“ሊከተለኝ የሚወድ… መስቀሉን ተሸክሞ ይከተለኝ”

ቀሲስ ፋሲል ታደሰ
ቀን፡ መስከረም 13 / 2003 ዓ.ም.

መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የሰው ልጆችን ፍቅር ስለገለጠበት ሕማምና ሞቱ ለደቀመዛሙርቱ ባስተማረበት ወቅት ለእነርሱም “እኔን ሊከተል የሚወድ ራሱን ይካድ ጨክኖም መስቀሌን ተሸክሞ ይከተለኝ” ብሏቸዋል፡፡ አስቀድሞ “የሰው ልጅ ይሰቀል ዘንድ ይገባዋል” በማለት ነገረ ድኅነትን የሚፈጽምልን በዕፀ መስቀሉ እንደሆነ ተናግሯል፡፡ ጊዜው ሲደርስም በቀራንዮ መስቀል ላይ ዋለ በገዛ ፈቃዱ ስለ ሰው ልጆች መዳን ቅድስት ነፍሱን ከቅዱስ ሥጋው ለየ፡፡ በአካለ ነፍስ ወደ ሲዖል ወርዶ ነፍሳትን ወደ ገነት አሸጋገረ፤ የዲያብሎስንም ሥራ በመስቀሉ ድል ነሣ ሰላምን አደረገ፡፡ “በእኛ የነበረውን የሚቃወመንንም በትእዛዛት የተጻፈውን የዕዳ ጽሕፈት ደመሰሰው እርሱንም /ዲያብሎስ/ በመስቀሉ ጠርቆ ከመንገድ አስወግደታል እንደሚል /ቆላ. 2÷20/

ቅዱስ ዮሐንስ “ወበዝንቱ ተዐውቀ ፍቅሩ ለእግዚአብሔር የእግዚአብሔር ፍቅሩ በዚህ ታወቀ” በማለት እንደገለጸው አምላካዊ ፍቅሩን በሕማማተ መስቀሉ አሳይቶናል  /1ኛ ዮሐ.4÷10/፡፡ ሕግን የጣስን ቅጣትም የሚገባን የሰው ልጆች ሆነን ሳለ ነገር ግን ከቸርነቱ ብዛት “የሟቹን ሞት አልወድም” በማለት በዘለዓለም ሞት ተቀጥተን እንድንኖር አልወደደምና በሕማማተ መስቀሉ “ደዌያችንን ተቀበለ ሕማማችንን ተሸከመ ስለ እኛም ታመመ… በእርሱ ቁስል እኛ ተፈወስን” /ሕዝ.18÷32፣ ኢሳ.53÷4/፡፡

የእግዚአብሔር ፍቅር በመስቀል እንደተገለጠ ሁሉ የሰው ልጆችም እርሱን የመውደዳችን መገለጫ መስቀሉን በመሸከም መከተል እንደሆነ በአምላካዊ ቃሉ አስተምሮናል፡፡ ይህም ማለት እንደ ጌታችን ረጅምና ክብደት ያለው ዕፀ መስቀልን በትከሻችን ተሸክመን ቀራንዮ እንድንጓዝ ሳይሆን መከራ መስቀሉ ስለ እኛ ሲል የፈጸመልን መሆኑን በማመን እና ተከታዮቹ በመሆናችን የሚመጣብንን መከራ በመታገሥ መኖር እንደሚገባን ሲያመለክተን ነው፡፡ በዚህም መሠረት “መስቀል መሸከም” የተባለው በዓለም ስንኖር በክርስትና ምክንያት የሚገጥመንን መከራ ነው፡፡ “በዓለም ግን መከራ ትቀበላላችሁ ነገር ግን ጽኑ እኔ ዓለሙን ድል ነስቼዋለሁና” እንዲል /ዮሐ.16÷33/፡፡ በወቅቱ ይህ ቃል የተነገራቸው ቅዱሳን ሐዋርያት መስቀሉን በመሸከም ማለትም ስለ ክርስትና ኑሮ የመጣባቸውን መከራ በመታገሥ እና ድል በመንሳት ኑረዋል ለዚህም ነው፡፡ “መንግሥተ ሰማያት በብዙ መከራ እንገባ ዘንድ ያስፈልገናል” በማለት በቃልም በተግባርም የገለጹት /ሐዋ.14÷22/፡፡ የክርስትና ጉዞ እንደ ቀራንዮ ጉዞ መከራ የበዛበት ነው፡፡ ፈቃደ ሥጋን እየታገሱ ለፈቃደ ነፍስ እየኖሩ ዓለምን፣ ዲያብሎስን እየተዋጉ እስከ ሞት በመጽናት ተጉዘው የክብር አክሊል የሚቀዳጁበት ሕይወት ነውና “እስከ ሞት ድረስም የታመንህ ሁን የሕይወት አክሊልንም እሰጥሀለሁ” ተብሎ እንደተጻፈ /ራእ.2÷10/፡፡

መከራ ከየት ይመጣል?

1. ከዲያብሎስ ጥንተ ጠላታችን ዲያብሎስ የሰው ልጅን በኃጢአት መጣል ቋሚ ሥራው ነው፡፡ ይልቁንም የመስቀሉን ዓላማ የያዙ ክርስቲያኖችን ይከታተላል፡፡ በተለያዩ ወጥመዶችም ለመያዝ እና መከራ ለማጽናት ይሞክራል፡፡ ቅዱስ ጴጥሮስ “ጠላታችሁ ጋኔን የሚውጠውን ፈልጐ እንደሚያገሳ አንበሳ ይዞራልና” ሲል ቅዱስ ጳውሎስም “ሰልፋችሁ ከጨለማ ገዦች…. ከክፋዎች አጋንንት ጋር ነው” በማለት ውግያውን ገልጾታል፡፡ ቅዱስ ዮሐንስ በራእይ መጽሐፉም በሰይጣን አማካኝነት የተለያዩ መከራዎች እንደሚመጡ ሲያስረዳ እንዲህ ብሏል “ትቀበለውም ዘንድ ስላለህ መከራ አትፍራ እነሆ እንድትፈተኑ ሰይጣን ከእናንተ አንዳንዶችን ወደ እስር ቤት እንዲገቡ ያደርጋል….”/ራእ.2÷10/ ቅዱሳን ከዲያብሎስ የመጣባቸውን መከራ በመታገሥ ለክብር እንደበቁ ገድላት ምስክሮች ናቸው፡፡ “ክርስቶስን በመከራ ትመስሉት ዘንድ ደስ ይበላችሁ” እንደ ተባለው ቅዱስን የመጣባቸውን መከራ በጸጋ በመቀበል ጌታቸውን መስለዋል /1ኛ ጴጥ. 4÷13/፡፡

ጠላታችን ዲያብሎስ ፈቃደ ሥጋን በማስወደድ፣ በደካማ ጐናችን በመፈታተን፣ በሥጋዊ ምኞት ለመጣል መከራ ያመጣብናል፡፡ ለእኛ አብነት እንዲሆነን በተፈጸመው የገዳመ ቆሮንቶስ የዲያብሎስ ፈተና እንደምንገነዘበው “ዛሬም ለእኔ ብትሰግድ፣ ብትገዛ…” በማለት በምኞት ዓለም በማስጐምጀት ከእግዚአብሔር ሊያርቀን ይታገለናል፡፡ ስለሆነም ጌታችንን በክብር የምንመስለው መስቀሉን በመሸከም ከመሰልነው እንደሆነ በማስተዋል ከዲያብሎስ በተለያዩ መንገዶች የሚመጡብንን መከራዎች በመታገሥ እና ድል በመንሣት ለመኖር መዘጋጀት ይጠበቅብናል፡፡ መስቀሉን የመሸከም መገለጫም የሚደርስብንን የተለያየ መከራ መታገሥ እንደሆነም በማስታወስ፤ ክብሩን በማሰብ፤ ክርስቲያናዊ ፈተናን ለመቋቋም እንበርታ፡፡ “ካለው ክብር ጋር ሲመዛዘን መከራው ምንም እንዳይደለ እናውቃለን” እንደሚል /ሮሜ. 8÷18/፡፡


2.    በራሳችን ክፉ ምኞት
– አንዳንድ ጊዜ ከመንፈሳልነት ርቀን የምናውጠነጥነው ክፉ ምኞት በራሳችን ሕይወት ላይ መከራ ሲያመጣብን ይስተዋላል፡፡ ቅዱስ ያዕቆብ “በእናንተ ዘንድ ጥልና መጋደል ከወዴት ይመጣሉ? በሰውነታችሁ ውስጥ የሚሠራውን ዝሙት ከመውደድ የተነሣ ከዚህ አይደለምን….” በማለት ከራስ ክፉ ምኞት መከራ እንደሚመጣ ያስገነዝበናል፡፡ በመንፈስ ስንዝል ኃጢአት መጓዝ እንጀምራለን፡፡ አምኖን በገዛ ምኞቱ ተፈትኖ በዝሙት እንደወደቀ ሁሉ ዛሬም በራሳችን ክፉ ምኞት በመገፋፋት በኃጢአት በመውደቅ ዳግማዊ አምኖን እንዳንሆን ያስፈልጋል /2ኛ ሳሙ.13÷1/፡፡  በአብዛኛው ያለፈቃዳችን የምንሠራው ኃጢአት እንደሌለ ልናጤን ይገባናል፡፡ ይህንንም “ነገር ግን እያንዳንዱ በራሱ ምኞት ሲሳብና ሲታለል ይፈተናል” እንዲል /ያዕ 1÷14/፡፡

በመሆኑም ለክፉ ምኞት ተጋላጭ የሆነውን ኅሊናችንን በመግዛት፤ ለመልካም ሥራ መነሣሣት መታገል በራሱ መስቀል መሸከም መሆኑን ዘወትር ልንዘነጋ አይገባንም፡፡ በፈቃደ ሥጋ ለተዘፈቅንም ከዚህ ለመውጣት የሚደረገው ትግል ተገቢ መሆኑን በመረዳት መንፈሳዊ ተጋድሎውን ልናፀና ይገባልና፡፡ “ሰውነቱን በመከራ የሚያሰቃያትን አመስግኑት” /ኢሳ. 49÷7/ ተብሎ እንደተጻፈ የፈቃደ ሥጋ ምኞት የሆኑትን ዝሙት፣ ሱሰኝነትን፣ መዳራት… የመሳሰሉትን ድል ለመንሣት መታገል የሚያስመሰግን ተግባር ነው፡፡ ስለዚህም የሥጋን ሥራ በመንፈሳዊ ሥራ በመተካት ከራሳችን ምኞት ፈተና እንዳይጸናብን መንገዱን ለመዝጋት እየጣርን በጾም በጸሎት ረድኤተ እግዚአብሔርን አጋዥ እናድርግ፡፡ “እንደ እግዚአብሔር ፈቃደ መከራን የሚቀበሉ ሰዎችም መልካም ሥራን በመሥራት ለታመነ ፈጣሪ ነፍሳቸውን አደራ ይስጡ” ተብሏልና /1ጴጥ.4÷19/፡፡

3.    ካላመኑ ወገኖች- በክርስትና ኑሮ ላይ መከራ ከሚመጣበት አንድ ካለመኑ ወገኖች ነው፡፡ ከዘመነ አበው ጀምሮ በአምልኮተ እግዚአብሔር የዳኑ ሰዎች እግዚአብሔርን ከማያምኑ ወገኖች መከራ ሲመጣባቸው ኖሯል፡፡ የግብጹ ፈርዖን እሥራኤል ላይ መከራ ማጽናቱ እና ከዐሥሩ የቅስፈት ዓይነቶች አለመማሩ ያለማመኑ ውጤት ነው፡፡ በመሆኑም እሥራኤል ባሕረ ኤርትራን ሲሻገሩ ፍጻሜው ስጥመት ሆኗል፡፡ ቅዱሳን ሐዋርያትን አይሁድ ጣዖት አምላኪዎች እና ጠንቋዮች መከራ ያጸኑባቸው እንደነበር በሐዋርያት ሥራ ተመዝግቧል፡፡ ለምሳሌ ኤልማስ የተባለ ጠንቋይ ወንጌልን እንዳይሰብኩ ሲፈታተናቸው፤ ሌሎች ደግሞ መጽሐፎቻቸውን በማቃጠል የአገልግሎት እንቅፋት ሆነውባቸዋል፡፡ እንደዚሁም በማሳደድ እና በመግረፍም ሄሮድስና ሌሎችም ዐላውያን ነገሥታት መከራ ያመጡባቸው ነበር፡፡ /ሐዋ.13÷8፤19÷19/ ለዚህም ነው፡፡ “መከራ ተቀብለን ተንገላተን ወንጌልን ተናገርን” በማለት ቅዱስ ጳውሎስ መከራቸውን የገለጸው /1ኛ ተሰ.2÷2/ በተጨማሪም ስደት መራብ መጠማት ነቀፋ.. እና የመሳሰሉት በአገልግሎታቸው ጊዜ የተለመደ መከራ ስለመሆኑ እና ነገር ግን የቅዱሳን አበው ጭንቀት ከሌሎች ስለሚመጣው መከራ ሳይሆን የአብያተ ክርስቲያናት ሐሳብ ስለመሆኑ ለቆሮንቶስ ክርስቲያኖች በጻፈው መልእክቱ አስገንዝቧል/ 2ኛ ቆሮ.11÷28/፡፡ የዘመነ ሰማዕታት ቅዱሳን ሰዎች ኑሮም እንደሚያስረዳው በየዋሻው እምነታቸውን የገለጡበት እና ደማቸውን ስለ ክርስትና ያፈሰሱት እንደእነ ዲዮቅልጥያኖስ እና መሰሎቹ ካመጡባቸው መከራ የተነሣ መሆኑን የቤተ ክርስቲያን ታሪክ ማስረጃ ነው፡፡ በዘመናችንም በተለያዩ መንገዶች በኢየሱስ ክርስቶስ የባሕርይ አምላክነት ካላመኑ ወገኖች መከራ ሊመጣ ይችላል፡፡ አይሁድ የክርስቶስን መስቀል እንደቀበሩ፤ የቤተ ክርስቲያንን ትውፊትና ሥርዓተ ትምህርት ለመቅበር በመሯሯጥ በተዋሕዶ እምነታቸው የዳኑትን ምእመናን እና አገልጋዮችን የሚፈታተኑ ተረፈ አይሁድ በየዘመኑ ይነሣሉና፡፡ “በመጣባችሁ መከራ አትደነቁ” እንደተባለ፤ ስለ ሃይማኖት ከማያምኑ /ከተጠራጣሪዎች/ በሚመጣው ፈተና ሳንታወክ በመንፈሳዊ ሕይወት እና በተዋሕዶ ትምህርት ልንጸና ይገባናል፡፡

ከላይ የጠቀስናቸውን የመከራ ምንጮች መሠረት አድርገን በዘመናችን ስላለው መከራም ልናተኩር ይገባናል፡፡ በክርስትና ኑሮ ላይ እየተፈታተኑን የሚገኙትን የመከራ ዓይነቶች ከራሳችን እና ከውጪ ብለን ብንጠቁም ለመረዳት ግልጽ ይሆናል፡፡ ለአብነት ያህልም ከራሳችን ከሚመጡብን የወቅቱ ችግሮት ሁለቱን እንመልከት፡፡

1.    ዓለማዊነት- “ወንድሞች ሆይ ይህን ዓለም አትውደዱ፤ ዓለምን መውደድ ከእግዚአብሔር ጋር ጥል ነው፡፡” ይላል ነገር ግን ከሰይጣን ግፊት ወይም ከራሳችን ከደካማ ጐን የተነሣ በመውደቅ ለዓለም ምርኮኛ መሆን የተለመደ ሆኗል፡፡ ዓለማዊነት ስንልም በዓለም ውስጥ የሚገኝ የኃጢአት ተግባራት መፈጸምን ነው በዘመናዊነት እና በሥልጣኔ ሰበብ ብዙዎች ለዕውቀትና ለልማት የሚሆነውን በጐ ነገር ከመቀስም ይልቅ ኃጢአታዊ ተግባራት ላይ ሲያተኩሩ ይታያል፡፡ ለምሳሌ ከመጾም መብላትን፣ ከማስቀደስ መተኛትን፣ ከመዝሙር ዘፈንን፣ በሥርዐት ከመልበስ ፋሽን መከተልን… የመሳሰሉትን ማዘውተሩ በዓለማዊ ምኞት የመጠመድ መገለጫ ነው፡፡ በአንድ ወቅት እሥራኤል ከሞዓብ መንደርና ተግባር በመተባበራቸው በጣዖት አምልኮ በዘፈን እና በዝሙት ሲወድቁ ለቅስፈት ተዳርገዋል፡፡ ዛሬም ቢሆን በክርስትና ኑሮ የሚጓዙ ኦርቶዶክሳዊያን ዕውቀት፣ ገንዘብ እና ሀገር መለወጥ ሲገጥማቸው በጐውን ከመጠቀም ይልቅ የሥልጣኔ ትርጓሜ ባለመረዳት የክርስትና ሕይወትን በዓለማዊነት ሲለውጡ በአነጋገር፣ በአለባበስ በውሎ…. በመሳሰሉት ምዓባዊ ሥራ መሥራት እየተብራከተ መጥቷል /ዘኁ.21/፡፡ ስንቶቻችን ነን ከዓለማዊነት ሸክም ርቀን ስለ እግዚአብሔር ፍቅር መስቀሉን ተሸክመን ለመኖር የተዘጋጀን? ዛሬ ዛሬ ከዓለማዊነት የተነሣ ቤተ ክርስቲያንን መከተል ሳይሆን ቤተ ክርስቲያን እንደ እነርሱ ፍላጐት እንድትከተላቸው የሚፈልጉ አይጠፋም፡፡ ለሥርዐት ከመገዛት ይልቅ “ምን አለበት፣ ምን ችግር? አለው” በሚል ቃላት ተደልለው ለቀኖና ቤተ ክርስቲያን ቸልተኛ ከመሆን እስከ ኑፋቄ መድረስ እየተለመደ ነው፡፡ ስለዚህም ለሥጋ ሥራ የሚያተጋውን ዓለማዊነትን አርቀን ለመንፈስ ፍሬዎች የሚያበቃውን ነገረ መስቀሉን እየሰብን ጌታችንን በእውነት ልንከተለው ይገባናል፡፡

2.  ፍቅረ ንዋይ– ባለንበት ወቅት በፍቅረ እግዚአብሔር እንዳንጸና ከሚፈታተነን አንዱ ገንዘብ ወዳድ መሆን ነው፡፡ ይሁዳ እንደ ሌሎቹ ደቀመዛሙርት መስቀሉን ተሸክሞ እንዳይከተል ጠልፎ የጣለው ኃጢአት ፍቅረ ንዋይ መሆኑ የታወቀ ነው፡፡ ዛሬስ ለምን በዐሥራት አልታመንም? ሰንበትና በዓላትን አላከበርንም…? ብለን ራሳችንን ብንመረምር ያለኝ ይበቃኛል የሚለውን ምክር ወደ ጐን ትተን በፍቅረ ንዋይ መጠመዳችንን የሚያሳይ ነው፡፡ የሙስና መብዛት፤ አጭበርባሪነት መበራከት፤ በንግድና በተለያዩ ዘርፎች አታላይነት ከመጠን ማለፉ ፍቅረ ንዋይ ሲጸናወተን እንጂ ሌላ ምን ሊሆን ይችላል? ቅዱስ ጳውሎስ “ገንዘብ መውደድ የክፋት ሁሉ ሥር ነው” በማለት እንደ ገለጸው ለገንዘብ ሲባል በየቤቱ፣ በየቢሮው፣ እና በተለያዩ ቦታዎች የክፉ ሥራ መበራከት የሰላም መጥፋት የአደባባይ ምስጢር አይደለምን? /1ኛ ጢሞ.6÷10/

ከውጪያዊ አካላት የሚመጡብንን የክርስትና ሕይወት እንቅፋቶች ለመዘርዘር ይህ አጭር ጽሑፍ በቂ አይሆንም፡፡ ነገር ግን ለአብነት ያህል አንዱን እንመልከት-

ሀ.   የሐሰት ክስ /ስም ማጥፋት/– ዲያብሎስ የታወቀው እና ሥራውን የጀመረው በሐሰት ንግግር መሆኑ ይታወቃል፡፡ በዓለመ መላእክት “እኔ ነኝ ፈጣሪ” ማለቱ እና አዳምና ሔዋንን በሐሰት ትምህርት ማጥመድ የሐሰት አባትነቱን አረጋግጦለታል፡፡ ጥንትም ሆነ ዛሬ በሐሰት አባትነቱን አረጋግጦለታል፡፡ ጥንትም ሆነ ዛሬ በሐሰት አንደበት የግብር ልጆቹ የሆኑ ሐሳዋውያን እውነተኞች በሐሰት ሲከስሱ እና ስማቸውን ሲያጠፉ ይገኛሉ፡፡ በእግዚአብሔር ቃል ጸንተው እውነትን ይዘው የሚታገሉትን ከሚገጥማቸው ፈተና አንዱ ከሐሰተኞች የሚሰነዘር ስም ማጥፋት ዘመቻ መሆኑ እየተለመደ መጥቷል፡፡ በመሠረቱ አይሁድ መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስን በሐሰት መክሰሳቸውን ያስተዋለ ክርስቲያን በዚህ ሊደነቅ አይገባውም፡፡ በዘመነ ብሉይ ሶስናን ብናስታውስ ያልፈጸመችውን እንደ ፈጸመችው አድርገው በሐሰት ከሰዋት ለፍርድ ያበቋት ረበናት ለጊዜው ስም ማጥፋቱ ቢሳካላቸውም እውነቱ ሲገለጥ ግን ውርደቱ እና ቅጣቱ በእነርሱ ላይ ሆኗል፡፡ ዛሬም በቤተ ክርስቲያን አገልግሎት የተጠመዱትን ከአባቶች እስከ ምእመናን በሚገኙ አገልጋዮች ላይ ስም ለማጥፋት የሚሯሯጡ ውሉደ ሐሰት ተበራክተዋል፡፡ ንስሐ ካልገቡ ፍጻሜያቸው እንደ ረበናቱ ይሆናል፡፡ ቅዱስ ጳውሎስ “በሌላ ትፈርድ ዘንድ ማነህ? … እርሱን እግዚአብሔር ሊያቆመው ይችላልና” /ሮሜ.14÷4/ በማለት እንዳስተማረው ሐሰተኞች የፈረዱባቸው ወገኖች አጥፍተው እንኳን ቢሆን ንስሐ ገብተው እንደሆነ ምን እናውቃለን? በውኑ የአገልግሎት ማኅበራትን አባቶችን የቤተ ክርስቲያን ሓላፊዎችን… ለማዋረድ በመሞከርስ የሚገኘው ጥቅም ምን ይሆን?

አንዳንድ ጊዜ የምንታማበት ነገር እውነት ከሆነም የታማው /የተተቸው/ አካል ልቡ ያውቃልና ራሱን ሊመረምር ይገባል፡፡ ሆኖም ግን ሐሰተኞች /ሰዳቢዎች/ ሊገነዘቡ የሚገባው ለሃይማኖት በመቅናት ከሆነ አገላለጹ ይህ እንዳልሆነ ተረድተው ይልቁንም ክርስቲያን ከባቴ አበሳ መሆን በፍቅር እና በቅርበት ስሕተተኞችን በምክርና በጸሎት በማገዝ ቢሆን የዓመፃ ሳይሆን የእውነት መሆኑ ግልጽ ይሆናል፡፡

ማጠቃለያ

የክርስትና ኑሮ አልጋ በአልጋ እንዳልሆነ ከልብ ከተረዳን እውነትን የያዘ ሁሉ ፈተና ሲገጥመው “መስቀሉን ይሸከም” የሚለውን ቃል ሊያስተውል ይገባል፡፡ የሚገጥመንንም መከራ በሚከተሉት ነጥቦች ድል መንሣት እንችላለን፡፡

1.   ትዕግሥት “ኢዮብ ታገሠ እግዚአብሔርም ሰማው” /ያዕ.5÷11/ ተብሎ እንደተጻፈ ትዕግሥት ይኑረን፡፡ የማይፈተን የተባረከ ነው አልተባለም፤ በፈተና የሚጸና እንጂ፡፡ በመሆኑም ከጌታችን እና እርሱን መስለው ከተገኙ ከቅዱሳን በመማር መስቀሉን በትዕግሥት ተሸክመን ልንጓዝ ይገባል፡፡ ቅዱሳን ሐዋርያትን መከራ አጽንተውባቸው በሸንጐ ሲያቆሟቸው በትዕግሥት ተቀበሉት፡፡ “በሸንጐ ፊት ስለተናቁ ደስ ብሏቸው ወጡ” እንደሚል መከራን በጸጋ ተቀበሉ /ሐዋ. 5÷41/፡፡

2.  ፍቅር– “ከክርስቶስ ፍቅር ማን ይለየናል? መከራ ወይስ ጭንቀት” /ሮሜ 8÷35/ እንደተባለ ፍቅር ያለው መከራን ይታገሣል /1ኛ ቆሮ.13÷7/፡፡ ሊያስፈራን የሚገባ ከእግዚአብሔር መለየት እንጂ፤ በእግዚአብሔር መንገድ ሆነን የሚገጥመን መከራ መሆን የለበትም፡፡ የክርስትና ሕይወትም ሆነ ፍቅረ እግዚአብሔር ዋና መገለጫው መከራ መቀበል መስቀሉን ተሸክሞ በፍቅር መኖር ነውና፡፡ በመሆኑም በትክክለኛ መንገድ ዓላማውን ተረድቶ የመጣ አገልጋይ አስፈሪ ነገሮች እንኳን ቢገጥሙት ወደኋላ አይሸሽም፤ ቅዱሳን ሁሉን ትተው እንደተከተሉት ፍቅረ እግዚአብሔር ራስን እስከ መስጠት ያደርሳልና /ማቴ.19÷19/፡፡

3.    ጽናት- እያንዳንዱ አገልግሎት የራሱ የሆነ ችግር አለው፡፡ ውጤቱም ጽናቱ ላይ ነው “እያንዳንዱ በራሱ ድካም መጠን የራሱን ደመወዝ ይቀበላል” የተባለው እንዲፈጸምልን ጽናት ወሳኝ ነው፡፡ “በሁሉ እንገፋለን እንጂ አንጨነቅም፤… እንሰደዳለን እንጂ አንጣልም…” ብሎ ቅዱስ ጳውሎስ እንደተናገረው ለአገልግሎት ያለንን ቁርጠኝነት በጽናት ልንገልጽ ይገባናል፡፡

በአጠቀላይ የክርስትና ሕይወት መከራው ብዙ ዋጋውም እጅግ ብዙ ነውና በትዕግስት፣ በፍቅር፣ በጽናት ሆነን እንትጋ በመከራ ጽናት መስለነው መስቀሉን ተሸክመን እስከሞት ከተጓዝን ክብርን ያቀዳጀናልና፡፡ በሁሉም ስለ ስሜ የተጠላችሁ ትሆናላችሁ እስከ መጨረሻ የሚጸና ግን እርሱ ይድናል እንደሚል /ማቴ.10÷22/፡፡

ምንጭ፡- ሐመር 18ኛ ዓመት ቁጥር 6 መስከረም 2003

ወስብሐት ለእግዚአብሔር