ሆሣዕና በአርያም

በወልደ አማኑኤል

ሆሣዕና በአርያም ማለት በሰማይ ያለ መድኃኒት ነው፡፡ ጌታችን በአህያ ውርንጫ ተቀምጦ ወደ ኢየሩሳሌም የገባበት ዕለት ከዘጠኙ ዐበይት በዓላት አንዱ ስለሆነ የክብረ በዓሉ ምስጋና በዋዜማው ይጀመራል፡፡ ቅዳሜ ከሰዓት በኋላ ካህናቱ ‹‹በእምርት ዕለት በዓልነ፣ በታወቀ የበዓላችን ቀን ከበሮ ምቱ›› በማለት የዋዜማውን ምስጋና ይጀምራሉ፡፡ የዋዜማው የምስጋና ቀለም እጅግ ሰፊ ስለሆነ በዚህ መዘርዘር አይቻልምና ከዋዜማው ፍጻሜ በኋላ ያለውን ሥርዓት እንመልከት፡፡

በሌሊተ ሆሣዕና ማኅሌት ከመቆሙ በፊት በካህኑ ተባርኮ በሰሙነ ሕማማት ሲነበብ፤ ሲተረጎም የሚሰነብተው ግብረ ሕማማት የተባለው መጽሐፍ ሲነበብ ነው፡፡ ‹‹ስቡሕ ወውዱስ ዘሣረረ ኩሎ ዓለመ››፣ ዓለምን ሁሉ የፈጠረ እግዚአብሔር ፍጹም የተመሰገነ ነው፡፡ የምስጋናዎች ሁሉ ርእስ የዕለቱ የማኅሌቱ ምሥጋና በካህናት በሊቃውንት ይፈጸማል፡፡

ከዐብይ ጾም መግቢያ ጀምሮ በዝምታ የሰነበቱት ከበሮና ጸናጽል የምስጋናው ባለ ድርሻዎች ናቸው፡፡ በዚህ የተጀመረው ማኅሌት ሌሊቱን ሙሉ አድሮ መዝሙር በሚባለው ምስጋና በኩል አድርጎ ሰላም በተባለ የምስጋና ማሳረጊያ ይጠናቀቃል፡፡

ሥርዓተ ዑደት ዘሆዕና

ሥርዓተ ማኅሌቱ ተፈጽሞ፤ ሥርዓተ ቅዳሴው ከመጀመሩ በፊት እስከዚያ ሰዓት ከነበረው ሥርዓት ለየት ያለ ነው፡፡ ይሔውም ሊቃውንቱ የዕለት ድጓ እየቃኙ፣ እየመሩና እየተመሩ፣ ዲያቆኑ ከመዝሙረ ዳዊት የዕለቱን በዓል የተመለከተ ምስባክ በዜማ እያሳመረ፣ ካህናቱም በዓሉን የተመለከተ የዕለቱ ተረኛ ካህን በማቴዎስ ወንጌል ፳፩፡፩-፲፫ ላይ ያለውን ኃይለ ቃል በሚያነብበት ወቅት በአራቱም መዓዘን ቤተ መቅደሱን አንድ ጊዜ ይዞሩታል፡፡

ለምሳሌ ከምዕራቡ ወደ ምሥራቅ ባለው በር ፊት ለፊት በመቆም መምህሩ ‹‹አርእዩነ ፍኖቶ ወንሑር ቤቶ፣ ወደ ቤቱም እንገባ ዘንድ መንገዱን አሳዩን፤››የሚለውን ድጓ ይቃኛሉ፡፡ ካህናቱ እየተከተሉ ያዜማሉ ዲያቆኑ ‹‹ዘምሩ ለእግዚአብሔር ዘየይድር ውስተ ጽዮን፤ በጽዮን የሚገለጥ እግዚአብሔርን አመስግኑ›› እያለ የዕለቱ ተረኛ ካህን ያዜማል፡፡ በዚህ ዐይነት መልክ በአራቱም መዓዝነ ቤተ ክርስቲያን ሥርዓተ ዑደቱ ይፈጸማል፡፡

ሥርዓተ ቅዳሴ ዘሆዕና

በዕለተ ሆሣዕና አሁንም የቅዳሴው አገባብ ሥርዓት ከሌሎች ዕለታት ለየት ያለ መሆኑን እንመለከታለን፡፡ ዲያቆናቱ ኅብስቱን በመሶበ ወርቅ ወይኑን በጽዋዕ ይዘው በምዕራብ በር በኩል ይቆማል፡፡ ሠራኢው ዲያቆን በዜማ አሰምቶ ‹‹አርኅው ኖኃተ መኳንንት፣ አለቆች ደጆችን /በሮችን/ ክፈቱ›› ይላል፡፡ ካህኑም በመንጦላዕት ውስጥ ሆኖ ‹‹መኑ ውእቱ ዝንቱ ንጉሠ ስብሐት››፣ ይህን የክብር ንጉሥ የኃያላን አምላክ እግዚአብሔር ነው፤ ብሎ ይመልሳል፡፡ ዲያቆኑ ሦስት ጊዜ የክፈቱልኝ ጥያቄያዊ ዜማውን ካዜመ በኋላ ‹‹ይባእ ንጉሠ ስብሐት››  የክብር ንጉሥ ይግባ ብሎ ፈቅዶለት ይገባል፤መዝ. ፳፫፥፯፡፡

ይህንንም አበው እንደሚከተለው ያመሰጥሩታል፤ አንደኛ ቅዱስ ገብርኤልና ወላዲተ አምላክ በምሥጢረ ብስራት ጊዜ የተነጋገሩት እንደሆነና በመጨረሻም ‹‹ይኩነኒ በከመ ትቤለኒ››፣ እንደ ቃልህ ይደረግልኝ ብላ መቀበሏን ያሳያል፡፡ ሁለተኛው ፈያታዊ ዘየማንና መልአኩ ኪሩብ በማእከለ ገነት የተነጋገሩትን በድርጊት ለማሳየት መሆኑን ያስተምራሉ፡፡ ዋናው ምሥጢር ግን ክርስቶስ ወደ ቤተ መቅደስ ሊገባ ሲል ብዙዎቹ እንዳይገባ ቢፈልጉም ከፊሎቹ ግን እንዲገባ መፍቀዳቸውን ያሳያል፡፡እንደተለመደው ሥርዓተ ቅዳሴው ከተጠናቀቀ በኋላ ‹‹እግዚአ ሕያዋን›› /የሕያዋን ጌታ/ የተሰኘው ጸሎት በካህናት ተደርሶ ለምእመናን ሥርዓተ ፍትሐት ይደረግላቸዋል፡፡ ከዚህ በኋላ ሥርዓተ ፍትሐት ስለማይደረግ፤ በሰሙነ ሕማማት የማይከናወኑ ምሥጢራት በዕለተ ሆሣዕና ይከናወናል፡፡

ምእመናኑ ተባርኮ የተሰጣቸውን የዘንባባ ዝንጣፊ በመያዝ ወደ እየቤታቸው ያመራሉ፡፡ የዘንባባው ምሥጢር የተጀመረው በታላቁ አባት በአብርሃም ነው፤ ኩፋ. ፲፫፥፳፩፡፡ ይህን የአባታቸውን ሥርዓት አብነት አድርገው እስራኤል የኤርትራን ባሕር ሲሻገሩ፣ ዮዲት ድል ባደረገች ወቅት ዘንባባ እየያዙ እግዚአብሔርን አመስግነውበታል፡፡ ጌታችን በዕለተ ሆሳሣና ወደ ኢየሩሳሌም ሲገባም ሽማግሌዎችና ሕፃናት የዘንባባ ዝንጣፊ ይዘው እንደተቀበሉት እናነባለን፡፡‹‹ኢትዮጵያዊያን ምእመናንም ክርስቶስ የሰላም ነጻነት የድኅነት አምላክ መሆኑን ለመመስከር ዘንባባውን ይዘው ወደ ቤታቸው ይገባሉ››፤በእጃቸውም እንደ ቀለበት ያስሩታል፡፡

ለበዓለ ሆሣዕና በሰላም ያደረሰን አምላክ ለብርሃነ ትንሣኤው በሰላም እንዲያደርሰን ቅዱስ ፈቃዱ ይሁንልን!