‹‹ለታመሙት መድኃኒት አንተ ነህ›› (የዐርብ ሊጦን)

መድኃኒት ለሰው ልጅ ፈውስ መሆኑን እንረዳ ዘንድ ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ  በሥጋ በተገለጠበት ማለትም በዘመነ ሥጋዌው አስተምሯል፡፡ በዚያን ጊዜም ብዙዎች ወደ እርሱ እየቀረቡ ማንነቱን ለማወቅ ይጥሩ እና ትምህርቱንም ይሰሙ ነበር፡፡ እርሱም በመካከላቸው ሆኖ ወንጌልን ይሰበክላቸው፤ የታመሙትንም ይፈውሳቸው፤ የእጆቹን ተአምራት ዓይተውም ሆነ ሰምተው ያመኑትንም ያድናቸው ነበር፡፡ ‹‹ለታመሙት መድኃኒት አንተ ነህ›› እንደተባለው ፈውሰ ሥጋ እርሱ ኢየሱስ ክርስቶስ እንደሆነም ተረዱ፡፡ (የዐርብ ሊጦን)

ጌታችን ወደ ቅፍርናሆም በገባ ጊዜ ልጁን እንዲያድንለት የጠየቀውን የመቶ አለቃውን ታሪክ መጥቀስ ለዚህ ምሳሌ ነው፡፡ እርሱም ወደ ጌታችን መጥቶ ‹‹አቤቱ ልጄ ሽባ ሆኖ እጅግ እየተጨነቀ በቤት ተኝቷል›› ብሎ ለመነው፡፡ ጌታችንም እኔ መጥቼ እፈውሰዋለሁ›› አለው፡፡ የመቶ አለቃውም ‹‹አቤቱ አንተ ከቤቴ ጣራ በታች ልትገባ አይገባኝም፡፡ ነገር ግን በቃልህ እዘዝ ልጄም ይድናል›› አለ፡፡ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስም የመቶ አለቃውን እምነት በማድነቅ እውነት እላችኋለሁ፣ በእስራኤል ሁሉ እንዲህ ያለ እምነት አላገኘሁም›› ብሎም መሰከረለት፡፡ ከዚያም ‹‹እንደ እምነትህ ይሁን›› አለው፤ በዚያችም ሰዓት ልጁ ዳነ፡፡  እምነት ኃይልን ታደርጋለችና ጌታችን በተቀደሱ እጁ እንኳን ሳይዳስሰው ልጁ በቃሉ ብቻ ተፈወሰ፡፡ (ማቴ.፰፤፭-፲፫)

አንድ ለምጻም ሰውም ወደ ጌታችን ቀርቦ ‹‹ጌታ ሆይ ብትወድስ ልታነጻኝ ይቻልሃልን›› ብሎ ቢጠይቀው እጁን ዘርግቶ ዳሰሰው፤ ቀጥሎም ‹‹እወዳለሁ ንጻ›› ብሎም ፈወሰው፤ ጌታችን ወደ ቅዱስ ጴጥሮስ ቤት በገባ ጊዜም አማቱን  በንዳድ ታማ ተኝታ አገኛት፤ እጇንም ይዞ በዳሰሳት ጊዜ ከደዌዋ ሁሉ ተፈውሳለች፡፡ (ማቴ.፰፥፪፤፲፬)

‹‹የእግዚአብሔር መንፈስ በውኃው ላይ ሰፍፎ ነበር›› ተብሎ እንደተጻፈ ጸበል የእግዚአብሔር መንፈስ ያደረበት በመሆኑ ብዙዎች ይፈወሱበታል፤ ከርኲስ መንፈስ፣ ከክፉ ደዌ እና ከበሽታ ሁሉ የሚዳንበት ነው። (ዘፍ. ፭፥፫)

በዮሐንስ ወንጌል እንደተጻፈውም ‹‹በኢየሩሳሌም በበጎች በር አጠገብ በዕብራይስጥ ቤተ ሳይዳ የምትባል አንዲት መጠመቂያ ነበረች፤ አምስትም መመላለሻ ነበረባት፡፡ በእነዚህ መጠመቂያዎችም ውስጥ የውኃውን መንቀሳቀስ እየጠበቁ በሽተኞችና ዕውሮች አንካሶችም ሰውነታቸውም የሰለለ ብዙ ሕዝብ ይተኙ ነበር፡፡ አንዳንድ ጊዜ የጌታ መልአክ ወደ መጠመቂያ ወርዶ ውኃውን ያናውጥ ነበርና እንግዲህ ከውኃው መናወጥ በኋላ በመጀመሪያ የገባ ከማናቸውም ካለበት ደዌ ጤናማ ይሆን ነበር፡፡›› (ዮሐ. ፭፥፪-፬)

ምእመናን በጸበል ይድኑ ዘንድ ሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያን ውኃውን የሚቀደሱበትን ሥርዓት ይፈጽማሉ፤ በዘመናችን ብዙዎች ከተያዙበት ደዌ ወይም በሽታ በጸበል ሲድኑ ዓይተናል ሰምተናልም፡፡ ለሕክምና ሆስፒታል ሄደው መዳን እንደማይችሉ ከተነገራቸው በኋላ ወደ ቅድስት ቤተ ክስቲያንና ገዳማት በመሄድ በጠበል ተጠምቀው ተፈውሰዋል፡፡ ዳግም ሲመረመሩም ፈውስ የሌላቸው ከሚባሉ በሽታዎች እንኳን ሳይቀር ነፃ መሆናቸው ተነግሯቸዋል፡፡ ከኤች አይ ቪ ኤድስ፤ ከካንሰር እና ከሌሎች መድኃኒት የለሽ በሽዎች የዳኑ ሰዎች በተለያዩ ጊዜ ምስክነታቸውን ሰጥተዋል፡፡ የእነርሱን ታሪክ እንደሰማነው እኛም በእምነት ሆነን በጸበሉ ከተጠመቅን በምድር ካለውና በምድር የሕክምና ጠበብቶች መድኃኒት ወይም ፈውስ የለሽ ከተባለለት ማንኛውም ደዌ፣ በሽታ ወይም ወረርሽኝ እንደሚያድነን የእግዚአብሔር ቃል የታመነ ነው፡፡ ምክንያቱም ‹‹እምነትህ አዳነችህ›› ተብሎ እንደተጻፈ የሚያድነን አዳኝነት በአምላካችን ላይ ያለን  ፍጹም እምነት ነውና፡፡ ከዚህ በተጨማሪም  የእግዚአብሔር ባለሟሎች የሆኑት ጻድቃን ሰማዕታት ሁሉም በተሰጣቸው የሰው ልጆችን የመጠበቅ የማማለድና የመፈወስ ቃል ኪዳንም በመታመን ከማንኛውም ደዌ ሥጋ ወይም በሽታ እንደምንፈወስም እምነት ሊኖረን ይገባል፤ በዚህም የማዳን( የመፈወስ) ቃል ኪዳን እንፈወሳለንና፡፡  (ሉቃ.፲፯፥፲፱)

በዚህ ጊዜ ለመጣብን መቅሠፍት መድኃኒት ላልተገኘለት የኮሮና በሽታም መድኃኒቱ በእምነት ሆኖ በጸበል መጠመቅ ነው፡፡ ሆኖም ለራስ ምታት እና ለትንሽ የቁርጥማት ሕመም መድኃኒት መውሰድ የለመደ ሕዝብ ጸበል ያድናል ብሎ ለማመን ያስቸግራል፤ አይደለም እንዲህ ዓይነት ገዳይ በሽታ ተስፋፍቶ ይቅርና ትንሽ ሕመም ሲይዘን እንኳን ወደ ሆስፒታል እንሮጣለን፡፡ ይህም በሳይንሳዊ ሕክምና እንድንመካ አድርጎናል፤ ትኩረታችንም ቴክኖሎጂ ባፈራቸው ሕክምናዎች ብቻ ሆኗል፡፡

ነገር ግን አሁን ባለንበት ዘመንም ሰዎች በተደረገላቸው ተአምር እየዳኑ የእርሱ ምስክሮች እንደሆኑ እየሰማን በጸበል ልናምን ይገባል፤ በተለይም ወደ ተለያዩ ገዳማት ብንሄድ በጸበል የተደረጉ ድንቅ ድንቅ ተአምራትን እናያለን፡፡

ጸበልተኞቹም በመጠመቃቸው ከያዛቸው ክፉ ደዌና ርኲስ መንፈስ በመዳናቸው ምስክርነትን ሲሰጡ እንሰማለን፡፡

የታመምን ሰዎችም  ከዚህ ክፉ በሽታ መዳን እንደምንችል አምነን እንጠመቅ፡፡ ፈውሰ ሥጋን የሚሰጥ አምላክ እርሱ ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ነውና እርሱ ፈጽሞ ያድነናል፤ አሜን፡፡