ሊቀ መላእክት ቅዱስ ዑራኤል

ዲያቆን ዮሐንስ ተመስገን
ሐምሌ ፳፤፳፻፲፭ ዓመተ ምሕረት

ዑራኤል ማለት “ብርሃነ እግዚአብሔር” ማለት ነው። “ዑራኤል ሥዩም ላዕለ ኵሎሙ ብርሃናት፤ ዑራኤል በብርሃናት ላይ ሁሉ የተሾመ ነው” እንዲሁም “ዑራኤል አሐዱ እመላእክት ቅዱሳን እስመ ዘረዓም ወዘረዓድ፤ ከቅዱሳን መላእክት አንዱ ዑራኤል በመብረቅና በነጎድጓድ የተሾመ ነው” እንዲል፡፡ (ሄኖክ ፮፥፪) ከሊቃነ መላእክት አንዱ መሆኑንና ፍርሃት ረዓድ ላለባቸው ረዳታቸው እንደሆነ የመላእክትን ነገር የተናገረ ሄኖክ ነግሮናል፡፡ “የእግዚአብሔር መልአክ በሚፈሩት ሰዎች ዙሪያ ይሠፍራል” በማለት ነቢዩ ዳዊት እንደተናገረ እግዚአብሔርን በሚፈሩና በሚያከብሩት ሰዎች ጭንቀት ጊዜ በመካከላቸው እየተገኘ ያጽናናቸዋል። (መዝ.፴፫፥፯) ምሥጢር ይገልጥላቸዋል፤ ከመከራ ሥጋ ከመከራ ነፍስ ይጠብቃቸዋል።

ቅዱስ ዑራኤል ምሥጢር ገላጭ ነው። ምሥጢር ማናገር የመንፈስ ቅዱስ ሥራ ቢሆንም የተሠወረውን መግለጥ፣ በአዲስ ቋንቋ ማናገር ለመላእክት የተሰጠ ጸጋቸው መሆኑም ግልጽ ነው። በዚህ ሀብትነትም የተወደደ ሥራ ለሚሠሩና እንዲያውቁ ለተፈቀደላቸው ሁሉ ቅዱስ ዑራኤል ምሥጢር ይገልጣል፤ ለዕዝራ ሱቱዔል የሆነለትም እንዲህ ነው።

መልአኩ ዑራኤል “አፍህን ክፈት፤ እኔም የማጠጣህን ጠጣ” … ብሎ አእምሮ ለብዎውን ገልጦለታል። (ዕዝ.ሱት. ፲፫፥፴፰) የዚህን ተአምር መታሰቢያ ሐምሌ ፳፪ በየዓመቱ ቤተ ክርስቲያናችን ታከብራለች። ለሄኖክም ምሥጢረ ሰማይንና ዕውቀትንም ሁሉ የገለጠለት እርሱ እንደሆነ በመጽሐፈ ሄኖክ ተጽፏል። (ሄኖክ ፳፰፥፲፫) አባ ጊዮርጊስ ዘጋስጫ ልቡናውን ያበራለት ይህ መልአክ እንደሆነ ገዳሙ ባሳተመው ገድሉ ላይ ተጽፏል። በዚህ አገልግሎቱም ሊቃውንቱ ከሣቴ ምሥጢር ይሉታል።

አፋቸውን ከፍተው የምስጋና ቃል ለሚናገሩ ሁሉ ክብርና ጥበቃን ከመላእክት እንደሚቀበሉ ከላይ በተመዘገበው የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል ለዕዝራ ሱቱዔል የተደረገለትን መረዳት ይገባል። ዕዝራ ለረጅም ወራት እግዚአብሔርን ደጅ ጸንቶ ነበር። የነገሩትን የማይረሳ እግዚአብሔር መልአኩን ላከለት፤ የሰማዩን ምሥጢርም ዐወቀ።

ይህ መልአክ እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ወደ ግብጽ ተራሮች በተሰደደች ጊዜ በመካከላቸው ሁኖ መንገድ ይመራቸው እንደነበር በድርሳነ ዑራኤል ተገልጿል። ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በቀራንዮ አደባባይ ደሙን በፈቃዱ ሲያፈስም በጽዋዕ የተቀበለው መልአክ እርሱ መሆኑን በዕለተ ዓርብ በሚነበበው ግብረ ሕማም ተጽፏል።

ሐምሌ ፳፪ ከሚታሰበው በዓሉ በተጨማሪም በሊቀ መላእክትነት የተሾመበትን በማሰብ ጥር ፳፪ ቀን፣ ከጌታችን የፈሰሰውን ደም በጽዋዕ የተቀበለበትን ቀን በማሰብ መጋቢት ፳፯ ቀን ይከበራል።

የሊቀ መላእክት ቅዱስ ዑራኤል አማላጅነትና ተራዳኢነት አይለየን፤ አሜን!