መልአከ ገነት ኃይለ ማርያም ፋንታሁን

መልአከ ገነት ኃይለ ማርያም ፋንታሁን አረፉ።

ከባህር ዳር ማእከል

ሰኔ 9 ቀን 2003 ዓ.ም

መልአከ ገነት ኃይለ ማርያም ፋንታሁንበባህር ዳር ከተማ በሚገኘው ፈለገ ገነት ቅዱስ ጊዮርጊስ ገዳምን ከ40 ዓመት በላይ በአስተዳዳሪነት ያገለገሉት መልአከ ገነት ኃይለ ማርያም ፋንታሁን በጠና ከታመሙ በኋላ በተወለዱ በ80 ዓመታቸው ግንቦት 30 ቀን 2003 ዓ.ም ከምሽቱ 2፡00 ሰዓት አርፈዋል። 

ሥርዓተ ቀብራቸው ብፁዓን አበው ሊቃነ ጳጳሳት ብፁዕ አቡነ ጴጥሮስ፣ ብፁዕ አቡነ ኤልያስና ብፁዕ አቡነ ቶማስ፣ ብፁዕ አቡነ ማርቆስ እንዲሁም ወዳጅ ዘመድና ቤተሰቦቻቸው በተገኙበት በፈለገ ገነት ቅዱስ ጊዮርጊስ ገዳም በዕለተ ሐሙስ ሰኔ 2 ቀን 2003 ዓ.ም ከቀኑ 5፡30 ተፈጽሟል፡፡

 
መልአከ ገነት ኃይለ ማርያም ከአባታቸው መምህር ፋንታሁን ጥሩነህ እና ከእናታቸው ወ/ሮ ውዴ አካሌ በምዕራብ ጎጃም ዞን በሜጫ ወረዳ በደብር መድኃኒት ማርያም ልዩ ስሟ ደረመኔ በተባለ ቦታ የተወለዱ ሲሆን እድሜያቸው ለትምህርት እንደደረሰ አባታቸው ተተኪ አገልጋዮችን ለማፍራት ባላቸው ልዩ ፍላጎት የተነሣ መንፈሣዊ ትምህርት ቤት በመግባት የቤተ ክርስቲያንን ትምህርት በትጋት በመማር እንዲሁ ደግሞ ወንበር ዘርግተው በማስተማር፣ ተተኪ ካህናትንና መምህራንን በማፍራት፣ ለከፍተኛ ማዕረግ የበቁ ጳጳሳትን በማፍራት፣ ከ300 በላይ መነኮሳትን አመንኩሰዋል። ከመነኮሱት ውስጥም ለፓትርያርክነት ማዕረግ የበቁ ያሉበት ሲሆን ፈለገ ገነት ቅዱስ ጊዮርጊስ ገዳምን ለ43 ዓመታት በማስተዳደር፣ በቤተ ክርስቲያኒቷ የተለያዩ የልማት ሥራዎች ላይ በመሣተፍ፣ ችግረኞችን በመርዳት፣ የተጣሉትን በማስታረቅ፣ ያዘኑትን በአባታዊ ምክር የሚያረጋጉ አባት እንደነበሩ አጭር የሕይወት ታሪካቸው ያስረዳል።