ማኅበረ ቅዱሳን ትእምርተ ሰላም

መስከረም 21 ቀን 2005 ዓ.ም.


በኢትዮጵያ ከጥቂት ዓመታት ወዲህ ከሃይማኖት አክራሪነት ጋር በተያያዘ አንዳንድ ግጭቶች መከሰታቸው ይታወቃል፡፡ መንግሥትም ለችግሩ  መፍትሔ ለመስጠት ጥረት እያደረገ ይገኛል፡፡ የአብዛኛዎቹ የ”ግጭት” ጠባይ ግን የተለየ ነበር፡፡ የሁለት እምነት ተከታዮች በመፎካከርና በመወዳደር ወይም ደግሞ ከተራ ጥላቻና ግለሰባዊ ግጭት አንሥተው ሃይማኖታዊ ያደረጉት አልነበረም፡፡

 

ከዚያ ይልቅ በአንድ ወገን ያሉት በማያውቁትና ባላሰቡት ሰዓት የደረሰ ድንገተኛ አደጋ ነበር ማለት ይቻላል፡፡ ጥቃቱን የፈጸሙትም የሚከተሉትን ሃይማኖት አባቶች ወካዮችና ከዚያው ከቤተ እምነታቸው ተከታዮች ሙሉ ይሁንታ አግኝተው የተላኩ አልነበሩም፡፡ ይህን የማድረግ ዓላማ ብቻ ሳይሆን በቂ ዝግጅትና ጥናት ያደረጉ የሃይማኖት አክራሪዎች መሆናቸው ከድርጊታቸውም፤ ከተገኘውም ማስረጃ ግልጽ ነበር፡፡

 

በተከታታይ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ምእምናንና አብያተ ክርስቲያናት ላይ በአርሲ ዞን ቆሬ ወረዳ በአንሻ ቀበሌ፣ በጅማና ኢሉአባቦራ ጥቃት ሲያደርስ የነበረው የአክራሪ እስልምና ቡድን ኢትዮጵያዊ መልኩን አሽቀንጥሮ ጥሎ እስላማዊ ዓለም ዓቀፋዊ ግዛትን ለማፋጠንና የምሥራቅ አፍሪካ ስልቱን ለመፈጸም እንደመሰናክል ያያትን የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያንን ለማስወገድ ያለመው እንቅስቃሴው አካል እንደነበረም እንገነዘባለን፡፡

 

ይህን ተከትሎም በሕዝቡ መካከል ለዘመናት አብሮ የመኖር ባህላችንን የሚፃረር ድርጊት እየተስተዋለ ነበር፡፡ በተለይ ደግሞ በክርስቲያኑና በሙስሊሙ ማኅበረሰብ መካከል በወቅቱ ተፈጥረው የነበሩት አዳዲስ ክስተቶች በሁለቱ ሃይማኖት ተከታዮች መካከል የማያባሩና መቆሚያ የሌላቸው ግጭቶች መፍጠር ዓላማ አድርገው የሚንቀሳቀሱ ባዕዳን ኀይሎች በአምሳላቸው የወለዷቸው አክራሪዎች የሚመሩት እኩይ ድርጊት መሆኑም ድርስ ነበር፡፡ ከጥቃቱ በኋላም መንግሥት ተገቢውን ትኩረት በመስጠት የተለያዩ የማስተማርና ሕግ የማስከበር ሥራዎችንም ሲሠራ እንደነበረም በሚገባ እናውቃለን፡፡

 

ትናንትም ሆነ ዛሬ ምልክቱ ሰላም እንጂ “አክራሪነት” ያልሆነው ማኅበረ ቅዱሳን ሀገራዊ ድርሻውን በሦስት መልኩ ተወጥቷል፡፡ የመጀመሪያው ከመጀመሪያው ጀምሮ ምእመናን አክራሪውን፣ ነባሩንና ሰላማዊውን እስልምና ነጥለው እንዲመለከቱ ከፍተኛውን ድርሻ ተወጥቷል፡፡ ሁለተኛ አክራሪዎቹ ለሚያነሷቸው ታሪካዊና ዶግማዊ ጥያቄዎች በተጻፉት ጽሑፎች መጠንና ቁጥር ጋር ሊነጻጸር ቀርቶ እዚህ ግባ የሚባል ባይሆንም መጠነኛ ምላሾችን ሰጥቷል፡፡ ሦስተኛ ተቻችሎና ተከባብሮ ስለመኖር ከየትኛውም አካል በፊትና በከፍተኛ ሽፋን ሠርቷል፡፡ ስለ አክራሪ እስልምናና ስለትንኮሳው እጅግ አነስተኛና ክስተት ተኮር የሆኑ መረጃዎችን በመስጠት ችግሩ ሲያጋጥም ለመንግሥት ማመልከት እንደሚገባ አቅጣጫ ለማሳየት ሞክሯል፡፡

 

ማኅበሩ ይህን በወቅቱ ያደረገው አንድን ነገር እየሰሙ እንዳልሰሙና እንደሌለ ከመቁጠር ይልቅ ችግሩን በትክክል አሳውቆ ለመፍትሔው መሥራት ይገባል ብሎ ስለሚያምንና መንግሥት በወቅቱ አክራሪነትን ለመግታትና ግጭቶችን ለማስወገድ እያደረገ የነበረውንም ጥረት የማገዝ ሀገራዊ ግዴታንም ከመወጣት አንጻር መሆኑንም ለመግለጽ እንወዳለን፡፡

 

ይሁንና ለቤተ ክርሰቲያኒቱ ተጨማሪ አስተዋጽኦ አበረክታለሁ ብሎ የተደራጀውንና ከሰላማዊ ባሕርይው በመነጨ የሃይማኖት አክራሪነት በጽናትና በአቋም እየታገለ ያለውን ማኅበረ ቅዱሳንን በተሳሳተ መረጃ በአክራሪነት የመፈረጅ አዝማሚያዎች በአንዳንድ አካላት እየታዩ መሆናቸውንም እንረዳለን፡፡

 

በማያወላዳ ሁኔታ ማኅበረ ቅዱሳን ትናንትም ሆነ ዛሬ የሃይማኖት አክራሪ አለመሆኑንና ማንንም ወደ ሃይማኖት አክራሪነት የሚመራ ተቋም አለመሆኑን ለመግለጽ እንወዳለን፡፡ የሃይማኖት ሥርዓታችንን አጥብቀን በመፈጸማችን እንታወቅ ይሆናል እንጂ የአክራሪነት ውጤት በሆኑት ጸብና ግጭት አንታወቅም፡፡ ያለ ስም ስም መስጠትና በተሳሳተ መረጃ መፈረጁ አንዳች መፍትሔ ሊሰጠው እንደሚገባ በጽኑ እናምናለን፡፡

 

ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የሃይማኖት አክራሪነትን አስመልክተው ለምክር ቤቱ አባላት ሲገልጹ ከሕዝብና ቤት ቆጠራ ውጤት ጋር አያይዘው “….አንዳንድ የማኅበረ ቅዱሳን አባላት….” ብለው መጥራታቸውን እንደምቹ አጋጣሚ የወሰዱ የማኅበሩን አገልግሎት የማይወዱና ምናልባትም ማኅበሩ ባይኖር በቤተ ክርስቲያኒቱ መሠረተ እምነት፤ ሥርዓተ አምልኮና ትውፊት ላይ የፈለጉትን ማድረግ የሚቻላቸው የሚመስላቸው አካላት የማኅበሩን ስም ማጥፋታቸውን እንደቀጠሉ ናቸው፡፡

 

እነዚህ ወቅታዊ ፓለቲካዊ ሁኔታዎችን የሚንተራሱ የተሐድሶ መናፍቃን አቀንቃኞች ከዚህ በፊት ከቅዱስ ሲኖዶስ ጋር ለማጣለት፣ ከሌሎችም አካላት ጋር በማጋጨት እየደከሙ ሳይሳካላቸው ሲቀር ደግሞ የወቅቱን የፓለቲካ ነፋስ ተጠቅመው መንግሥታዊ አካላትን በማሳሳት በማኅበረ ቅዱሳን መቃብር ላይ ቆመው ቅዠታቸው እውን ሆኖ ለማየት ሲባዝኑ እያስተዋልንም ነው፡፡ ስለዚህም መንግሥታዊ አካላት በእነዚህ አካላት በደረሳቸው የተሳሳተ መረጃ ተመሥርተው ማኅበሩን ከመፈረጃቸው በፊት በቂ ጥናትና አስፈላጊውን ጥንቃቄ እንደሚያደርጉም እምነታችን ነው፡፡

 

ማኅበረ ቅዱሳን በግልጽና በይፋ ከሚሠራው ሥራ ውጭ በስውር የሚሠራው አንዳች ነገር የለም፡፡ ሥራዎቹን ከሌሎች ሥራዎች ጋር ማጥናትና በንጽጽር መመልከት እውነታውን ለመረዳት በእጅጉ ይጠቅማል፡፡ ከዚህ አልፎ ግን በቤተ ክርስቲያኒቱ ላይ በግልጽም ሆነ በስውር ሊያደርሱት የፈለጉትን የሃይማኖት ብረዛና ክለሳ ያልተሳካላቸው አጽራረ ቤት ክርስቲያን በሚሰጡት የተሳሳተ መረጃ ተመሥርቶ ትእምርተ ሰላም /የሰላም ምልክት/ የሆነውን ማኅበር መፈረጅ አይገባም፡፡

 

ማኅበረ ቅዱሳን በቤተ ክርስቲያኒቱ መዋቅር ሥር ያለ የቤተ ክርስቲያኒቱን አስትምህሮና መሠረተ እምነት የሚጠብቅ፣ በራሱ አቅምም መሠረት የማስጠበቅ ድርሻውን የሚያበረክት፣ በቅዱስ ሲኖዶስ የጸደቀ ደንብ የተሰጠውና በእርሱም መሠረት ብቻ የሚሠራ ማኅበር እንጂ ራሱን የቻለ የእምነት ሴክትም አይደለም፡፡

 

አባላቱም በአብዛኛው ከፍተኛ ትምህርት የተማሩ፣ በሀገሪቱ ተቋማት ውስጥ ታላቅ ሀገራዊ ሓላፊነትን የሚወጡ፣ ከፊሎቹም በከፍተኛ የሓላፊነት ቦታዎች ላይ ያሉ፣ ለሀገርና ለሕዝብ በሚሰጠው አገልግሎትም ሓላፊነት የሚሰማቸው ዜጎች እንጂ ከክርስትናው አስተምህሮም ሆነ ከኅሊና የተነሣ የማያደርጉትንና ሊያደርጉም የማይችሉትን አክራሪነት ለማኅበሩ አባላት መስጠት አይገባም እንላለን፡፡

 

መንግሥት እንደ ሀገር መሪነቱ የእምነት መሪዎችን ቀርቦ ማወያየቱ፣ ብቅ ጥልቅ፣ ብልጭ ድርግም የሚሉ የእምነት ነክ “ግጭቶች” ለማስወገድ የሚያደርገው ጥረት በሚያስመሰግነውም የችግሩ ሰበዝ ከየት እንደሚመዘዝና የተፈጠረውንም ችግር ከመሠረቱ ለመፍታት ጉዳዩን በጥልቀት ከሚያውቁት ወገኖች መረጃ የመሰብሰቡን ሥራ አጠናክሮ ሊቀጥል ይገባል፡፡

 

በሀገራችን አሁን ምልክቱ በጉልህ እየታየ ያለው የሃይማኖት አክራሪነት እንቅስቃሴ በብዙኃኑ የክርስትናውም ሆነ የእስልምናው ተከታይ ዘንድ ተቀባይነት የሌለው ተግባር ነው፡፡ የዚሁ አካል የሆነው ማኅበረ ቅዱሳንም እንደ ትናንቱ ሁሉ ዛሬም ጥብዓት በተሞላው ቁርጠኝነት የሚታገለው ነው፡፡ በመሆኑም መንግሥት አሁን እያደረገ ያለው የፀረ አክራሪነት ትግል እንደተጠበቀ ሆኖ በትክክል የአክራሪነት ጠባዩ ከየትኛው አቅጣጫ እንደመጣና ምንጩ የትና ምን እንደሆነ በመለየት ትክክለኛውን ብያኔ ሊሰጥ ይገባል እንላለን፡፡

 

በአንዳንድ አካላት የተሳሳተ አቻ ለመፍጠር ሲባል በጥቅል ለሃይማኖት ተቋማትና ተከታዮቹ የሚቀመጠውም ፍርጃ ሊስተካከል እንደሚገባውና በተገቢው አካል ተገቢውን ሥዕል ማግኘት እንዳለበትም እምነታችን ነው፡፡

 

በመጨረሻም ማኅበረ ቅዱሳን አክራሪነትን እንደሚያወግዝ አበክረን እንገልጻለን፡፡ በተጨማሪም ማኀበሩ ከዚህ በፊት እንዳደረገው ሁሉ ሰላምን አንግቦ ስለ ሰላም ከመንግሥትና መንግሥታዊ ካልሆኑም ሆነ ከሌሎች የሃይማኖት ተቋማት ጋር ለመሥራት ከመቼውም ጊዜ በላይ ዝግጁ መሆኑን ለመገለጽ እንወዳለን፡፡ በዚህም ትልቅ ሀገራዊ ሓላፊነትንና የዜግነት ድርሻውን በመወጣት አመርቂ ውጤት እንደሚያስመዘግብም ያምናል፡፡

 

ወስብሐት ለግእግዚአብሔር


  • ምንጭ፡- ስምዐ ጽድቅ 19ኛ ዓመት ቁጥር 23 2004 ዓ.ም.