tena gedamate

ማኅበረ ቅዱሳን የአልባሳት ማሰባሰቢያ መርሐ ግብር አዘጋጀ

ታኅሣሥ 18 ቀን 2006 ዓ.ም.

በታመነ ተ/ዮሐንስ

tena gedamateበኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ማኅበረ ቅዱሳን ‹‹የአብነት መምህራንና ተማሪዎችን ጤና ለመጠበቅ›› በሚል ከታኅሣሥ 1 እስከ ጥር 6 ቀን 2006 ዓ.ም ድረስ የሚቆይ መርሐ ግብር አዘጋጀ፡፡

የማኅበሩ የቅዱሳት መካናት ልማትና ማኅበራዊ አገልግሎት ክፍል በሥሩ የአብነት ትምህርት ቤቶች ማጠናከሪያና ማቋቋሚያ መርሐ ግብርን ነድፎ በሁሉም አኅጉረ ስብከት በመቶ ሰባ ሁለት የአብነት ትምህርት ቤቶች ላይ ተግባራዊ በማድረግ ላይ ይገኛል፡፡ የአብነት ት/ቤቶች እየገጠሟቸው ካለው የገንዘብ፣ የቀለብ፣ የአልባሳት፣… ችግሮች ጎን ለጎን በጤና መስኩ ያለው ተግዳሮት ጊዜ የማይሰጥ ሆኖ በመገኘቱ ይህ መርሐ ግብር ለሁለተኛ ጊዜ ሊዘጋጅ ችሏል፡፡

የጤና ችግሩ ከመምህራን አኳያ ሲታይ ምትክ የማይገኝላቸውንና በጽሑፍ ያልሰፈሩ መንፈሳዊ ዕውቀቶችን የያዙ ሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያንን እየነጠቀ ያለ ሲሆን፤ በአብነት ተማሪዎች አንጻር ከታየ ደግሞ የሚገዳደረውን ዘመናዊነት ተቋቁመው የነገ የቤተ ክርስቲያን አገልጋይ ለመሆን የሚያደርጉትን ተጋድሎ ይበልጥ ፈተና ውስጥ የሚጥል እየሆነ ይገኛል፡፡ ከምንም በላይ የዚህ ችግር ዋነኛ ሰለባ የሚሆኑት ተማሪዎች ሲሆኑ ለዚህም ተጠቃሽ የሚሆነው ምክንያት የመኖሪያና የመማሪያ አካባቢያቸው የተፋፈገ በመሆኑ በበሽታ ተሸካሚ ነፍሳት፣ በትንፋሽና መሰል በሆኑ መንገዶች ለተለያዩ በሽታዎችና ወረርሽኞች ይጋለጣሉ፡፡

የአገልግሎት ክፍሉ ከሚሰጠው ልማት ላይ ያተኮረ የመካናት ድጋፍ በተጨማሪ ማኅበረሰቡ ውስጥ ባለው ሰፊ የማኅበራዊ አገልግሎት ድርሻ ምክንያት ይህንን መርሐ ግብር በድጋሚ ሊያዘጋጅ በቅቷል፡፡ በዚህም መሠረት ሕዝበ ክርስቲያኑ፣ በጎ አድራጊ ድርጅቶችና ግለሰቦች የተለያዩ የንጽሕና መጠበቂያ ቁሳቁስሶችን ማለትም እንደ ሳሙና፣ የውኃ ጀሪካን፣ የልብስ ማጠቢያ…እንዲሁም የተለያዩ አልባሳትን በመደገፍ ክርስቲያናዊ ርኅራኄውን ያሳይ ዘንድ ማኅበሩ ጥሪውን ያስተላልፋል፡፡ በዚህ መርሐ ግብር ከ10,000 በላይ ተማሪዎችን ለመታደግ የሚያስችሉ ቁሳቁሶችን ለማሰባሰብ ታቅዷል፡፡