‹‹ለነገ አትጨነቁ፤ ነገ ለራስዋ ታስባለችና›› (ማቴ.፮፥፴፬)

ዲያቆን ያሬድ ጋሻው

መስከረም ፳፮ ቀን ፳፻፲፬ ዓ.ም

ጭንቀት እንደ የማኅበረሰቡ አኗኗርና የኑሮ ፍልስፍና የሚሰጠው ትርጉም ከቦታ ቦታና ከሰው ሰው ይለያያል። የሕዝቦቻቸው መሠረታዊ ፍላጎቶች ባልተሟሉባቸው አንዳንድ ሀገራት ምጣኔ-ሀብታዊ አለመረጋጋት በብዛት የሚስተዋል የጭንቀት መንሥኤ ነው። በአንጻሩ ብዙዎቹ ዜጎቻቸው የቅንጦት ሕይወት በሚመሩባቸው ‹ሥልጡን› ሀገራት ደግሞ፥ ደስታ ይገኝባቸዋል ተብለው የሚጀምሩ የዝሙት፣ የሱስ፣ የዘፈን… የመሳሰሉት እኩይ ተግባራት ከጊዜያት በኋላ እግዚአብሔርን ፍለጋ በሚቃትተውና እውነተኛ ደስታ ምን ማለት እንደሆነ አንጠርጥሮ በሚያውቀው ውሳጣዊ ኅሊናቸው ዕረፍት የለሽ ሙግት የተነሣ ደስታ ሰጪነታቸው አብቅቶ መዳረሻቸው ጭንቀት ይሆናል። በጣም የሚያሳዝነው ደግሞ ለዚህ ኅሊናዊ ምሪት የሚሰጡት መልስ በአብዛኛው አሁንም ተቃራኒውን መሆኑ ነው። ‹‹ለምንድነው የምኖረው?›› ለሚለው ጥያቄያቸው መልሳቸው ‹‹ለምንም!›› የሚል ይሆንና የሕይወታቸውን ፍጻሜ ያበላሸዋል።

ምን ያስጨንቃችኋል? የምትበሉትና የምትጠጡት፤ የምትለብሱትስ የላችሁምን?
ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በወንጌል ‹‹ስለዚህ እላችኋለሁ፥ ስለ ነፍሳችሁ በምትበሉትና በምትጠጡት፥ ወይም ስለ ሰውነታችሁ በምትለብሱት አትጨነቁ፤ ነፍስ ከመብል ሰውነትም ከልብስ አይበልጥምን?›› በማለት አስተምሯል፡፡ በእርግጥም አምላካችን የነገረን ይህንን ነው። ሰው ምን እበላለሁ? ምን እጠጣለሁ? ይል ዘንድ አይገባውም። ‹‹ወደ ሰማይ ወፎች ተመልከቱ፤ አይዘሩም፤ አያጭዱምም፤ በጎተራም አይከቱም፥ የሰማዩ አባታችሁ ይመግባቸዋል። እናንተ ከእነርሱ አትበልጡምን?!›› እንዲል፤ (ማቴ.፮፥፳፭-፳፮)

ፈጣሬ ዓለማት እግዚአብሔር፥ መጋቤ ፍጥረታትም እንደሆነ ለምናምን ለእኛ ለክርስቲያኖች፥ መብል መጠጥ የሚያስጨንቅ ጉዳይ አይደለም። ይህ ማለት ግን ከእኛ የሚጠበቅ ድርሻ የለም ማለት አይደለም። የገበሬውን ድርሻ እንወጣለን፥ እግዚአብሔር ደግሞ የአምላክነቱን ድርሻ ይወጣል። መሬቱን ማረስና ማለስለስ፤ ዘሩንም በእምነት ወደ ምድር ልብ መዝራት የእኛ የገበሬዎቹ ድርሻ ነው። ‹‹በዝናብ አብቅሎ በፀሐይ አብስሎ›› ምግባችንን መስጠት ደግሞ የእግዚአብሔር ድርሻ ነው። አምስት እንጀራና ሁለት ዓሣ ማቅረብ የእኛ የተመጋቢዎቹ ድርሻ ነው። ይህንን አበርክቶ እኛን ማጥገብ ደግሞ የመጋቢው የእግዚአብሔር ድርሻ ነው።… ስለዚህ አትጨነቁ። ‹‹ስለ ልብስስ ስለምን ትጨነቃላችሁ? የሜዳ አበቦች እንዴት እንዲያድጉ ልብ አድርጋችሁ ተመልከቱ፥ አይደክሙም አይፈትሉምም፤ ነገር ግን እላችኋለሁ፥ ሰሎሞንስ እንኳ በክብሩ ሁሉ ከእነዚህ እንደ አንዱ አልለበሰም።›› አባታችን አዳም ሕግ ተላልፎ የጸጋ ልብሱ በተገፈፈ ጊዜ ነበር ራቁትነት ተሰምቶት ቅጠል ያገለደመው። ሰውነቱም አሳፍሮት በገነት ዛፎች መካከል የተደበቀው። ዛሬም ከጸጋ እግዚአብሔር ስንርቅ በልተን አንጠግብም፤ ጠጥተን አንረካም፤ ለብሰን አንደምቅም። ስለዚህ ጸጋ እግዚአብሔርን ለማግኘት እንትጋ። ‹‹እለ ይዘርዑ በአንብዕ ወበሐሤት የአርሩ፤ በልቅሶ የሚዘሩ፥ በደስታ ይሰበስባሉ›› እንዲል፤(ማቴ.፮፥፳፰-፳፱፣መዝ. ፻፳፭፥፭)

በጸጋ እግዚአብሔር ደስ እንሰኝ ዘንድ ጸጋ ማግኛውን መንገድ አንሰቀቀው። አንዳንዴ እኒህ ሁሉ ነገሮች ተሰጥተውንም እንጨነቃለን። ‹‹ምሳሌም ነገራቸው እንዲህ ሲል፦አንድ ባለጠጋ ሰው እርሻው እጅግ ፍሬያማ ሆነችለት። እርሱም፦ፍሬዬን የማከማችበት ሥፍራ አጥቻለሁና ምን ላድርግ? ብሎ በልቡ ዐሰበ። እንዲህ አደርጋለሁ፤ ጎተራዬን አፍርሼ ሌላ የሚበልጥ እሠራለኹ፥ በዚያም ፍሬዬንና በረከቴን ሁሉ አከማቻለሁ። ነፍሴንም፦አንቺ ነፍሴ፥ ለብዙ ዘመን የሚቀር ብዙ በረከት አለሽ ዕረፊ፥ ብዪ፥ ጠጪ፥ ደስ ይበልሽ እላታለሁ አለ። እግዚአብሔር ግን፦አንተ ሰነፍ፥ በዚች ሌሊት ነፍስህን ከአንተ ሊወስዷት ይፈልጓታል፤ ይህስ የሰበሰብኸው ለማን ይሆናል? አለው። ለራሱ ገንዘብ የሚያከማች፥ በእግዚአብሔር ዘንድም ባለጠጋ ያልሆነ እንዲህ ነው።›› ይህ ሰው ባለጠግነቱ በራሱ ባልጎዳው ነበር። ነገር ግን ድሆችን ሳያስብ ስለገዛ ራሱ መብልና መጠጥ ሲጨነቅ በሞት ተቀድሟል። እርሻው እንዲሰምርለት የረዳውን እግዚአብሔርን ስላላከበረ በእጅጉ ተጎድቷል።… ስለዚህ አትጨነቁ። (ሉቃ.፲፮፥፲፮-፳፩)

✟ ለምን መኖር እንዳለባችሁ አላወቃችሁም?
በዚህ ምድር የምንወጣው የምንወርደው በሰማያት ለማረፍ ነው። የእግዚአብሔርን አርአያና አምሳል ይዘን ስለተፈጠርን ዘለዓለማዊነት በውስጣችን አለ። ስለዚህ በዚህ የምንፈተነው ለዘለዓለማዊ ክብር እንጂ ለዘለዓለማዊ ፍዳ እንዳንሆን ነው። ይህ ምድር ጥንቱንም ርስትነቱ የእኛ የሰው ልጆች አልነበረም። የእኛ ርስታችን ገነት ናት። በዚህ ያለነው በእንግድነት ነው። ‹‹እነሆ፥ እኛ በሕይወት የምንኖርበት ዘመናችን ግን ይህ ነው፦ ሰው ብዙ ዘመን ኖረ ቢባል ሰባ ዘመን ነው፤ እጅግም ቢበዛ ሰማንያ ዘመን ነው።›› ስለዚህ አትጨነቁ። (ኩፋሌ ፲፯፥፲፭)

✟ እግዚአብሔርን ፈልጋችሁ አጣችሁትን?
ልበ አምላክ ቅዱስ ዳዊት፦ ‹‹ከመንፈስህ ወዴት እሄዳለሁ? ከፊትህስ ወዴት እሸሻለሁ? ወደ ሰማይ ብወጣ፥ አንተ በዚያ አለህ። ወደ ሲኦልም ብወርድ፥ በዚያ አለህ። እንደ ንስር የንጋትን ክንፍ ብወስድ፥ እስከ ባሕር መጨረሻም ብበር፥ በዚያ እጅህ ትመራኛለች፥ ቀኝህም ትይዘኛለች።…›› ሲል አድንቋል። እኛም ይህንን እናደንቃለን። እርሱ የሌለበት ከቶ የት ነው? ‹‹ሰማይን የፈጠረ እርሱ ነው፥ ምድርንም የፈጠረ እርሱ ነው። ለመለኮቱ ጥንት የለውም። ላይ የለውም ታችም የለውም። ርዝመት የለውም፥ ቁመት የለውም። ቀኝ የለውም፥ ግራም የለውም፥ መካከል የለውም፥ በዓለም ዳርቻ ሁሉ የመላ ነው እንጂ፤ ከመላእክት ሁሉ ኅሊና የተሠወረ ነው፤ ባሕርዩን የሚያውቀው የለም፤ በእጁ የፈጠረውንም የሚቆጥረው የለም።›› (መዝ. ፻፴፰፥፯-፲፣ ቅዱስ ጎርጎርዮስ ዘኑሲስ)

እግዚአብሔር በክብሩ ከፍጥረታት ኅሊና እጅግ የራቀ ነው። አስቦና ተጨንቆ የሚደርስበትም የለም። ነገር ግን እግዚአብሔር በሥራውና በፍቅሩ ለሰው ልጆች ሁሉ ቅርብ ነው። እርግጥ ነው፤ የልቡቻችንን ደጃፎች ለእርሱ ለመክፈት በዘገየን ጊዜ እግዚአብሔር በረድኤት ይርቀናል። ነገር ግን ከመኝታችን ተነሥተን በትጋትና በፍቅር እንፈልገው እንጂ አንጨነቅ። እስኪ ለአፍታ ያህል የጠቢቡን መዝሙር እናሰላስል?! ‹‹ሌሊት በምንጣፌ ላይ፥ ነፍሴ የወደደችውን ፈለግሁት። ፈለግሁት አላገኘሁትም። እነሣለሁ በከተማይቱም እዞራለሁ፥ ነፍሴ የወደደችውን በጎዳናና በአደባባይ እፈልጋለሁ፤ ፈለግሁት አላገኘሁትም። ከተማይቱን የሚዞሩት ጠባቂዎች አገኙኝ፤ ነፍሴ የወደደችውን አያችሁትን? አልኋቸውም። ከእነርሱም ጥቂት እልፍ ብዬ ነፍሴ የወደደችውን አገኘሁት፤ ያዝሁትም፤ ወደ እናቴም ቤት ወደ ወላጅ እናቴም ዕልፍኝ እስካገባው ድረስ አልተውሁትም።›› እንዲል፤ ጩኸን መልስ ያላገኘንበት፤ ፈልገን ያጣንበት ጊዜ ይኖራል፥ ግን ፍለጋችንን እንቀጥል፤ ከተማ ጠባቂዎችንም (መምህራንን) እንጠይቃቸው። አድራሻውን በእርግጥም ያውቁታል።… በመጨረሻም እግዚአብሔርን እናገኘዋለን። ከሩቅ ሳይኾን በቅርባችን፥ ከውጭ ሳይሆን በውስጣችን እናገኘዋለን። ከእርሱም ጋር በፍቅር ተጣብቀን እንኖራለን።… ስለዚህ አትጨነቁ። (መሓ.፫፥፩-፬)

አንድ አምላክ ለሆነ ለአብ ለወልድ ለመንፈስ ቅዱስ ምስጋና ይሁን፤ አሜን!!