“መራሔ ፍኖት” መንፈሳዊ ጉዞ ለግቢ ጉባኤያት ተዘጋጀ

መጋቢት 25 ቀን 2005 ዓ.ም.

በእንዳለ ደምስስ

በማኅበረ ቅዱሳን አዲስ አበባ ማእከል አስተባባሪነት በ60 ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ሥር ለሚገኙ 5000 /አምስት ሺህ/ ግቢ ጉባኤያት ተማሪዎች  “መራሔ ፍኖት” /መንገድ መሪ/ የተሰኘ መንፈሳዊ ጉዞ ወደ ሱሉልታ ደብረ ምሕረት ቅድስት ሥላሴ ቤተ ክርስቲያን በዕለተ ሆሣዕና ሚያዚያ 20 ቀን 2005 ዓ.ም. መዘጋጀቱን የአዲስ አበባ ማእከል ዋና ጸሐፊ አቶ ካሳሁን ኃይሌ ገለጹ፡፡

የጉዞውን መሠረታዊ ዓላማ አስመልከቶ አቶ ካሳሁን ኃይሌ ሲገልጹ “በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ውስጥ የሚገኙ ግቢ ጉባኤያት የአንድነት መንፈስ እንዲኖራቸው ለማድረግ፤ እንዲሁም በግቢ ጉባኤያት የማይሳተፉ የቅድስት ቤተ ክርስቲያን ልጆችን በግቢ ጉባኤያት ውስጥ የሚሰጠውን መንፈሳዊ ትምህርት እንዲማሩ ለማነሳሳት ታስቦ የተዘጋጀ መርሐ ግብር ነው” ብለዋል፡፡

በመርሐ ግብሩ ላይ የተለያዩ መንፈሳዊ ዝግጅቶች የሚቀርቡ ሲሆን በዋነኛነት ተማሪዎች በቀለም ትምህርታቸው፤ በመንፈሳዊ ሕይወታቸውና አገልግሎታቸው እንዴት ስኬታማ መሆን ይችላሉ? በሚል ርዕስ ከዚህ በፊት በግቢ ጉባኤት ውስጥ በመማርና በማገልገል ላይ የነበሩ ወንድሞችና እኅቶች ተሞክሯቸውን ያካፍላሉ፡፡ እንዲሁም ተማሪዎች ለሚያቀርቧቸው በቀለም ትምህርታቸውና በመንፈሳዊ ሕይወታቸው የሚያጋጥሟቸውን ፈተናዎችና ተያያዥነት ያላቸው ጥያቄዎቻቸው በሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያን ምላሽ ይሰጥባቸዋል፡፡

በዚህም መሠረት ተማሪዎች ያሏቸውን ጥያቄዎች እስከ ሚያዚያ 10 ቀን 2005 ዓ.ም. ድረስ በኢሜይል አድራሻ Mfenot2005@gmail.com ፤ በስልክ  09 11 89 89 90 / 09 11 36 16 92 መላክ እንደሚችሉ  አቶ ካሳሁን ኃይሌ ገልጸዋል፡፡ በተጨማሪም የቲኬት ሽያጩ በሁሉም ግቢ ጉባኤያት ሥራ አስፈጻሚዎች፤ በማኅበረ ቅዱሳን ንዋያተ ቅድሳት መሸጫ ሱቆችና መዝሙር ቤቶች እንዲሁም በአዲስ አበባ ማእከል ጽሕፈት ቤት ውስጥ ማግኘት እንደሚቻል አስታውቀዋል፡፡