ምሕረት ሥጋዊና ምሕረት መንፈሳዊ

መስከረም ፭ ቀን ፳፻፲፭ ዓመተ ምሕረት

የምሕረት አምላክ ቸሩ ፈጣሪያችን እግዚአብሔር ኃጢአት በደላችንን ሁሉ ታግሦ እንደ ሥራችን ሳይሆን እንደ ቸርነቱ ለአዲሱ ዓመት አበቃን፡፡ ዕድሜ ለንስሓ ዘመን ለፍስሐ ያደለን አምላካችን በሰጠን የተፈጥሮ ጸጋ ተጠቅመን ከክፉ መንገዳችን እንድመልስ፣ ከኃጢአት እንድንነጻ እንዲሁም በጎ ሥራ እንድሠራ ነው፡፡ ምሕረቱ የበዛ ቁጣውም የራቀ ቸርነቱ አያልቅምና በእርሱ ጥላ ሥር ተጠልለን በሥነ ምግባር እንድንኖር መልካም ፈቃዱ ሆነ፡፡ ይህንንም በቅዱሳን ልጆቹ ላይ ፈጽሞ አሳይቶናል፡፡ በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ስም ክርስቲያን የተባልን በሙሉም ምሕረትን ስለማድረግ ልናውቅ ያገባናል፡፡ ሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያን ምሕረት በሁለት እንድሚከፈል ያስተምሩናል፤ እነርሱም ምሕረት ሥጋዊና ምሕረት መንፈሳዊ ናቸው፡፡

ምሕረት ሥጋዊ

በሥጋ ምሕረት ማድረግ ለተቸገረ ሰው የሚያስፈልገውን ነገር ማድረግ ነው፡፡ ይህም ካለን ንብረት ወይም ገንዘብ ከፍለን የተራቡትን ማብላት፣ የተጠሙትን ማጠጣት፣ የተራቆቱትን ማልበስ፣ የታመሙትን ማስታመም እንዲሁም ለችግራቸው መድረስ ይሆናል፡፡

ለዚህም ማንሣት የምንችለው አንድ ታሪክ በመጽሐፍ ቅዱስ ተመዝግቦ ይገኛል፡፡ አንድ ሀብታም ሰው ነበር፡፡ ይህም ሰው ከሚኖርበት ደጅ የሚኖር በቁስል ሕመም የተያዘ አልዓዛር የተባለ አንድ ድኃ ነበር፡፡  ሀብታሙ ሰው ከሚመገበው ፍርፋሪ ያገኝ ዘንድ ይወድ ነበር፡፡ ሆኖም ግን ባለጸጋው ዘወትር ተድላና ደስታ ከማድረግ ውጪ ለአልዓዛር በማዘን አልመገበውም፤ አላስጠጋውምም፡፡

ከዕለታት በአንዱ ቀንም ድኆው ሞተ፤ ቅዱሳን መላእክትም ነፍሱን ወደ ሰማይ አሳርገው ከቅዱስ አባታችን ከአብርሃም አጠገብ አኖሩት፡፡ ባለጸጋውም ደግሞ ሞተ፤ መልአከ ጽልመትም ነፍሱን በጭንቅ ወደ ሲኦል አስገቧት፡፡ በዚያም ሳለ በሥቃይ ሆኖ ወደ ላይ ተመለከተ፤ አበ አብርሃምንም ከሩቅ አየው፤ ከአጠገቡም አልዓዛርን ተቀምጦ ተመለከተ፡፡ እርሱም እንዲህ አለ፤ ‹‹አባት አብርሃም ሆይ፥ እዘንልኝ፤ በዚህች እሳት እጅግ ተሠቃይቻለሁና ጣቱን ከውኃ ነክሮ ምላሴን ያቀዘቅዝልኝ ዘንድ አልዓዛርን ላከው፡፡›› አብርሃም ግን እንዲህ ብሎ መለሰለት፤ ‹‹ልጄ ሆይ፥ አንተ በሕይወትህ ተድላና ደስታ እንዳደረግህ አልዓዛርም እንዲሁ ሁልጊዜ በችጋር እንደነበረ ዐስብ፤አሁን ግን እንዲሁ እርሱ በዚህ ፈጽሞ ተድላና ደስታ ያደርጋል፤ አንተ ግን መከራ ትቀበላለህ፡፡ ከዚህም ሁሉ ጋር ከዚህ ወደ እናንተ ማለፍ የሚሹ እንደማይችሉ፣ ከእናንተ ወገን የሆኑትም ወደ እኛ እንዳይሻገሩ በእኛና በእናንተ መካከል ታላቅ ገደል አለ፡፡›› ባለጸጋውም በመቀጠል እንዲህ አለ፤ ‹‹አባት አብርሃም ሆይ፥ አልዓዛርን ወደ አባቴ ቤት እንድትልከው እለምንሃለሁ፡፡ አምስት ወንድሞች ስለ አሉኝ ይንገራቸው፤ እነርሱም ደግሞ ወደዚህች የሥቃይ ቦታ እንዳይመጡ ይስሙ፡፡›› አብርሃምም ‹‹ሙሴና ነቢያት አሉአቸው፤ እነርሱን ይስሙ›› አለው፡፡ ባለጸጋውምመልሶ ‹‹የለም፤ ‹‹አባት አብርሃም ሆይ፥ ከሙታን አንዱ ወደ እነርሱ ካልሄደና ካልነገራቸው ንስሓ አይገቡም›› አለው፡፡ በመጨረሻም አብርሃም ‹‹ሙሴንና ነቢያትን ካልሰሙማ ከሙታን ተለይቶ የተነሣ ቢኖርም እንኳ አይሰሙትም፤ አያምኑትምም›› በማለት ከሥጋ ሞት በኋላ ንስሓ መግባትም ሆነ ምሕረትን መለመን እንደማይቻል ነግሮታል፡፡ (ሉቃ.፲፮፥፲፱-፴፩)

ባለጸጋው ሰው በሕይወት በምድር በነበረበት ጊዜ ለድኃው አዝኖና ምሕረትን አድርጎ ቢያበላው፣ ቢያጠጣው፣ ቢያለብሰው እንዲሁም ቢያስታምመው ኖሮ በሲኦል ነፍሱ አይሠቃይም ነበር፡፡ በሥጋ ምሕረትን ያላደረገ በነፍሱ ምሕረትን እንደማይገኝ ከዚህ ታሪክ መረዳት ይቻላል፡፡

ምሕረት መንፈሳዊ

አንድን ሰው ከኃጢአቱ ተመልሶ በንስሓ ሥርየትን ያገኝ ዘንድ መርዳት የመንፈሳዊ ምሕረትን ማድረግ ነው፡፡ በዓለም የሚኖርን ወይም ኃጢአተኛን ሰው ምሕረትን እንዲያገኝ ወይም ንስሓ እንዲገባ መርዳት ይቻላል፡፡ አምላካችን እግዚአብሔርን የሚቀርብበትን እውነተኛውን መንገድና ሥርዓት በማስተማር፣ በማስረዳትና በመምከር ካስፈለገም በመገሠጽ ሰው እንዲድን መርዳት ተገቢ ነው፡፡ በቅዱሳት መጻሕፍት ከመጽሐፍ ቅዱስ ጀምሮ በተለያዩ ታሪኮች ላይ ተመዝግቦ እንደምናገኘው አሕዛብን በክህደት፣ ከምንፍቅናና ከተሳሳተ እምነት በመመለስ በክርስትና ጥምቀት ሽህ አእላፍን ያዳኑ ቅዱሳን አባቶች፣ ነቢያት፣ ሐዋርያት፣ መነኮሳት እንዲሁም ሌሎች ጻድቃን ሰማዕታት እንደነበሩ ገድላቸው ምስክር ነው፡፡

በአሁኑ ጊዜ ደግሞ ምእመኑን እንደ በግ መንጋ እየጠበቁ ከጥፋትና ከሞተ ነፍስ እንዲታደጉ አደራ የተቀበሉት ሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያን፣ ካህናትና ሌሎች አገልጋዮች ናቸው፡፡ ሆኖም ግን  የመንፈሳዊ ምሕረት የሚጠበቀው ከሁላችን እንደሆነ በማመን ልንተገብረው ይገባል፡፡ ለምሳሌ ከቤተሰባችን አባላት፣ ከባልንጀሮቻችን ወይም ከዘመድ አዝማዶቻችን መካከል የተጣሉ ቢኖሩ ማስታረቅ እንዲሁም ስለ ይቅርታና ምሕረት ማስተማር ያስፈልጋል፡፡ ጌታችን ኢየሱስ በወንጌል  ‹‹የሚያስታርቁ ብፁዓን ናቸው፤ የእግዚአብሔር ልጆች ይባላሉና›› በማለት አስተምሮናልና፡፡ (ማቴ.፭፥፱) ከባልጀራው ጋር ተጣልቶ እግዚአብሔርን ያስቀየመውን በመካከላቸው ዕርቅ እንዲኖር ማድረግ በአጠቃላይ መንፈሳዊ ሕይወቱ እንዳይጎሰቁል፣ እንዳይደክምና ከጽድቅ እንዳይጎድል መርዳት ነው። ያስቀየመንን ወይም ያስከፋንን ሰው ይቅር ማለት ደግሞ ከተበዳዩ የሚጠበቅ ምግባር እንደሆነ ጌታችን እንዲህ ብሎ አስተምሯል፤ ‹‹ምሕረት የሚያደርጉ ብፁዓን ናቸው፤ ምሕረትን ያገኛሉና፡፡›› (ማቴ.፭፥፯)

በተጓዳኝ ከቤተ ክርስቲያን ርቀውና በምድራዊ ሥራ ተጠምደው በሃይማኖታቸው የደከሙና የዛሉ ወዳጆቻችንን ወይም በቅርብ የምናውቃቸውን ሰዎች መርዳት አስፈላጊ ነው፡፡ ይህንን ማድረግ የምንችለው ደግሞ ቅዱሳት መጻሕፍትን እንዲያነቡ በመጋበዝ፣ አብረናቸው ወደ ቅድስት ቤተ ክርስቲያን በመሄድ በጋራ ጸሎት በማድረግ፣ በማስቀደስ፣ በመማር፣ በዓላትን በማክበርና ቅዱሳንን በቤታችን በአንድነት በመዘከር ነው፡፡ ከዚህም ባሻገር በአጽዋማት ጊዜ አብሮ አጥቢያ ቤተ ክርስቲያናት፣ አቢያተ ቤተ ክርስቲያናትና ገዳማት በመሄድ በጾም፣ በጸሎትና በስግደት እንዲተጉ መርዳት ይቻላል፡፡

ዓለም በአሁኑ ጊዜ መከራና ችግር ጸንቶባት ልጆቻ በየቦታው በሥቃይ እና ችጋር ባሉበት ጊዜ አሳሳቹ ብዙ ነውና ክርስቲያኖች በሃይማኖት ጸንተን በክርስቲያናዊ ሕይወት ለመኖር እርስ በእርስ ልንደጋገፍ ይገባል፡፡ አምላካችን ስንዋደድ፣ ስንተዛዘንና አንድነት ሲኖረን በመካከላችን ስለሚኖርልን የመዳን ተስፋችን የሰፋ ይሆናል፡፡ ስለዚህም በመተሰሰብ፣ በፍቅርና በአንድነት መኖር ያስፈልጋል፡፡

የምሕረት አምላክ እግዚአብሔር ምሕረቱን ያድለን፤ አሜን፡፡

ወስብሐት ለእግዚአብሔር!