ልደታ ለማርያም

ዲያቆን ተስፋዬ ቻይ
ሚያዚያ፤፳፻፲፭ ዓመተ ምሕረት

ውድ የእግዚአብሔር ልጆች! ለከበረው ጤንነታችሁ እንዴት አላችሁ? ነቢየ እግዚአብሔር ንጉሥ ዳዊት በመዝሙሩ ‹‹እነሆ እስራኤልን የሚጠብቅ አይተኛም፤ አያንቀላፋምም…›› በማለት እንደተናገረው ሁሌ ከክፉ የሚጠብቀን ፈጣያችን በቸርነቱ ለዚህ አድርሶናልና ምስጋና ይድረሰው አሜን!!! (መዝ.፻፳፩፥፬)

ልጆች! ትምህርት እንዴት ነው? እየበረታችሁ እንደሆነ ተስፋ እናደርጋለን? በርቱ! መቼም ሁላችንም ስናድግ መሆን የምንፈልገው ነገር አለ፤ ያ ምኞታችን የሚሳካው ታዲያ ጠንክረን ስንማር ነውና ለትምህርታችን ትኩረት ሰጥተን እንማር!

ውድ የእግዚአብሔር ልጆች! በቀን ውስጥ ያሉንን ሰዓታት በመርሐ ግብር ብንከፋፍላቸው የትምህርት ጊዜ፣ የጥናት ጊዜ፣ እንደ አቅማችን ቤተሰብ የምናግዝበት (ቤት ውስጥ ቀለል ያሉ ሥራዎችን) የምንሠራበት ጊዜ፣ መጽሐፍ ቅዱስ የምናነብበት ጊዜ፣ መዝሙር የምንሰማበት ጊዜ፣ የጨዋታ ጊዜ ብለን በመመደብ በዚህ ልንመራ ይገባል፤ ይህ ለነገው ኑሮአችን ትልቅ ትምህርት ይሆነናል፡፡ የዓመቱ ትምህርትም እየተጠናቀቀ ስለሆነ በርትታችሁ ተማሩ፤ በጥሩ ውጤት ከክፍል ክፍል ለመዘዋወርም አጥኑ፤ መልካም ንባብ!

ውድ የአግዚአብሔር ልጆች! ዛሬ የምንነጋራችሁ የእመቤታችን የቅድስት ድንግል ማርያምን ልደት ይሆናል! እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም አባቷ ቅዱስ ኢያቄም እናቷ ደግሞ ቅድስት ሐና ይባላሉ፤ ሁለቱም እግዚአብሔርን የሚፈሩ መልካም ነገርን የሚሠሩ ደጋጎች ነበሩ፤ ለችግረኞችም ይረዱ ነበር፤ ደግሞም ጸሎትን አብዝተው ይጸልዩ ነበር፡፡

ልጆች! የሚገርማችሁ ነገር ቢኖር የወለዱት ልጅ ግን አልነበራቸውም፤ በዚህም በጣም አዝነው እግዚአብሔር ልጅ ይሰጣቸው ዘንድ አጥብቀው ለመኑ፤ ታዲያ አንድ ቀን ለጸሎት ወደ ቤተ መቅደስ ሄደው ሲመለሱ ሰዎች ሕፃን ልጆቻቸውን ይዘው ሲሄዱ ቅድስት ሐና አየችና “እኔም ልጅ ውልጄ እንደዚህ አብሬ ብሆን” ብላ ተመኘች፤ በዚህም አዘነች፡፡ እግዚአብሔርም የቅድስት ሐናንና የቅዱስ ኢያቄምን ጸሎት ሰማቸው፤ እመቤታችንንም ሰጣቸው፤ እመቤታችን ገና ሳትወለድ በእናቷ በቅድስት ሐና ማኅጸን ሳለች አንድ ቤርሳቤ የምትባል ዓይኗ የማያይ ሴት ነበረችና የቅድስት ሐናን ሆድ ነክታ ዓኗን ብታስነካው የጠፋው ዓይን በራ፡፡
እንደገናም በሌላ ጊዜ የቅድስት ሐና ዘመዷ የነበረ አንድ የሞተ ሰው ስለሞተ ወደ ለቅሶ ቤት ስትሄድ የቅድስት ሐና ጥላ ሲነካው ከሞት ተነሣ፤ በዚህን ጊዜ በወቅቱ የነበሩት ሰዎች ቀኑባት፤ ሊገድሏቸውም ይፈልጓቸው ጀመር፡፡

ውድ የእግዚአብሔር ልጆች! በወቅቱ የነበሩ ሰዎች እመቤታችን ገና ሳትወድ በእናቷ በቅድስት ሐና ማኅጸን ሳለች ማየት የማይችልን ዓይን ስላበራች፣ ሞቶ የነበረን ሰው ስላነሣች ቅድስት ሐናን ቅዱስ ኢያቄምን ለመግደል የተነሡት ገና ሳትወለድ እንዲህ ተአምር ስላደረገች ነበር፡፡ ከዚያም የእግዚአብሔር መልአክ ለቅዱስ ኢያቄም በህልሙ ተገለጸለትና “ሊገድሏሁ ይልጋሉና ከዚህ አገር ወደ ሌላ ሂዱ” አላቸው፡፡
ውድ የእግዚአብሔረ ልጆች! ቅዱስ ኢያቄምና ቅድስት ሐና የእግዚአብሔር መልአክ እንደነገራቸው ሊባኖስ ወደተባለ ተራራ ሸሽተው ሄዱ፤ በዚያም ሳሉ ግንቦት አንድ ቀን እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም በሊባኖስ ተራራ ተወለደች፤ ልጅ አልነበራቸውምና በጣም ደስ አላቸው፤ ዘመዶቻቸውም ተሰበሰቡና በአንድ ላይ በመሆን እግዚአብሔርን አመሰገኑ፡፡ ልጆች! እመቤታችን በሊባኖስ ተራራ ላይ እንደምትወለድ ነቢዩ ሰሎሞን ትንቢት ተናግሮ ነበር፤ ‹‹..ሙሽራዬ ሆይ ከሊባኖስ ከእኔ ጋር ነይ፤ ከሊባኖስ ከእኔ ጋር ነዩ…›› (መኃ.፬፥፰)፡፡

ውድ እግዚአብሔር ልጆች! እመቤታችን በተወለደች ጊዜ ለሰው ልጆች ሁሉ ታላቅ ደስታ ሆነ! ምክንያቱም ጌታችን የሚወለደው ከእርሷ ነውና እርሱ ተወልዶ ጠላታችን ዲያቢሎስን ድል አድርጎን ወደ ገነት ዳግመኛ የምንገባው በእርሱ ነውና የእመቤታችን መወለድ ለእኛ ታላቅ ደስታ ነው!ቅዱስ ኢያቄምና ቅድስት ሐና ስሟን ማርያም አሏት፡፡

ልጆች! ‘ማርያም’ ማለት ‘ስጦታ’ ማለት ነው፤ ለጊዜው ስጦታ መባሏ ልጅ ላልነበራቸው በሰዎች ዘንድ ሲነቀፉ ለነበሩ ለእናትና ለአባቷ ቢሆንም ፍጻሜው ግን ስጦታ የተባለችው ለሰው ልጆች ሁሉ ነው፤ ልጆች ማርያም ማለት ሌላኛው ትርጉሙ ከእግዚአብሔር ምሕረትን ለሰዎች የምታሰጥ የሰዎችን ልመና ወደ እግዚአብሔር የምታደርስ ማለትም ነው፡፡ የእመቤታችን ልደት የእኛም ልደታችን ነው! ምክንያቱም ያጣነውን ልጅነት የተመለሰልን ዳግመኛ የእግዚአብሔር ልጆች የተባልነው እርሷ በወለደችልን በጌታችን በመድኃኒታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ነውና፡፡ ስለዚህ ልደቷን ደስ ብሎን እናከብረዋለን!

ልጆች! እመቤታችን በተወለደች ጊዜ ቤተ ዘመድ ተሰብስቦ ንፍሮ ቀቅሎ፣ ቂጣ ጋግሮ በደስታ እንዳከበረ ዛሬም በሠፈራችን ሰብሰብ ብለን በአንድ ላይ ሆነን በደስታ ልደቷ እናከብራለን፤ ልጆች! የእመቤታችን የልደት ቀን በጨለማ ለነበረው የሰው ልጅ የብርሃን ምልክት የታየበት ጠላታችን ዲያብሎስ የደነገጠበት ፍጥረት ሁሉ ደስ የተኘበት ዕለት ነውና ደስ ብሎን ቤተ ክርስቲያን በመሄድ ፣ በማስቀደስ፣ በደስታ እናክብረው!

ፈጣሪያችን እግዚአብሔር ከእመቤታን ረድኤት በረከቷን ያድለን፡፡ አሜን!!! ቸር ይግጠመን !

ስብሐት ለእግዚአብሔር
ወለወላዲቱ ድንግል
ወለመስቀሉ ክቡር አሜን!!!