግግሮች የተቆጣ ልብን የሚያበርዱ፣ የተራራቀን የሚያቀራርቡ፣ የጠብ ግድግዳን የሚያፈርሱ፣ ክፉዎችን በፍቅር ለይቅርታ የሚያንበረክኩ ይሁኑ! ከተዋሕዶ ሃይማኖት ከሥላሴ ልጅነት አያናውጸን! የመከራን ቀን ዝም ብዬ እጠብቃለው፤ ምንም እንኳ በለስም፣ ባታፈራ በወይንም ሐረግ ፍሬ ባይገኝ፣ የወይራ ሥራ ቢጎድል፣ እርሾችም መብልን ባይሰጡ፣ በጎች ከበረቱ፣ ቢጠፉ ላሞችም፣ በጋጡ ውስጥ ባይገኙ፣ እኔ ግን በእግዚአብሔር ደስ ይለኛል፤ በመድኃኒቴ አምላክ ሐሤት አደርጋለሁ፡፡ ጌታ እግዚአብሔር ኃይሌ ነው›› እንዲል! (ዕን.፫፥፲፯)

ስብሐት ለእግዚአብሔር

ወለወላዲቱ ድንግል

ወለመስቀሉ ክቡር አሜን!!!