‹‹ሕግህ ለእግሬ መብራት ለመንገዴም ብርሃን ነው›› (መዝ፣ ፻፲፰፥፻፭)

የእግዚአብሔር ሕግ ብርሃን ነው፤ ‹‹ሕግህ ለእግሬ መብራት፥ ለመንገዴ ብርሃን ነው›› ብሎ ነቢዩ ዳዊት እንደተናገረው ከዚህ ከጨለማ እና ከተወሳሰበ ዓለም ከፈተና ያወጣን ዘንድ በትእዛዙ ልንኖር ይገባል፡፡ ማንኛውም ፍጡር የአምላኩን ስም የሚሰማበት ጊዜም ሆነ ሥፍራ  ይኖራልና ፈጣሪያችን እውነት እና ሕይወትም መሆኑን ተረድተን በመንገዱ መጓዝ የእኛ ፈንታ ነው፡፡  (መዝ፣ ፻፲፰፥፻፭)

ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ‹‹እኔ መንገድና እውነት ሕይወትም ነኝ›› ብሏልና የፈጠረንን አምላክ እግዚአብሔርን ማወቅ በሕጉም መመራት ከሁላችንም ይጠበቃል፤ ‹‹አንድ ጌታ፤ አንድ ሃይማኖት፤ አንዲት ጥምቀት›› እንደተባለውም የኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ሃይማኖት ተከታይ በመሆን እና ክርስቲያናዊ ሕይወትን አውቆ በመረዳት የእውነት መንገድ መከተል ተገቢ ነው፡፡ ይህንም ለመረዳት በመመራት በቤተ ክርስቲያን በመኖር እውነትን ልናውቃት ይገባል፤ ቸሩ አምላክ እግዚአብሔርም መንገዱን ይመራናል፡፡ (ዮሐ. ፲፬፥ ፮፤ ኤፌ. ፬፥፭)

ሆኖም በእምነት እና በበጎ ምግባር ያልተደገፈ ማንኛውም ክርስቲያናዊ ጉዞ በእግዚአብሔር ዘንድ ዋጋ አይኖረውምና ወደ ርሱ አያደርሰንም፡፡ ሁሉን የሚያይ አምላካችን ልባችንን እና ኵላሊታችንን ይመረምራልና የውስጣችንን ክፋት ስለሚያውቅ ቅድስት ቤተ ክርስቲያንን በድፍረት በመርገጣችንም በኋላኛው ዓለም ይቀጣናል፡፡

ነገር ግን ይህንን እውነት የማያውቁ ከሐድያን በተሳሳተ ጎዳና እየተጓዙ መሆናቸውን እስኪዘነጉ ድረስ ጠላት ዲያብሎስ ያስታቸዋል፤ ራሳቸውም ከመጥፋታቸው ባሻገር ለሰው ልጅ ሁሉ ጥፋት ምክንያት ሆነዋል፡፡ ከቤተ ክርስቲያን ሥርዓት የወጣ ምግባር ከመፈጸም ባሻገር ልጆቻቸውም ኃጢአትን ከሕፃንነታቸው ጀምሮ እንዲሠሩ ተጽዕኖ ስለሚያሳድሩባቸው አስተዳደጋቸውም ሆነ የሚጓዙበት መንገድ ከእግዚአብሔር የራቀ ይሆናል፡፡ ‹‹ሕፃናትን ወደ እኔ ይመጡ ዘንድ አትከልክሏቸው›› ብሎ ጌታችን መድኃታችን ኢየሱስ ክርስቶስ እንደተናገረ፤ ልጆች ገና ልሳናቸው ሲከፈት እና አእምሮአቸው ነገሮችን መለየት ሲጀምር ስለ እግዚአብሔር አምላክነት መንገርና ማሳወቅ አለባቸው፡፡ ቅዱስ ቊርባንንም መቀበል መብት አላቸውና ወደ ቤተ ክርስቲያን ወስዶ እንዲቆርቡ ማድረግ የወላጆች ድርሻ ነው፡፡ ዕድሜያቸውም ለትምህርት እንደደረሰም ሰንበት ትምህርት አስገብተው ወንጌልንና ክርስቲያናዊ ሥነ ምግባርን እንዲያውቁ ማድረግ ይጠበቃባቸዋል፡፡ (ማር. ፲፥፲፬)

ያለመታደል ሆነና ብዙ ሰዎች በዚህ ዘመን ምድራዊ ሕይወትን በማስበለጥ፣ ለጊዜያዊ ድሎት ቅድሚያ በመስጠት እና ለኃጢአት በመሸነፋቸው በተሳሳተ መንገድ ላይ ይገኛሉ፤ ‹‹ዘመናዊነት ነው›› በሚል ሰበብም ኑሮአቸውን ሀብት ለማካበት፣ ጊዜያዊ ደስታን ለማግኘት እና ጥቅምን በማሳደድ ላይ ትኩረታቸውን በማድረግ  ይኖራሉ፡፡ በዚህም ውሎአቸውን አልባሌ ነገርሮች እና ሥፍራዎች ያሳልፋሉ፡፡ ልጆቻቸውንም የሚወስዷቸው ወደ እነዚህ ሥፍራዎች  በመሆኑ ልጆቻቸው ከልጅነት ጀምሮ እውነትንም ሆነ የሕይወትን መንገድ ማወቅ እና መለየት ይቸግራቸዋል፡፡ መጥፎ ምግባርን ሲፈጽሙ ‹‹በርቱ›› እየተባሉ በማደጋቸው መጥፎ መሆንን ‹‹ትክክል ነው›› ብለው በአእምሮአቸው ውስጥ እንዲያስቡ ያደርጋል፡፡ ይህም ከልጅነታቻው አብሮአቸው ስለሚያድግ በጎ ምግባር ለመፈጸም ዕድል እንኳን ቢገጥማቸው ሽንፈት መስሎ ይሰማቸዋል፡፡ በተባለሸ አስተሳሰብ፣ በመጥፎ ምግባር፣ በክፋትና በጭካኔ ዕድሜያቸውን በሙሉ ኃጢአት ሠርተው ለንስሓ መብቃት አቅቷቸው ይሞታሉ፡፡

አንዳንዶች ደግሞ በመጥፎ ጓደኛ ወይም በሌሎች ተጽዕኖ ወደ ተሳሳተ አቅጣጫ በመጓዝ ለጥፋት ተዳርገዋል፤ እነርሱም የመኖራቸው ትርጉም ሳይገባቸው በመጥፊያው ጎዳና እየተጓዙ ናቸው፡፡ ይህን ተረድተው ከተሳሳተው መንገድ መመለስ እንዲቻል ግን  ሁሉም በእምነት እና በሃይማኖት ጸንተው ሊኖሩ ይገባል፡፡ እውነቱ ይህ ነው፤ የሰው ዘር በሙሉ የተፈጠረው አንድ አምላክ እግዚአብሔርን በማመን እና በሕጉ በመመራት እንዲኖር እና በእውነት መንገድ እንዲጓዝ ነው፡፡

ዛሬ ግን ብዙዎች እውነትን ክደዋል፤ ለሰይጣንም ተገዝተዋል፡፡ የዕለት ምግባራቸውም በክፋት፣ በተንኮል እና በመጥፎ ምግባር የተሞላ ሆኗል፡፡ ጥቅምን በመሻት አንደበታቸው በሐሰት ተሞልቶ ከእውነት ርቀዋል፤ ኃጢአት ከመልመዳቸው የተነሳ በድፍረት የሚፈጽሙት ክፋታቸው እና ኀፍረታቸው በገሀድ እየታየ ነው፡፡ እርስ በርስ መናናቅ፣ መጨካከን፣ መጠላላት እና መገዳደልም የተለመደ ሆኖአል፤ እኛም ሰዎች ዋጋ በሌለው ነገር ሲጣሉና ሲገዳደሉ አይተናል፤ ሰምተናልም፡፡ ዘር ለይቶ በቡድን በመደራጀትም ሰዎችን ለማጥፋት ሥራዬም ብለው የተነሡ ሰዎች እየተበራከቱ በመሄዳቸው ብዙዎች ለሞት ተዳርገዋል፤ ለንስሓም ሳይበቁ ተቀጥፈዋል፡፡

በአሁኑ ጊዜም ዓለም ከዚህ ለበለጠ ችግር እና ቸነፈር ተጋልጣለች፤ መድኃኒት ስለሌለው የኮሮና ቫይረስ በተደጋጋሚ መረጃዎች እየወጡ ይገኛሉ፤ በየዕለቱ ብዙዎች በወረርሽኙ እየተጠቁ ነው፡፡ ይህም በኃጢአታችን ምክንያት መሆኑ በመጽሐፍ ቅዱስ ተጽፏል፡፡ ‹‹ስለዚህ ቍጣዬን አፈሰስሁባቸው፥ በመዓቴም እሳት አጠፋኋቸው፤ መንገዳቸውንም በራሳቸው ላይ መለስሁ፥ ይላል ጌታ እግዚአብሔር›› እንዲል፤ ስለዚህም ወረርሽኙ ዛሬ ላይ በየትኛውም ዓለም የሚገኙ የሰው ልጆችን በየዕለቱ በፍጥነት እየቀጠፈ ነው፡፡  (ሕዝ. ፳፪፥ ፴፩)

ሰው በኃጢአት ከመጥፋት ይልቅ በንስሓ መመለስ እና መዳን ሲገባው በሠራው ሥራ በሀብቱ ብዛትና በሥልጣኔው ምጥቀት እየተመጻደቀ፣ የአምላኩን የእግዚአብሔርን ክፉ ሕግ ከተላለፈ ትእዛዙንም ካፈረሰ እግዚአብሔር ቀናዒ አምላክ ነውና ትዕቢተኞችን ይቀጣቸዋል፡፡

ይህንን እውነት የተረዳ ሰውም የእግዚአብሔርን ሕግ በማክበርና በሕግና ሥርዓቱ በመወሰን ፤ ከኃጢአት ነጽቶ በቅን ልቡናም ሆኖ አምላኩን በቅንነት ማገልገል ሊኖር ይገባል፡፡