ምሥጢረ ጥምቀት

ክፍል ሁለት

ዲያቆን ተስፋዬ ቻይ  

ግንቦት ፴፤፳፻፲፮ ዓመተ ምሕረት

ውድ የእግዚአብሔር ልጆች! እንዴት አላችሁልን? በዓለ ሃምሳ ተብሎ የሚታወቀውን ወቅት እንዴት እያሳለፋችሁት ነው? መቼም ልጆች! ጾም የለም ብላችሁ ጸሎት ተግቶ ከመጸለይ፣ ቤተ ክርስተያን በሰንበት በዕረፍት ጊዜያችሁ ሄዶ ማስቀደስን እንደማትዘነጉ ተስፋ እናደርጋለን!

በዘመናዊ ትምህርታችሁም ሁለተኛው የመንፈቀ ዓመት እየተገባደደ በመሆኑ ለማጠቃለያ ፈተና የምትዘጋጁበት ወቅት በመሆኑ በርትታችሁ አጥኑ፤ መልካም! አሁን ለዛሬ ወዳዘጋጀንላችሁ ትምህርት እናምራ! ባለፈው የትምህርት ክፍለ ጊዜያችን ‹‹ምሥጢረ ጥምቀትን›› ተምረን ነበር፤ ዛሬ ደግሞ ምሥጢረ ጥምቀትን ቀጣይ ክፍለ ትምህርት እንማራለን፤ ተከታተሉን!

ጥምቀት የሚለውን የቃል ትርጉም፣ ጌታችን ለምን እንደተጠመቀ፣ እኛ ደግሞ ለምን እንደምንጠመቅ፣ ስንጠመቅ የምናገኘውን ክብር (ጸጋ) ተምረን ነበር፤ ዛሬ ደግሞ በተወለድን በአርባና በሰማንያ ቀናችን ስንጠመቅ ስለሚፈጸምልን ሥርዓት እንማማራለን፡፡

የእግዚአብሔር ልጆች ለመሆን ስንጠመቅ ወንዶች በተወለድን በአርባኛው ቀን፣ ሴቶች ደግሞ በሰማንያ ቀን በወላጆቻችንን እቅፍ ሆነን በቤተ ሰቦቻችን ታጅበን ወደ ቅድስት ቤተ ክርስቲያን በመምጣት እንጠመቃለን፡፡

አቤት ያን ቀን ለእኛ! ዳግመኛ ከእግዚአብሔር የምንወለድበትን ቀን የሚፈጸመውን ሥርዓት የወላጆቸቻችንና የቤተ ሰቦቻችንን ደስታ የማወቅና የመረዳት ተሰጥቶን ቢሆን ከእነርሱ ይልቅ እኛ ምን ያህል በተደሰትን! ምክንያቱም ያቺ ዕለት ለእኛ በሕይወታችን ካሉ ሁሉ ታላቀ ዕለት ናትና፡፡

ይገርማችኋል የእግዚአብሔር ልጆች! ሥርዓተ ጥምቀቱ ከመፈጸሙ በፊት አባቶች ካህናት፣ ዲያቆናት ልንጠመቅበት በተዘጋጀው ማይ (ውኃ) ጸሎት ያደርሱበታል፤ ከዚያም ካህኑ ‹‹አሐዱ አብ ቅዱስ፤ አሐዱ ወልድ ቅዱስ፤ አሐዱ ውእቱ መንፈስ ቅዱስ፤ አንዱ አብ ቅዱስ ነው፤ አንዱ ወልድ ቅዱስ ነው፤ አንዱ መንፈስ ቅዱስ ነው›› ብለው ማዩን (ውኃውን) ይባርኩታል፤ ያም በእግዚአብሔር ስም ሲባረክ (ሲቀደስ) ውኃ መሆኑ ይቀርና ወደ ማየ ገቦ ይለወጣል፡፡

ውድ የእግዚአብሔር ልጆች! ማየ ገቦ ማለት ምን መሰላችሁ? ጌታችን በዕለተ ዓርብ አምላካችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ እኛን ለማዳን በመስቀል ላይ በተሰቀለ ጊዜ አንድ ለንጊኖስ የተባለ ጭፍራ (ወታደር) መጣና የጌታችንን ጉኑን በጦር ወጋው፤ የዚያን ጊዜ ደምና ውኃ ከጐኑ ፈሰሰ (ወጣ)፡፡ (ዮሐ. ፲፱፥፴፬) ያ ማየ ገቦ (የጎን ውኃ) ይባላል፤ ከጌታችን በጦር ከተወጋው ጎኑ የፈሰሰልን የምንጠመቀውም በዚህ ውኃ ነው፡፡

ውድ እግዚአብሔር ልጆች! በምንጠመቅምበት ቀን ካህኑ የክርስትና ስም ይሰይመናል፤ ስንወለድ ወላጆቻችን ስም ያወጡልናል፤ ክርስትና ልንነሣ ስንመጣ ደግሞ ቅድስት ቤተ ክርስቲያን የማይጠፋ ስምን ትሰጠናለች፡፡ በቤተ ክርስቲያን መንፈሳዊ አገልግሎት ስንፈልግ የምንጠራው ቤተ ክርስቲያን በሰጠችን የክርስትና ስም ነው፡፡ የክርስትና ስም መጽሐፍ ቅዱሳዊ ትውፊት ያለው ነው፡፡ ይህም እግዚአብሔር አብራምን አብርሃም፣ ያዕቆብን እስራኤል፣ ሰምዖንን ጴጥሮስ፣ ሳውልን ጳውሎስ በማለት ስማቸውን እንደለወጠው ያለ ነው፡፡ (ስማቸውን እንደቀየረላቸው ነው)፡፡

በምንጠመቅበት ጊዜ ደግሞ ስለ እምነታችን ባለው ነገር ሁሉ ኃላፊነት የሚወስዱ የክርስትና አባትና እናት እንዲኖረን ይደረጋል፤ ይህንን ሥርዓት ያበጁልን (የጀመሩት አባት) በአራተኛው መቶ ክፍለ ዘመን የነበሩት የቤተ ክርስቲያናችን የመጀመሪያው ኤጲስ ቆጶስ አባ ሰላማ ከሣቴ ብርሃን ናቸው። ዓላማውም መንፈሳዊ ዝምድናን (አበ ልጅነትን) ማጠናከሪያ መንገድ ነው። የክርስትና አባትና እናት ክርስትና ያነሧቸው ልጆች በሥጋ ከወለዷቸው ልጆች ሳይለዩ ሕፃናቱ ዕድሜያቸውም ለትምህርት ሲደርስ መሠረታዊ የሃይማኖት ትምህርት የማስተማር ግዴታ እንዳለባቸው የተጠማቂውን ሕፃን ጣት በመያዝ ቃል ይገባሉ፤ ሕፃኑን (ሕፃኗን) ወክለው የሃይማኖት ጸሎት ይጸልያሉ። በገቡት ቃል መሠረት በተግባር የመተርጎም ኃላፊነት አለባቸው።

ውድ የእግዚአብሔር ልጆች! ሕፃኑ ሊጠመቅ ሲል ዲያቆኑ በሁለት እጆቹ ወደ ላይ ከፍ አድርጎ በመያዝ ‹‹ለአብ አሰግድሃለሁ፤ ለወልድ አሰግድሃለሁ፤ ለመንፈስ ቅዱስ አሰግድሃለሁ›› በማለት መጀመሪያ ወደ ምዕራብ አቅጣጫ፣ በመቀጠል በመጠመቂያው ገንዳ አንጻር (ትይዩ) ወደ ምሥራቅ በማዞር ሕፃኑን (ሕፃኗን) ያሰግዳል፤ ይህም ምሳሌነቱ ወደ ምዕራብ መዞሩ በሲኦል በመከራ እንደነበርን ወደ ምሥራቅ መመለሳችን ደግሞ ወደ ገነት የመመለሳችን ምሳሌ ነው፡፡

ከዚያም ካህኑ ተቀብሎ በመጠመቂያው ገንዳ (በተዘጋጀው ጸበል) ውስጥ ሦስት ጊዜ ብቅ ጥልቅ እያደረገ ያጠመምቃቸዋል፤ ሦስት ጊዜ መሆኑ የቅድስት ሥላሴ ሦስትነት ምሳሌ ነው፤ የአጠማመቁ ሥርዓት ተመሳሳይ መሆኑ የአንድነታቸው ምሳሌ ነው፡፡ የመንፈስ ቅዱስ ጸጋን የሚያሳድርብን ቅብዐ ሜሮን  (ቅዱስ) ቅባትን በተለያየ የሰውነታችን ክፍል ይቀቡናል፤ የመንፈስ ቅዱስ ጸጋም አድሮብን የእግዚአብሔር (የቅድስት ሥላሴ) ልጆች እንሆናለን፡፡ (ከርከዴን ገጽ ፲፭)

በአንገታችንም የክርስተናችን ምልክት የሆነውን ማዕተብ (ክር) እናስራለን፤ ‹‹ማዕተብ›› የሚለው ቃል ‹‹ዐተበ›› ካለው የግእዝ ግሥ የተገኘ ሲሆን ትርጉሙም ‹‹አመለከተ››  ማለት ነው። ስለዚህ ማዕተብ ማለት ምልክት ማለት ነው። (አለቃ ኪዳነ ወልድ ክፍሌ መዝገበ ቃላት ገጽ ፮፻፬)

በሃይማኖት አምነው ለተጠመቁ ክርስቲያኖች የሚሰጥ ምልክት (መታወቂያ) ወይም ማኅተም ማዕተብ በሦስት ዓይነት ቀለም (ጥቁር፣ ቀይ፣ ነጭ ክሮች) መሆኑ የሦስትነት (የሥላሴ) ምሳሌ ነው። ሦስቱ ክሮች ደግሞ በአንድ ተገምደው መሠራታቸው የእግዚአብሔር የአንድነቱ ምሳሌ ነው። ክርስቲያን ማዕተብ በማሰሩ ስለ ክርስቲያንነቱ ሳያፍር ይመሰክርበታል፤ አጋንንትን ድል ይነሣበታል፡፡ ተጸልዮበት ተባርኮ የሚታሠር ነውና ከቤተ ክርስቲያን በረከትን ያገኝበታል፡፡  ማዕተብ ማሰርን ያስጀመረው ቅዱስ ያዕቆብ ዘእልበረዲ ክርስቲያኖችን ከመናፍቃን ለመለየት ማዕተብ ያስርላቸው እንደነበር በመጻሕፍት ተጽፏል፡፡ (ከርከዴን መጽሐፍ ገጽ ፲፭) ቀጥሎም ከቅዱስ ቁርባን እንቀበላለን፤ ከዚያም አዲስ ሕይወትን እንጎናጸፋለን፤ የቤተ ክርስቲያን አባል እንሆናለን፤ የእግዚአብሔር ልጆች እንሰኛለን፡፡

ውድ እግዚአብሔር ልጆች! እጅግ ጥልቅና ሰፊ ከሆነው ከምሥጢረ ጥምቀት ትምህርት በመጠኑ ተመልክተናል፡፡ እንግዲህ በጥምቀት ያገኘናትን ልጅነት እስከመጨረሻ በመጠበቅ ሥነ ምግባርን በመፈጸም ልንገልጣት ያስፈልጋል፤ መልካምነት የሚጀምረው ከቤታችን ነው፤ ክርስትናን ልንጠራባት ሳይሆን ልንኖራት ነውና የተቀበልናት፤ መልካም ሥነ ምግባር ያለውን ታዛዦች ጎበዞች፣ አስተዋዮች መሆን አለብን፡፡ ቸር ይግጠመን!!!

ስብሐት ለእግዚአብሔር

ወለወላዲቱ ድንግል

ወለመስቀሉ ክቡር አሜን!!!