ሰባቱ ሊቃነ መላእክት

ክፍል አንድ

ሊቀ መላእክት ቅዱስ ሚካኤል

ዲያቆን ተስፋዬ ቻይ

ኅዳር ፱ ቀን ፳፻፲፭ ዓመተ ምሕረት

ውድ የእግዚአብሔር ልጆች! እንዴት አላችሁ? ትምህርት እንዴት ነው? እየበረታችሁ ነውን? የሩብ ዓመት የምዘና ፈተናስ እንዴት ነው? መቼም ትምህርቱን በትኩረት ከተከታተላችሁ የምዘና ጥያቄዎችን እንደምትሠሩት ጥርጥር የለውም! በተለይ ልጆች መምህራን የሚነግሯችሁን በትኩረት በማዳመጥ፣ መጻሕፍትን በማንበብና ያልገባችሁን በመጠየቅ ጥሩ ውጤት ማስመዝገብ አለባችሁ፡፡ መልካም! ውድ የእግአብሔር ልጆች ለዛሬ ምንማረው ከሰባቱ ሊቃነ መላእክት መካከል አንዱ ስለሆነው ስለ ቅዱስ ሚካኤል ነው፡፡

ውድ የእግዚአብሔር ልጆች! አምላካችን እግዚአብሔር በዕለተ እሑድ ቅዱሳን መላእክትን ፈጥሯቸዋል፤ እነርሱም እግዚአብሔርን የሚያመሰግኑና እኛንም የሚጠብቁ ናቸው፤ ነቢዩ ንጉሥ ዳዊት በመዝሙሩ ‹‹የእግዚአብሔር መላእክት በሚፈሩት ሰዎች ዙሪያ ይሰፍራሉ፤ ያድናቸውማል››  በማለት እንደ ገለጸልን  ቅዱሳን መላእክት እኛን ከክፉ ነገር ይጠብቁናል፡፡ (መዝ.፴፬፥፯)

ውድ እግዚአብሔር ልጆች! ታዲያ እኛ የእነርሱን ጥበቃና ርዳታ ስንፈልግ እግዚአብሔርን  እንድንፈጽመው ያዘዘንን ትእዛዝ ስንፈጽምና  ጥሩ ሥነ ምግባራት ሲኖረን ነው፡፡ ልጆች! መላእክት በተፈጥሮ ብዙ ቢሆኑም የመላእክት አለቃ የሚባሉ ግን ሰባት ናቸው፤ ከእነዚህም የመላእክት ሁሉ አለቃ አንዱ ቅዱስ ሚካኤል ነው፤ ሚካኤል ማለት ‹‹ማን እንደ እግዚአብሔር›› ማለት ሲሆን ከእግዚአብሔር ተልኮ ሰዎችን በችግራቸው የሚረዳና ፈጣሪውንም የሚያመሰግን መልአክ ነው፡፡

ውድ የእግአብሔር ልጆች ! ቅዱስ ሚካኤል በመጽሐፍ ቅዱስ እንዲሁም በድርሳነ ቅዱስ ሚካኤል እንደተጻፈልን ለችግራቸው ደርሶ የልባቸውን የፈጸመላቸው፣ ከመከራ ያዳናቸው፣ ከሰይጣን ተንኮል የታደጋቸው ብዙ ሰዎች ናቸው፡፡ ሁል ጊዜ በየወሩ በ፲፪ (ዐሥራ ሁለት) ቀን መታሰቢያ በዓሉን እንዘክራለን፤ በዓመት ውስጥ ኅዳርና ሰኔ ወር ላይ ደግሞ ዓመታዊ ክብረ በዓሉ ይዘከራል፡፡

ውድ የእግዚአብሔር ልጆች! ታሪኩ ብዙ ቢሆንም በኅዳር ፲፪ ቀን የሚከበርበትን በመጠኑ እንነገራችኋለንና አጽንዖት (ትኩረት) ሰጥታችሁ ተከታተሉን፡፡ መልካም! ኅዳር ፲፪ ቀን ቅዱስ ሚካኤል የመላእክት ሁሉ አለቃ አድርጎ እግዚአብሔር የሾመበት ቀን ነው፤ ሌላው ደግሞ ልጆች እስራኤላውያንን ከፈርኦን ሠራዊት የታደገበት በዓል ነው፤ እስራኤላውያን ከግብጽ አገር በስደት (በመከራ) ከነበሩበት እግዚአብሔር ሲያወጣቸው ሊቀ ነቢያት ሙሴን መርጦት ሕዝቡን እየመራ ከግብጽ ወደ ከነዓን ወደ ተባለች አገራቸው ይመራቸው ጀመር፡፡ ይገርማችኋል ልጆች! ፈርዖን የተባለው የግብጽ ንጉሥ ሕዝቡን ሊይዛቸው ብዙ ሠራዊት (ወታደር) አስከትሎ ከኋላቸው ሲከተላቸው እስራኤላውያን ለማምለጥ ወደ ፊት ሲሄዱ ሊቀ መላእክት ቅዱስ ሚካኤል ከፊታቸው እየመራ መልካሙን መንገድ ያሳያቸው ነበር፡፡ እንደገናም መንገዱ በረሃ ነበርና ፀሐይ እንዳይነካቸው በደመና እየጋረደ ማታ ደግሞ ሲሆን እንዲታያቸው ብርሃን (ፋና) እያበራላቸው ይጓዙ ነበር፡፡

አያችሁ ልጆች! ለዚህ እኮ ነው ነቢዩ ዳዊት ‹‹ይጠብቁህ ዘንድ መላእክቱን ስለ አንተ ያዝዛቸዋልና››  ያለው መልካም ከሆንንና የእግዚአብሔርን ትእዛዝ ከጠበቅን ክፉ ነገር እንዳይነካንና መንገዳችን እንዲቀና እግዚአብሔር ቅዱሳን መላእክቱን ይልክልናል፡፡ (መዝ.፺፥፲፩) ታዲያ አንድ ጊዜ እስራኤላውያንን ያሳድድ የነበረው ፈርኦን ከኋላ ሲከተላቸው እነርሱም ወደ ፊት ሲሄዱ በጣም ትልቅ ባሕር አጋጠመቸው፡፡ ልጆች! ሕዝቡ ከኋላቸው ፈርኦን ነበር፤ ከፊታቸው ደግሞ ትልቅ ባሕር ነበር፡፡ የዚህን ጊዜ በጣም ተጨነቁ፤ ፈሩም፤ ወዴት እንደሚሄዱ አማራጭ አጡ፡፡

ከዚያም ይመራቸው የነበረው ሊቀ ነቢያት ሙሴ ወደ እግዚአብሔር ጸለየ፤ እግዚአብሔርም እንዲረዳቸው ቅዱስ ሚካኤልን ላከላቸው፡፡ ከዚያም ነቢዩ ሙሴ በበትሩ ባሕሩን ሲነካው ያ ትልቁ ባሕር ሁለት ቦታ ክፍል አለ፡፡ ይገርማችኋል ልጆች! ውኃው እንደ ግድግዳ ቀጥ ብሎ ቆመ፤ ከዚያም ቅዱስ ሚካኤል እየመራቸው ለሁለት በተከፈለው ባሕር መካከል ሕዝቡ ተሻገሩ፡፡

ልጆች! እግዚአብሔር ሁሉን ማድረግ የሚቻለው አምላካችንና ፈጣሪያችን ነው፡፡ ባሕሩን በቅዱስ ሚካኤል አማካኝነት ደረቅ አደረገላቸውና በውስጡ አልፈው ሄዱ፤ ይገርማችኋል! ያሳድዳቸው የነበረው ፈርኦን ተከትላቸው፤ ለሁለት ተከፍሎ እንደግድግዳ (ግንብ) በቆመው ባሕር ውስጥ ሠራዊቱን (ወታደሩን) አስከትሎ  ገባ፡፡ ከዚያም ሕዝቡ ሁሉ ባሕሩን አቋርጠው እንደጨረሱ የፈርኦን ሠራዊቶች ከመካከል ሲገቡ ሊቀ ነቢያት ሙሴ ባሕሩን በበትሩ ነካው፤ በዚያን ጊዜ መልአኩ ቅዱስ ሚካኤል ያንን ባሕር ወደ ቦታው እንዲመለስ ሲያደርገው እንደ ግንብ የነበረው ውኃ ፈሰሰ፤ ከዚያም ፈርኦንና ሠራዊቱ በባሕር ውስጥ ሰጠሙ፡፡

ውድ የእግዚአብሔር ልጆች! በመጀመሪያ እግዚአብሔር ፈርኦንን ሊያስተምረው ብዙ ተአምራትን እያደረገ አሳይቶት ነበር፡፡ ፈርኦን ግን ሳያምን ስለቀረና በትእቢቱ የተነሣ እምቢ በማለቱ በመጨረሻም በኤርትራ ባሕር ሰጠመ፡፡ ሕዝቡም ጠላቶቻቸውን ለቀጣላቸውና እነርሱንም ከመከራ ላዳናቸው አግዚአብሔር ‹‹እግዚአብሔርን እናመስግነው፤ምስጉን ነው የተመሰገነ…›› እያሉ ዘመሩ፡፡

ውድ የእግዚአብሔር ልጆች! እግዚአብሔርን የታመነ መከራ ቢገጥመውም ቅዱሳን መላእክቱን ልኮ ያድነዋል፤ እስራኤላውያን በእግዚአብሔር ታምነው ስለነበር በችግራቸው ጊዜ ቅዱስ ሚካኤልን ላከላቸው፡፡ መልአኩ በመንገዳቸው እየመራና የሚያስፈለጋቸውን እያደረገ ጠላቶቻቸውን በመቅጣት ጭንቀታቸውን አራቀላቸው፤ ከመከራ ታደጋቸው፡፡

ውድ የእግዚአብሔር ልጆች! ከእስራኤላውያን ታሪክ ምን እንማራለን እግዚአብሔርን የሚያምን በመከራው ጊዜ ቅዱሳን መላእክት እንደሚላኩላት፣ ሕጉንና ትእዛዙን ማክበር እንዳለብን፣ ቅዱሳን መላእክትን በችግራችን ጊዜ ስንጠራቸው ፈጥነው እንደሚያድኑን ተምረናል፡፡ ሌላው ደግሞ ልጆች! የሚነገረውን የማይሰማና ከጥፋቱ የማይመለስ መጨረሻው መጥፋ እንደሆነ አይተናል፡፡  ፈርኦን የተባለው ጨካኝ ንጉሥ የእግዚአብሔርን ልጆች መከራ ሲያሳያቸው እግዚአብሔር ተአምራት አድርጎ ከጥፋቱ እንዲመለስ ነገረው፤ እርሱ ግን አልመለስም አለ፤ በመጨረሻም በባሕር ውስጥ ሰጠመ፡፡

ልጆች! አመጸኛና ተው የሚሉትን የማይሰማ መጨረሻው ጥፋት ነው፡፡ ታላላቆቻችንን የሚነግሩንን መስማትና ከጥፋት እንድንመለስ ሲመክሩን መመለስ አለብን፡፡ ፈርኦን ተው ሲባል እምቢ አለ፤ ግን በመጨረሻ ተቀጣ።

ውድ የእግዚአብሔር ልጆች! ለዛሬ ከሰባቱ ሊቃነ መላእክት መካከል አንዱ ስለ ሆነው ስለ ሊቀ መላእክት ቅዱስ ሚካኤል ካደረጋቸው ብዙ ድንቅ ተአምራቶቹ በኅዳር ፲፪ ቀን የሚታሰበውን ብቻ በጥቂቱ ነግረናችኋል፡፡ በቀጣይ ደግሞ የሌሎቹን ሊቃነ መላእክት ታሪክ እንነግራችኋለን፤ ይቆየን! ደኅና ሁኑ ልጆች!

ስብሐት ለእግዚአብሔር

ወለወላዲቱ ድንግል

ወለመስቀሉ ክቡር አሜን!!!