‹‹ለሰዎች ትታዩ ዘንድ፥ ምጽዋታችሁን በሰዎች ፊት እንዳታደርጉ ተጠንቀቁ!›› (ማቴ. ፮፥፩)

ምጽዋት የሚለው የግእዝ ቃል ትርጉሙ ስጦታ፣ ችሮታ ወይንም ልግስና ማለት ነው፡፡ መመጽወት አንዱ ክርስቲያናዊ ምግባር በመሆኑ በእምነት ሊደረግ ይገባል፡፡  በቤተ ክርስቲያን ውስጥ የሚደረግ የገንዘብ ስጦታ ሆኖ ሙዳዬ ምጽዋት ውስጥ የሚከተት ሲሆን ሌላው ደግሞ ለድሆች የምናደርገው ማንኛውም ዓይነት የምግብ፣ የአልባሳት እና የገንዘብ እርዳታ ነው፡፡ እኛ ክርቲስያኖች ምጽዋትን እናደርግ ዘንድ ተገቢ በመሆኑ የተራቡትን ማብላት፣ የተጠሙትን ማጠጣትን የተራቆቱትን በማልበስ ልንረዳቸው ይገባል፡፡

ምጽዋት እግዚአብሔር ከሰጪዎች ጋር የሚሰጥ፤ ከተቀባዮች ጋር ሁኖ የሚቀበል፤ በመስጠትና በመቀበል፤ በሰዎች መካከል መተሳሰብና መረዳዳት እንዲኖር፤ ሀብትን ለሀብታሞች የሚሰጠው ከእነርሱ የሚያንሱትን እንዲያስተናግዱበት ነው፡፡ ብላቴን ጌታ ኅሩይ ወልደ ሥላሴ ምጽዋትን የተረጎሙት እንዲህ በማለት ነው ‹‹ምጽዋት ማለት የዕለት ምግብና የዓመት ልብስ ለቸገራቸው ሰዎች ገንዘብ መስጠት ነው፤ ደግሞም ምክር ለቸገራቸው መምከር፣ ትምህርት ለቸገራቸው ማስተማር ምጽዋት ነው፡፡›› (ጎሐ ጽባሕ ገጽ ፳፬)

ምጽዋትን ለተቸገረ ሰው የሚሰጥ ሰው ለእግዚአብሔር መስጠቱ ነው፡፡ ጠቢቡ ሰሎሞንም     ‹‹ለደኃ ቸርነትን የሚያደርግ ለእግዚአብሔር ያበድራል በጎነቱንም መልሶ ይከፍለዋል›› ይላል (ምሳ. ፲፱÷፲፯)

ምጽዋት ብልሆች ሰዎች በእግዚአብሔር ዘንድ የሚያስቀምጡት አደራ ነው፡፡ ደካሞችን በጉልበት፣ ያልተማሩትን በዕውቀት፣ የሙያ ርዳታ የሚስፈልጋቸውን በሙያ መርዳት፣ ምጽዋት ነው፡፡ ምጽዋት መስጠት አስፈላጊ እንደሆነ ምጽዋት ሰጪዎችም በእግዚአብሔር ዘንድ የሚጠብቃቸው ከፍተኛ ዋጋ እንዳላቸው በብሉይና በሐዲስ ኪዳናት በሰፊው ተገልጦ ይገኛል፡፡ ‹‹ድሆች ከምድር ላይ አይታጡምና በሀገር ውስጥ ላለ ደኃ ለተቸገረውም ወንድምህ እጅህን ትከፍታለህ ብዬ አዝዝሃለሁ›› እንዲል፡፡ (ዘዳ. ፲፭÷፲፩)

‹‹ወንድምህ ቢደኸይ እጁ ቢደክም አጽናው፤ እንደ እንግዳ እንደመጻተኛ ከአንተ ጋር ይኑር›› እንደተባለውም ልዑል እግዚአብሔርም ከመሥዋዕት ይልቅ ምጽዋትን አብልጦ እንደሚወድ በነቢያቱ አንደበት ተናግሯል፡፡ ‹‹……እኔ የመረጠሁት ጾም …እንጀራህን ለተራበ ትቆርስ ዘንድ ስደተኞች ደሆችን ወደ ቤትህ ታገባ ዘንድ የተራቆተውን ብታይ ታስበው ዘንድ አይደለምን?›› መጥምቀ መለኮት ቅዱስ ዮሐንስ በትምህርቱ ተማርከው ለመጠመቅ የመጡትን ሰዎች እንዲህ በማለት የምጽዋትን አስፈላጊነት አስተምሯቸዋል፡፡ ‹‹ሁለት ልብስ ያለው ሰው ለሌላው ያካፍል፤ ምግብም ያለው እንዲሁ ያድርግ›› ይላል፡፡ (ኢሳ. ፶፯÷፯፣ ሉቃ፫÷፲፩)

ክርስቲያኖች የሚመጸውቱት ከተረፋቸው ሳይሆን ካላቸው ነው፤ ለዚህም ምክንያቱ ደግሞ አስቀድመን እንዳየነው ምጽዋት ትልቅ የክርስትና ቁልፍ በመሆኗ ነው፡፡ ብዙዎቻችን የኃጢአት ሥር በተባለው በገንዘብ መውደድ ልባችን ስለታሰረ ምጽዋት የሚመስለን ከተትረፈረፈው ኪሳችን አንድ ብር ለነዳይ መስጠት ነው፡፡ ምጽዋት ብድሩ ከልዑል እግዚአብሔር ይገኛል በሚል እምነት ለተቸገሩ ሰዎች የሚሰጥ ልግስና እንደመሆኑ አቀራረቡ ከግብዝነትና ከከንቱ ውዳሴ የጠራ መሆን እንዳለበት ጌታችን አስተምሯል፡፡ የድሆችን ጩኸት ሰምቶ በችግራቸው በመድረስ ምላሽ የሚሰጥ እሱ በተቸገረ ጊዜ በጎ ምላሽ ከእግዚአብሔር ዘንድ ያገኛል፡፡ ምጽዋት የክፉ ጊዜ ዋስትና ነውና፡፡ (ሉቃ፳፩÷፩-፬)

ቅዱስ ዳዊት ‹‹ብፁዕ ዘይሌቡ ላዕለ ነዳይ ወምስኪን እምዕለት እኪት ያድኅኖ እግዚአብሔር፣ እግዚአብሔር የዐቅቦ ወያሐይዎ ወያበፅዖ ዲበ ምድር፤›› ለችግረኛና ለምስኪን የሚያስብ ምስጉን ነው እሱንም እግዚአብሔር ከክፉ ቀን ያድነዋል፡፡››  ጠቢቡ ሰሎሞንም ‹‹ፈኑ ኅብስተከ ውስተ ገጸ ማይ እስመ በብዙኅ መዋዕል ትረክቦ፤›› እንጀራህን በውኃ ፊት ላይ ጣለው ከብዙ ዘመን (ቀን) በኋላ ታገኘዋለህና›› እንዴት ሰው ዐይኑ እያየ እንጀራውን በውኃ ላይ ጥሎ ከብዙ ቀን በኋላ ያገኘዋል ልንል እንችላለን፤ እንጀራህን በውኃ ላይ ጣለው ማለት ምጽዋትህን ለተቸገሩት ለድኆች ስጥ ማለት ነው፡፡ ከብዙ ቀን በኋላ ታገኘዋለህ ማለት የምጽዋቱን ዋጋ በገነት በመንግሥተ ሰማያት ታገኘዋለህ ማለት ነው፡፡ በውኃ ውስጥ የጣሉት እንዳይታይ ሰውረህ ሳትታይ ምጽዋት ስጥ ውኃ የበላው እንዳይገኝ ከዚያ ተመጽዋች ዋጋ አገኛለሁ ሳትል ምግብህን በከርሠ ርኁባን መጠጥህን በጕርዔ ጽሙኣን አኑር ማለት ነው፡፡ (መዝ. ፵÷፩-፪፣ መክ ፲፩÷፩፣ ዘሌ.፳፭÷፴፭፣ዘዳ.፲፭፥፯)

ምጽዋት የሚመጸውቱ ሰዎች የሚጠቀሙትን ያህል የማይመጸውቱ ሰዎች ይጎዱበታል፤ ብዙ በረከትንም ያጣሉ፡፡ በመጨረሻ የፍርድ ጊዜም ወቀሳ ተግሣጽ ፍዳ ይጠብቃቸዋል፡፡ ሰው ከሚረገምባቸው የጥፋት ሥራዎች አንዱ ለድኆች አለማዘንና አለመራራት ነው፡፡ ‹‹እስመ ኢተዘከረ ይግበር ምጽዋተ ሰደደ ብእሴ ነዳየ ወምስኪነ፤ ምጽዋትን ያደርግ ዘንድ አላሰበም፤ ችግረኛና ምስኪን አሳዷልና›› ይላል፡፡ ምጽዋት በመስጠት ሰው ፈጣሪውን በሥራ ይመስለዋል፡፡  ራሱን መርዳት የሚችል ሰው የሰውን ገንዘብ አይቀበል ወጥቶ ወርዶ ራሱን ይርዳ፡፡

ምጽዋት ከክፉ ታድናለች፤ ኃጢአትን ታስተሠርያለች፡፡ ውኃ እሳትን እንዲያጠፋ ምጽዋትም ኃጢአትን ታጠፋለች፡፡ ሊቁ ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ ደግሞ ‹‹ወእመ ትብሎ አንሰ ወሀብኩከ ብዙኀ ጊዜ እብለከ ኢትበልዕኑ አንተ በኵሉ ጊዜ፣ ብዙ ጊዜ ሰጠሁት ይበቃዋል አትበል አንተ ጠዋት ማታ ትበላ የለምን? እንደራስህ አታየውምን?›› ይላል፡፡ ምጽዋት የሚሰጠው ለሰዎች መልካም ነገር በማድረግ ከእግዚአብሔር መልካም ነገር ለማግኘት ነው፤ ‹‹ስጡ ይሰጣችኋል›› ተብሏልና፡፡ (ማቴ.፲፥፰፣፪ኛቆሮ.፱፥፯—፲፪)

በምጽዋት የተጠቀሙ ብዙዎች ናቸው፡፡ ምናሴ ጠላቶቹ ከመከሩበት መቅሠፍት የዳነው ምጽዋትን በመመጽወቱ ነበር፡፡ የጌታችን ትእዛዝ፣ ፈቃድና ትምህርት መሠረት አድርገው ያስተማሩ ቅዱሳን ሐዋርያትም ‹‹ካለው የሚሰጥ ብፁዕ ነው›› በሚል ኃይለ ቃል የምጽዋትን ነገር ትኩረት ሰጥተውታል፡፡ (የሐዋ.ሥራ ፳÷፴፮) ዕዝ ፱÷፭)

ምጽዋትን በፍቅር መመጽወት ይገባል፡፡ ቅዱስ ያዕቆብ ‹‹በጎ ለማድረግ ዐውቆ ለማይሠራው ኃጢአት ነው፡፡›› ይህን በጎ ምግባር ሠርተን እንድንጠቀም የእጃችንን እስራት አምላካችን ይፍታ በእርግጥ የእግዚአብሔር ስጦታውን በቃላት ተናግረን አንጨርሰውም፡፡ (ያዕ. ፬÷፲፯)

ምጽዋት ስናደርግ  ከልብ ከመነጨ አዘኔታ እንጂ ለታይታ ወይንም በሰዎች ዘንድ ሙገሳንና አድናቆትን ፈልገን መሆን የለበትም፡፡ እንዲሁም ልብስ፣ ጫማ ወይንም ብር ስለሰጠናቸው ብቻ እግዚአብሔር አምላክ በበጎ ያስብልናል ማለት አይደለም፡፡ ምክንያቱም እርሱ ልብና ኩላሊትን የሚመረምር አምላክ በመሆኑ ለይስሙላ የምናደርገውን ሁሉ ያውቃልና፡፡ ስለ ምጽዋትም በማቴዎስ ወንጌል እንዲህ ተጽፏል፤ ‹‹ለሰዎች ትታዩ ዘንድ፥ ምጽዋታችሁን በሰዎች ፊት እንዳታደርጉ ተጠንቀቁ፤ ያለበለዚያ በሰማያት ባለው በአባታችሁ ዘንድ ዋጋ የላችሁም፡፡ ምጽዋታችሁን በምታደርጉበት ጊዜ፣ ግብዞች በሰዎች ዘንድ ሊመሰገኑ በምኩራብና በአውራ ጎዳና እንደሚያደርጉት በፊታችሁ መለከት አታስነፉ፤ እውነት እላችኋለሁ፥ ዋጋቸውን ተቀብለዋል፡፡ አንተስ ምጽዋትህን በምታደርግበት ጊዜ ቀኝህ የምትሠራውን ግራህ አትወቀው፡፡ ምጽዋትህን በስውር ይሁን፤ በስውር የሚያህ አባትህም በግልጥ ዋጋህን ይሰጥሃል፡፡›› ይህንንም በመረዳት ማንኛውንም ክርስቲያናዊ ምግባር ስንፈጽም በእምነት ይደረግልናል በማለት እንዲሁም የምንመጸውተውን ነገር በሙሉ ፈቃደኝነት መስጠት ያስፈልጋል፡፡ መመጽወታችን ለታይታ እንዲሆን ስንፈልግ በሙሉ ልብ አንመጸውትም፤ በልባችንም ጥርጣሬ ያድርብናል፡፡ በመሆኑም በጎ አድራጎታችን (ምጽዋታችን) በእግዚአብሔር ፊት ተቀባይነት አያገኝም፡፡ (ማቴ. ፮፥፩)

ሰዎች ድኆችን ሊረዱ እንደሚሹ በመናገር የገንዘብና ቁሳዊ እርዳታ ያደርጋሉ፤ በተለይም በዓለም ውስጥ እውቅና ያላቸው ሰዎች በተለያዩ የመገናኛ ብዙኃኖች ላይም ያስነግራሉ፤ ሆኖም ‹‹ግብዞች በሰዎች ዘንድ ሊመሰገኑ በምኩራብና በአውራ ጎዳና እንደሚያደርጉት በፊታችሁ መለከት አታስነፉ፤›› እንደተባለው  ከንቱ ውዳሴን እንጂ በረከትን አያስገኝልንም፡፡  በብዙ ሰዎች ፊት ሙገሳን ያስገኘልን ተግባር በኋላ ለጥፋታችን ይሆናልና ልንጠነቀቅ ይገባል፡፡ ምጽዋት ተቀባይነት የሚኖረው በሃይማኖት ውስጥ በእምነት ጸንተን ክርስቲያናዊ ሕይወትን ስንኖር ነው፡፡

ብዙ ሰዎች በዚህ ጊዜ ለድኆች የተለያየ ዓይነት እርዳታ ሊያደርጉ ይችላሉ፤ ሆኖም በተለየ እምነት ውስጥ ሆኖ የምጽዋትን ትርጉም ያውቁታል ማለት አይቻልም፡፡ ምክንያቱም በአንድ በኩል የእግዚአብሔርን ሕግ እየተላለፉ በሌላ ደግሞ ካካበቱት ሀብት የተወሰውን ለድኃ መስጠት አጓጉል ተግባር ነው፡፡ ድኆችን የመርዳት ሐሳቡ በጎ ሆኖ ሳለ ምጽዋት ክርስቲያናዊ ምግባር መሆኑን ተረድተው በሕይወቱ ውስጥ ሊኖሩ ይጠበቅባቸዋል፡፡ ምጽዋታቸው ተቀባይነት እንዲኖረው በሕጉ ሊኖሩ ይገባል፡፡