መልካም አገልግሎት

ሚያዚያ ፰፤ ፳፻፲፮ ዓ.ም.

መንፈሳዊ ሕይወት ከሚገለጽበት ዋነኛና ተቀዳሚ ተግባራት ከሆኑት መካከል መልካም አገልግሎት አንዱ ነው፡፡ አገልግሎትን መልካም የሚያደርገውን ተግዳሮቶቹን ለይቶ ማወቅ ደግሞ ከማንኛውም መንፈሳዊ አገልጋይ ይጠበቃል፡፡ ይህም የእምነታችን፣ የሃይማኖታችን፣ የመንፈሳዊ ዕውቀታችንና ክርስቲያናዊ ተግባራችን መለኪያ ነው፡፡

በኅብረትም ሆነ በተናጠል የምናከናውነው መንፈሳዊ አገልግሎት ለአምላካችን እግዚአብሔር የሚቀርብ ነው፡፡ ከመነሻው ጀምሮ እርሱን ለማወቅ፣ ለመረዳትና ለማገልገል የምንማረው መሠረታዊ ትምህርት፣ እምነታችንና ምግባራችን ዘወትር የምንጸልየው ጸሎት፣ የምንጾማቸው የዐዋጅና የፈቃድ አጽዋማት እንዲሁም ለቅድስት ቤተ ክርስቲያን የምናበረክተው መባ፣ ምጽዋትና ችሮታ ለመልካም አገልግሎት የሚያበቁ ናቸው፡፡

በተጓዳኝም የጽዋና የአገልግሎት ማኅበር በመመሥረት ቅዱሳንን በመዘከርና መታሰቢያቸውን በማድረግ ለፈጣሪያችን መልካም አገልግሎት እናደርጋለን፡፡ አምላካችንን ደስ ከሚያሰኙት ተግባራት መካከል ቅዱሳን ከራሳቸው አልፎ ለሌሎችም ድኅነት እንዲተርፉ የሰጣቸውን የምሕረት ቃል ኪዳን በማሰብ ስንዘክር ነው፡፡ የቅዱሳን አባቶችንና እናቶችን፣ የጻድቃን፣ የሰማዕታትን ገድል መዘከር፣ የተወለዱበትን፣ ያረፉበትን እንዲሁም ቃል ኪዳን የተቀበሉበትን የተቀደሱ ዕለታትን ማሰብ፣ መዘከርና ማክበር እግዚአብሔር ደስ የሚያሰኝ መልካም አገልግሎት ነው፡፡ በአንድ ቅዱስ ስም በየወሩም ሆነ በዓመት አንዴ ነዳያንን ማብላት፣ ማጠጣት፣ ለተራቆቱ ማልበስና የተቸገሩትን መርዳት መልካም አገልግሎት ነው፡፡ ‹‹ነቢይን በነቢይ ስም የሚቀበል የነቢዩን ዋጋ ይወስዳል፤ ጻድቁንም በጻድቅ ስም የሚቀበል የጻድቁን ዋጋ ይወስዳል›› እንዲል፡፡ (ማቴ.፲፥፵፩)

በሀገራችን በርካታ ጽዋ ማኅበራት ተመሥርተው መንፈሳዊ አገልግሎት በመስጠት ላይ ይገኛሉ፡፡ እነርሱም ቅዱሳንን ከመዘከር፣ ድሆችን ከመመገብ፣ ከማልበስ፣ ለችግራቸው ደርሶ ከመርዳት በተጨማሪ የእግዚአብሔርን ቅዱስ ቃል በማስተማርና በመንፈሳዊ ሕይወታቸው በመርዳት ከቤተ ክርስቲያን ጎን የቆሙ ጥቂት አይደሉም፡፡

በቤተ ክርስቲያን ሕግና ሥርዓተ ደንብ እንዲሁም ቃለ ዐዋዲ መሠረት ከሚንቀሳቀሱ የአገልግሎት ማኅበራት መካከል ማኅበራችን ማኅበረ ቅዱሳን ቀዳሚ ተጠቃሽ ነው፡፡ ከሠላሳ ዓመት በላይ አገልግሎት ሲሰጥና ከ፲፻፹፬ ዓ.ም. ጀምሮ የቤተ ክርስቲያንን አገልግሎት በመደገፍ ላይ ያለው ማኅበረ ቅዱሳን የነበረበትን አስቸጋሪና ፈታኝ ወቅት በእግዚአብሔር አጋዥነት አልፎ እዚህ ደርሷል፡፡ በእነዚህም ዓመታት ተልእኳዊ ጉዞው በተግዳሮቶች የተሞላ ቢሆንም አገልግሎቱን ማስፋት ማኅበር ነው፡፡ በተለይም ትምህርተ ወንጌል በሀገሪቱ እንዲሁም በመላው ዓለም እንዲስፋፋ ዘመናዊ የማሠራጫ መንገዶችን በመጠቀም ግቢ ጉባኤያትና ምእመናን በሃይማኖትና በቤተ ክርስቲያን ሥርዓት በማነፅ የቤተ ክርስቲያንንን ትውፊት እንዲጠብቁና እንዲያቆዩ ማድረግ አስችሎታል፡፡

ወንጌል በመንፈሳዊ ጉባኤያት ላይ ከተጀመረበት ጊዜ አንሥቶ የማኅበረ ቅዱሳን ትሩፋት አገልጋዮች በዐውደ ምሕረት ጉባኤዎች በተለይም በበበዓላትና በሰንበት ያለማቋረጥ ትምህርተ ወንጌልን አስፋፍተዋል፡፡ የማኅበሩ ቀደምት አገልጋዮች እና ሌሎችም በትሩፋት የሚያገለግሉ መምህራን ለስብከተ ወንጌልና ለመንፈሳዊ ጉባኤ መስፋፋት ትልቅ አስተዋፅኦ አበርክተዋል፡፡

የማኅበረ ቅዱሳን የትሩፋት አገልጋዮች ከደቡብ ኢትዮጵያ አስከ ሞያሌ ኬንያ ጠረፍ ድንበር ድረስ በመሄድ ወንጌል ያልተዳረሰባቸው ቦታዎች ላይ ተደራሽ ከማድረግ አንጻር የማኅበሩ ትሩፋት መምህራን ወጥተዋል፤ ወርደዋል፤ ብዙም ለፍተዋል፡፡ በዚህም መልኩ ከከተማ እስከ ገጠር፣ በወረዳ ማእከላት ከዚህም አልፎ ተርፎ በደቡብ አፍሪካ እንዲሁም በውጭ ሀገራት ማለትም በአሜሪካና በአውሮፓ ባሉ ማእከላት ባለው የመዋቅር ሰንሰለት ከዋናው ማእከል እስከ ግንኙነት ጣቢያ አንድ ወይም ሁለት አባላት አስካሉበት ድረስ የወንጌል ጉባኤያት ይዘጋጃሉ፡፡ ጉባኤያትን ከማስፋፋትና ምእመናን ከማስተማር አንጻር በመምህርን የሚዘጋጁ ጉባኤያት ሰፊና ብዙ አካባቢዎችን ያዳረሱ፣ ሰዎች ፈጣሪያቸውን እንዲያውቁ፣ ወደ አምላካቸው እግዚአብሔር እንዲቀርቡ፣ ሥርዓተ ጋብቻቸውን በቅዱስ ቁርባንና በሥርዓተ ተክሊል እንዲፈጽሙ የወጣቶችን የልቡና ዓይን ያበሩ መንፈሳዊ ጉባኤያትን በማዘጋጀት የማኅበሩ አበርክቶ የላቀ ነው፡፡

ማኅበረ ቅዱሳን በትሩፋት የሚያገልግሉ ብዙ ካህናት፣ ዲያቆናት፣ ሰባክያነ ወንጌል አሉት፤ ከዚህም በተጨማሪ በየዓመቱ ከግቢ ጉባኤያት በብዙ ሺዎች የሚቆጠሩ በዝዋይ፣ በጅማና በመላ የሀገሪቱ የካህናት ማሠልጠኛዎች ያስመርቃል፡፡ ከእነዚህ ውስጥም የተወሰኑት በወንጌል አገልግሎት ተሠማርተው፡፡ እነዚህ አገልግሎቶች ለቤተ ክርስቲያን ትልቅ ሚና ያበረከቱ ስለሆኑ በቀላሉ የሚታዩ አይደሉም፡፡

ማኅበራችን የስብከተ ወንጌልን በማስፋፋት እና በማጠናከር ረገድ በተለያየ ጊዜ በሀገረ ስብከቱ በተመረጡ ወረዳዎችና አጥቢያዎች እንዲሁም ርእሰ ጉዳዮች ጉባኤያትን በመዘርጋት ትምህርተ ወንጌል ሲያስፋፋ የተለያዩ ሥልጠናዎችን በመስጠት ምእመናንና አገልጋዮች እንዲጸኑና እንዲበረቱ እንዲሁም ከቅድስት ቤተ ክርስቲያን የወጡትን ወደ ቅድስት ቤተ ክርስቲያን እንዲመለሱ አድርጓል፡፡ በተለይም ከዋናው ማእከል በሚደረገው ድጎማ በተለያዩ ሀገረ ስብከቶች እና ቋንቋንዎች አገልጋዮችን በድጎማ በመቅጠር አገልግሎቱ በንግሥ በዓል፣ በሠርግ ሥነ ሥርዓት፣ በልቅሶ እንዲሁም የቤት ለቤት አገልግሎት ጭምር በመስጠት ለምእመናን የሥላሴ ልጅነት እንዲያገኙ አድርጓል፡፡

በተጨማሪም ከዋናው ማእከልና ከበጎ አድራጊ ምእመናን ጋር በመተባበር ወቅቶቹን ጠብቀው በተለያዩ ቋንቋዎች የሚያገለግሉ ሰባኪያንን እንዲሁም መምህራነ ንሰሓ (አበ ነፍስ) ካህናትን በማሠልጠን የስብከተ ወንጌል ተደራሽነትን ለማስፋፋት ተችሏል፡፡ ሥልጠናዎቹም ሲሠጥባቸው የነበሩትም (በጽርሐ ጽዮንና በዝዋይ ማሠልጠኛዎች ሥልጠናዎችን እየወሰዱ ሲሆን አገልጋዮች በአገልግሎት ተሠማርተው ይገኛሉ፡፡

ስብከተ ወንጌል ባልተስፋፋባቸው ወረዳዎች ሐዋርያዊ ጉዞ በማድረግ ወንጌልን ለምእመናን ማድረስ እንዲሁም በዓመት ሁለት ጊዜ የሐዊረ ሕይወት ጉዞ በማድረግ በከተማ እና በገጠር ላሉ ምእመናን ወንጌልን ማስተማር ተችሏል፡፡ ማእከላት ባደረጉት የሐዊረ ሕይወት ጉዞ ምእመናን የስብከተ ወንጌል አገልግሎት በሰፊው አግኝተዋል፡፡ በተለያየ ጊዜ በሃይማኖት ምክንያት የሚነሡ የተለያዩ ጥያቄዎች በመምህራን መልስ እንዲያገኙ ተደርጓል፤ በተለይም በተለያዩ አህጉረ ስብከት የነበረው መጠነ ሰፊ የተሐድሶ መናፍቃን እንቅስቃሴ በማእከላቱ አዘጋጅነት በተሰጠ ሰፊ የጸረ ተሐድሶ ሥልጠናና ጉባኤ ግልጽ እንቅስቃሴያቸውን ለመግታት የተቻለና ምእመናንም ሰፊ ትምህርት እንዲያገኙ፣ በጉዞ በሄዱባቸው አብያተ ክርስቲያናትም በአገልግሎት እንዲበረቱ የተለያዩ ድጋፎች አድርጓል፡፡ ለምሳሌ የተጓደሉ ንዋየ ቅድሳትን ማሟላት፣ ካህናትን ለአገልግሎት መመደብ እና የመሳሰሉት ድጋፍ ተደርጓል፡፡

ከዚህም በተጨማሪ ተማሪዎችን በሁለቱም ብቁ አገልጋዮች ለማድረግ ከዋና ትምህርታቸው በተጨማሪ የትምህርተ ሃይማኖት፣ የቤተ ክርስቲያንን ታሪክ፣ ሥርዓትና ትውፊትን የሚማሩ ተማሪዎችን በአቡነ ጎርጎርዮስ ትምህርት ቤቶች እያስተማረ ይገኛል፡፡

በማኀበረ ቅዱሳን መዋቅር ውስጥም የግቢ ጉባኤያት ማስተባበሪያ አገልግሎት አንዱ ሲሆን ግቢ ጉባኤያትን በማደራጅትና በማስተባበር እያገለገለ ነው፡፡ በግቢ ጉባኤያት አገልግሎት ማስተባበሪያ አማካኝነት በአሁኑ ወቅት በሀገር ውስጥ ፬፻፸፭ (አራት መቶ ሰባ አምስት) በውጭ ሀገራት ፲፰ (ዐሥራ ስምንት) ቨርቹዋል በኋላም በግቢ አገልግሎት መስፋፋት ምክንያት በማስተባባሪያ ደረጃ እንዲዋቀር ተደርጓል፡፡ በሥሩም ሦስት የሚሆኑ ዋና ዋና ክፍሎች አሉት፡፡

በሁሉም ግቢ ጉባኤያት ወጥ የሆነ እና ደረጃውን የጠበቀ ትምህርት ለማስተማር ይቻል ዘንድ ሥርዓት ትምህርት በመቅረጽ ፬፻፸፩ (በአራት መቶ ሰባ አንድ) የሀገር ውስጥ ግቢ ጉባኤያት ተግባራዊ እያደረገ ይገኛል፡፡ በተዘጋጀው ሥርዓተ ትምህርት መሠረት ፳ (ሃያ) መጻሕፍት ታትመው በግቢ ጉባኤያት አገልገሎት በመስጠት ላይ ናቸው፡፡ አዲስ አበባ የሚገኘው የማኀበረ ቅዱሳን ዋናው ማእከል ጽሕፈት ቤት ሕንጻ ግንባታ በታቀደለት ጊዜ እንዲጠናቀቅ የግቢ ጉባኤያት ድርሻ ከፍተኛ ነበር፡፡ (ጉባኤ ቃና ዘኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ጋዜጣ፤ ፫ኛ ዓመት፤ ቁጥር ፬፤ ሚያዝያ ፳፻፪ ዓ.ም)

ከዚህ በተጨማሪ በዋናው ማእከል የሚካሄዱ ሐዊረ ሕይወት ጉዞዎች አሉ፤ በአንድ ጉዞ 8000 – 15000 ሕዝብ በማሳተፍ ብዙ ምእመናን በወንጌል እንዲረኩ የብዙዎች ጥያቄዎች በምክረ አበው መርሐ ግብር አማካኝነት እንዲመለሱ በማድረግ ታላቅ የስብከተ ወንጌል ሥራ አከናውኗል፡፡ ሌላው በዋናው ማእከል የሚከናወነው የሐዋርዊ ጉዞ ነው፡፡ ከሠላሳ ያላነሱ ሰዎች ሰው የሚሳተፍባቸው ናቸው፤ መደበኛ መምህራንንና ዘመርያንን በማካተት፣ በትንሹ ዐሥራ አምስት ቀን የሚፈጅ ጉዞ በማድረግ እስከ ሰባት የሚደርሱ ከተሞችን አካሎ የሚመለስ የመንፈሳዊ ጉባኤ ያደርጋል፤ በሐዋርያዊው ጉዞ ላይም መምህራኑ ስብከተ ወንጌልን ከዝማሬ ጋር ያቀርባሉ፡፡ እነዚህ አገልጋዮች የዓመት ፈቃዳቸውን ጭምር በመጠቀም ለወንጌል መስፋፋት ከፍተኛ ዋጋ ከፍለዋል፡፡

ከዚህ በተጓዳኝ ከሀገር ውጭ ያለውን የማኅበረ ቅዱሳን የወንጌል አገልግሎት ወይም የመንፈሳዊ ጉባኤ አድማስ አርቀን ብንመለከተው በጣም ሰፊ ነው፡፡ በኬንያ፣ በደቡብ አፍሪካ፣ በአሜሪካ፣ በአውስትራሊያ፣ በአረብ እና በአውሮፓ ሀገራት ስብከተ ወንጌልን በማስፋፋት ረገድ ከፍተኛ አስተዋፅኦ አድርጓል፡፡
ትምህርተ ወንጌል በሀገሪቱ ውስጥና ውጭ ባሉ ዩኒቨርስቲዎችና ኮሌጆች ዓቅም በፈቀደ መጠን ቃለ እግዚአብሔርና ሥርዓተ ቤተ ክርስቲያን በተለያየ መንገድ ሲያስተምር ቆይቷል፡፡ የዐውደ ምሕረት ስብከቶችና ትምህርቶች፣ ሥልጠናዎች እና ዐውደ ርእያት እንዲሁም የኀትመት ውጤቶች ዋናዎቹ የማስተማሪያ መንገዶች ናቸው።

ማኅበሩ ስብከተ ወንጌልን ከሚያስፋፋባቸው መንገዶች በኅትመትም የሚያቀርባቸው ትምህርቶች ለብዙኃሃን ተደራሽ መሆን የቻለ ነው፡፡ መምህርን በሚያዘጋጁት መጻሕፍት፣ ሐመር መጽሔት፣ ስምዐ ጽድቅ ጋዜጣና መጽሔተ ተልእኮን በመሰሉ የኅትመት ሥራዎች ብዙዎችን ያስተምራል፡፡

ማኅበረ ቅዱሳን ስብከተ ወንጌል ከሚያስፋፋባቸው መንገዶች ኤሌክትሮኒክስ ሚዲያዎቹ የጎላ ድርሻ አላቸው፡፡ ማኅበሩ በእነዚህ ሚዲያዎቹ የሚያስተላልፋቸውን ትምህርተ ሃይማኖት በተደራጀ መልኩ ወደ ምእመናን ለማድረስ ያመች ዘንድ የሚዲያ ዋና ክፍል ያዋቀረ ሲሆን ይህም የቴሌቭዥን አገልግሎት ተቋም ነው፡፡

ማኅበሩ ይህን ክፍል በተቋም ደረጃ ባቋቋመ በአጭር ጊዜያት ውስጥ ለቅድስት ቤተ ክርስቲያንና ለሀገር የሚጠቅሙ በርካታ ሥራዎችን ሠርቷል፡፡ ለብዙ ነፍሳትም የመዳን ምክንያት ሆኗል፤ ስለ ማኅበረ ቅዱሳን ምንነት ያልተረዱ ሰዎችም ማኅበሩን በግልጽ እንዲያውቁ አድርጓል፡፡ በመሆኑም አገልገሎቱን መጠቀም የሚፈለጉ አካልት ዕለት ዕለት በቁጥር እና በዓይነት በመጨመራቸው በዓለማዊ ሚድያ ላይ ተጨማሪ ሆኖ መንፈሳዊ መርሐ ግብር ማቅረብ ያስከተለው ክፍተት፣ የማኅበሩ የአየር ሰዓትን ለማሳደግ ፍልጎት በመጨመሩ በአሌፍ ቴሌቭዥን ጣቢያ ላይ የነበረውን የአየር ሰዓት ኪራይ ለሁለት ዓመታት ሲጠቀም ቆይቶ ከ፳፻፲፪ ዓ.ም. ከመስከረም ወር ጀምሮ የራሱን የ፳፬ (ሃያ አራት) ሰዓት መንፈሳዊ የቴሌቭዥንም ጣቢያ ሊከፍት ችሏል፡፡ በዚህም ቀድሞ የነበረው አገልግሎት በቂ ባለመሆኑ እና የበለጠ አገልግሎቱን በተለያዩ ቋንቋዎች ተደራሽ ለማድረግ በልዑል እግዚአብሔር መልካም ፈቃድ ‹‹የማኅበረ ቅዱሳን ቲቪ›› የሚል የሙሉ የ፳፬ ሰዓት አገልግሎት መስጠት ጀምሯል።

በማኅበሩ የቴሌቭዥን ጣቢያም በአማርኛ፣ በትግርኛ፣ በኦሮምኛ፣ በእንግሊዘኛና በሌሎችም ቋንቋዎች ተዘጋጀተው የሚቀርቡ መርሐ ግብሮች (በመደበኛና ኦን ላይን የሚተላለፉ)፣ የድምጽ ሥርጭት መርሐ ግብሮች፣ በሸክላ የሚቀርቡ ልዩ ልዩ ትምህርቶችን እና ስብከቶችን እንዲሁም በዘጋቢ የድምጽ ወምስል መርሐ ግብራት መምህራንንና ሌሎች አባላቱን በማስተባበር የስብከተ ወንጌል በዓላም ደረጃ እንዲስፋፋ የበኩሉን ጥረት አድርጓል፡፡

ስብከተ ወንጌልን ለማስፋፋት ካለው ቁርጠኝነት የተነሣ ማኅበረ ቅዱሳን ከኅትመትና መገናኛ ብዙኃን በተጨማሪ በመዛግብት እና መረጃ ክፍል ሥር በ፲፱፻፺፩ ዓ.ም. የአማርኛ ድረ ገጽን በመዘርጋት አገልግሎቱን ቀጠለ፤ ብዙም ሳይቆይ የኦሮምኛና ከእንግሊዘኛው ድረ ገጾች በተጨማሪ ፌስ ቡክ፣ ቴሌግራም፣ ትዊተር እንዲሁም ኢንስተግራም በመክፈት ወንጌልን ለአንባቢያን ተደራሽ እያደረገ እስከ አሁን ጊዜ ደርሷል፡፡ ማኅበሩ የሚያሠራጫቸው መርሐ ግብር የቤተ ክርስቲያናችንን ትምህርተ ሃይማኖት፣ ሥርዓትና ትውፊት የጠበቁ፣ ታሪክ የማያፋልሱ፣ የምእመናንን መንፈሳዊና ማኅበራዊ ሕይወት የሚያሳድጉ ክርስቲያናዊ ሥነ ምግባርን የሚያስተምሩ እንዲሆኑ ለማድረግ የአርትዖት አገልግሎት ማስተባበሪያ አቋቁሞ በከፍተኛ ጥንቃቄ አገልግሎት እየሰጠ ይገኛል፡፡ ሥነ ጽሑፎች (ኪናዊ) እና የሥነ ሥዕል አገልግሎት ሥራዎች በማኅበራዊ መገናኛ ብዙኃን ወቅቱን ተከትሎ ለአንባብያን ተደራሽ እንዲሆኑ እያደረገ ነው፡፡

በትምህርትና ሐዋርያዊ አገልግሎት የስብከተ ወንጌል ማስፋፋት መርሐ ግብር በኩል አባላት አብያተ ክርስቲያናት ባልተገነቡባቸውና ስብከተ ወንጌል ተደራሽ በማይሆንባቸው ወደ የተለያዩ ክፍለ ሀገራት በመሄድ በመጀመሪያ ትምህርተ ወንጌልን በማስተማር ኢ-አማንያኑን እያጠመቀ በርካቶችን ወደ ክርስትና እምነት እየመጣ ይገኛል፡፡ በተለይም ከ፳፻፪-፳፻፲፩ ባሉት ዓመታት በቤንሻንጉል ጉሙዝ፣ መተከል፣ አርባ ምንጭ፣ ጂንካ፣ ደቡብ ኦሞ እና ሌሎችም ክፍለ ሀገራት በመዘዋወር፣ በስብከተ ወንጌል በማነጽና በማጥመቅ ከፍተኛ ችግር ላለባቸው ሙያው ውስጥ ባሉ አባላት የምክር አገልግሎት ይሰጣል፡፡

በዚህም ሐዋርያዊ ተልእኮ ማኅበሩ በስብከተ ወንጌል አገልግሎት ተደራሽ ባለመሆናቸው ተስፋ በመቁረጥ የጠፉ፣ ከቤተ ክርስቲያን የቀሩ ወጎኖችን ወደ ቅድስት ቤተ ክርስቲያን ሰብሰቧል፤ ጠፍተው የነበሩ እና ቅድስት ቤተ ክርስቲያንን ለዘመናት ተስፋ ሲያደርጉ የነበሩ ወገኖችን ተምረውና አምነው በመጠመቅ የቅድስት ቤተ ክርስቲያን አባል እንዲሆኑ አድርጓል፡፡

ስመ እግዚአብሔር የማይጠራባቸውና ስብሐተ እግዚአብሔር ያልደረሰባቸው አካባቢዎች ስመ እግዚአብሔር እንዲጠራና ስብሐተ እግዚአብሔር እንዲዳረስ አስችሏል፤ ከአዳዲስ አማንያን መካከል አገልጋይ ሰባክያነ ወንጌልን፣ ዲያቆናትንና ካህናትን አፍርቷል፤ ሰንበት ትምህርት ቤቶች በሌሉባቸው አካባቢዎች የሕፃናትንና የወጣቶች ጉባኤዎችን እንዲመሠረቱ ከማድረጉም ባሻገር የተመሠረቱትንም አጠናክሯል፡፡ ኦርቶዶክሳዊ ወገኖች በሌሉባቸው አካባቢዎች የሐዋርያዊ አገልግሎት ተደራሽ እንዲሆን በማድረግ ኦርቶዶክሳዊ ትውፊትና ሥርዓት አስፋፍቷል፡፡

ማኅበሩ እነዚህን መንፈሳዊ አገልግሎት ተደራሽ ከማድረጉም በላይ አዳዲስ አማንያን እንዲሁም ምእመናን በሃይማኖት ጸንተው እንዲኖሩ ለማስቻል የተለያዩ መርሐ ግብራትንና ሥልጠና በማዘጋጀትና ተሳትፎአቸው በመጨመር ያግዛቸዋል፡፡ በርካታ ኢ-መደበኛ አባላትንም ማፍራት በመቻሉ አገልግሎቱ ከጊዜ ወደ ጊዜ ጨምሯል፡፡

ከዚሁ ጋር ተያይዞም ማኅበረ ቅዱሳን የኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ሃይማኖት እንዲስፋፋና የአማንያኑ ቁጥር እንዲጨምር ለማድረግ ከሥር መሠረቱ በተለይም ሕፃናቱን በትምህርተ ሃይማኖትና በቤተ ክርስቲያን ሥርዓት ኮትኩቶ ለማሳደግ የአብነተ ትምህርት ቤቶችን እያስፋፋ ይገኛል፡፡ የማኅበሩ የቅዱሳት መካናትና መንፈሳዊ ትምህርት ቤቶች አገልግሎት ማስተባበሪያ ከተዋቀረበት ዓመተ ምሕረት ጀምሮ አብነት ትምህርት ቤቶች ባልተስፋፉባቸው አካባቢዎች የአብነት ትምህርት ቤቶችን የማስፋፋት ነባሮቹን ደግሞ የማጠናከር ሥራ ሠርቷል፡፡ በዚህም የአብነት ትምህርት ቤቶች፣ ገዳማትና የገጠር አብያተ ክርስቲያናት በሁለንተናዊ መልኩ የሚጠናከሩበትን መንገድ አመቻችቷል፡፡ ገዳማትም ራሳቸውን በኢኮኖሚና በልማት እንዲችሉ የተለያዩ ፕሮጀክቶችን በመቅረጽ ተግባራዊ አድርጓል፡፡

ረድኤተ እግዚአብሔር አይለየን፤ አሜን!!!