atena 2006 2

ሀገር ዓቀፍ ዐውደ ጥናት ተካሔደ

ጳጉሜን 3 ቀን 2006 ዓ.ም.

እንዳለ ደምስስ

በማኅበረ ቅዱሳን ጥናትና ምርምር ማእከል የተዘጋጀው 6ኛው ሀገር ዓቀፍ ዐውደ ጥናት ጳጉሜን 1 ቀን 2006 ዓ.ም. በማኅበሩ ሕንፃ መሰብሰቢያ አዳራሽ ተካሔደ፡፡

atena 2006  2ለአንድ ቀን በተዘጋጀው ዐውደ ጥናት 6 በምርምር ማእከሉ የተመረጡ ጥናቶች ቀርበዋል፡፡ በዚህም መሠረት በሰሜን ወሎ ሀገረ ስብከት በመቄት ወረዳ የደብረ ገነት ናዙኝ ማርያምና የአቡነ አሮን መንክራዊ ፍልፍል አብያተ ክርስቲያናት ታሪክ፤ ኪነ ሕንፃ፤ ተንቀሳቃሽ ቅርስና ያሉበት ሁኔታ በሚል ርዕስ በዲያቆን ፀጋዬ እባበይ በዲላ ዩኒቨርስቲ የአርኪዮሎጂ መምህር የመጀመሪያውን ጥናት አቅርበዋል፡፡

የደብረ ገነት ናዙኝ ማርያምና የአቡነ አሮን መንክራዊ ገዳማት የተረሱ ፍልፍል አብያተ ክርስቲያናት መሆናቸውን የገለጹት ጥናት አቅራቢው፤ ፍልፍል አብያተ ክርስቲያናቱ በከፍተኛ ጉዳት በአደጋ ውስጥ እንደሚገኙና በጥናት ላይ የተደገፈ ጥገና እንደሚያስፈልጋቸው ተናግረዋል፡፡

ናዙኝ ማርያም ሁለተኛው የኢትዮጵያ ጳጳስ የነበሩት አቡነ ሙሴ በ4ኛው መቶ ክፍለ ዘመን እንዳነጿት አብራርተው፤ ቤተ ክርስቲያኗ ለአክሱማውያን ውቅር አብያተ ክርስቲያናት መሠረት፤ አለበለዚያም ለኋለኞቹ ድልድይ እንደሆነች በጥናታቸው ዳስሰዋል፡፡በመቄት ወረዳ ብቻ ከ19 በላይ ፍልፍል አብያተ ክርስቲያናት ሲገኙ 13ቱ በአቡነ ሙሴ፤ ሁለቱ ደግሞ በአቡነ አሮን እንደታነጹ ገልጸዋል፡፡

atena 2006  1ሁለተኛው ጥናት ሥነ ምኅዳርን ያማከለ የአካባቢ ጥበቃ እቅድ የደብረ ሊባኖስ ገዳም ደን የሥነ ምኅዳር አገልግሎት ለማሳደግ በሚል ርዕስ በመስፍን ሳህሉ በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ የአካባቢ ጥናት ተማሪ የቀረበ ሲሆን፤ የደብረ ሊባኖስን ገዳም ደን የሥነ ምኅዳር አገልግሎት ለማሳደግ በርካታ ሥራዎች መሠራት እንደሚገባቸው በጥናት አቅራቢው ተገልጿል፡፡ ቀድሞ የነበረው ተፈጥሯዊ ደን መመናመን፣ በተለያዩ ምክንያቶች መሬቱ እየተራቆተ መምጣቱ፤ የአፈሩ መሸርሸር፣ ለጐርፍ አደጋ ገዳሙ መጋለጡንና የአካባቢው የአየር ጸባይ መለዋወጥ ገዳሙን ለከፍተኛ አደጋ እንዳጋለጠው ጠቅሰዋል፡፡

በዲያቆን ሔኖክ ሐይሉ /MA/ ከማኅበረ ቅዱሳን ጥናትና ምርምር ማእከል የቀረበው 3ኛው ጥናት የተቀናጀ ሃይማኖታዊ እና የምክክር /counseling/ መርህ የካህናትን የማማከር ክሂል በማሳደግ ረገድ ያለው ውጤታማነት ከኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን አንጻር በሚል ርዕስ ላይ ትኩረት ያደረገ የምክክር ባለሙያዎች ማሰልጠኛ ቢጋር አዘጋጅተው አቅርበዋል፡፡

የንስሐ አባቶች ከንስሐ ልጆቻቸው ጋር ያላቸውን ግንኙነት ለማጠናከር ዘመኑን የዋጀ ዘመናዊ የሥነ ልቦና የማማከር አገልግሎት ሥልጠና ቢወስዱ ውጤታማ የቤተ ክርስቢተያንን አገልግሎት ለመተግበር እንደሚረዳቸው ጠቁመዋል፡፡ የንስሃ ልጆቻቸው ኃጢአታቸውን ተናዝዘው፤ ንስሃ ገብተው፣ ቀኖናቸውን ተቀብለው ወደ ቅዱስ ሥጋውና ክቡር ደሙ የመቅረብ ሂደት እንደተጠበቀ ሆኖ፤ በጓደኝነት፤ በትዳር፣ እንዲሁም በማኅበራዊ ሕይወት ውስጥ ለሚገጥማቸው መሰናክል የንስሐ አባቶች የሥነ ልቦና የማማከር አገልግሎት ላይ እውቀት ኖሯቸው ከልጆቻቸው ምክክር ቢያደርጉ አገልግሎቱን የተሟላ ሊያደርገው እንደሚችል በጥናቱ ተጠቁሟል፡፡

በሦስቱም ጥናቶች ላይ ከተጋባዥ የቤተ ክርስቲያን አባቶች፣ ምሁራንና ከተሳታፊዎች ጥያቄና አስተያየት ቀርቦ ሰፊ ውይይት ተደርጎባቸዋል፡፡

ከሰዓት በኋላ በቀጠለው ዐውደ ጥናት የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የብራና መጻሕፍት ይዞታቸው፤ ያካተቷቸው ምሥጢራትና ከባሕር ማዶ ስለሚገኙት መጻሕፍት በሚል ርእስ መጋቤ ሐዲስ ሮዳስ ታደሰ የቅድስት ሥላሴ መንፈሳዊ ኮሌጅ የሐዲስ ኪዳን ትርጓሜ መምህር ጥናታቻውን አቅርበዋል፡፡

ቤተ ክርስቲያናችን ካሏት በብዙ ሺህ ከሚቆጠሩ አስደናቂ የብራና መጻሕፍት መካከል ቀዳሚዎቹ የዓለም የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት ሊቃውንት ለምስክርነት የሚጠቀሙባቸው ረጅም ዘመናትን ያስቆጠሩ የብሉይ፤ የሐዲስ ኪዳን፣ የጸዋትወ ዜማ፣ የጸሎትና የምስጋና መጻሕፍት፣ መጻሕፍተ ሊቃውንት እና የሃይማኖት መጻሕፍት፣ መጻሕፍተ መነኮሳትና ሌሎችም መጻሕፍት በተለያዩ ምክንያቶች ከሀገር ወጥተው በውጭ ሀገራት እንደሚገኙ ገልጸዋል፡፡

በተለያዩ ዓለማት ያሉ ተመራማሪዎች እነዚህ ሁሉ ጥበባት በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን እንዳሉ በማወቃቸው መጻሕፍቱን በተለያዩ አጋጣሚዎች ከሀገራችን እንዲወጡ አድርገዋል፡፡ እንደ ምሳሌም ጀምስ ብሩስ /ከ1768-1773/ መጽሐፈ ሔኖክን እና በርካታ መጻሕፍትን ይዘው እንደወጡ በጥናቱ ተጠቅሷል፡፡

በዚህም መሠረት በቫቲካን ቤተ መጻሕፍት 1082፣ በእንግሊዝ 850፣ በጀርመን 734፣ በጣሊያን 550 ወዘተ የብራና መጻሕፍት እንደሚገኙ በጥናታቸው አካትተዋል፡፡

በዶ/ር አምሳሉ ተፈራ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የፊሎሎጂ ትምህርት ክፍል ሓላፊ የቀረበው ጥናት የአማርኛ ሥርዓተ ጽሕፈት በቤተ ክህነት ሊቃውንት እይታ በሚል ርዕስ ሲሆን፤ እንደ ኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ሊቃውንት የፊደላት ምንጫቸው ከፈጣሪ የተገኘ፣ ለሄኖስ በሰማይ ሰሌዳ ላይ ለመጀመሪያ ጊዜ የተገለጸና፤ የግዕዝ ፊደላት ከዚያን ጊዜ ጀምሮ በሥራ ላይ መዋላቸውን ገልጸዋል፡፡ አማርኛን በተመለከተም ከግዕዙ የወሰዳቸው 26 አናባቢዎች እንዳሉ ሆነው፤ በኋላ 7 ከዚያም /ቨ/ን በመጨመር 34 እናት ፊደላት /consonants/፤ እንዲሁም 4 ደቃልው /labioverals/ /ኰ፣ጐ፣ቈ፣ኈ/ ፊደሎች አሉት:: 20 ፍንድቅ ፊደላትን /ሏ፣ ሟ፣ ሷ፣ ሯ…./ በመጨመር የአገልግሎት አድማሱን ማስፋቱን በጥናታቸው ጠቅሰዋል፡፡ በዚህም መሠረት 278 ድምጽ ወካይ ፊደላት /characters/ አሉት፡፡

atena 2006  3ከፊደላት ጋር የሚከሰቱ ችግሮችን አስመልክቶም በአማርኛ ፊደል ገበታ ላይ ተመሳሳይ ድምጽ ያላቸው ስለሚገኙ፤ በአጻጻፍ ረገድ በርካታ ልዩነቶች መኖራቸው፤ ራብዕ ድምጸት ያላቸው ከግእዙ ጋር ተመሳሳይነት ያላቸው ፊደላት መኖራቸው፤ ሳድስና ሳልስን እያቀያየሩ መጠቀም፣ ደቃልውና ፍንድቅ ፈደላትን በዝርዝር የመጠቀም ዝንባሌ፣ በመሠረታዊ ቃሉ ላይ የሌለውን ቃል መጨመር፣ የአናባቢዎች ቅጥል አለመለየት ችግሩን ይበልጥ እንዳሰፋው ጠቁመዋል፡፡

ይህ ችግር በምሁራን ዘንድ ሞክሼ ቃላት ይቀነሱ፤ አይቀነሱ የሚለው ሐሳብ ዛሬም ድረስ እያከራከረ እንደሚገኝ ገልጸዋል፡፡ አማራጮችንም በተመለከተ የኢትዮጵያ ቋንቋዎች አካዳሚ በ1973 ዓ.ም. ተመሳሳይ ድምጽ ያላቸው ፊደሎች ከገበታው ላይ ተቀንሰው በአንድ ፊደል ብቻ ይወከሉ የሚል ሲሆን፣ የቤተ ክህነት ሊቃውንት አቋም ደግሞ ፊደላት የፈጣሪን ቸርነት የሚገልጹ እና ከእሱ የተገኙ ስለሆኑ ሁሉም ጠንቅቆ ሊጽፋቸው ይገባል እንጂ በፍጹም ሊቀነሱ አይገባም፡፡ ፊደላቱ በሙሉ መንፈሳዊ፣ ተፈጥሯዊና ሙያዊ ትርጓሜ ስላላቸው ያንን ያጣሉ በማለት ይገልጻሉ፡፡

አማርኛ እንዴት ሥርዓተ ጽሕፈቱን ይጠብቅ የሚለውን እንደመፍትሔ ሲያቀርቡም የአማርኛ ሥርዓተ ጽሕፈት መጠበቅ ይገባዋል፡፡ ይህ ሊሆን የሚችለው ግን እየተጠቀምንበት የሚገኘውን የግዕዙን ሥርዓተ ሰዋሰውና የትውስት ቃላት እንዳሉ መጠበቅ ሲቻል ነው ብለዋል፡፡

የአማርኛ ፊደል የሚጽፍ ሁሉ ፊደላቱን እንዲጠነቀቅ ማስተማር፣ በባለሙያ የተሠናዱ የሥርወ ቃላት መዝገበ ቃላት እና የሰዋሰው መጻሕፍትን ማዘጋጀት፣ ያሉት ፊደላት እስካሁን ድረስ ሲጻፉ ኖረዋል በዚህም እጅግ በርካታ መጻሕፍትና የሥነ ጽሑፍ ውጤቶች ተመርተዋል፣ አገልግሎትም እየሰጡ ስለሚገኙ የፊደላቱ መብዛትና መመሳሰል አሳሳቢ እንዳልሆነና ሥርዓተ ጽሕፈቱን ከቅድመ ትምህርት ቤት ጀምሮ በየደረጃው ወጥነት ባለው መንገድ ማስተማር ወዘተ.. እንደመፍትሔ አቅርበዋል፡፡

የመጨረሻው ጥናት ክርስቲያናዊ ጾም በሰው ልጅ ጤና ላይ የሚያሳድረው ተጽእኖ ጾም ከተለያዩ ሃይማኖቶች አንጻር በሚል በዲያቆን ታደሰ አለሙ በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ FDS እና የሥነ ምግብ የዶክትሬት ተማሪ ቀርቧል፡፡ በቀረቡ ጥናቶች ላይ በርካታ ሐሳቦችን በማንሳት ውይይት ተደርጎባቸዋል፡፡ 

 

በመጨረሻም የማኅበረ ቅዱሳን የጥናትና ምርምር ማእከሉ ከቤተ ክርስቲያናችን ሊቃውንትና ከተመራማሪ ምሁራን የሚቀርቡለትን ጥናቶች ጠቃሚነታቸውን መርምሮ ለውይይት ማቅረቡን እንደሚቀጥል፤ አቅሙ ያላቸው ተመራማሪዎች ለቤተ ክርስቲያን የሚጠቅሙ ምርምሮችንና ጥናቶችን እንዲያቀርቡ ማእከሉ እንደሚያበረታታ የማእከሉ ሰብሳቢ ዶ/ር አባተ መኩሪያው ገልጸዋል፡፡