‹‹ለተቀበሉት ሁሉ ግን÷ በስሙ ለሚያምኑት ለእነርሱ የእግዚአብሔር ልጆች ይሆኑ ዘንድ ሥልጣንን ሰጣቸው›› (ዮሐ. ፩፥፲፪)

ዲያቆን ዮሴፍ ከተማ

ሰዎች ከአምላክ ድኅነትን ያገኙ ዘንድ አንድም የሥለሴ ልጅነትን በምሥጢረ ጥምቀት ሊቀበሉና የእግዚአብሔርን ልጅነት ማግኘት ያስፈልጋቸዋል፡፡ ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ስለዚህ ምሥጢር ኒቆዲሞስን ባስተማረበት በዮሐንስ ወንጌል ጀምሮ ስናነብ እንዲህ ብሏል ‹‹እውነት እውነት እልሃለሁ ሰው ከውኃና ከመንፈስ ቅዱስ ካልተወለደ በቀር ወደ እግዚአብሔር መንግሥት ሊገባ አይችልም፡፡ ከሥጋ የተወለደ ሥጋ ነው፤ ከመንፈስም የተወለደ መንፈስ ነው፤ ዳግመኛ ልትወለዱ ያስፈልጋችኋል ስላልሁ አታድንቅ፡፡›› (ዮሐ. ፫፥ ፭)

የክርስትናን ጥምቀት ስንጠመቅ የእግዚአብሔር ልጀነትን እናገኛለን፡፡ ይህም ልጅነት በራሱ የሰው ልጅ ከመጀመርያው የነበረው፣ በውድቀትም ያጣው፣ በክርስቶስ መምጣትም መልሶ ያገኘው፣ እስከዘለዓለሙም ገንዘቡ አድርጎት የሚኖረው ማንነቱ ነው፡፡

ይህንንም ቅዱስ ዮሐንስ በወንጌሉ ‹‹ለተቀበሉት ሁሉ ግን በስሙ ለሚያምኑት ለእነርሱ የእግዚአብሔር ልጆች ይሆኑ ዘንድ ሥልጣንን ሰጣቸው፤ እነርሱም ከእግዚአብሔር ተወለዱ እንጂ ከደም ወይም ከሥጋ ፈቃድ ወይም ከሰው ፈቃድ አልተወለዱም›› በማለት አስረተድቷል፡፡ (ዮሐ. ፩፥፲፪-፲፫)

ቅዱስ ጳውሎስም ስለዚህ ምሥጢር ሲናገር አንዲህ ይላል ‹‹በእምነት በኩል ሁላችሁ በኢየሱስ ክርስቶስ  የእግዚአብሔር ልጆች ናችሁ›› ካለ በኋላ ይህም እንዴት ሊሆን አንደቻለ ጌታችን በዮሐንስ ወንጌል ያስተማረውን በማያያዝ፤ ‹‹ከክርስቶስ ጋራ አንድ ትሆኑ ዘንድ የተጠመቃችሁ ሁሉ ክርስቶስን ለብሳችኋልና›› ብሏል፡፡ በዚህም ከሥጋዊ ማንነት ወደ መንፈሳዊ ማንነት፣ ማደጋችንን የበለጠ ሲያጠይቅ ደግሞ ‹‹ከክርስቶስ ጋራ አንድ ትሆኑ ዘንድ የተጠመቃችሁ ሁላችሁ ክርስቶስን ለብሳችኋልና፤ አይሁዳዊ ወይም የግሪክ ሰው የለም፤ ባሪያ ወይም ጌታ የለም፣ ወንድ ወይም ሴት የለም ሁላችሁ በክርስቶስ ኢየሱስ አንድ ሰው ናችሁና፡፡›› (ገላ. ፫፥፳፮-፳፰)

ሁላችን የእግዚአብሔር ልጆች ስንሆን፣ ጊዜያዊው ሥጋዊ ማንነት ሳይለየን ሁላችን መንፈሳውያን፣ በመንፈስ ቅዱስም እንደ አንድ ሰው የምንቆጠር የእግዚአብሔር ልጆች ነን ማለት ነው፡፡ ይሄን የልጅነት ጸጋም ያገኘን ሁሉ፣ እያንዳንዳችን በሀገር ዜግነት፣ በቆዳ ቀለም፣ በባህል፣ በቋንቋ፣ በዘር ወዘተ. ሳንለያይ ፍጹም አምላካዊ በሆነ አንድነት አንድ የምንሆንበት እንጂ ከሃይማኖት በፊት በነበረው የሥጋ ማንነትና አስተሳሰቡ ጋር ቀላቅለን፣ ጎራ ለይተን የምንቆምበት፣ ጉድለትና ሕፀፅ ያለበት እንዳልሆነ ይነግረናል፡፡

የዚህ ፍጹም አንድነት መሠረቱም እራሱ እግዚአብሔር እንጂ የሰው ፈቃዳዊ ስምምነት እንዳልሆነ እንዲህ እንረዳለን፤ ‹‹እኔ የወይን ግንድ ነኝ፣ እናንተ ደግሞ ቅርንጫፎች ናችሁ፡፡›› (ዮሐ. ፲፭፥፭)

ስለዚህ ክርስቲያኖች እንደ አንድ ዛፍ ቅርንጫፎች፣ የሕልውናችን መሠረት በወይን ግንድ የተመሰለው ኢየሱስ ክርስቶስ ነው፡፡ የወይን ግንድ ቅርንጫፎችን ሁሉ እንደሚሸከም፣ እኛንም እርሱ ይሸከመናል፤ ግንዱ ለቅርንጫፎቹ ለእያንዳንዱ የሚያስፈልገውን እንደሚያቀርብ፣ የትኛውም ቅርንጫፍ ከግንዱ ከተለየ ስለዚህ ሕልውናው አንደሚያከትም ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስም ለእያንዳንዳችን የሚያስፈልገንን ያደርግልናል፤ ይልቁንም የወይን ግንዱ ምግብና ውኃ ለቅርንጫፎች በማቅረብ ልምላሜ እንዲኖራቸው እንደሚያደርግ፣ እኛም በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ሥጋና ደም የዘለዓለም ሕይወት ያለን እንሆናለን፤ ከእርሱ በተለየን ቅጽበትም ከዚህ ዕጣ ፈንታ ውጪ እንሆንና ለዘለዓለም ሞት እንዳረጋለን፤ ያለ እርሱ ሕይወት የለንምና፤ በዚህ ብዙ ማመስጠር እንችላለን፡፡ ‹‹አይሁድ ብንሆን የግሪክ ሰዎችም ብንሆን፣ ባርያዎችም ብንሆን፣ ጨዋዎችም ብንሆን እኛ ሁላችን በአንድ መንፈስ አንድ አካል እንድንሆን ተጠምቀናልና፡፡ ሁላችንም አንዱን መንፈስ ጠጥተናልና›› ብሏል፡፡( ፩ኛ ወደ ቆሮንቶስ ሰዎች ፲፪፥፲፫) ይሄን የሐዋርያውን አገላለጽ ስናብራራው ደግሞ ኦሮሞ ብንሆን፣ አማራ ብንሆን፣ ትግሬ ብንሆን፣ ጋሞ ብንሆን፣ ጉራጌ ብንሆን፣ ከገጠር ብንሆን፣ ከተሜም ብንሆን፣ ደሆች ብንሆን፣ ባለጸጎች ብንሆን፣ የተማርን ብንሆን፣ መሃይም ብንሆን . . . ወዘተ እኛ ሁላችን በአንድ መንፈስ አንድ አካል እንድንሆን ተጠምቀናልና፡፡ ሁላችንም አንዱን መንፈስ ጠጥተናልና  እንደማለት ነው፡፡ ቅዱስ ጳውሎስ ቀጥሎም፤ ‹‹አካል ብዙ ብልቶች እንጂ አንድ ብልት አይደልምና፣ እግር እኔ እጅ አይደሉምና የአካል ክፍል አይደለሁም ብትል፣ ይህን በማለትዋ የአካል ክፍል መሆንዋ ይቀራልን? ጆሮም፡- እኔ ዓይን አይደለሁምና የአካል ክፍል አይደለሁም ቢል ይህን በማለቱ የአካል ክፍል መሆኑ ይቀራልን? አካል ሁሉ ዓይን ቢሆን መስማት ወዴት በተገኘ….. እናንተም የክርስቶስ አካል ናችሁ እያንዳንዳችሁም ብልቶች ናችሁ›› (፩ ቆሮ ፲፪፥፰፫-፳፯) ይለናል፡፡

ስለዚህ በክርስትና ያለን የእግዚአብሔር ልጅነት የዚህ የመንፈስ ቅዱስ የተዋጀ አንድነት አካል መሆን ነው፡፡ ፍጹም የሆነው ዘለዓለማዊ ድኅነትም የሚገኘው በዚሁ አንድነት ውስጥ ብቻ ነው፤ ከዚህ አንድነት መለየት ከክርስቶስ መለየት ነው፡፡ የክርስቶስ አካል እንደመሆናችን መጠን ደግሞ ይህን ኃላፊነት በተለያየ መልኩ በሕይወታችን ልንተገብር እንደሚገባ መረዳት ያስፈልጋል፡፡

ክርስቲያኖች ከአምላካቸው የተቀበሉትን ትእዛዝ መፈጸምም አለባቸው፡፡ ወላጆች ልጆቻቸውን በልጅነት ጥምቀት በማስጠመቅ፣ በቤተ ክርስቲያን ሥርዓት በማሳደግ እና ሥርዓተ አምልኮቱን እንዲፈጽሙ በመርዳት ማሳደግ አለባቸው፡፡ ይህንንም መጀመር ያለባቸው ልጆቹ ሰባት ዓመት ሲሞላቸው እንደሆነ የቤተ ክርስቲያን አስተምህሮ ላይ ተጠቅሷል፡፡ አንዳንድ ወላጆች ግን ሕፃንነትንና ልጅነት ለይቶ ባለማወቅ ይሁን ባለመረዳት ልጆቻቸው መጾም፣ መጸለይ፣ መስገድ እና በቤተ ክርስቲያን አምልኮት ውስጥ መሳተፍ በሚገባቸው እድሜ ላይ ሲደርሱ ‹‹ልጄ ገና ሕፃን ነው/ናት/፤ የእኔ ልጅ ምን አጥፍቶ/አጥፍታ/ ወይም በምን ኃጢአቱ/ኃጢአቷ ይጾማል/ትጾማለች›› የሚሉም አሉ፡፡ ነገር ግን ልጆች በሕገ እግዚአብሔር እንዲኖሩና ሥርዓቱን እንዲጠብቁ ቃሉ ያዛልና ይህን ኃላፊነት ወላጆች ሊወጡ ይገባል፡፡ ይህ ካልሆነ ግን ልጆቻቸው ከእነርሱ እኩል ተጠያቂ ይሆናሉና ኃጢአታቸውን በንስሐ ሊያነጹ እንደሚያስፈልግ ማሳወቅ ይጠበቅባቸዋል፡፡