ለሲኖዶሳዊ ልዕልና መከበር የምእመናን ድርሻ ከፍተኛ ነው!

ክፍል ሁለት

ዲያቆን ይትባረክ መለሰ
ሐምሌ ፳፬፤፳፻፲፭ ዓመተ ምሕረት

፪.፩. ሲኖዶሳዊ ልዕልና እንዲሸረሸር ያደረጉ ምክንያቶች፡-

ተወዳጆች በክፍል አንድ ስለ ሲኖዶሳዊ ልዕልና መከበር የምእመናን ድርሻ ከፍተኛ መሆኑን አንድ ጽሑፍ አድርሰናችሁ ነበር፤ ክፍል ሁለትን እነሆ ብለናል!

ከጥቂት ዓመታት ወዲህ እንደ ሀገር ትልቅ ችግር ገጥሞናል፡፡ የቅዱስ ሲኖዶስን ልዕልና የሚዳፈሩ፣ የሚያወጣቸው ሕጎች እና ውሳኔዎች እንዳይፈጸሙ የሚሠሩ፣ ሲኖዶሱን ለመከፋፈል፣ ሚዛኑን እንዲስት፣ ለአገልግሎት እንዳይተጋ፣ አደራውን እንዳይጠብቅ፣ በሕዝቡ ዘንድ ውዥንብሮች የሚፈጥሩና የሚከፋፍሉ፣ ከሲኖዶሱ የበለጠ ሐሳባቸው የሚደመጥ ግለሰቦችና ቡድኖች መፈጠራቸው ብዙ ውጫዊና ውስጣዊ ቅንጅት የፈጠሩ አካላት ቀላል የማይባል ችግር እየፈጠሩ ይገኛሉ፡፡

ይህም ቅድስት ቤተ ክርስቲያንን ደካማና መሪ የሌላት አስመስሏታል፤ ቁሳዊና መንፈሳዊ ሀብቷን መጠበቅ እንዳትችልና ለውስጣዊና ለውጫዊ ጠላት እንድትጋለጥ ያደረገ ሲሆን የከፋው ደግሞ ያለስሟ ስም እንዲሰጣት፣ የታሪክ ሽሚያ እንዲደረግባት፣ ትውልዱ በተዛባ መንገድ እንዲረዳት፣ በእርሷ እንዳይጠቀም፣ ይልቁንም በጥላቻ እንዲነሣባት ሀገራዊ ውለታዋንም እንዳያስታወሰው አድርጎታል፡፡ ከፍተኛ የሆነ የሚድያ ዘመቻ ይከፈትባታል፤ የጥቃት ሰለባ እንድትሆን፣ ሀብቷ ለውድመት አማኞቿም ለሞትና ለስደት እንዲዳረጉ አድርጓል፡፡

በሀገር አቀፍ ደረጃ የፖለቲካ ተሰሚነት እና ውክልና እንዳይኖራት፣ እጅግ ብዙ ችግር እንዲከባት ተሠርቷል፤ አሁንም እየተሠራ ይገኛል፡፡ ይህንም ለማድረግ የተቻለው በተቀናጀ ስልት ሲሆን ሲኖዶሱ ክብሩ ልዕልናው እንዳይጠበቅ በማድረግ፣ የመሪነት ሚናውን እንዳይወጣ፣ የተጠራበትን ሰማያዊ ተልእኮውን እንዳያሳካ፣ በመከፋፈል እና በራሱ ውስጣዊ አጀንዳ እንዲጠለፍና፣ ውሳኔው መሬት እንዳይነካ በማድረግ ነው፡፡ ከምንም በላይ መሪና ተመሪ እንዳይገናኙ፣ ሲኖዶሱ በምእመናን ዘንድ ተቀባይነት እንዲያጣ አድርጎታል፡፡ ‹‹መሪ የሌላቸው ሕዝቦች እንደረገፉ ቅጠሎች እንደተረበረቡ ግንዶች ናቸው›› እንዲሉ መሪ የማሳጣት መሪና ተመሪን የማለያየት ሥራ ነው፤ የተሠራው አሁንም እንደቀጠለ ነው፡፡

ለዚህም የችግሮቹ ምንጭ ከሁለት ወገን የመጡ ናቸው ብሎ መናገር ይቻላል፡፡

፩. ውስጣዊ ምክንያቶች ፪.ውጫዊ ምክንያቶች ናቸው፡፡

፪.፩.፩. ውስጣዊ ምክንያቶች /የችግር ምንጮች/

ውስጣዊ የሆነው ችግር ዘርፈ ብዙ ነው፡፡ የተወሰነውን ለማየት ያክል

ሀ. ከራሱ ከቅዱስ ሲኖዶሱ አባላት የሚመነጩ ችግሮች እየተበራከቱ መምጣታቸው
• የራሱ የቅዱስ ሲኖዶሱ አባላት ዘመኑን የዋጀ አሠራርን አለመከተል፤
• ክብረ ክህነት ተገቢውን ቦታ አለማግኘቱ፤
• የፖለቲካና የብሔርተኝነት ዝንባሌ ያላቸው አንዳንድ የሲኖዶስ አባላት መታየታቸው፤
• የጳጳሳት አመራረጥና ሹመት አሰጣጥ ተአማኒነት የጎደለው ከሲሞናዊነት፣ ከብሔርተኝነት እና ከፖለቲካ አመለካከት ጋር በተያያዘ የሚነቀፉ፣ በኅብረተሰቡ ዘንድ የመልካም አስተዳደር ችግር ፈጥረዋል ተብለው ነቀፌታ የገጠማቸው እንዲሁም የሥነ ምግባር ጉድለት ያለባቸውን ወዘተ ወደ ሹመት መምጣት፤
• ከመንፈስ ቅዱስ ከሥራ ይልቅ የመንግሥትን አቋምና አጀንዳ የሚያራምዱ መኖራቸው
• የወሰኑት ውሳኔ የት እንደደረሰ ወረድ ብለው መፈጸሙን የመከታተልና ባልፈጸሙት አካላት ላይ ተገቢውን ርምጃ የመውሰድ ቁርጠኝነት አለመኖር፤
• የውጭ/የፖለቲከኞችን/ ጣልቃ ገብነት የመፍቀድ/የመፈለግ ዝንባሌ መታየት፤
• መንፈሳዊ እና ቁሳዊ አስተዳደሩ አለመለየቱና በተገቢው ሰው አለመመራቱ
• ‘አጥማቂ ነን፤ ነቢይ ነን፤ ባሕታዊ ነን’ የሚሉ ሥርዓተ ቤተ ክርስቲያንን የሚጥሱ ሕዝቡን በሐሳብ የሚከፋፍሉ ሥርዓት አልበኞችን አለመገሥፅ ዝምታን መምረጣቸው ወዘተ፡፡
በመጽሐፈ ዲድስቅልያ ላይ ‹‹ሴቶችና ሕዝባዊ የክህነትን ሥራ አይሥሩ፤ እንዳያጠምቁ፤ በአንብሮተ እድም እንዳይባርኩ፤ በረከተ ኅብስቱንም እንደይሰጡ›› ሲሉ ቅዱሳን ሐዋርያት አዘዋል፡፡ (ዲድስቅልያ ፲፬፥፮ እና አንቀጽ ፲፭፥፩)
• አሁን ግን ሲኖዶሱንና አባላቱን ብሎም የክህነትን ክብር ያቃለሉና የተዳፈሩ፣ በማን ክህነት እንደተሰጣቸው፣ የትና በማን እንደመነኮሱ የማይታወቁ ምእመኑን የሚበዘብዙ ሥርዓት የጣሱ ‘አጥማቂ ነን፤ ባለ ሕልም ነን፤ እንባርካለን” እያሉ የሚያውኩትን ዝም በማለታቸው፣ ደረጃው አድጎ በብሔር ተደራጅቶ ማኅበር ማቋቋም፣ ቤተ ክህነት ማቋቋም እያለ ሲኖዶስ እስከማቋቋም የደረሰ ድፍረትን በእንቁላሉ መቅጨት አለመቻላቸው፤
• የመንግሥትን ጣልቃ ገብነት ባለመቃወማቸው፣ ሥርዓት አልበኞችን መገሠፅ፣ ድኃ ተበደለ ፍርድ ተጓደለ ብሎ መናገር ድምጽ ለሌላቸው ድምጽ አለመሆናቸው ነው፡፡ አንዳድ አባቶች አልፎ አልፎ ደፍረው መንግሥትን ሲገሥፁ እንደብርቅና ድንቅ እየታየ እንደ ጀግና እንዲቆጠሩና እነርሱን ለማጀግን ብዙኃኑን ለመተቸት ዕድል ሲፈጥር ይታያል፡፡

ለ. በቅድስት ቤተ ክርስቲያን መዋቅሮች ግልጸኝነትና ተጠያቂነት መጥፋቱ፡-

በመምሪያዎች፣ በሀገረ ስብከቶች፣ በወረዳ ቤተ ክህነትና በአጥቢያ አብያተ ክርስቲያናት ያለው አሠራር ግልጸኝነትና ተጠያቂነት የለውም፡፡ ከዚህም የተነሣ የሰው ሀብት፣ የፋይናንስና የንብረት አስተዳደሩ ሁሉም በራሱ አሳታፊ፣ ግልጽ እና ከአድልዎ የጸዳ በሆነ መንገድ አለመመራቱ፤ ሙሰኞች፣ ፖለቲከኞች፣ አማሳኞች፣ ያልተማሩ እና ቤተ ክርስቲያኒቱን በውል የማያውቋት፣ ጥቅመኞች፣ መናፍቃን ሳይቀሩ በመዋቅሩ ተሰግስገው እንዲዘርፏት፣ ስሟ እንዲጠፋ፣ ትክክለኞቹ ልጆቿ አንገት እንዲደፉና ከመዋቅሯ እንዲገፉ፣ ምእመናንም እንዲያፍሩና እንዲሸማቀቁ በር የከፈተ መሆኑ ነው፡፡ ይህም ከፍተኛ የመልካም አስተዳደር ችግሮችን ከመፍጠሩም በላይ ሲኖዶሳዊቱን ልዕልናው እንዲጠፋ፣ ውሳኔውም እንዳይከበር አንድ ምክንያት ሆኗል፡፡

ሐ. ምእመኑ ከዕለት ወደ ዕለት እያደገ የመጣውን መንፈሳዊ ዕውቀቱን ለትችትና ለነቀፋ መጠቀሙ

ወቅቱ ምእመኑ በተለይም ወጣቱ ትውልድ አንጻራዊ መንፈሳዊ ዕውቀት በንባብም በትምህርትም በልዩ ልዩ መንገድ ያገኘበት ነው፡፡ የሚያውቀውን የሚኖርበት የሕይወት ለውጥ አምጥቷል ማለት ባይቻልም፡፡ ነገር ግን ያወቀውን ዕውቀት አባቶቹን ለመተቸትና ለማቃለል ምክንያት ሆኖታል፡፡ ይህም በራሱ በአሁኑ ወቅት ለቅድስት ቤተ ክርስቲያን ታላቅ ፈተና እየሆነባት ይገኛል፡፡ ምክንያቱም አባቶችን ነቅፎ ለነቀፋ እየሰጠና ክብረ ክህነትን እያዋረደ በመሆኑ ነው፡፡

የተወደዳችሁ አንባብያን! ውስጣዊ ችግሮች እነዚህ ብቻ አይደሉም፤ ነገር ግን ለማሳያ ያክል እነዚህን ጠቀስን እንጂ፡፡ በክፍል ሦስት ውጫዊ ምክንያቶችን ይዘን የምንቀርብ ይሆናል፤ እስከዚያው ቸር ይግጠመን!

ይቆየን!