‹‹ማእከለ አሥዋክ ዘጸገየት ጽጌ ሃይማኖት፤ በእሾሆች መካከል የበቀለች የሃይማኖት ተክል- ቤተ ክርስቲያን››

(ቅዱስ ያሬድ)

በነቢያት ትንቢት በሐዋርያት ስብከት በክርስቶስ ደም የተመሠረተችው ቅድስት ቤተ ክርስቲያን ዘወትር ውድቀትና ጥፋቷን በሚሹ የውስጥና የውጭ ጠላቶቿ በዘመናት መካከል እጅግ በርካታ የሚባሉ ግፍና መከራዎችን አሳልፋለች፡፡እነዚህ ግፍና መከራዎችም ታሪክና ትውልድ የማይረሳቸው የዘመን ጠባሳዎቿ ሆነው አልፈዋል፡፡

አብያተ ክርስቲያናትን በአዋጅ አዘግተው አብያተ ጣዖታትን በአዋጅ ካስከፈቱት ከሐዲያን ነገሥታት ከእነ ዲዮቅልጥያኖስ መክስምያኖስ ዱድያኖስ ንግሥት አውዶክስያ እና ከሌሎቹ የግብር አበሮቻቸው ዘመን ጀምሮ ይህቺ ቅድስት ቤተ ክርስቲያን በዘመናት መካከል ሕንፃዎቿ ሲፈራርሱ መምህራን ሊቃውንት ምእመናንና ካህናቶቿ በቤተ መቅደስ በሰይፍ ሲታረዱ በመጋዝ ሲሰነጠቁ በመንኰራኵር ሲፈጩ ወደ ጥልቅ ገደል ወደ እቶነ እሳትና ወደ አራዊት ጉድጓድ ሲወረወሩ እንደ ፈጣሪያቸው እንደ ክርስቶስ ሲሰቀሉ ቅዱሳት መጻሕፍቷና የከበሩ ንዋያተ ቅድሳቶቿ ሲዘረፉ ሲቃጠሉ ቅዱሳት ማካናቷ (ይዞታዎቿ) ሲነጠቁ እነዚህ ሁሉ መከራዎች በቅድስት ቤተ ክርስቲያን ላይ ሲፈራረቁባት ኖረዋል፡፡

ይህ ሁሉ ሲሆን ግን ‹‹የገሃነም ደጆች ያነዋውጧት ዘንድ አይቻላቸውም›› ተብሎ እንደተጻፈ ይህቺ ቅድስት ቤተክርስቲያን በእነዚህ ሁሉ መከራዎች ውስጥ ብታልፍም ከፊት ከኋላዋ የሚገፋት የመከራ ማዕበል ሳያናውጻት ሃይማኖቱንና ባህሉን የሚጠብቅ ለነፃነቱ ለሀገሩና ዳር ድንበሩ ክብር የሚሠዋ ፈጣሪውን የሚያከብር ለመሪዎቹም የሚገዛ ግብረ ገባዊ ትውልድን በመቅረጽ ረገድ ጉልህ ድርሻን በማበርከት በሥነ ፊደል፣ በሥነ አኃዝ፣ በሥነ ሥዕል፣ በሥነ ጽሑፍ፣ በሥነ ጥበብ፣ በኪነ ሕንፃና በሥርዓተ ሕግ ቀረጻ ሀገራዊ ክብርንና ዕሴቶችንም በማስጠበቅ በሀገር ግንባታ የሀገር ባለውለታነቷን በብቃት እያስመሰከረች እስከዚህኛው ዘመን ደርሳለች፡፡

በሚዳሰሱና በማይዳሰሱ ልዩ ልዩ መንፈሳዊና ቁሳዊ ቅርሶቿ የኢትዮጵያ መልካም ገጽታ በዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ፊት ጎልቶ እንዲወጣና ዕውቅናን እንዲያገኝ ያደረገች መንፈሳዊት ተቋም መሆኗን በግልጽ ያሳየቸው ታላቋ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ይህንን ታላቅነቷንም መሪዎች እንኳን ሳይቀሩ ‹‹ኦርቶዶክስ ሀገር ናት›› በማለት ኦርቶዶክስ ከተቋም በላይ ከፍ ብላ የምትታይ ታላቅ ሀገር መሆኗን በዐደባባይ በአንደበታቸው መስክረውላታል፡፡

ታዲያ ይህ ባለውለታነቷ በትውልድ ልቡና ውስጥ ተዘንግቶ ውለታዋ ወርቅ ላበደረ ጠጠር አለዚያም ባጎረስኩ እጄን ተነከስኩ ዓይነት ሆኖ ወርቅ የሰጠችው የመጨረሻው ዘመን ዓመፀኛ ትውልድ በላይዋ ላይ ጠጠርን እየደፋ ጥበብን ያጎረሰችበት እጅዋንም መልሶ እየነከሰ ዕለት ዕለት በመከራ ውስጥ እንዲታልፍ ያለፈውን የመከራ ዘመንም እንዲትደግም እያደረጋት ይገኛል፡፡ በዚህም ምክንያት የሚነድባትን እሳት ለማጥፋት የካህናትና ምእመናን ወገኖቿን ሕይወት ከሞት ለመታደግ በአጠቃላይ የሆነባትንና እየሆነባት ያለውን መከራዋን ሁሉ ለማስታገሥ ሀገርን ከሚመሩና በየደረጃው ከሚያስተዳድሩ የተለያዩ የመንግሥት ባለሥልጣናት የሀገር ሽማግሌዎች የሃይማኖት አባቶች የጎሣ መሪዎች ጋር ደግማ ደግጋማ መክራለች በልዩ ልዩ ሚዲያዎችም የሚፈጸምባትን ጥቃት መንግሥት እንዲያስቆም የምእመናን ልጆቿንም ሕይወት ከአጥፊዎች እንዲታደግ ለመገናኛ ብዙኃን በሰጠቻቸው ጋዜጣዊ መግለጫዎች ደጋግማ ጠይቃለች፤ አሳስባለች፡፡

በከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ላይ አጥልቶ የሚታየው የጥቃት ድባብ ወደ ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት እንዲማሩ ልጆቻቸውን የላኩ ወላጆችንም ሆነ ተማሪዎችን በተረጋጋ መንፈስ እንዲኖሩ የሚፈቅድ አይደለም። በአንዳንድ ቦታ አልፎ አልፎ እየተከሰቱ ያሉ አደጋዎችና ሁከቶች ወላጆችን ለከፍተኛ ሥጋትና ጭንቀት እየዳረጋቸው ነው፡፡

በሀገር ውስጥና በውጭ ሀገራት በሚኖሩ ኦርቶዶክሳውያን ታይተው የማይታወቁ የሚመስሉ ሰላማዊ ሰልፎችንም በማድረግ በእኔ ላይ በካህናትና ምእመናን ልጆቼም ላይ እየተፈጸመ ያለውን አሰቃቂ ግፍ መንግሥት ያስቁምልኝ በማለት ያለማቋረጥ ድምጽዋን እስከ ዓለማቀፉ ማኅበረሰብ አሰምታለች፡፡ ይሁን እንጂ ነገሩ ‹‹አውቆ የተኛን ቢቀሰቅሱት…›› እስኪመስል ድረስ ጩኸቷን ሰምቶ ምላሽ የሚሰጣት፣ ከሚፈጸምባት አሰቃቂ ግፍ ከሚደርስባትም ጽኑ መከራ የሚታደጋት አካል ማግኘት አልቻለችም፡፡

ሊቁ ቅዱስ ያሬድ ‹‹ማእከለ አሥዋክ ዘጸገየት ጽጌ ሃይማኖት፤ በእሾሆች መካከል የበቀለች የሃይማኖት ተክል›› በማለትስለ ቅድስት ቤተ ክርስቲያን አስቀድሞ በድጓው እንደተናገረው ቅድስት ቤተክርስቲያን ከቀደመው ዘመን ማለትም በክርስቶስ ደም ከተመሠረተችበት ጊዜ ጀምሮ አኗኗሯ ሁሉ ውድቀቷንና ጥፋቷን በሚሹ በአሕዛብ በመናፍቃንና በዓላውያን ነገሥታት በእነዚህ እሾሆች መካከል ነው፡፡

በዘመናት መካከል እጅግ በጣም አሳዛኝ መከራዎችን ያሳለፈችው ቅድስት ቤተ ክርስቲያን ጉዞዋን የመከራ ጉዞ እንዲሆን ካደረጉት ውስጥ በዙሪያዋ የበቀሉት እሾሆች ማለትም ግራኝ አሕመድና ዮዲት ጉዲት ተጠቃሾች ሲሆኑ እነዚህ  እሾሆች የፈጸሙባት ግፍ ያደረሱባትም መከራ በትውልድ አእምሮ ሲታወስ እጅግ በጣም የሚዘገንን ነው፡፡ ታሪካዊ ጠባሳውም ከቅድስት ቤተክርስቲያንና ከምእመናን ልጆቿ ሕሊና ውስጥ ፈጽሞ የሚጠፋ አይደለም፡፡ ዛሬ ደግሞ በዘመናችን በቀደመው መጥፎ የመከራና የሥቃይ ዘመኗ የሆባትን ትውስታዋን የሚያገረሹ በዙሪያዋ የበቀሉ ሌሎች እሾሆች (ቋንቋ ተኮር፣ ዘር ተኮርና ሃይማኖት ተኮር ጥቃቶች) አበባዎቿን ምእመናን ፍሬዎቿን ካህናትን ንዋያተ ቅድሳትን እያረጋፏቸው ይገኛሉ፡፡

በዘመናችን ቋንቋን ሽፋን ባደረገ ሥውር ተልእኮ አንዱ ቋንቋን አጀንዳ አድርጎ በመነሣት አሐቲ (አንዲት) የሆነችውን ቅድስት ቤተክርስያንን ነፍስና ሥጋዋን ለሁለት ካልከፈልኩ በማለት ሲፈትናት ይህንንም እንደ አጋጣሚ በመጠቀም በእጅአዙር የሚጠመዝዟት ፖለቲከኞች ሳይቀሩ በፖለቲካ ችግር ውስጥ ሊዘፍቋት ሲሞክሩ ይስተዋላሉ፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ የዘር ፖለቲካን አንግቦ በክርስቶስ ክርስቲያን ለተሰኙት ኦርቶዶክሳውያን ሁሉ እናት የሆነችውን ዓለማቀፋዊቷን ቤተክርስቲያንን የአንድ ብሔር የእምነት ተቋም ክርስትናንም የአንድ አካባቢ ማኅበረሰብ ሃይማኖት አድርጎ የመመልከት አባዜ የተጠናወታቸው የተማሩ የሚባሉ ነገር ግን ካልተማረው ማኅበረሰብ በታች ሆነው ብሔርንና ሃይማኖትን መለየት የተሳናቸውን ምሁራንን እየተመለከትን ነው፡፡

አንድ ተማርኩ ነኝ ባይ ቀርበው በሀገራዊ ወቅታዊ ጉዳዮች ዙሪያ ከጋዜጠኛ ጋር ውይይት ባደረጉበት ወቅት ‹‹በአባቶቻችን ጊዜ አንድ መቶ ወንድ በዚህ ወደ ወንዝ ይነዳል አንድ መቶ ሴት ደግሞ በዚያ ወደ ወንዝ ይነዳል  በማይታወቅ ቋንቋ ቄሱ አንድ ነገር መርመር ያደርጋል ከዚያም አንድ እፍኝ ውኃ ሴቶቹ ላይ ወርውሮ አንድ እፍኝ ውኃ ወንዶቹ ላይ ወርውሮ ከዚህ መልስ ወልደ ማርያም ከዚህ መልስ ወለተ ማርያም እያለ ነበር የሚያጠምቀው በእሱ ነው ኢትዮጵያዊ የሚሆነው›› ብለው እንደተናገሩ የቅርብ ቀን ትውስታችን ነው፡፡

ከዚያ በመቀጠል ደግሞ ‹‹በእርስዎ አረዳድ ሰዎች በዚያ በጥምቀቱ ላይ የሚቀበሉት አማራነትን ነው? ወይስ ክርስትናን?›› ተብለው ከጋዜጠኛ ለቀረበላቸው ጥያቄ ምላሽ ሲሰጡም ‹‹በትክክል  አማራነትን ነው የሚቀበሉት ክርስቲያን ማለት አማራ ማለት ነው አማራ ማለትም ክርስቲያን ማለት ነው፡፡ ከኦሮሞነት የሚያፀዳው ጥምቀቱ ነው ከኦሮሞነት ሊያጸዱ ነው የሚጠምቁት›› ብለው በተናገሩበት ወቅት በከፍተኛ የትምህርት ደረጃ ላይ የሚገኙ ምሁራን እንኳን ሳይቀሩ በአስተሳሰባቸው ካልተማሩ ነገር ግን እንደዚህ ካሉት ምሁራን በላይ የላቀ አስተሳሰብ ካላቸው ቤተሰቦቻችን አንሰው አይተናቸዋል፡፡ እንግዲህ እንደ ግለሰቡ አነጋገር ኦርቶዶክሳዊት ቅድስት ቤተክርስቲያን አዳዲስ አማንያንን ወንጌለ መንግሥትን አስተምራ የምታጠምቀው ሰማያዊቷን የክርስቶስን መንግሥት ለማውረስ ሳይሆን ብሔርተኝነትን ወይም አማራነትን ለማላበስ ወይም ደግሞ ከአንድ ብሔር ወስዳ የሌላኛው ብሔር አካል ለማድረግ ነው፡፡ ግለሰቡ ይህንን የተናገሩት በቅድስት ቤተክርስቲያን ላይ ያላቸውን ታላቅ ጥላቻ ለመግለጽ እንጂ ቤተክርስቲያን ምእመናንን አስተምራ የምታጠምቀው ብሔርተኝነትን ለመጫን እንዳልሆነ ይጠፋባቸዋል ብለን በፍጹም አናምንም፡፡

መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስም በመዋዕለ ስብከቱ በምድር ላይ እየተመላለሰ ወንጌልን ሲያስተምር በነበረበት ጊዜም ‹‹የሚወደኝ ቢኖር መስቀሌን ይሸከምና ይከተለኝ›› በማለት የሰዎችን ፈቃድ መሠረት አግርጎ ተከተሉኝ አለ እንጂ አምላክ በመሆኑ ክርስትናን አስገድዶ በማንም ላይ አልጫነም፡፡ ቅድስት ቤተ ክርስቲያንም የክርስቶስን ወንጌለ መንግሥት ለሰው ልጆች የምትሰብከው በደሙ የመሠረታትን የራሱን የክርስቶስን ትምህርት አብነት አድርጋ ነው፡፡

ይህ የግለሰቡ አነጋገር በዘር ፖለቲካና በጎጠኝነት አስተሳሰብ የተጠመዱ አካላት ብሔርንና ሃይማትን በአንድ ጨፍልቀው በመመልከት ቤተክርስቲያንን የአንድ ብሔር ወይም የአንድ አካባቢ ማኅበረሰብ የእምነት ተቋም፣ ኦርቶዶክሳዊት ክርስትናንም የአንድ ብሔር ሃይማኖት ሆና እንዲትታሰብ ለማድረግ ሲሆን ይህም በመንጋ በተደራጁ የጥፋት ኃይሎች ዘንድ አሁን ላይ በሚታየው ቤተክርስቲያንን፣ ክርስትናንን ክርስቲያኖችን የማጥፋት ዘመቻ የመጀመሪያዋ የጥቃት ዒላማና ሰለባ እንዲትሆን አድግርጓታል፡፡

ሚዲያው የራሳቸው ስለሆነ ብቻ የሕዝቦችን ነፃነትና ክብርን የሚገፋ የሀገርን ደኅንነትም የሚያናጉና በክፉ አስተሳሰባቸው ሌሎችን የሚያከፉ በንግግራቸው ከማስተማር ይልቅ ማሳመጽን ከፍቅር ይልቅ የጥላቻ አስተሳሰብን የሚያራምዱና የሚዲያን መርሕ መሠረት አድርገው የማይናገሩ አካላትን ወደሚዲያቸው በማምጣት በሕግ ከተቀመጠው ገደብም አልፈው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ለሦስት ሺህ ዘመናት ታፍራና ተከብራ በኖረችበት ሀገሯ ከዶግማዊ ቀኖናዊና ትውፊታዊ አስተምህሮዋ ውጭ የሆኑ የአስተምህሮዋንም ባሕርይ ፈጽመው የማያውቁ ግልሰቦች ከአስተምህሮዋ በተቃራኒ ስለቆሙ ወይም እርሷ ከአስተምህሮአቸው በተቃራኒ ስለሆነች እንዲህ ዓይነቱን ከእውነታው ጋር ፍጹም ተቃራኒ የሆነ ትችትን ነቀፌታንና ሃይማኖታዊ ክብርን የሚጋፉ ንግግሮችን እንዲናገሩ የሚያደርጉ፣  የአንዲትን ታላቅ ቤተክርስቲያን አስተምህሮ በአላዋቂዎችና በተቃራኒ ጎራ በተሰለፉ ግልሰቦች የሚያስተቹ  የሚዲያ ባለቤቶች እንደዚሁም ተጋባዥ ግለሰቦቹ በሕግ ሊጠየቁ ይገባል፡፡

ከሐምሌ ወር ፳፻፲ ዓ.ም በሶማሌ ጅግጅጋ በቤተክርስቲያንና በኦርቶዶክሳውያን ላይ ከተደረገው የጥፋት ዘመቻ ጀምሮ እስከ አሁን ድረስ በሀገራችን ልዩ ልዩ አካባቢዎች በቅድስት ቤተክርስቲያንና በኦርቶዶክሳውያን ምእመናን ላይ እየተፈጸመ ያለው አሰቃቂ ጥቃት ለዚህ ዓይነተኛ ማሳያ ነው፡፡

ገዢ ሕግና ሕገ መንግሥት ጨዋ ሕዝብና አስተዋይ ምሁራን ያሏትን ሀገር ምራቃቸውን ያልዋጡ ጽንፈኞች በመንጋ እየፈረዱ ሰላማውያን የሆኑ ምእመናን ወገኖቻችንን በመንጋ ሲያርዱ አብያተ ክርስቲያናትንም ሲያቃጥሉ ሰላምና ፀጥታ አስከባሪው በጥቃት ወቅት አካል በሀገር ውስጥ የሌለ እስኪመስል ድረስ የሚደርሰው የነደደ እስትን ለማጥፋት አለዚያም የሞተውን አስከሬኑን ለማንሣት ነው፡፡ አራጆች ተይዘው በሕግ ፊት ለፍርድ አይቀርቡም ፍትሕና የሕግ የበላይነትም ሥፍራቸውን ለመንጋ ፈራጆች ትተዋል፡፡ በመጽሐፍ ‹‹እግዚአብሔር ሀገርን ካልጠበቀ ጠባቂዎች በከንቱ ይደክማሉ›› ተብሎ እንደተነገረ የሀገርን ደኅንነትና ፀጥታ በማስጠበቅ ከእንደዚህ ዓይነቱ የመንጋ ጥቃትም ሀገርን ይጠብቃል ሕዝብንም ከጥፋት ይታደጋል ተብሎ እምነት የተጣለበት ሕዝባዊ ፖሊስና የመከላከያ ኃይል እግዚአብሔር ሀገርን ካልጠበቀ የጠባቂዎች ድካም ሁሉ ከንቱ መሆኑን በዚህ ዘመን በትክክል አይተንበታል፡፡

በተለይም አንዳንድ የፖሊስ አካላት የተሠጣቸውን ሕዝባዊ አደራ በመዘንጋት ከሀገር ይልቅ ብሔርንና ሃይማኖታዊ ጎጠኝነትን በማስቀደም ፀጥታን የማስከበር ፍትሕንም የማስጠበቅ ኃላፊነታቸውን በአግባቡ ባለመወጣታቸው ምክንያት ማኅበረሰቡ በፖሊስና በሌላው የፀጥታ አካላት ላይ እምነት እንዳይኖረው አድርጎታል፡፡ ከዚህም የተነሣ በአካባቢው ጥቃት በሚፈጸምበት ወቅት ወደ ፀጥታ አካላት ሄዶ የድረሱልኝ ከማሰማት ይልቅ ወደ ቤተ ክርስቲያን በመሸሽ በዚያ መጠለልን እየመረጠ ይገኛል፡፡

የሀገሪቱን ልዩ ልዩ አካባቢዎች ትኩረት አድርጎ ከቋንቋ ወደ ብሔር ከብሔር ደግሞ ወደ ቋንቋ ሲዛመት የሰነበተው የግጭት ወረርሽኝ በሰሞንኛው የጥቃት ሰለባ ደግሞ ትኩረቱን ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ሃይማኖት ላይ በማድረግ በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የሚማሩ ኦርቶዶክሳውያን ተማሪዎችን ተረኛና የጥቃቱ ዒላማዎች አድርጓቸው ሰንብቷል፡፡ መነሻውን በወልድያ ዩኒቨርሲቲ ያደረገው ይህ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ተማሪዎች ግጭት በሀገሪቱ በተለይም በኦሮምያ ክልል በሚገኙ በርካታ ዩኒቨርሲቲዎች የሚማሩ ተማሪዎችን የጥቃት ሰለባ አድርጓቿል፡፡ ግጭቱ ከመጀመሪያው ብሔር ተኮር ይዘት ያለው ቢመስልም በስተኋላ ግን ትኩረቱን ሙሉ በሙሉ ወደ ሃይማኖት ቀይሮ ለበርካታ ኦርቶዶክሳውያን ተማሪዎች ሕይወት መጥፋትና አካል መጉደል ከትምህርት ገበታቸውም መፈናቀል ምክንያት ሆኗል፡፡ ወላጆችም ስንቅ ሰንቀው የላኳቸውን ልጆቻቸውን ተምረው ተመርቀው ይመጣሉ ሲሉ ነገሩ ከታሰበው በተቃራኒው ሆኖ አስከሬናቸው እንዲመለስላቸው አድርጓቸዋል፡፡

የሀገርንና የሕዝብን ደኅንነት የመጠበቅና የማስጠበቅ ኃላፊነት ያለበት መንግሥት ሀገር የሆነችው ‹‹ኦርቶዶክስ›› ስትጠፋ ካህናትና ምእመኖቿ የጥፋት ኃይሎች ዒላማ ሆነው በዐደባባይ በእሳት ሲቃተሉ በሰይፍ ሲታረዱ ለዘመናት ያፈራቻቸው ኪነ ሕንፃዎቿ ቅርሶቿና የከበሩ ንዋያተ ቅድሳቶቿ በወንበዴዎች ሲዘረፉና ሲወድሙ መንግሥት የሆነውንና የሚሆነውን ሁሉ እያየ እየሰማ በደብዳቤም ሆነ በአካል እየተነገረው፣ በኦርቶዶክሳዊ ሰልፎቿና በጋዜጣዊ መግለጫዎቿ ያስተላለፈቻቸውን ጥብቅ መልእክቶችም ሆነ ያሰማቻቸውን የድረሱልኝ ጩኸቶች አስቸኳይ ጉዳዩ በማድረግ ከሚደርስባት መከራ ሊታደጋት ፈጽሞ አልተቻለውም፡፡

አባቶቻችን መንግሥት ባልነበረበት ዘመን የቀደመ ልዕልናዋን በማስጠበቅ ታፍራና ተከብራ እንዲትኖር ያደረጓትን ቤተ ክርስቲያንን ዛሬ ሀገርንና ሕዝብን እያስተዳደረ ያለ መንግሥት የዚችን ታላቅ ቤተ ክርስቲያን ደኅንነት ማስጠበቅ ከተሳነው፤ በጽንፈኛ ወራሪዎች በየዐደባባዩ እንደ በግ የሚታረዱትን የምእመናንን ሕይወትም ከሞት መታደግ ከልተቻለው ‹‹እረኛው በጎችን መጠበቅ ከተሳነው በጎች እርስ በእርሳቸው ይጠባበቃሉ›› እንዲሉ ከዚህ በኋላ ኦርቶዶክሳውያን በተጠናከረ ኃይል ተደራጅተው እርስ በእርሳቸው መጠባበቅ ይኖርባቸዋል፡፡ በዚህ ሰዓት ብቸኛ መፍትሔ የሚሆነውም ይህ ብቻ ነውና፡፡ ምእመናን የእግዚአብሔርን ቤተመቅደስና ንዋያተ ቅድሳቱን ሁሉ ነቅተን መጠበቅ እንዳለብን በመጽሐፍ ‹‹የማደሪያውን ሥራ ይሠሩ ዘንድ የመገናኛውን ድንኳን ዕቃ ሁሉ ይጠብቁ›› እንደዚሁም ‹‹መቅደሱንና መሠዊያውን ጠብቁ… እንደዚሁም ወንዶችሁሉ እንደ ቁጥራቸው… መቅደሱን ይጠብቁ ነበር›› ተብሎ የተጻፈው የእግዚአብሔር ቃል የሚያስተምረን ይህንን ነው፡፡ (ዘኁ.፫፥፰-፳፰)

የእግዚአብሔርን ቤተ መቅደስ ነቅቶ የመጠበቅ ድርሻ ለምእመናን ብቻም ተለይቶ የተሰጠም እንዳልሆነም አባቶቻችን ካህናትም በቤተመቅደሱ ከትመው በንቃት የመጠበቅ ድርሻ እንዳለባቸው ‹‹ሌዋውያን በምስክሩ ማደሪያ ዙሪያ ይሥፈሩ የምስክሩን ማደሪያም ይጠብቁ›› የሚለው የእግዚአብሔር ቃል ይነግረናል፡፡ (ዘኁ.፩፥፶፫)

ዛሬ ላይ በኵራት አሉን የምንላቸው የከበሩ ንዋያተ ቅድሳትና የብራና ቅዱሳት መጻሕፍት አባቶቻችን በቀደሙት የቤተክርስቲያን የመከራ ዘመናት በዱር በገደል በዋሻ በፍርኩታ በባሕር ውስጥና በከርሠ ምድርም ሳይቀር በመሠወር ጠብቀው ስላቆዩልን ነው፡፡ ስለሆነም የዘመናችንም ምእመናንና ካህናት የቀደሙትን አባቶቻችንን እምነትና ጥንካሬ አርአያ፣ ረድኤተ እግዚአብሔርንም አጋዥ በማድረግ ቅድስት ቤተክርስቲያንና የከበሩ ንዋያተ ቅድሳቷን ከጽንፈኛ ኃይሎች ለመታደግ እስከ ሞት ድረስ መሥዋዕትነትን በመክፈክ ለመጪው ትውልድ በክብር ማስተላለፍ አለብን፡፡

ምንጭ፡-ስምዐ ጽድቅ ጋዜጣ ኅዳር ፳፻፲፪ ..