“ልትድን ትወዳለህ?” (ዮሐ.፭፥፭)

ዲያቆን ሰሎሞን እንየው
መጋቢት ፩፤ ፳፻፲፭ ዓመተ ምሕረት

ቅድስት ቤተ ክርስቲያናችን የዐቢይ ጾም ሳምንታትን በቅዱስ ያሬድ ስያሜ መሠረት አራተኛውን ሳምንት መጻጉዕ ብላ ታከብራለች። “መፃጉዕ” ማለት “ድውይ፥ በሕመም የሚሠቃይ፥ የአልጋ ቁራኛ” ማለት ነው። ይህንንም ስያሜ እንዴት እንደመጣ ለማየት በዕለቱ የሚነበበውን የወንጌል ክፍል ብንመለከት እንዲህ ይላል። “ከታመመ ሠላሳ ስምንት ዓመት የሆነው አንድ ሰው ነበረ፤ ኢየሱስ ይህን ሰው ተኝቶ ባየ ጊዜ፥ እስከ አሁን ብዙ ዘመን እንዲሁ እንደ ነበረ አውቆ ‘ልትድን ትወዳለህ’ አለው። ድውዩም ጌታ ሆይ አዎን! ውኃው በተናወጠ ጊዜ በመጠመቂያይቱ ውስጥ የሚያኖረኝ ሰው የለኝም እንጂ፤ ነገር ግን እኔ በመጣሁ ጊዜ ሌላው ቀድሞኝ ይወርዳል አለ። ጌታ ኢየሱስም ‘ተነሣና አልጋህን ተሸክመህ ሂድ’ አለው። ወዲያውም ሰውዬው ዳነ፤ አልጋውንም ተሸክሞ ሄደ፤ ያም ቀን ሰንበት ነበረ” ይላል። (ዮሐ.፭፥፭-፲)

ቅዱስ ያሬድ ከዚህ የወንጌል ክፍል በመነሣት “አሕየዎ ኢየሱስ ለመጻጉዕ ወፈወሶ በዕለተ ሰንበት አሕየዎ ኢየሱስ ለመፃጉዕ፤ ኢየሱስ መፃጉዕን በዕለተ ሰንበት አዳነው በማለት ይዘምራል። በዚህ ሳምንትም ጌታችን ድውያነ ሥጋን በታምራት ድውያነ ነፍስን በትምህርት ስለፈወሰበት፣ ለጊዜው በእግር በኋላ በግብር ስለተከተሉት ሐዋርያት የማዳን ሥራ፣ ዛሬም በቤተ ክርስቲያን ስለሚደረገው ድኅነት የምንማርበት ሳምንት ነው። ቅዱስ ያሬድ በጸናው ለመናገር “መፃጉዕ’ ብሎ ስያሜውን ጠራው እንጅ። በመግቢያው ላይ እንዲህ ይላል፤ “ወልደ እግዚአብሔር ተአምረ ገበረ አሕየወ በሥልጣኑ ዓይነ ዕውረ፤ …በሰንበት ፈወሰ ዱያነ ወከሠተ አዕይንተ ዕውራን” በማለት የእግዚአብሔር ልጅ ታምራትን እንደሠራ፣ በሥልጣኑ ዕውራንን እንዳበራና ድውያንን እንደፈወሰ ይነግረናል።

በርእሳችን ቀዳሚ ወደ አደረግነው ሐሳብ እንመለስ፤ ከደውየው ጽናት የተነሣ ስሙ እንኳን የተረሳ፣ ረጅም ዓመታት በደዌ ዳኛ በአልጋ ቁራኛ በመያዙ መፃጉዕ፣ በሽተኛው፣ በደዌ የተያዘው እየተባለ ስለሚጠራው በቤተ ሳይዳ በጠበል ሥፍራ የተኛውን በሽተኛ በዓይነ ኅሊናችን እንመልከተው፤ በእግረ ኅሊናችን ወደ ቤተ ሳይዳ እንገሥግሥ፤ በዚች የይቅርታ በር ለሠላሳ ስምንት ዓመት ከአልጋው ተጣብቆ የሚኖረውን መጻጉዕ ለትንሽ ደቂቃ አብረነው እንቆይ።

መፃጉዕ የእግዚአብሔርን ምሕረት እየተጠባበቀ ለረጅም ዘመን ኑሮአልና ከውኃ ዳር ሁኖ ብርድና ሙቀት፣ ውርጭና ፀሐይ፣ ቀንና ሌሊት እየተፈራረቀበት ከአልጋው ውጭ ዘመድ የሌለውን የእምነቱን ጽናት አስተውሉ። ዛሬ ችግራችንን ለእግዚአብሔር ነገርን ለአንድ ሰዓት እንኳን መታገሥ አቅቶን ከይቅርታዋ በር የኮበለልን ለእኛ የተሠጠን ሊቁ ኤስድሮስ የተኛበትን አልጋ “የብረት አልጋ ነው” በማለት ተርጉመውታል። (ትርጓሜ ወንጌል ዘዮሐንስ ምዕራፍ ፭) እውነት ነው! ለሠላሳ ስምንት ዓመት የሚቆይ ጠንካራ አልጋ ቢሆን ነውና። ነገር ግን ብረት ውርጭ ይስባል፤ ቀዝቃዛ ነው፤ ይህን ታግሦ ምሕረት እየተጠባበቁ መኖር ምን ይደንቅ!

የቤተ ክርስቲያን ልጆች! ዛሬም የይቅርታ የምሕረት በር በሆነችው ቤተ ክርስቲያን ብዙ መጻጉዎች የእኛን ርዳታ ሽተው እጃቸውን ዘርግተው እየተጠባበቁን ነውና ሰው እንሁንላቸው። “ተርቤ አላበላችሁኝም፣ ታምሜ አልጎበኛችሁኝም”… የሚለን አምላካችን በድውያን ላይ አድሮ ስለሚኖር ነውና። (ማቴ.፳፭፥፴፩-፵፮) የተቸገረውንና የታመመውን ሰው አልፈን ክርስቶስን ፍለጋ ቤተ መቅደስ ብንገባ አናገኘውምና ሕሙማነ ነፍስን በትምህርት ሕሙማነ ሥጋን በእንክብካቤ እናግዛቸው። ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ ምጽዋትን ሲተረጉም “ፍቅር” በማለት ይጠራዋል። ምጽዋት መስጠት ፍቅር መስጠት ነውና፤ ታዲያ ክርስቶስን ምን ያህል አፍቅረነዋል?

መፃጉዕ በዚያች አልጋ ላይ ተጣብቆ የውኃውን መናወጽ ይጠባበቃል። በሰንበት መልአኩ መጥቶ ሲያናውጸው ሰው ባለመኖሩ ምክንያት ቀድመውት እየገቡ አለመዳኑን ስናይ የሰው መድኃኒቱ ሰው መሆኑን እንረዳለን። መፃጉዕም ሰው የለኝም ያለ ሠላሳ ስምንት ዓመት የሚያበላው፣ የሚያጠጣው፣ የሚያለብሰው፣ ሰው አልኖር ብሎ ሳይሆን የክርስቶስን ሰው መሆን ሲጠባበቅ በነበረው በአዳም ቃል ተገብቶ እየተናገረ ነው። መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በኢየሩሳሌም በበጎች በር በዕብራይስጥ ቤተ ሳይዳ በምትባል በመጠመቂያ ቦታ ተገኘ። በበጎች በር ያለውም ክርስቶስ ደግ እረኛ በመሆኑ በበጎች በር መጣ ተባለ፤ መልካም እረኛ በበር ይመጣልና። በዚህ ጊዜ መፃጉዕን አገኘው፤ እርሱም “ወይቤሎ እግዚእ ኢየሱስ ትፈቅድኑ ትሕየው፤ ልትድን ትወዳለህን” አለው። መፃጉም “እወ እግዚኦ” አዎ፤ አቤቱ አለ። ኢየሱስም የመፃጉዕን መልስ ከሰማ በኋላ “ተንሥእ ወንሣእ ዓራተከ ወሑር፤ ተነሥና አልጋህን ተሸክመህ ሂድ” አለው። (ዮሐ.፭፥፭-፲)

ሠላሳ ስምንት ዓመት በአልጋ ቁራኛ ይሠቃይ የነበረው መፃጉዕ በአንድ ጊዜ ዳነ፤ ከሕመሙም ተፈወሰ፤ ያንን የብረት አልጋ ተሸክሞ ወጣ። ማንም ባልነበረበት ሰዓት ያልተለየችውን አልጋ ውለታዋን ሊከፍል ይዞ ወጣ። ቅዱስ ዳዊት የተናገረው በእኛ ላይ አልተፈጸመም? “እንጀራዬን የበላ በእኔ ላይ ተረከዙን አነሣ” እንዲል፤ (መዝ.፵፩፥፱) በተለይም እናታችን ቤተ ክርስቲያን በልጅነት አክብራ ወተት እየመገበች አሳድጋን ዛሬ ያንን ርስተን በሐሰት ስንወነጅላት፣ ጥለናት ስንኮበልል ሳስብ “መጻጉዕ ምን ያህል ከእኛ የላቀ ምሁር ነው” እላለሁ።

ጌታችን ወደ ቤተ ሳይዳ መጥቶ መፃጉን “ልትድን ትወዳለህ” ብሎ መጠየቁን ስናይ ይደንቃል! ምሕረትንና ድኅነትን እየተጠባበቀ የኖረው ሰው “አልድንም” የሚል መልስ ሊሰጥ እንደማይችል የታወቀ አይደል? ታዲያ ስለምን ጠየቀው ቢሉ የነፃነት አምላክ ነውና እኛን ሳያስፈቅድ እንደማይሠራ ለማጠየቅ ነው። ምሥጢሩ ግን በዕለተ ዓርብ ጌታን በጥፊ ከመቱት ሰዎች አንዱ ይህ መጻጉዕ ነበርና “ስለምን በጥፊ ትመታዋለህ” ቢሉት ሳልፈልግ አድኖኛል እንጂ ‘አድነኝ ብየው አይደለም እንዳይል’ ሰበብ እንዳያገኝ ነው።”

ክርስትያኖች እናንተስ ልትድኑ ትወዳላችሁ? ወይስ እኛ አልታመምንም ትሉ ይሆን? እኔ ግን እላለሁ ፈውስ የሚያስፈልገን መፃጉዕዎች ነንና የይቅርታ በር ወደ ሆነችው ቤተ ክርስቲያን እንገሥግሥ። ዛሬ ሕዋሳቶቻችን ታመው እቤት መዋል ጀምረናልና መዳንን እንሻ። እስኪ ልጠይቃችሁ! ዓይኖቻችን አልታመሙን? ክርስቶስ በፊታችን እንደተሰቀለ ሆኖ መመልከት ይችላሉን? ጀሮአችንስ ይሰማልን? ቤተ ክርስቲያን ስትጣራ ሰምተናት እናውቃለን? እንጃ! የታመሙት ሕዋሳቶቻችን ይፈወሱ ዘንድ እንደ መጻጉዕ ከቤተ ክርስቲያን አንለይ! በእዚያ ሆነን የክርስቶስን መምጣት እንጠባበቅ እንጅ።

እግዚአብሔር አምላክ ከወደቅንበት የኃጢያት ባርነት ያድነን ዘንድ መጣ። አምላካችን ተራ የማንጠብቅበት ለሁሉ የሚበቃ፣ ፍጹም የሆነ ድኅነት የምናገኝበትን ዘለዓለማዊ የሆነ መብልንና መጠጥን የምሕረት በር በሆነችው ቤተ ክርስቲያን ሰጠን። ቅዱስ ኤፍሬም እንዲህ ብሎ እንደነገረን “ከዕፀ ሕይወት እንበላ ዘንድ አደለን፤ ይኸውም የክርስቶስ ሥጋና ደም ነው።” (ውዳሴ ማርያም ዘሐሙስ ክፍል ሁለት) በዚህ አለመኖር ደግሞ ጌታን በጥፊ ከመምታት አይተናነስም። ጥፊያችን ደግሞ ሰበብ አልባ ነውና ከጥቅም አልባ ሰበብ በቸርነቱ ይጠብቀን።

ወስብሐት ለእግዚአብሐር
ወለወላዲቱ ድንግል
ወለመስቀሉ ክቡር አሜን።