ሆሣዕና

በመ/ር ኃይለ ማርያም ላቀው

መጋቢት ፳፱ ቀን ፳፻፱ ዓ.ም

‹ሆሣዕና› የሚለው ቃል ‹ሆሼዕናህ› ከሚለው የዕብራይስጥ  ቃል የተወሰደ ሲኾን፣ ትርጕሙም እባክህ አሁን አድን› ማለት ነው፡፡ ‹‹አቤቱ እባክህ አሁን አድን፤ አቤቱ እባክህ አሁን አቅና፡፡ በእግዚአብሔር ስም የሚመጣ ቡሩከ ነው፤›› ተብሎ እንደ ተጻፈ (መዝ. ፻፲፯፥፳፭-፳፮)፡፡ የሆሣዕና በዓል ጌታችን አምላካችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በአህያ ጀርባ ተቀምጦ ወደ ኢየሩሳሌም ሲገባ አዕሩግም ሕፃናትም ‹‹ሆሣዕና ለዳዊት ልጅ፣ በጌታ ስም የሚመጣ የተባረከ ነው፣ ሆሣዕና በአርያም›› እያሉ ጌታችንን በክብር መቀበላቸው የሚታወስበት በዓል ነው፡፡

በሌላ አገላለጽ ይህ በዓል ‹የጸበርት እሑድ› (Palm Sunday) ይባላል፡፡ ታሪኩም የመልካም ምኞትና የድል አድራጊነት መገለጫ ኾኖ ከደገኛው አባታችን ይስሐቅ ልደት ጋር ተያይዞ የመጣ ነው፡፡ ሣራ ልማደ እንስት ከተቋረጠባት በኋላ ዅሉን ቻይ አምላክ ይስሐቅን በሰጣት ጊዜ ዘመዶችዋ የተሰማቸውን ደስታ ለመግለጽ የዘንባባ ዝንጣፊ በመያዝ እግዚአብሔርን አመስግነዋል፡፡ እስራኤል ከአስከፊው የግብጻውያን አገዛዝ ተላቀው ባሕረ ኤርትራን በደረቅ ሲሻገሩ የተሰማቸውን እጥፍ ድርብ ደስታ በገለጡ፣ እንደዚሁም ዮዲት የተባለች ንግሥተ እስራኤል ሆሎፎርኒስ የተባለ አላዊ ንጉሥን ድል ባደረገች ጊዜ ቤተ እስራኤል እንደ ሰንደቅ ዓለማ የዘንባባ ዝንጣፊ በመያዝ ወደ አደባባይ ወጥተው የተሰማቸውን ደስታ ገልጸዋል፡፡

በዘመነ ሐዲስም መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የሰውን ዘር ከዲያብሎስ ቁራኝነት፣ ከሲኦል ባርነት ነጻ ለማውጣት ወደ ዙፋን መስቀሉ በተጓዘ ጊዜ ሕፃናት እና አዕሩግ ነጻ የሚወጡበት ቀን መድረሱን እግዚአብሔር አመላክቷቸው ዘንባባ በመያዝ ዘምረዋል (ሉቃ. ፳፪፥፲፰)፡፡ በዚህ ዕለት በቤተ ክርስቲያን ዘንባባ እየተባረከ ለሕዝቡ ይታደላል፡፡ እስራኤል ዘሥጋ ዘንባባ በመያዝ እግዚአብሔርን እንዳመሰገኑ እኛ እስራኤል ዘነፍስም ዘንባባ (ጸበርት) በግንባራችን በማሰር በዓሉን እናከብራለን፡፡ በዕለተ ሆሣዕና አዕሩግና ሕፃናት ‹‹ለዳዊት ልጅ መድኃኒት መባል ይገባዋል›› እያሉ ዘምረዋል፡፡

ይህ ዅሉ በአንድ ወገን የነበረው የአቀባበል ሥነ ሥርዓት ሲኾን፣ በሌላ በኩል የነበረው አቀባበል ደግሞ እጅግ የሚያሳዝን ነበር፡፡ ሥርዓተ ኦሪትን፣ ትንቢተ ነቢያትን በሚገባ እንከተላለን ይሉ የነበሩ ጸሐፍት ፈሪሳውያን ጌታችንን ‹‹ደቀ መዛሙርትህን ገሥፃቸው›› ነበር ያሉት፡፡ ጌታችንም መልሶ፡- ‹‹እነዚህ ዝም ቢሉ ድንጋዮች ይጮኻሉ›› በማለት ሕያዋን ሰዎች ብቻ ሳይኾኑ ግዑዛን ፍጥረታትም እርሱን እንደሚያመሰግኑ አስረድቷቸዋል፡፡ ቅናት አቅላቸውን ያሳታቸው ፈሪሳውያን የሕዝቡን ምስጋና ወደ ጥላቻ እንዲለወጥ በማድረጋቸው በዕለተ ሆሣዕና ዘንባባ ይዘው ይዘምሩ የነበሩ ጭምር በዕለተ ዓርብ ‹‹ይሰቀል!›› እያሉ በጌታችን ላይ ጮኸዋል፡፡

መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በአህያ ጀርባ ላይ ተቀምጦ ወደ ኢየሩሳሌም ሲገባ በነቢዩ ዘካርያስ፡- ‹‹እነሆ ንጉሥሽ ጻድቅና አዳኝ ነው፤ ትሑትም ኾኖ በአህያም፣ በአህያዪቱ ግልገል በውርንጫዪቱ ላይ ተቀምጦ ወደ አንቺ ይመጣል፤›› ተብሎ የተነገረው ትንቢት ተፈጽሟል (ዘካ. ፱፥፱፤ ማቴ. ፳፩፥፬፤ ማር. ፲፩፥፩-፲፤ ሉቃ. ፲፱፥፳፰-፵፤ ዮሐ. ፲፪፥፲፭)፡፡ ጌታችን በአህያ ጀርባ ተቀምጦ ወደ ኢየሩሳሌም መግባቱ የሰላም ንጉሥ መኾኑን ያመለክታል፡፡ እስራኤል ዘመነ ምሕረት ሲኾንላቸው አባቶቻቸው በአህያ ጀርባ ተቀምጠው ይታዩ ነበር፡፡ ጌታም እውነተኛ ሰላም ይዤላችሁ መጣሁ ሲለን በአህያ ጀርባ ወደ ቤተ መቅደስ ሕይወታችን ተጉዟል፡፡

መድኃኒታችን ክርስቶስ መላእክት በዕለተ ልደቱ ‹‹በሰማይ ለእግዚአብሔር ምስጋና ይገባዋል፤ በምድርም ሰላም ለሰዉ ዅሉ ይሁን›› እያሉ የዘመሩለት የሰላም ባለቤት ነው (ሉቃ. ፪፥፲፫)፡፡ በመዋዕለ ትምህርቱም ‹‹ሰላሜን እሰጣችኋለሁ›› ብሎ አስተምሮናል (ዮሐ. ፲፬፥፳፯)፡፡ ሰላሙን የሚሰጥበት ዕለት መቃረቡን ለማመልከት ጌታችን በአህያ ጀርባ ተቀምጦ ወደ ቤተ መቅደስ መጣ፡፡ በሌላ በኩል በአህያ ጀርባ መቀመጡ ኅቡዕ ምሥጢር አለው፡፡ በአህያ ጀርባ የተቀመጠ ሰው ሌላውን አሳድዶ አይዝም፤ እርሱም ሮጦ አያመልጥም፡፡ በዚህም ጌታችን በእምነት ለሚፈልጉት የሚገኝ፣ ለማይፈልጉት ግን የማይገኝ አምላክ መኾኑን አስተምሯል፡፡

ለታሰሩት መፈታትን ሊሰብክ ሰው የኾነው ጌታችን ከማሰሪያዋ በተፈታች አህያ እንደ ተቀመጠ ዅሉ ዛሬም ከኃጢአት እስራት በተፈታ ሕይወት አድሮ የሕሊና ሰላምን ይሰጣል፡፡ የአህያን ጀርባ ያልናቀ ጌታችን ትሑት ሰብእና እና የተሰበረ ልቡና ወዳለው ሰው ዘወትር ይጓዛል፡፡ እርሱ የተዋረደውንና የተሰበረውን ልብ አይንቅምና (መዝ. ፶፥፲፯፤ ኢሳ. ፷፮፥፪)፡፡ ስለዚህ የእግዚአብሔር ቤተሰቦች ፀሐይ ዕድሜአችን ሳትጠልቅ በእምነት እግዚአብሔርን እንፈልገው፡፡ ሰላሙን ይሰጠን ዘንድም ንስሐ ገብተን ‹‹ሆሣዕና በአርያም›› እያልን እናመስግነው፡፡

ወስብሐት ለእግዚአብሔር፡፡

ምንጭ፡- ሐመር ዘኦርቶዶክስ ተዋሕዶ፣ መጋቢት/ሚያዝያ ፲፱፻፺፮ ዓ.ም፡፡