በእውነት ደዌያችንን ተቀበለ፤ ሕማማችንን ተሸከመ፤ ስለመተላለፋችን ቆሰለ፤ በእርሱም ቍስል እኛ ተፈወስን (ኢሳ.፶፫፥፬‐፮)

መምህር ቢትወደድ ወርቁ
መጋቢት ፳፰፤፳፻፲፭ ዓመተ ምሕረት

ሰባት የጾምና የጸሎት ሳምንታትን አሳልፈን፣ “ሆሣዕና በአርያም” ብለን አምላካችን በመቀበል፣ የጌታችን የመድኃኒታችን የኢየሱስ ክርስቶስ ሕማሙን፣ መገፈፍ መገረፉን፣ መሰቀልና መሞቱን እንዲሁም የድኅነታችንን ዕለት ትንሣኤን በተስፋ ለምንጠብቅበት ለሰሙነ ሕማማት ደርሰናልና አምላካችን እንኳን ለዚህ አበቃን!

ነቢዩ ኢሳይያስ “በእውነት ደዌያችንን ተቀበለ፤ ሕማማችንን ተሸከመ፤ ስለመተላለፋችን ቆሰለ፤ በእርሱም ቍስል እኛ ተፈወስን” በማለት የተናገረው ትንቢታዊ ቃል ይፈጸም ዘንድ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ እኛን ከፍዳና ከዘለዓለማዊ ሞት ለማዳንና ከዲያብሎስም ቁራኝነት ነፃ ለመውጣት ሲል ዐሥራ ሦስቱን ሕማማተ መስቀልና ሌሎቹንም ጸዋትወ መከራዎች የተቀበለበት ሳምንት ‘ሰሙነ ሕማማት’ ትርጓሜው “የመከራና የሥቃይ ሳምንት” ማለት ነው፡፡ (ኢሳ.፶፫፥፬‐፮)

አራተኛው ምእተ ዓመት ድረስ ጌታችን ከጾመው ጾም ጋር ሳይሆን ለብቻው ይታሰብ እንደነበረ የቤተ ክርስቲያን ታሪክ ያስረዳል፡፡ ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በእርሱ ላይ የደረሱትን ሕማማት ሁሉ በትዕግሥት ተቀብሎና በመስቀል ላይ ተሰቅሎ የሞተው ዐርባውን ጾም ከፈጸመ በኋላ ከሦስት ዓመታት በላይ ካስተማረና ቤተ ክርስቲያንን ካደላደላት በኋላ ነውና፡፡ በዐራተኛው ምእት ዓመት ግን ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ከጾመው ጾመ ዐርባ ቀጥሎ ከትንሣኤ በፊት ባለው ሳምንት “ሰሙነ ሕማማት” እንዲታሰብ ተደርጓል፡፡ በዚህም ምክንያት የጾሙ ጊዜ ከስድስት ወደ ሰባት ሳምንታት ከፍ ብሏል፡፡ የዚህ የሰሙነ ሕማማት መታሰቢያ ጾም መጨረሻው የዐቢይ ጾምም መጨረሻ ስለሆነ ጾሙ በአክፍሎት ይደመደምና ከእሑድ መንፈቀ ሌሊት ጀምሮ በዓለ ትንሣኤው ይከበራል፡፡

በሰሙነ ሕማማት መጀመሪያ በሆሣዕና ዕለት የሚፈጸሙት ሥርዓቶች ለምሳሌ የዘንባባ ዝንጣፊ ባርኮ ለምእመናን ማደል፣ የዘንባባውን ዝንጣፊ በእጅ ይዞ መዘመርና በቤተ ክርስቲያን ዙሪያ ዑደት ማድረግ፣ በቤተ ክርስቲያኑ በሮችና ማዕዘኖች የዳዊት መዝሙራትን እየዘመሩ ወንጌልን ማንበብ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ለድኅነተ ዓለም የፈጸማቸውን እያንዳንዱን ነገሮች ያሳዩናል፡፡ ዘንባባ የክብርና የድል ምልክት ከመሆኑም በላይ ድርጊቱና አፈጻጸሙ ደግሞ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በድል አድራጊነት ወደ ኢየሩሳሌም በገባበት ጊዜ ሕዝቡ ሕፃናትን ጨምሮ “ሆሣዕና በአርያም፣ በጌታ ስም የሚመጣ የተባረከ ነው” እያሉ በታላቅ ምስጋናና ክብር እንደተቀበሉት የሚያመለክት ነው፡፡ (ማቴ.፳፩፥፩-፲) በጸሎተ ሐሙስ ዕለትም ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ጌታና መምህር ሲሆን በትሕትና ራሱን ዝቅ አድርጎ የደቀ መዛሙርቱን እግር ያጠበ መሆኑን ለማስታወስና ምሳሌውን ለመከተል ሲባል በቅዱስ ፓትርያርኩ፣ በአበው ሊቃነ ጳጳሳትና በካህናት የካህናትንና የምእመናንን እግር የማጠብ ሥርዓት ይፈጸማል፡፡

የሰሙነ ሕማማት ዕለታት

እሑድ (ዕለተ ሆሣዕና)

ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ወደ ኢየሩሳሌም በገባ ጊዜ ሕፃናትና ሽማግሌዎች፣ በጠቅላላ ሕዝቡ ሁሉ ልብሳቸውን እያነጠፉና ቅጠል እየጎዘገዙ፣ በእጃቸውም የድል አድራጊነት ምልክት የሆነውን የዘንባባ ዝንጣፊ እያያዙ በዝማሬና በታላቅ ክብር ተቀብለውታል፡፡

ዕለተ ሰኞ

በቤተ መቅደሱ ውስጥና በዙሪያው ይሸጡና ይገዙ የነበሩትን ከቤተ መቅደስ ያስወጣቸው፣ የገንዘብ ለመዋጮች ገበታዎችንና የርግብ ሽያጮችን ወንበሮች ገልብጦ ሁሉንም ከቤተ መቅደሱ በጅራፍ እየገረፈ ያስወጣቸው፣ ፍሬ አልባ የሆነችውንም በለስ የረገማት በዚሁ ዕለተ ሠኑይ ነው፡፡ በበለስም አንፃር ኃጢአትን እንደረገመ ሊቃውንት ያስተምራሉ፡፡

ዕለተ ማክሰኞ

ሰኞ የረገማት በለስ ማክሰኞ ደርቃ ተገኝታለች፡፡ የበለሲቱ መረገምና መድረቅ ቀድሞ በአዳም በኩል የመጣውና ከትውልድ ወደ ትውልድ ሲተላለፍ የኖረው መርገምና ፍዳ በክርስቶስ ሞት መወገዱን ያመለክታል፡፡ ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በዚሁ በማክሰኞ ቀን ስለግብር አከፋፈል፣ ስለትንሣኤ ሙታንና የዳዊት ልጅ የሚባል ማን እንደሆነ በመግለጥ መጻሕፍትን እየጠቀሰ ፈሪሳውያን ያስተምራቸውና ስለ ልቡናቸው ድንዳኔም ይገሥፃቸው የነበረው በዚሁ በዕለተ ሠሉስ ነው፡፡ (ማቴ. ፳፫፥፩-፴፱) በለምፃሙ በስምዖን ቤት ማርያም እንተ እፍረት (ባለሽቶዋ ማርያም) ሽቶ የቀባችው፣ የአስቆርቱ ይሁዳ ጌታውን ለማስያዝ ከአይሁድ ጋር በድብቅ የተነጋገረው በዚሁ በዕለተ ማክሰኞ ነው፡፡ (ማቴ.፳፮፥፩)

ዕለተ ረቡዕ

አይሁድ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ እንዲያዝና እንዲገደል ለማድረግ ውሳኔ የወሰኑበት እና ምክር የፈጸሙበት ቀን ነው፡፡ እንዴት እንደሚይዙት፣ ማን እንደሚያስይዛቸውና መቼ እንደሚይዙት በዚሁ ዕለት ወስነዋል፡፡ ለክፉ ሥራቸው ተባባሪ ያደረጉትም ከዐሥራ ሁለቱ ደቀ መዛሙርት መካከል የጥፋት ልጅ የሆነውን የአስቆርቱ ይሁዳን ነበር፤ ስለዚህ ዕለተ ረቡዕ ምክር የተፈጸመበትና ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ተይዞ በመስቀል ሞት እንዲገደል ውሳኔ የተላለፈበት ቀን በመሆኑና ውሳኔውም ተግባራዊ ሆኖ ጌታችን የተሰቀለውና የሞተው በዕለተ ዓርብ በመሆኑ የክርስቶስን መከራና የሰውን ልጅ ድኅነት ለማስታወስ ሲባል ከትንሣኤው በኋላ ባሉት ሃምሳ ቀናት ካልሆነ በቀር በየሳምንቱ ረቡዕና ዓርብ ጾመ ድኅነት በሚል ስያሜ እንዲጾም ተደርጓል፡፡

ዕለተ ሐሙስ

በዚህ ዕለት ጧት የፋሲካን በዓልና ዝግጅት እንዲያዘጋጁ ደቀ መዛሙርቱን ወደ ከተማ የላከ ሲሆን ሐሙስ ማታ ለመጨረሻ ጊዜ የፋሲካን በዓል ከደቀ መዛሙርቱ ጋር አክብሯል፡፡ በዚሁ ዕለት የኦሪቱን ሥርዓት ለውጦ አዲስ ሥርዓተ ቁርባን ሠርቷል፡፡ (ማቴ.፳፮፥፳፮-፳፯)

ጌታችን ከእኔ ተማሩ በማለት እንዳስተማረን ለፍጥረቱ መሪ ለትሩፋት ጀማሪ ለመሆንና ለአብነት በጌቴ ሴማኒ የጸለየው በዚህ በዕለተ ሐሙስ ነው፡፡ (ማቴ.፲፩፥፳፰፣፳፮፥፵) ጸሎትን በተግባር ካስተማረን በኋላም “ወደ ፈተና እንዳትገቡ ጸልዩ” በማለት ለጊዜው ለደቀ መዛሙርቱ በፍጻሜ ለምእመናን በሙሉ መመሪያና ትምህርት ሰጠ፡፡ (ሉቃ.፳፪፥፵) ይሁዳም የአይሁድን ጭፍሮች እየመራ ወደ እርሱ ወደ ክርስቶስ በመቅረብ “ሰላም ለአንተ ይሁን” በማለትና በሽንገላ በመሳም ለጭፍሮቹ አሳልፎ የሰጠው በዚሁ በዕለተ ሐሙስ ማታ ነው፡፡ (ሉቃ.፳፪፥፵፯) የደቀ መዛሙርቱን እግር በማጠብ ”እኔ ጌታና መምህር ስሆን እግራችሁን ከአጠብኩ እናንተ ደግሞ እርስ በርሳችሁ እግራችሁን ትተጣጠቡ ዘንድ ይገባችኋል፤ እኔ ለእናንተ እንዳደረግሁ እናንተ ደግሞ እንዲሁ ታደርጉ ዘንድ ምሳሌ ሰጥቻችኋለሁ” በማለት ትሕትናን በተግባር እየተረጎመና በድርጊት እያሳየ ለቀደ መዛሙርቱ ያስተማረው በዚሁ ዕለት ነው፡፡ (ዮሐ.፲፫፥፲፫-፲፭) ይህ ቀን ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በመከራው ጊዜ ፍጹም ሰው መሆኑን ለማስረዳት በተዋሐደው ሥጋ ወደ ባሕርይ አባቱ ወደ አብ የጸለየበትና ስለጸሎትም ያስተማረበት በመሆኑ ዕለቱ ጸሎተ ሐሙስ በመባል ይታወቃል፡፡

ዕለተ ዓርብ

ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ለአይሁድ ተላልፎ ከተሰጠበት ጊዜ ጀምሮ ሌሊቱን በሙሉ ከአንዱ ገዥ ወደ ሌላው ገዥ፣ ከአንዱም ሊቀ ካህናት ወደ ሌላው ሊቀ ካህናት እያመላለሱት በሐሰት ሲከሱትና ሲያስመሰክሩበት፣ ሲኮንኑትና ሲወነጅሉት አድረው ዓርብ ጠዋት ወደ ገዥው ወደ ጲላጦስ ዘንድ ቀርቦ ሞት የማይገባው አምላክ በግርግርና በጩኸት ብዛት በመስቀል ላይ ተሰቅሎ እንዲሞት የተወሰነበት ዕለት ነው፡፡ በዚሁ በዕለተ ዓርብ በቀትር ጊዜ ስድሰት ሰዓት ሲሆን ንጹሐ ባሕርይ መድኃኒተ ዓለም ኢየሱስ ክርስቶስ ያላንዳች ጥፋት እንደ ወንጀለኛ ተቆጥሮ በወንበዴዎች መካከል በመስቀል ላይ ተሰቅሏል፡፡ ከስድስት ሰዓት እስከ ዘጠኝ ሰዓትም በመስቀል ላይ ሆኖ ብዙ ተአምራትን ፈጽሞ ሰባቱ አጽርሐ መስቀልን (ሰባቱን የመስቀል ላይ ንግግሮች) ተናግሮ፤ በዘጠኝ ሰዓትም ተጠማሁ ሲላቸው ያቀረቡለትን መራራ ሐሞትና ከርቤ ከቀመሰ በኋላ “ተፈጸመ” የሚለውን የመጨረሻ ቃል ተናግሮ ቅድስት ነፍሱን ከቅዱስ ሥጋው ለይቶ በራሱ ፈቃድ የመጣበትን የማዳን ሥራ ፈጽሟል፡፡ (ዮሐ.፲፱፥፴)

ክርስቶስ በሰሙነ ሕማማቱና በዕለተ ስቅለቱ የተቀበላቸው ፀዋትወ መከራዎች እጅግ በጣም ብዙዎች እንደሆኑ ከቅዱሳት መጻሕፍት መረዳት የሚቻል ሲሆን በተለይ በግብረ ሕማማቱና ድርሳነ ማሕየዊ በተሰኙ መጻሕፍት በዝርዝር ተገልጠው ይገኛሉ፡፡ ከነዚህም ውስጥ ዐሥራ ሦስቱ ሕማማተ መስቀል የተባሉት ጥቂቶቹ ናቸው፡፡ እነርሱም ተአስሮ ድኅሪት (ወደ ኋላ መታሰር) ተስሕቦ በሐብል (በገመድ መጎተት)፣ ወዲቅ ውስተ ምድር (በምድር ላይ መውደቅ) ተከይዶ በእግረ አይሁድ (በአይሁድ እግር መረገጥ)፣ ተገፍዖ ማእከለ ዓምድ (በምሰሶዎች መካከል መገፋት) ተጸፍኦ መልታሕት (በጥፊ መመታት) ተቀሥፎ ዘባን፣ (ጀርባውን መገረፍ) ተኮርዖተ ርእስ፣ (ራሱን መመታት) አክሊለ ሶክ (የሾኽ አክሊል መቀዳጀት) ፀዊረ መስቀል (መስቀል መሸከም)፣ ተቀንዎ በቅንዋት (በምስማር መቸንከር) በመስቀል መሰቀልና ሰሪበ ሐሞት (መራራ ሐሞት መጠጣት ናቸው፡፡ መድኃኒታችን በዕፀ መስቀል ሳለ ዓርብ ከስድስት ሰዓት እስከ ዘጠኝ ሰዓት ባለው ጊዜ ፀሐይ ጨልሟል፤ ጨረቃ ደም ሆኗል፤ ከዋክብት ረግፈዋል፤ ዐለቶች (ድንጋዮች) ተሰነጣጥቀዋል፤ መቃብራት ተከፍተዋል፤ ሙታን ተነሥተዋል፤ የቤተ መቅደሱ መጋረጃ ማንም ሳይነካው ለሁለት ተከፍሎዋል፡፡

ዕለተ ቅዳሜ (ቀዳም ሥዑር)

ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በአካለ ሥጋ በመቃብር ነበር፤ መቃብሩም በጭፍሮች ይጠበቅ ነበር፡፡ ክርስቶስ በአካለ ሥጋ ከዓርብ ዐሥራ አንድ ሰዓት እስከ እሑድ መንፈቀ ሌሊት ድረስ በመቃብር ውስጥ የነበረ ሲሆን በአካለ ነፍስ ደግሞ ወደ ሲኦል ወርዶ ከአዳም ጀምሮ በሲኦል ውስጥ ለነበሩ ነፍሳት ነፃነትን ሰብኮላቸዋል፡፡ ከሲኦል ወጥተው ወደገነት እንዲገቡ አድርጓቸዋል፡፡ በአጠቃላይ እስከ ክርስቶስ ሞት ድረስ በፍርድ ግዞት ውስጥ ያሉትን ሁሉ በመከራውና በሞቱ ድል አጎናጽፏቸዋል፡፡ በኃጢአት ባርነት ውስጥ የነበሩት ሁሉ ሙሉ ነፃነትን አግኝተው የእግዚአብሔርን መንግሥት የመውረስ ዕድልን አግኝተዋል፡፡

እንበለ ደዌ ወሕማም እንበለ ጻማ ወድካም ያብጽሐነ ለብርሃነ ትንሣኤሁ እግዚአብሔር በፍስሐ ወበሰላም፤ ያለ ደዌ፣ ያለ መከራ፣ ያለ ድካም እግዚአብሔር በደስታና በሰላም ለብርሃነ ትንሣኤው ያድርሰን!

ምንጭ ፡- በደብረ አሚን ተክለ ሃይማኖት ቤተ ክርስቲያን የምክሐ ደናግል ማርያም ሰንበት ትምህር ቤት ትምህርታዊ ቡክሌት፣ ሰሙነ ሕማማት ፡- ቀሲስ ዶ/ር መስገቡ ካሣ ወርሐ መጋቢት ፳፻ ዓም