ሃይማኖት

ዲያቆን ተስፋዬ ቻይ
የካቲት ፲፫፤፳፻፲፮ ዓመተ ምሕረት

ውድ የእግዚአብሔር ልጆች! እንዴት አላችሁልን! የዕረፍት ጊዜን እንዴት አሳለፋችሁት? መቼም እርግጠኛ ነን ጎበዝና አስተዋይ ልጆች በመሆናችሁ የግማሽ ዓመት የዕረፍት ጊዜን ቤተ ክርስቲያን በመሄድ፣ ለቀጣይ የትምህርት ጊዜ በመዘጋጀት፣ አነስተኛ ውጤት ያመጣችሁበትን የትምህርት ዓይነት በቀጣይ ለማሻሻል ስታቀዱ እንደ ነበር እናምናለን፡፡

ብዙ ጊዜ እንደምንነግራችሁ አሁን ያላችሁበት ዕድሜ በምድራዊ ኑሮ ለነገ ማንንታችሁ መሠረት የምትጥሉበት ስለ ሆነ ጨዋታ እንኳን ቢያምራችሁ ቅድሚያ የምትሰጡት ለትምህርት መሆን አለበት! መልካም!

ሌላው ደግሞ መዘንጋት የሌለባችሁ ነገር በሰንበት ቤተ ክርስቲያን በመሄድ፣ መንፈሳዊ ትምህርት መማር እንዳለባችሁ ነው፤ ሁለቱን አስተባብራችሁ በመያዝ የነገዋን አገር፣ የነገዋን ቤተ ክርስቲያን በኃላፊነት ለመረከብ ከአሁኑ ጎበዝና አስተዋይ መሆን ይጠበቅባችኋል! መቼም ልጆች! ይህ የታላቅነት ምክራችንን ሳትሰለቹ ለተግባራዊነቱ እንደምትተጉ አንጠራጠርም፡፡

አሁን ደግሞ ለዛሬ ወደ አዘጋጀንላችሁ ትምህርት እናምራ! ባለፈው የእምነታችን መጠሪያ ስለ ሆነው ስማችን መቼ፣ እነ ማን፣ ለምን እንደ ሰየሙትና የስሙን ትርጉም ነግረናቸሁ ነበር፤ ዛሬ ደግሞ ሃይማኖት በሚል ርእስ እንማራለን፤ መልካም!

ሃይማኖት ማለት “ማመን፣ መታመን፣ እምነት፣ ጽኑ ተስፋ፣ በልብ በረቂቅ ሐሳብ የሚሣል ማለት ነው፡፡ (አለቃ ኪዳነ ወልድ ክፍሌ መዝገበ ቃላት፣ ገጽ ፫፻፷፱) “ለዚህ ዓለምና ለፍጥረት ሁሉ አስገኚ (ፈጣሪ) አለ” ብሎ ማመን ነው፡። ይህ የሁሉ ፈጣሪ ደግሞ እግዚአብሔር ነው! ታዲያ ሁሉን ያስገኘ (የፈጠረ) እግዚአብሔር መሆኑን ያወቅነው በሃይማኖት ነው፤ በእምነት ነው፤ በኋላም “መንግሥተ ሰማያትን ያወርሰናል” ብለን ጽኑ ተስፋ እናደርጋለን፡። ሃይማኖት የሚፈጸም፣ የሚሆን፣ በዓይን የማይታይ፣ በሥራ የሚገለጥ ረቂቅ የሆነ ነው፡፡

ውድ የእግዚአብሔር ልጆች! ሃይማኖት ከእግዚአብሔር ጋር የምንገናኝበት ረቂቅ የሆነ (በዓይን የማይታይ) መንገድ ነው፤ መንገድ ሩቅ እና ሩቅ ያሉትን ሰዎች እንደሚያገኛኝ ሃይማኖትም የፍጥረታት ፈጣሪ እግዚአብሔርን እና እኛን ሰዎችን ስለምታገናኘን በመንገድ ተመሰለች፡፡

ሃይማኖት ያለው ሰው የሚደርስበትን ችግር (መከራ) ሁሉ የሚቋቋምበትን ኃይል ያገኛል፤ ይበረታል፤ በፈተና ወቅት ይጸናል፤ እንደገናም የሚፈልገውንም ነገር ከእግዚአብሔር ያገኛል፤ ቅዱስ ዮሐንስ ወንጌላዊ በመልእክቱ የእምነትን ኃያልነት እንዲህ በማለት ገልጾታል፤ ‹‹…ዓለምንም የሚያሸንፈው እምነታችን (ሃይማኖታችን) ነው፡፡›› (፩ኛ ዮሐ.፭፥፬)

ውድ የእግዚአብሔር ልጆች! ሃይማኖት እኛ ሰዎች የእግዚአብሔር ልጆች የምንሆንባት፣ የዓለማት ፈጣሪ እግዚአብሔር እንደሆነ የምናውቅባት፣ የጠላታችንን ሰይጣን ክፋት፣ ፈተና የምንመክትባት ጋሻችን ናት! ሃይማኖት (እምነት) ካለን ኃይልን፣ ብርታትን እናገኛለን፤ አውሬም አያስደነግጠንም፤ እሳትም አያስፈራንም፤ ምክንያቱም ባመንን ጊዜ የታመነው አምላክ እግዚአብሔር ከእኛ ጋር ስለሚሆን ሁሉን የማድረግ ኃይል ጥበብ ይሰጠናል፡፡

ውድ የእግዚአብሔር ልጆች! ስለ ሃይማኖት በጥቂቱ ገለጽን እንጂ ሃይማኖት ብዙ ምሥጢር እና ትርጉም ያላት ናት! እምነትን (ሃይማኖትን) ከምግባር ጋር ማጣጣም ያስፈልጋል፤ እምነትና ሥነ ምግባር አብረው ሲሆኑ ነው እምነታችን ጽኑ ሆኖ ኃይልና ብርታት የሚሆነን፤ ስለዚህ ሃይማኖታችንን በሥራ እንግለጠው፡፡

ለምሳሌ ብንወስድ ልጆች! እኛ በሕይወታችን በቤት ውስጥ፣ በሰፈር ውስጥ፣ በትምህርት ቤት፣ ምን ያህል ታማኞች እንሆን? አያችሁ! በእግዚአብሔር የሚያምን ሰው፣ እምነት ያለው፣ ምግባሩም የቀና፣ መልካም ሥራን የሚሠራ፣ ከክፋት እና ከተንኮል የራቀ መሆን አለበት፡፡ በእግዚአብሔር ማመናችንና እርሱን መውደዳችንን የምንገልጥበት አንዱ መንገድ መልካም ሥራን በመሥራት ነው፡፡
ቅዱስ ጳውሎስ በኤፌሶን አገር ለነበሩ ምእመናን በላከው መልእክቱ ላይ ‹‹..ፍሬ ከሌለው ከጨለማ ሥራ ጋር አትተባበሩ…›› በማለት እንደ መከራቸው እምነታችን በሥራ የተገለጠ ፍሬን የሚያፈራ፣ ጨለማ ከተባለ ክፉ ምግባር መለየት እንዳለበት አስተምሮናል፡፡ (ኤፌ.፭፥፲፩)

እምነት (ሃይማኖት) ከምግባር ጋር የነበራቸው ቅዱሳን አባቶቻችንና እናቶቻችን በእምነታቸው ብዙ ድንቅ ነገር አድርገዋል፤ እሳት ውስጥ ቢገቡም እሳቱ አላቃጠላቸውም፡፡ በትንቢተ ዳንኤል ታሪካቸው የተጻፈልን ሦስቱ ሕፃናት በእምነትና በምግባራቸው ጸንተው በነበረ ጊዜ ጣዖታትን የሚያመልክ፣ እግዚአብሔርንም የማያውቅ ናቡከደነጾር የተባለ ንጉሥ እሳት ውስጥ በጣላቸው ጊዜ ቅዱስ ገብርኤል ከእግዚአብሔር ተልኮ በመምጣት አድኗቸዋል፡፡ (ዳን. ፫፥፲፱-፳፯)

ነቢዩ ዳንኤል በአንበሳ ጉድጓድ እንዲበሉት በተጣለl ጊዜ ሃይማኖት ከምግባር ጋር አስተባብሮ በመያዙ አንበሶቹ ሳይበሉት ቀረ፡። (ዳን.፮፥፲፮-፳፬)

ውድ የእግዚአብሔር ልጆች! ሃይማኖት ያለውን ሰው ከብዙ መከራ እግዚአብሔር ያድነዋል፤ ታዲያ እምነታችንን (ሃይማኖታችን) በመልካም ሥራ ልንገልጠው ያስፈልጋል፤ ታዛዦች፣ ቅን እና ለሰው በጎ ነገር የሚያስብ፣ ካለው የሚያካፍል፣ ለሰዎች የሚያዝን፣ ጓደኛውን የሚወድ፣ የሚረዳና መልካም የሚያስብ በመሆን በእግዚአብሔር ማመናችንን መመስከር አለብን፤ ትምህርታችን እንደዲገለጥ፣ ያቀድነው እንዲሳካ፣ ካሰብነው እንድንደርስ በእግዚአብሔር፣ በወላጆቻችን ፣ በጓደኞቻችን እንታመን!

ቸር ይግጠመን!!!

ስብሐት ለእግዚአብሔር
ወለወላዲቱ ድንግል
ወለመስቀሉ ክቡር አሜን!!!