ለቤተ ክርስቲያናችን አንድነት ዕርቅና ሰላም መሠረት ናቸው

መስከረም 22 ቀን 2005 ዓ.ም.


የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን በየዘመኑ የተለያዩ ፈተናዎች የተፈራረቁባት ሲሆን ቤተ ክርስቲያኒቱ የእግዚአብሔር ማደሪያ ነችና የመጣውን የፈተና ጎርፍና ነፋስ ሁሉ ተቋቁማ አሁን ላለንበት ዘመን ደርሳለች፡፡ የዐላውያን ገዢዎችን ሰይፍ ከውስጥም ከውጭም የነበሩ መናፍቃንን ቅሰጣ ተሻግራ እስከአሁን የሐዋርያትን፣ የቅዱሳን ሊቃውንትን የአትናቴዎስን የቄርሎስን ሃይማኖት ይዛ ተገኝታለች፡፡፡ ስለዚህም ቤተ ክርስቲያን የሚመጡባትን ፈተናዎች የምታደንቅ፣ በዚያም ተስፋ የምትቆርጥ አይደለችም፡፡ ሁል ጊዜም ቢሆን የገሃነም ደጆች የሚሰብቁት ግልጽና ስውር ጦር እንዳለ ስለምታውቅ ከሚመጣው ፈተና ሁሉ አሸንፋ ትወጣ ዘንድ ወደ አምላኳ ትለምናለች እንጂ፡፡

 

በዚህ ባለንበትም ዘመን ቤተ ክርስቲያናችን ካጋጠሟት ከባድ ፈተናዎች አንዱ ለሃያ ዓመታት ያህል የቆየው የአባቶች መለያየት ጉዳይ ነው፡፡ እንዲህ ያሉ ታሪኮች በቤተ ክርስቲያን ታሪክ ውስጥ እንግዳ ነገር ባይሆኑም የሚያስከትሉት ጉዳት ግን ቀላል የማይባል ነው፡፡ በማወቅም ባለማወቅም ከውስጥ ወይም ከውጪ በሆኑ ምክንያቶች እንዲህ ያሉ መለያየቶች ሊከሰቱ ይችላሉ፡፡ ዋናው ነጥብ ግን ከርስትና በሃይማኖት ምክንያት ካልሆነ በቀር ለመለያየት፣ መንጋን ለመበተን ወይም ለመከፋፈል የሚያበቃ ሥነ ኅሊና /ሞራል/ የሚሰጥ ሃይማኖት አይደለም፡፡ ሃይማኖታችን ተስፋ እንድናደርግ የሚነግረንን የእግዚአብሔር ጸጋ ሁሉ መንግሥቱንም ማግኘት የሚቻለው የዕርቅና ሰላም ሕይወት ሲኖረን ነው፡፡ ጌታችን “እኔ እንደወደድኳችሁ እርስ በእርሳችሁ ትዋደዱ ዘንድ ትእዛዜ ይህች ናት” እንዳለ የሕጉ ሁሉ ፍጻሜ ነው፡፡ /ዮሐ.15፥12/ እርስ በእርስ ብቻም ሳይሆን ብንችል ከሁሉም ጋር በሰላም እንድንኖር ታዘናል፡፡ ያለሰላምና ፍቅር ቤተ ክርብስቲያንን ማነጽ ማጽናትም አይቻልም፡፡

 

በ1983 ዓ.ም. ጀምሮ ቤተ ክርስቲያናችን ያጋጠማት መከፋፈል ከግብጽ ቤተ ክርስቲያን ሞግዚት አስተዳደር ነጻ ወጥተን እንደ እግዚአብሔር ፈቃድ በተመሠረተው መንበረ ፓትርያርክ ጥንካሬ እና አሠራር ላይ ጥያቄም የሚያስነሣ ሆኗል፡፡ በቤተ ክርስቲያን የውጪና የሀገር ውስጥ የአገልግሎት እንቅስቃሴዎችም ላይ ተፅዕኖ ማሳደሩ አልቀረም፡፡ ቤተ ክርስቲያን የሲኖዶሱ፣ የስደተኛው፣ የገለልተኛው ወዘተ እየተባለች ሁሉም እንደፈቃዱ የሚኖርባት ሆና ቆይታለች፡፡

 

እነዚህ ነገሮች ዕረፍት የነሧቸው የተለያዩ ወገኖችም በአባቶች መካከል ያሉ ችግሮች እንዲፈቱ የተለያዩ ጥረቶች ሲያደርጉ ቆይተዋል፡፡ ይሁን እንጂ ችግሮቹ እልባት አግኝተው ቤተ ክርስቲያኒቱ ወደቀድሞው አንድነቷ ሳትመለስ በሂደት ላይ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ጳውሎስ ዐረፉ፡፡ የእርሳቸው ዕረፍትን ተከትሎም ችግሮቹ የበለጠ እንዳይወሳሰቡና መቋጫ ሳያገኙ ወደባሰ ቀውስ፣ አለመረጋጋትና ማባሪያ ወደሌለው መወጋገዝ እንዳይገባ እስከቀጣዩ ፓትርያርክ ሢመት ድረስ አስፈላጊውን ሁሉ ጥረት ከመቼው ጊዜ በላቀ ሁኔታ እንዲቀጥል ብፁዓን አባቶችን ጨምሮ ሁሉም ወገን ግፊት እያደረገ ነው፡፡

 

አገልግሎቱን አጠናክሮ የቤተ ክርስቲያኒቱን መልካም ነገር ሁሉ ማየት ዋነኛ ግቡ የሆነው ማኅበረ ቅዱሳንም የቤተ ክርስቲያናችን አንድነት ጉዳይ በእጅጉ ያሳስበዋል፡፡ መለያየቱ በሚሰጠው አገልግሎት ላይ ከፍተኛ ጫና ማሳደሩን በተጨባጭ ያየው ማኅበረ ቅዱሳን ለሁሉም የቤተ ክርስቲያን የአገልግሎት ቤተሰቦች ጉዳዩ አንገብጋቢ መሆኑን ይረዳል፡፡

 

በዚህ መለያየት ውስጥ ዓላማቸውን ለመፈጸም ይጥሩ የነበሩ ግለሰቦችና ቡድኖች በቤተ ክርስቲያናችን መዋቅር ውስጥ ለመንሰራፋትም ይውተረተሩ እንደነበር ይታወቃል፡፡ አገልግሎታችንም በሚፈለገው ደረጃ በፍጥነት ሄዷል ማለት አይቻልም፡፡ በርካታ ምእመናን በመናፍቃን ተወስደዋል፡፡ ቤተ ክርስቲያን የሚፈለገውንም ያህል ሀገራዊ አስተዋጽኦ ስታደርግ ቆይታለች ለማለት አያስደፍርም፡፡

 

ሌሎች ምክንያቶችም እንዳሉ ሆነው ይኸው በአባቶች መካከል ያለው መለያየትም ከላይ ለዘረዘርናቸው ውስንነቶች የራሱ አስተዋጽኦ ነበረው፡፡ መንበረ ፓትርያርክና ቅዱስ ሲኖዶስ ከአንድ ሺሕ ስድስት መቶ ዓመታት በኋላ ከግብጽ ቤተ ክርስቲያን አስተዳደራዊ ቁጥጥር ተላቀው ያገኙትን መንፈሳዊ ሥልጣንና መንበር በተሻለ አሠራር ወደላቀ የአገልግሎት አቅም የሚያደርሱበትን ሁነኛ ጊዜዎች በእነዚህ መለያየቶች ምክንያት አባክነዋል ማለት ይቻላል፡፡ የተሻለ የስብከተ ወንጌል አገልግሎት መስፋፋት ማሳየት ሲቻል ወደ ኋላ ለመመለሱ አስተዋጾኦ አድርጓል፡፡ ይህ በሁሉም ልብ ያለ ሐዘን እንዲቀረፍ አባቶች ጥረት ሲያደርጉ ቢቆዩም በቀላሉ ተፈቶ ቤተ ክርስቲያንን አንድ ማድረግ ሳንችል መዘግየታችን ትውልዳችንንም የሚያስወቅስ ሆኗል፡፡

 

ይሁን እንጂ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ጳውሎስ በሕይወት እያሉ ተጀምሮ የነበረው የዕርቅና ሰላም ሂደት አሁን እልባት እንዲሰጠው የሚያስገድድ ሁኔታ ውስጥ መግባታችንን ማኅበረ ቅዱሳን ያምናል፡፡ ማኅበራችን የዕርቅና ሰላሙ ጉዳይ አስተዳደራዊ ጉዳይ ብቻም ሳይሆን የክርስቲያናዊ ሕይወትና ሥነ ምግባር ጉዳይ መሆኑ እንዲታሰብበት ይሻል፡፡ ስለዚህ አፋጣኝ እርምጃ መውሰድና ችግሩን ለመፍታት በሚያሳምን ደረጃ መንቀሳቀስ ይጠይቃል፡፡ ጉዳዩም ክብደት እንዲሰጠው ይፈልጋል፡፡ የምናገለግላት ቤተ ክርስቲያን በየምክንያቱ እየተለያየች ባለብዙ መዋቅር ስትሆን ማየት የማይታገሱት ነገር ነው፡፡ የዕርቅና የሰላም ሂደቶቹም ውጤት በግልጽ እየቀረቡ ሕዝበ ክርስቲያኑም ግፊት እንዲየደርግባቸው ይሻል፡፡

 

ለዚህም በደሙ የዋጃትን ቤተ ክርስቲያን እንዲጠብቁ ለመንጋውም እንዲጠነቀቁ አደራ የተሰጣቸው ብፁዓን አባቶች ድርሻ የጎላ ነው፡፡ ዕርቅና ሰላምን በቤተ ክርስቲያን አስፍኖ የቤተ ክርስቲያንን አንድነት ማጽናት ይጠበቅባቸዋል፡፡ ለአገልግሎት የሚመች ስልታዊ አካሄድ አሠራርና አደረጃጀት እንዲሰፍን መፍቀድ ይጠበቅባቸዋል፡፡ ይህንንም ከእግዚአብሔር የሆነውን አደራ ከመጠበቅ አንጻር፣ ለአገልግሎቱ ስኬት ከማምጣት፣ ምእመናን በአገልግሎቱ ረክተው እንዲጸኑ ከማድረግ፣ በታሪክ ውስጥ ተጠያቂ ካለመሆን አንጻር ሁሉ ሓላፊነትን ሊወጡ ይገባል፡፡

 

ሁሉም የክርስቲያን ወገን ቢሆን ሊረዳው የሚገባው የሰበሰበችን ቤተ ክርስቲያን እጅግ ታሪካዊ ባዕለጸጋና አኩሪ መሆኗን ነው፡፡ የሊቃውንቱ የቅዱስ ያሬድ የአባ ጊዮርጊስ ዘጋስጫ፣ የእነ አቡነ ተክለሃይማኖት የእነ አቡነ ኤዎስጣቴዎስ ቤተ ክርስቲያን መሆኗን ልንረዳ ይገባል፡፡ ብዙ ዋጋ ተከፍሎባታል፡፡ ስለዚህ ክብርና አንድነቷን ዕርቅና ሰላምን በማስፈን ልናጸና ይገባል፡፡ ላለብን ችግር መፍትሔ የሚሰጠውም ፈጣሪ መሆኑን በማመን ብፁዓን አባቶችን በጸሎት መርዳት ይገባል፡፡ የቤተ ክርስቲያኒቱን አንድነት በጥብቅ እንደምንፈልገውም በተገኘው አጋጣሚ ሁሉ መግለጽ ግፊትም ማድረግ ይገባናል፡፡ ለሚፈለገው አንድነት ደግሞ መሠረቱ ዕርቅና ሰላም ነው፡፡

 

ቤተ ክህነቱም እግዚአብሔር ያለፈውን ይቅር እንዲለን፣ ከሚመጣውም እንዲጠብቀን ስለ አንድነታችን በጸሎት ሊተጋ ይገባል፡፡ ያለፈው መልካም ያልሆነው ነገር ሁሉ ሊረሳ፣ በጎው ደግሞ ሊወሳ ይገባል፡፡ በጎ ፈቃድና ሰላምን መውደድ ከሊቀ ካህናት ኢየሱስ ክርስቶስ የተማርነው የተረዳነው ነውና ሁሉም ወገን ያንኑ እንዲያጸና መምከር ይጠበቅበታል፡፡

 

ማኅበረ ቅዱሳንም በበኩሉ ከዚህ ቀደም ይዞት የቆየውን ይህንኑ አቋም አሁንም ለማስተጋባት የተገደደው ከችግሩ ወቅታዊነትና ከጊዜው አንገብጋቢነት የተነሣ ነው፡፡ ስለዚህ ችግሩ ከምንም ዓይነት መዘዝ በጸዳ ሁኔታ፣ ቀኖናዊና ሃይማኖታዊ መሠረቶች ተጠብቀው ዕርቅና ሰላምን የማስፈን እንቅስቃሴው በሚያሳምን ደረጃ ሊኬድበት ይገባል፡፡ የአባቶችና የሀገር ሽማግሌዎችም ጥረት ሊመሰገን እንደሚገባው ማኅበረ ቅዱሳን ያምናል፡፡ ውጤት እስከሚገኝ ለሂደቱ አስፈላጊውን ሁሉ አስተዋጽኦ ሊያበረክት መዘጋጀቱን ለሁሉም ወገን ሊገልጽ ይወዳል፡፡

ወስብሐት ለእግዚአብሔር

  • ምንጭ፡- ሐመር መጽሔት 20ኛ ዓመት ቁጥር 5 2005 ዓ.ም.