መስቀል የሰላም መሠረት ነው

በለሜሳ ጉተታ

መስቀል  የሰላም መሠረት፤ ሰላምም የመስቀል ፍሬ ነው፡፡ በግእዝ ሰላም የሚለው ቃል ትርጉም ‹‹ፍጹም ጤና፣ ዕረፍት፣ እርቅ፣ ሰላምታ፣ የቡራኬና የምርቃት ቃል፣ ሰው ሲገናኝና ሲለያይ የሚናገረው›› ነው፡፡ መስቀልና ሰላም አንዱ የአንዱ መሠረት አንዱ የአንዱ ፍሬ ሆነው የተሳሰሩትም በዚህ ምክንያት ነው፡፡ ሰላም ለሰው ልጅ የግል ሕይወት፣ ለቤተሰብ፣ ለማኅበረሰብ፣ ለሀገርና ለዓለም በጣም አስፋላጊ ከሆኑ ነገሮች አንዱ በመሆኑ ልዩነት የለበትም፤  ሰላምን የሚሰጥ ደግሞ እግዚአብሔር ብቻ ነው፡፡

መስቀል በቤተ ክርስቲያን ጉልላት ላይ ሲታይ፣ በክርስቲያኖች አንገት ላይ ሲንጠለጠል፣ መስቀል በክርስቲያኖች እጅ ሲያዝ እና መስቀል በክርስቲያኖች አካልና ልብስ ላይ ሲቀረጽ ስለ ሰላም ያመልክታል፡፡ በርግጥ ሰው በውስጡ የሌለውን ሰላም በእጅ መስቀልን በመያዝ በአካሉና በልብሱ ላይ በሚቀርጸው የመስቀል ምልክት ብቻ ሊያገኘው አይችልም፡፡ መስቀል ሰላም የሚሆነው በመስቀል ላይ የተሰቀለውን ክርስቶስን በማመንና የመስቀሉን ምሥጢር በማወቅ ለእግዚአብሔር መኖር እንዲሁም የሰላም ጠንቅ የሆነውን ኃጢአትን በመተውና በክርስቲያናዊ ሕይወት መኖር ሲቻል ነው፡፡

መስቀል ሰባቱ መስተጻርራን የታረቁበት እና አንድ የሆኑበት የእግዚአብሔር ሥራ እንደሆነ መምህራን ይተረጒማሉ፡፡ ሰባቱ መስተጻርራን የተባሉትም ነፍስና ሥጋ፣ ሰውና መላእክት፣  ሰውና እግዚአብሔር ሕዝብና አሕዛብ ናቸው፡፡ በእነዚህ መስተጻርራን መካከል ያለው ዋና ችግርም ኃጢአት ነው፡፡  በሰውና በእግዚአብሔር መካከል የነበረውን መልካም  ግንኙነት ያበላሸ ድርጊት ኃጢአት ነው፡፡ ያም ሰላማዊ ግንኙነት ከተበላሸ በኋላ በሰውና በሰው መካከልም ሰላማዊ ግንኙነት እንደገና ታደሰ፡፡ ስለዚህም መስቀል  የሰላም መሠረት፤ ሰላምም የመስቀል ፍሬ ነው እንላለን፡፡ የመስቀልንና የሰላምን ትስስር  በክርስቶስ መስቀል የተገኘው ሰላም ለግል ሕይወታችን፣ ለቤተሰባችን፣ ለማኅበረሰባችን፣ ለሀገራችን እንዲሁም ለዓለማችን ያለውን ጥቅም ለመረዳት መስቀልን ከሰላም፤ ሰላምን ከመስቀል ለይተን ማየት የለብንም፡፡

መስቀል መጀመሪያ የኃጢአተኞች መቅጫ (መስቀያ) ነበረ፤ አሁን ግን መስቀል እግዚአብሔር ዓለምን በልጁ ሞት ያዳነበት ምሥጢር ነው፡፡ ስለ ሰው ልጆች ኃጢአት ክርስቶስ በመስቀል ላይ በመሞቱ ምክንያት የመስቀል ምሥጢር ማዳን፣ ማስታረቅ፣ ሰላምን መስጠት መሆኑ ተገልጿል፡፡ የሰው ልጅ ሰላም አጥቶ የኖረበት ዋና ምክንያት ኃጢአት መሥራቱ መሆኑ ይታወቃል፡፡ በዚህም መሠረት በሰውና በእግዚብሔር እንዲሁም በሰውና በሰው ማካከል የነበረው ሰላም ጠፋ ደፈረሰ፤ የጥል ግድግዳም ተገነባ፡፡

በዓለም ውስጥ ሰላም እንዳይኖር የሚያደርጉ ብዙ ምክንያቶች ስላሉ ዓለም በተፈጥሮና ሰው ሠራሽ አደጋዎች ምክንያት በታላቅ ሥጋት ላይ ወድቃ ትገኛለች፡፡ ሀገራትም ከውጭና ከውስጥ የሚነሣባቸውን ጠላት ለመከላከል ብዙ ገንዘብ አውጥተው የፀጥታ ጥበቃ ያካሄዳሉ፡፡ በተለመደው የዓለም አሠራር የሰላም ምልክት ነጭ ርግብ ሥዕል ከነወይራ ቀንበጡ በጋዜጣውና በመጽሔቱ ላይ ይሳላል፤ ስለሰላም በመገናኛ ብዙኃን ብዙ ይባላል፤ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የሰላም መልእክተኞችም በየቦታው በአስታራቂነት ይሯሯጣሉ፡፡ ዓለም ስለሰላም ወጡ ወረዱ ብዙ አስተዋጽኦ አደረጉ የምትላቸውን ትሸልማለች፡፡ ይህ በየቦታው በሰዎች የሚደረገው ሩጫና ግርግር፣ የሚሰማው ጩኸትና የተከሰተውን ውጥረት በመጠኑ ለማርገብ እንጂ እውነተኛን ሰላም ለማስፈን አልቻለም፤ እውነተኛና ዘላቂ ሰላም የሚገኘው ከእግዚአብሔር ነውና፡፡

ሰላም የእግዚአብሔር ስጦታ ነው

እግዚአብሔር የሰላም አምላክ ነው፡፡ ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ ‹‹የሰላም አምላክ ከሁላችን ጋር ይሁን፤ አሜን›› (ሮሜ.፲፭፥፴፫) ማለቱም ይህንን ያስረዳል፡፡ ጌታችን ከትንሣኤው በኋላም ለሐዋርያት ‹‹ሰላም ለእናንተ ይሁን›› ይላቸው የነበረውም ለዚህ ነው (ዮሐ. ፳፥፲፱-፳፫)፡፡ ስለ ሰላም እግዚአብሔር የተስፋ ቃላት ሰጥቶናል፡፡ እውነተኛ ሰላም የሚገኘው ከእርሱ መሆኑን መጻሕፍት እንዲህ በማለት ይገልጻሉ፡፡ ‹‹በምድራችሁም ላይ ሰላምን እሰጣለሁ›› (ዘሌዋ.፳፮፥፮)፡፡ ‹‹ሰላሜን እሰጣችኋለሁ›› (ዮሐ.፲፬፥፳፯)፡፡ ‹‹እግዚአብሔር ሕዝቡን በሰላም ይባርካል››፡፡ (መዝ.፳፰፥፲፩) ‹‹ሰላምን ለሕዝብና ለቅዱሳኑ፤ ልባቸውንም ወደ እርሱ ለሚመልሱ ይናገራል›› (መዝ.፹፬፥፰፡፡ ‹‹አቤቱ ሥራችንን ሁሉ ሠርተሃልና ሰላምን  ትሰጠናለህ›› (ኢሳ.፳፮፥፲፪)፡ ‹‹ሕዝቤም በሰላም ማደሪያ፣ በታመነም ቤት፣ በጸጥተኛ ማረፊያ ይቀመጣል›› (ኢሳ.፴፪፥፲፰) ይላል እግዚአብሔር በማለት በስፋትና በምልዓት ገልጾታል፡፡

እግዚአብሔር የሚሰጠውን ሰላም ለማግኘት በጎ ሰው መሆን ያስፈልጋል፡፡ ከክፋት መራቅ፣ መልካም ሥራ ማድረግ፣ በጎነትን መውደድና ሃይማኖትን በምግባር መግለጽ ይኖርብናል፡፡ ከልዩነት ሐሳብና ተግባራትም መራቅና ፍቅርንም ገንዘብ ማድረግ ያስፈልጋል፡፡ እግዚአብሔር በነቢያት ‹‹ሰላምን እሰጣችኋለሁ›› በማለት ለሕዝቡ ቃል ገባ፡፡ ክርስቶስም ለደቀ መዛሙርቱ ‹‹ሰላምን እተውላችኋለሁ፣ ሰላሜንም እሰጣችኋለሁ፤ እኔ የምሰጣችሁ ዓለም እንደሚሰጠው አይደለም፤ ልባችሁ አይደንግጥ፤ አትፍሩም›› (ዮሐ.፲፬፥፳፯) በማለት እውነተኛው ሰላም ከማን እንደሚገኝ ተናገረ፡፡

ይህ ሰላም መቼ ይገኛል? እንዴትስ ይገኛል? ለሚለው ጥያቄ ደግሞ እያንዳንዱ ሰው በእግዚአብሔር አምኖ በእርሱ ፍቅር ራሱን ሲመራ ነው፡፡ ሰው ራሱንና ባልንጀራውን እንዲሁም ተፈጥሮን መጥላቱና መጉዳቱ ከእግዚአብሔር ጋር የመጣላቱ ውጤት ነው፡፡ ስለሆነም አሁኑኑ ከእግዚአብሔር ጋር እንድንስማማና ሰላም እንዲኖረን ቴማናዊው ኤልፋዝ በመጽሐፈ ኢዮብ ‹‹አሁንም ከእርሱ ጋር ተስማማ፣ ሰላምም ይኑርህ፣ በዚያም በጎነት ታገኛለህ›› ( ኢዮብ ፳፪፥፳፩) እያለ የመከረንን ምክር ልንፈጽም ይገባል፡፡ ‹‹የሰላም ጌታ ራሱ በሁሉ መንገድ ሰላምን ይስጣችሁ›› (፪ተሰ.፫፥፲፮) የሚለው የሐዋርያው የቅዱስ ጳውሎስ ቃልም ከዚህ ጋር የሚሔድ ነው፡፡ እግዚአብሔር የሚሰጠን ሰላም አእምሮን ሁሉ የሚያሳርፍ ሰላም ነው፡፡ ቃሉም ‹‹ሁሉ የሚገኝበት፥ ከልቡናና ከሐሳብ ሁሉ በላይ የምትሆን የእግዚአብሔር ሰላም በኢየሱስ ክርስቶስ ልባችሁንና ሐሳባችሁን ታጽናው›› (ፊልጵ.፬፥፯) ይላል፡፡

ክርስቶስ የሰላም አለቃ ነው፤ እርሱም ሰላማችን ነው (ኤፌ.፪፲፬)

የሰላም አለቃ የሆነው ክርስቶስ በሰውና በእግዚአብሔር እንዲሁም በነፍስና በሥጋ መካከል ሰላምን ለማምጣት በመስቀል ላይ ተሰቅሎ ስለሞተ ሰላም በመስቀል ላይ የፈሰሰው የክርስቶስ ደም ፍሬ ነው፡፡ ‹‹ሁሉንም በእርሱ ይቅር ይለው ዘንድ በመስቀሉ ባፈሰሰው ደም በምድርና በሰማያት ላሉ ሰላምን ምን አደረገ›› (ቆላ.፩፥፳) ተብሎ እንደተጻፈ ክርስቶስ ሰላማችን ነው፡፡

ለዚህም ሰላምን ሊሰጠን ክርስቶስ በመስቀል ላይ በፍቅር ደሙን አፈሰሰ፡፡ ይህ ስለ ፍቅር የፈሰሰው ደም የሰላማችን ምንጭ ነው፤ ይህ ደም የፈሰሰበት መስቀል ደግሞ የሰላማችን መሠረትና ምልክት ነው፡፡ ቅዱስ ያሬድ መስቀልና ሰላም እንዴት እንደተሳሰሩ ሲገልጽ እንዲህ ብሏል፣ ‹‹መስቀል ብርሃን ለኩሉ ዓለም መሠረተ ቤተ ክርስቲያን ወሃቤ ሰላም መድኃኔ ዓለም መስቀል ለእለ ነአምን መድኅን … መስቀል ለዓለሙ ሁሉ ብርሃን ነው፤ መስቀል የቤተ ክርስቲያን መሠረት ነው፤ ሰላምን የሚሰጥ መድኃኔዓለም ነው፤ መስቀል ለምናምን ለእኛ መድኅን ነው ብሎታል››፡፡ይህም ማለት በመስቀል ላይ ተሰቅሎ ዓለምን ያዳነው መድኃኔዓለም ሰላምን የሚሰጥ አምላክና ቤተ ክርስቲያንን በመስቀሉ የመሠረተ እንደሆነ የሚገልጥ ነው፡፡ የክርስቶስ ሞት (መሰቀል) ቤተ ክርስቲያን የበቀለችበትና የተመሠረተችበት፣ ያደገችበት ወደ ፊትም የምትኖርበት ምሥጢር ነው፡፡

የእግዚአብሔር ሰላም በልባችን ይኖራል፡፡ ‹‹በአንድ አካል የተጠራችሁለት የክርስቶስ ሰላም በልባችሁ ጸንቶ ይኑር፤ ክርስቶስንም በማመስገን ኑሩ›› (ቆላ.፫፥፲፭) መባልም ለዚህ ነው፡፡ ልብን መግዛት የሚችል ሰላም ካለ ሌሎች የአካል ክፍሎች ሁሉ በልብ ትእዛዝ ሥር ናቸውና ለዚህ እውነተኛ ሰላም ተገዝተዋል ማለት ነው፡፡ አሁን ሰው በእውነተኛ ዕረፍት ውስጥ ነው ማለት እንችላለን? ከዚህ ሰላም ውጭ መሆን ምን ያህል አሳዛኝ ነገር እንደሆነ በምን መንገድ ሊገለጽ ይችላል?

ሰላም የመንፈስ ፍሬ ነው፡፡ ጥልና ክርክር የሥጋ ፍሬዎች እንደሆኑ ሁሉ (ገላ. ፭፥፳) ሰላምም የመንፈስ ፍሬ ነው፤ ሰላም ያለው ሰውም መንፈሳዊ ነው፤ ራሱ ሰላማዊ መሆንን ብቻ ሳይሆን ሌሎችም ሰላማውያን እንዲሆኑና በሰላም እንዲኖሩ የሰላምን ወንጌል በመስበክ ይሠራል፡፡ (ማቴ.፭፥፱፤ ኤፌ.፮፥፲፭)፡፡ የእግዚአብሔርን ሰላም በሕይወታችን እንኖረው ዘንድ ይገባል፤ የእግዚአብሔር ቃል ‹‹እርስ በእርሳችሁም በሰላም ሁኑ›› (ተሰ.፭፥፲፫)፡፡ ‹‹ሰላምን ሻት፥ ተከተላትም›› (መዝ.፴፫-፥፲፬) ይላልና፡፡

የሰላም አስፈላጊነት ከእግዚአብሔር ቃልና ከእግዚአብሔር ጸጋ እና ምሕረት አስፈላጊነት ተለይቶ የሚታይ አይደለም፡፡ ስለ ሰላም የምንይዛቸው የተለያዩ አቋሞች ሲታዩ የልዩነቱ መነሻ ምክንያት ስለ ሰላም ምንጭ መለያየታችን ነው፡፡ ሰላም ከእግዚብሔር ለሰው ልጆች የሚሰጥ ታላቅ ስጦታ ነው፡፡ የሰላም መጥፋት ዋና ምክንያትም ከሰላም መገኛ ከእግዚአብሔር ጋር መጣለት ወይም መራቅ እርሱንም አለማምለክ ነው፡፡ ይህን እውነት የማያምኑ ሌሎች ሰላምን እነርሱ ሊያመርቱትና ሊሰጡት የሚችሉት የሰው ልጅ የጥረት ውጤት አድርገው ያቀርቡታል፡፡ እርግጥ ነው ሰው በተፈጥሮው ሰላምን የሚወድ ፍጡር ነው፡፡ ስለዚህም ሰላምን ለማግኘት የሚችለውን ጥረት ሁሉ ያደርጋል፡፡ ነገር ግን በሰው ተፈጥሮ ውስጥ ኃጢአት ስለሠረፀ ዓለም በክፋት ተይዟል፡፡ ዓለም የችግሩን ምንጭ ማየት ባይችልም የኃጢአት ውጤት የሆነው የሰላም መታጣት ግን ሁልጊዜ ሕይወቱን ሲያውከው ይኖራል፡፡

ቤተ ክርስቲያን የሰው ልጆች ኃጢአትን በመሥራት የሰላም አባት ከሆነው ከእግዚአብሔር ጋር እንደተጣሉ እንዲሁም እርስ በእርሳቸውም በኑሮው ሰላምን ማግኘት እንዳልቻሉ  ታስተምራለች፡፡ ይህ የታጣው ሰላምም የሰላም አለቃ በሆነው በክርስቶስ እንደገና በመስቀሉ ምክንያት እንደተገኘ ታውጃለች፡፡ ይህ የሃይማኖት ምሥጢር ስለሆነ ሁሉም ይስማማበታል ተብሎ አይጠበቅም፤ የሚስማሙበት እግዚአብሔርን የሚያምኑና የእግዚአብሔርን ቃል ወይም ፈቃድ የሚያውቁ ናቸው፡፡ እነዚህ የእግዚአብሔር ፈቃድና አሠራር የገባቸው የቤተ ክርስቲያን ልጆች ደግሞ የሰላምን አስፈላጊነት ከሰላም መታጣት ዋና ምክንያት፤ ከሰላም ምንጭ ማንነትና ሰላም አሁንም ቢሆን ሊገኝ ከሚችልበት እውነት አንጻር ለሰው ልጆች ሁሉ ማስተማር ይጠበቅባቸዋል፡፡

ክርስቲያኖች በሙሉ የቤተ ክርስቲያንንም ሆነ የሀገርን ሰላም ለመጠበቅ ኃላፊነታችንን በአግባቡ ልንወጣ ይገባል፡፡ በመሆኑም ሰላም የእግዚአብሔር ስጦታ መሆኑንና የሰላምን አስፈላጊነት ለሰው ልጆች ሁሉ ማስተማር ይገባናል፡፡ የሰው ክፉ ጠባይ በትምህርት ይስተካከላል፤ ያላመነው ወደ እምነት ሕይወት የሚመለሰው፣ ኃጢአተኛው ጻድቅ የሚሆነውና ሰላምን የማይፈልግ ሰው ሰላምን የሚያገኘው በዕውቀት ነው፡፡ ትምህርተ ወንጌል ደግሞ ለዚህ ተግባር ከአምላክ የተሰጠች ሰማያዊት ሕግ ናትና ለሰላም መስፈን የሰላም ወንጌልን መስበክ ይገባል፡፡

በአጠቃላይ ሰላምን መጠበቅ የቤተ ክርስቲያንና የመንግሥት ኃላፊነት መሆኑን ተገንዝበን ስለ ሰላም በጋራ መሥራት ይገባናል፡፡ ሰላም የሰው ልጅ መሠረታዊ ፍላጎትና የህልውና መሠረት ነው፡፡ ሰላም የሰው ልጆች ሁሉ የጋራ ፍላጎት እንጂ የአንድ ቡድን አመለካከት ወይም ርእዮተ ዓለም አይደለም፡፡ ሁሉን የሰው ልጆች ከምናገለግልባቸው ነገሮች አንዱ ሰላምን ለሰው ልጆች ሁሉ መስጠት ነው፡፡ ስለዚህ ቤተ ክርስቲያን የሰላም መገኛ ኢየሱስ ክርስቶስን ምሳሌ በማድረግ ለሰው ልጆች ሁሉ ሰላም ማስፈን ይገባታል፤ የመስቀል መሠረትም ይህ ነው፡፡

የሰላም አምላክ የሀገራችንንና የሕዝቧን ሰላምጠብቅ፣ ሰላሙንም ይስጠን፤አሜን!!