ምሥጢረ ሥጋዌ

ዲያቆን ተስፋዬ ቻይ  

ሚያዚያ ፴፤፳፻፲፮ ዓመተ ምሕረት

ውድ የእግዚአብሔር ልጆች! እንዴት አላችሁልን! እንኳን ለብርሃነ ትንሣኤው አደረሳችሁ! የትንሣኤ በዓል እንዴት ነበር? ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ እኛን ለማዳን በፈቃዱ በቅዱስ መስቀል ላይ ተሰቅሎ በመቃብር ሦስት ቀንና ሦስት ሌሊት ከቆየ በኋላ ሞትን ድል አድርጎ ተነሣ፤ ይህች ዕለት ታላቅ ዕለት ናት!

ልጆች! በሰንበት ትምህርት ቤት በመግባትም ተማሩ፤ በቤተ እግዚአብሔር ማደግ መታደል ነው! ሌላው ደግሞ በዘመናዊ ትምህርታችሁም በርቱ! ሁለተኛው የመንፈቀ ዓመት እየተገባደደ ነው! ምን ያህል ዕውቀትን አገኛችሁ? ትናንት ከነበራችሁ ላይ የተለየ ነገር ምን ጨመራችሁ? ይህን ጥያቄ ሁል ጊዜ ራሳችንን ልንተይቀው ይገባል፡፡ መልካም! አሁን ለዛሬ ወዳዘጋጀንላችሁ ትምህርት እናምራ፤ ባለፈው ምሥጢረ ሥላሴን ተምረን ነበር፤ ዛሬ ደግሞ ስለ ምሥጢረ ሥጋዌ እንማራለን፤ ተከታተሉን!

ሥጋዌ “ተሠገው” ከሚለው ግእዝ ቃል የወጣ ሲሆን ትርጉሙም “ሥጋ ሆነ፤ ተዋሐዳ ወይም ሰው ሆነ፤ ሥጋ መሆን፣ ሥጋ ባሕርይ፣ መግዘፍ” ማለት ነው፡፡ (አለቃ ኪዳነ ወልድ ክፍሌ መዝገበ ቃላት ገጽ ፮፻፹፩) ምሥጢረ ሥጋዌ የአምላክ ሰው የመሆን ምሥጢር፣ ሥጋ መሆን ምሥጢር ነው፡፡ ምሥጢረ ሥጋዌ ምሥጢር የተባለበት ምክንያት እግዚአብሔር ዓለምን ከፈጠረበት ጥበቡ ይልቅ ዓለምን ያዳነበት ጥበቡ ይረቃልና ነው፡፡ ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ ‹‹እግዚአብሔርን የመምሰል ምሥጢር ያለ ጥርጥር ታላቅ ነው፤ በሥጋ የተገለጠ….›› እንዲል፤ (፩ጢሞ. ፫፥፮) ምሥጢረ ሥጋዌ የእግዚአብሔር ወልድ ሰው የመሆን ከእመቤታችን ከቅድስት ድንግል ማርያም መወለዱን የሚያስረዳ ታላቅ ምሥጢር ነው፡፡

ውድ የእግዚአብሔር ልጆች! ለምን ሰው ሆነ ስንል የአዳምና የሔዋንን ታሪክ መመልከት ግድ ይለናል፤እግዚአብሔር አዳምን በመልኩና በምሳሌው በክብር ፈጥሮ በገነት አኖረው፤ በገነት በሚኖርበት ጊዜ ምን ማድረግ እንዳለበትና እንደሌለበት እንዲህ የሚል ሕግንና ትእዛዝን ሰጠው፤  ‹‹… ከገነት ዛፍ ሁሉ ትበላለህ፤ ነገር ግን መልካሙንና ክፉውን ከሚያሳውቀው ዛፍ አትብላ፤ ከእርሱ በበላህ ቀን ሞትን ትሞታለህ›› አለው፡፡ (ዘፍ.፪፥፲፯)

አዳም ሰባት ዓመት በገነት ሕግ አክብሮ ትእዛዝ ፈጽሞ ኖረ፤ (ኩፋሌ ፬፥፲፬) ነገር ግን አዳምና ሔዋን በከይሲ ዲያቢሎስ አሳሳችነት አትንኩ የተባሉትን ነኩ፤ ያልተሰጣውን አምላክነት ፈለጉ፤ በደሉ፤ የተጎናጸፉት የብርሃን ልብስ ተገፈፈ፤ ልጅነትን፤ ክብርን፣ ሕይወትንና ገነትን አጡ፤ ከእግዚአብሔር ተጣሉ፤ በደላቸው አስፈረደባቸው፤ ጠላት ዲያሎስ በባርነት ገዛቸው፤ ያም መከራ ለሰው ልጆች ሁሉ ደረሰ፡፡ ‹‹ስለዚህ ምክንያት ኃጢአት በአንድ ሰው ወደ ዓለም ገባ፤ በኃጢአትም ሞት፡፡ እንደዚሁም ሁሉ ኃጢአትን ስላደረጉ ሞት ለሰው ሁሉ ደረሰ…›› እንዲል፡፡ (ሮሜ.፭፥፲፪)

አዳምና ሔዋን በዚህም ተስፋ ሳይቆርጡ ንስሓ ገቡ፤ ተጸጸቱ፤ አለቀሱ፤ እግዚአብሔርም ከ፶፻፭፻ (ከአምስት ሺህ አምስት መቶ) ዘመን በኋላ ሊያድናቸው ቃል ገባ፤ ተስፋን ሰጣቸው፡፡ (ሲራክ ፳፬፥፬-፮፣ ተአምረ ኢየሱስ ሁለተኛ ተአምር ቁጥር ፲፭-፲፮)

በተለያዩ ዘመናት በነቢያት አድሮ ትንቢትን አናገረ፤ ብዙ ምሳሌንም አስመሰለ፤ የመከራው ጊዜ ሲያበቃ ቅዱስ ገብርኤልን ወደ እመቤታችን ላከው፤ ቅዱስ ገብርኤልም እንዲህ ሲል ለእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም አበሠራት፤ ‹‹…ማርያም ሆይ፥ በእግዚአብሔር ፊት ጸጋ አግንተሻልና አትፍሪ፤ እነሆ ትፀንሻለሽ ወንድ ልጅም ትወልጃለሽ፤ ስሙንም ኢየሱስ ትይዋለሽ …፤›› (ሉቃ.፩፥፴) እመቤታችንም ጌታችንን በድንግልና ፀንሳ በድንግልና ወለደችው፤ እረኞችም አመሰገኑ፤ ሰብአ ሰገልም ወርቅ፣ ዕጣንና ከርቤን ስጦታ አመጡለት፡፡

ንጉሥ ሄሮድስም ‹‹ተወለደ›› የሚለውን ሲሰማ ሊገለው በፈለገ ጊዜ ለእኛ አርአያ ሊሆንና እኛን ከስደት ሊመልሰን በሕፃንነቱ ከእመቤታችን ከቅዱስ ዮሴፍና ከቅድስት ሰሎሜ ጋር ተሰደዱ፤ ከስደትም መልስ ጌታችን ቅዱስ ዮሴፍን እያገለገለው ለእመቤታችንም እየተላላከ አደገ፡፡ (ተአምረ ኢየሱስ ተአምር አምስት) ፴ (ሠላሳ) ዓመት በሆነው ጊዜ በዮርዳኖስ ወንዝ ተጠመቀ፤ የምሥራቹን  ወንጌል ዞሮ አስተማረ፤ ስለ እኛ ሲል በመስቀል ላይ ተሰቀለ፤ ሞትን ድል አድርጎ ተነሣ፤ ወደ ሰማይም ዐረገ፤ ለቅዱሳን ሐዋርያት፣ለሰባ ሁለቱ አርድእት፣ ለሠላሰ ስድስቱ ቅዱሳን አንስት በአጠቃላይ ለ ፻፳ /መቶ ሃያ/ ቤተ ሰብ መንፈስ ቅዱስ ጸጋን ላከላቸው፡፡ (የሐ.ሥራ.፩፥፲፭፣፪፥፩)

ውድ የእግዚአብሔር ልጆች! ምሥጢረ ሥጋዌ አምላክ ሰው የመሆኑን ምሥጢር የምንማርበት ነው፤የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስን ከሰማያት ወርዶ በምድር ላይ ሲመላለስ ያደረጋቸውን በአጭሩ ተመለከትን፤ አሁን ደግሞ ‹‹አምላክ ለምን ሰው ሆነ›› የሚለውን እንመልከት፡፡

ለካሣ፡- ካሣ የበደለው ወገን ለተበዳዩ የሚያቀርበው በጎ ምላሽ ወይም ስጦታ ነው፤  አዳም ደግሞ የበደለውን እግዚአብሔር የሚክስበት ነገር የለውም፤  ‹‹የኃጢአት ደሞዝ ሞት ነው፡፡›› (ሮሜ ፮፥፳፫) ሞት የተፈረደበት አዳም መካስ አልቻለም፡፡ እግዚአብሔር አዳም በበደለ ራሱ ሊክሰው ቃል ኪዳን በገባለት መሠረት ለእኛ ሲል ሰው ሆነ፤ ‹‹….እንግዲህ ልጆች በሥጋና በደም ስለሚካፈሉ እርሱ ደግሞ በሞት ላይ ሥልጣን ያለውን በሞት እንዲሽር፣ ይኸውም ዲያቢሎስ ነው፤ በሕይወታቸውም ሁሉ ስለ ሞት ፍርሃት በባርነት ይታሠሩ የነበሩትን ሁሉ ነጻ እንዲያወጣ በሥጋና በደም እንዲሁ ተካፈሉ›› እንዲል፡፡ (ዕብ.፪፥፲፬)

የዲያቢሎስን ጥበብ በጥበቡ ሊሽር፡- ጠላታችን ዲያሎስ በእባብ ሥጋ አድሮ አዳምና ሔዋንን ዋሽቶ ‹‹አምላክ ትሆናላችሁ›› ብሎ አሳስቷቸው ነበር፤ እግዚአብሔር ዲያበሎስን ሊያሳፍር እኛን ሊያከብር የዲያብሎስን ጥበብ በጥበቡ ሊሽር ከሰማየ ሰማያት ከልዑል መንበሩ ወረደ፤ ከእመቤታችን ከቅድስት ድንግል ማርያም ከሥጋዋ ሥጋ ከነፍሷ ነፍስን ነሥቶ ሰው ሆነ (ተወለደ፤ በዚህም የዲያብሎስን ጥበብ ሻረ፡፡ ‹‹…የዲያብሎስን ሥራ እንዲያፈርስ የእግዚአብሔር ልጅ ተገለጠ…›› እንደተባለው፤ (፩ ዮሐ.፫፥፱) አዳምን ያሳሳተ ዲያብሎስን ፈጣሪያችን ክርስቶስ በመስቀል ላይ ድል አድርጎ አዳምን ከባርነት ነጻ አወጣው፡፡ (ቆላ.፪፥፲፬)

የሰውን ልጅ ከጠፈበት ለመፈለግ፡- አዳም በበደለ ጊዜ ከበለስ ሥር ተደበቀ በዚህን ጊዜ እግዚአብሔር       ‹‹አዳም ወዴት ነህ …››  አለው፤ (ዘፍ.፫፥፲)  አዳም በበደሉ ከፈጣሪው ዕቅፍ ወጣ፤ በኃጢአት ዓለም ጠፋ፤ ጌታችንም የጠፋውን አዳም ለመፈለግ ለጸጋ እግዚአብሔር የራቀዉን ከክብር ሕይወት የተለየውን፣ ከብርሃን ወደ ጨለማ ከገነት ወደ ምድር የተሰደደውን አዳም ሊፈልግ አላዋቂ ሥጋን እንደሚዋሐድ ሊያጠይቅ ይህን ተናገረ፤ ጌታችን አዳምን ሊያድን ሊፈልግ እንደመጣ ሲገልጽም ‹‹የሰው ልጅ የጠፋውን ለማዳን መጥቷልና፤ ለአንድ ሰው መቶ በጎች ቢኖሩት ከእርሱ አንድ ቢባዝን  ዘጠና ዘጠኙን በተራራ ትቶ ሄዶም የባዘነዉንም አይፈልግምን…..››‹‹እንደዚሁ ከእነዚህ ከታናናሾቹ አንዱ እንዲጠፋ በሰማያት ያለው አባታችሁ ፍቃድ አይደለም፡፡›› (ማቴ. ፲፰፥፲፪)

የሰዉ ልጆች ልያዩት ይመኙት ነበር፡ – በብሉይ ኪዳን የነበሩ አባቶቻችን እግዚአብሔርን ብዙ ጊዜ ሊያዩት ይመኙ ነበር፤ በአንድ ወቅት ሊቀ ነቢያት ሙሴ ‹‹እባክህ ክብርህ አሳየኝ››  በማለት ጠይቆ ነበር፤ እግዚአብሔርም ‹‹ሰው አይቶኝ አይድንምና ፊቴን ማየት አይቻልህም›› በማለት ነገረው፤ በኋላ ዘመን ወደ ምድር ሲመጣ ግን እንደሚያየው ቃል ገባለት፡፡ (ዘጸ. ፴፫፥፳)  ለዚህም ነው ሰዎች ሊያዩት ይመኙ ነበርና ከእመቤታችን በተወልደ  ጊዜ ሰዎች አዩት፤ ቅዱስ ዮሐንስ ወንጌላዊው በመልእክቱ እንዲህ ገልጾልናል፤ ‹‹ስለ ሕይወት ቃል ከመጀመሪያው የነበረውንና የሰማነውን በዓይኖቻችንም ያየነውን፣ የተመለከትነውን እጆቻችንም የዳሰሱትን እናወራለን፡፡ ….፡፡›› (፩ዮሐ.፩፥፩-፬)

ለሰው ልጅ የሰጠውን የተስፋ ቃል ሊፈጽም፡- ለአዳምና ለሔዋን በገባላቸው ቃል ኪዳን መሠረት ያንን ተስፋ ሊፈጽም ተወለደ፤ ለዚህም ነው ቅዱስ ጳውሎስ ‹‹ነገር ግን የዘመኑ ፍጻሜ በደረሰ ጊዜ፣ እግዚአብሔር ከሴት የተወለደውን፣ ከሕግም በታች የተወለደውን ልጁን ላከ፤ እንደ ልጆቹ እንሆን ዘንድ ለሕግ በታች ያሉትን ይዋጅ ዘንድ …..›› እንዳለ እኛን ሊያድነን ቃሉን ሊፈጽም ሰው ሆነ፡፡ (ገላ.፬፥፬)

ውድ የእግዚአብሔር ልጆች! እጅግ ጥልቅና ሰፊ ከሆነው ከምሥጢረ ሥጋዌ ትምህርት በመጠኑ ተመልክተናል፤ አምላካችን ለምን ሰው እንደሆነ ተማርን፤ አዳምና ሔዋን ሕግ በመተላለፋቸው ትእዛዝ ባለማክበራቸው ብዙ መከራ እንደ ገጠማቸው፤ ትእዛዝንን መጣስ ለመከራ ስለሚዳርግ ታዛዦችና የታላላቆችን ቃል የምናከብር መሆን እንዳለብን ያስተምረናል፡፡

እንዲሁም ልጆች! አምላካችን እኛን ለማዳን የከፈለልን ዋጋ ምን ያህል ታላቅ እንደሆነም ተገንዝባችኋል አይደል? እኛም ሕጉንና ትእዛዙን አክብረን መኖር አለብን እሺ ልጆች! መልካም በዓለ ሃምሳ ይሁንላችሁ! ቸር ይግጠመን!

ስብሐት ለእግዚአብሔር

ወለወላዲቱ ድንግል

ወለመስቀሉ ክቡር አሜን!!!