ወጣትነትና ታማኝ አገልጋይነት

ወጣትነትና ታማኝ አገልጋይነት

ክፍል ሁለት

በዲ/ን ወልደ ቂርቆስ ደሳለኝ

   . አልችልም/አይገባኝም ማለት

ትሕትና ራስን ዝቅ ማድረግ ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በመዋዕለ ሥጋዌው በተግባር ሠርቶ፣ በቃል አብራርቶ፣ በምሳሌ አጉልቶ ያስተማረን፤ አባቶችም በመንፈሳዊ ክብር ከፍ ከፍ ያሉበት ታላቅ ጸጋ ነው፡፡ ስለዚህም ነው ቅዱሳት መጻሕፍት ደግመው ደጋግመው ስለ ትሕትናና ራስን ዝቅ ስለማድረግ በአጽንዖት የሚነግሩን፡፡ “ትሕትናና እግዚአብሔርን መፍራት ባለጠግነት፣ ክብር፣ ሕይወትም ነው” እንዲል (ምሳ. ፳፪፥፬)፡፡ በመንፈሳዊ አገልግሎት ራስን ዝቅ አድርጎ ቅድሚያ ለሌሎች መስጠት የተገባ እንደሆነ ብርሃነ ዓለም ቅዱስ ጳውሎስ “እያንደንዱ ባልንጀራው ከርሱ ይልቅ እንዲሻል በትሕትና ይቁጠር” (ፊልጵ. ፪፥፫) ሲል ይነግራል፡፡

ነገር ግን ትሕትናችን፣ ራስን ዝቅ ማድረጋችን ለእይታ እታይ ባይነትና ከንቱ ውዳሴ ሰለባ የሚያደርገን ከሆነ በልቡናችን አንዳች የትሕትና ፍሬ ሳይኖር ውስጣችን በትዕቢት ወደ ላይ ተወጥሮ ውጫዊ አካላችን ለብቻው የሚያጎነብስ ከሆነ ትሕትናችን ለምድራዊ ክብር መሻት፣ ዓለማዊ ሀብትን በማየት አለዚያም ራሳችንን ከኃላፊነት ከአገልግሎትና መታዘዝ ለመሸሽ የመደበቂያ ምሽግ ሆኖ ካገለገለ በውኑ ይህንን በቅዱሳት መጻሕፍት ሚዛንነት ትሕትና ነው ማለት አይቻልም፡፡ በዘመናችን ብዙ ወጣቶች ወደ ቤተ ክርስቲያን ቀርበው በአገልግሎት ተሳትፈው የበረከት ተቋዳሽ እንዳይሆኑ ትልቅ እንቅፋት እየሆነባቸው ያለ ጉዳይ ትሕትናን የሚመስል፣ ነገር ግን ትሕትና ያልሆነ የአልችልም ባይነት ስሜት፣ ራስን ዝቅ በማድረግ እየተደበቀ ከኃላፊነትና ከአገልግሎት የመሸሽ ልማድ ነው፡፡

የሰው ልጅ በአስተሳሰቡና በአመለካከቱ አልችልም፣ ደካማ ነኝ የሚል ስሜት ካሳደረ፣ የእግዚአብሔርን ረዳትነት ተማምኖ “ወደ እርሱ ቅረቡ ያበራላችሁማል፣ ፊታችሁም አያፍርም” (መዝ. ፴፫፥፭) እንዲል መዝሙረኛው ቅዱስ ዳዊት ወደ ቤተ ክርስቲያን ቀርቦ ለተግባር፣ ለድርጊት መቸም ቢሆን ውስጣዊ መነሣሣትና ቁርጠኝነት አይኖረውም፡፡ ሰው የሚያስበውን ያንኑ ይመስላል እንዲል አስተሳሰባችን ከተግባራችን ጋር የተቆራኘ ነው፡፡ በቤተ ክርስቲያናችን ይህ የአስተሳሰብ ደካማነት፣ እምነት ጎደሎነት ወይም የጥርጥር መንፈስ ተብሎ ይገለጻል፡፡ በውኃ ላይ መራመድን ሽቶ በመሐል በመጠራጠሩ ሊሰምጥ የነበረውን ቅዱስ ጴጥሮስን ማሰብ ያስፈልጋል፡፡ ሊቀ ሐዋርያት ቅዱስ ጴጥሮስ በጥብዓት ከተጓዘ በኋላ በመሐከል ግን የጥርጠር መንፈስ ወደ እርሱ ገባና እምነተ ጎደሎ በመሆኑ እንደተገሠጸ ቅዱስ መጽሐፍ ይነግረናል (ማቴ. ፲፬፥፳፬)

በእርግጥ አበው ነቢያት፣ ሐዋርያት፣ ሊቃውንት፣ ጻድቃን ሰማዕታት ለታላቅ አገልግሎትና ተልእኮ ከፈጣሪ ጥሪ ሲደረግላቸው ከልብ በመነጨ መንፈሳዊ ትሕትና “ይህንን ጥሪ እቀበል ዘንድ እኔ ምንድን ነኝ፤ እኔ ደካማ ሰው ነኝ” ሲሉ የተሰጣቸው ተልእኮ ታላቅነትን፣ የእነርሱን ደካማነት አሳይተዋል፡፡ ነገር ግን ይህንን ብለው ከኃላፊነትና ከአገልግሎት አልሸሹም ይልቅ ሰማያዊ ተልእኳቸውን በትጋትና በብቃት ተወጡ እንጂ፡፡ ሊቀ ነቢያት ሙሴ ሕዝበ እስራኤልን ከፈርዖን ግፍና ባርነት ነጻ ያወጣ ዘንድ መመረጡን በሰማበት በዚያች ቅጽበት “እኔ ኮልታፋ ምላሴም ጸያፍ የሆነ ሰው ነኝ፤ ትናንት ከትናንተ ወዲያ ባሪያህንም ከተናገርከኝ ጀምሮ አፈ ትብ ሰው አይደለሁምን፡፡” (ዘጸ. ፬፥፲) እንዲል፡፡ ይህንን ማለቱ ተልእኮውን ከመወጣት አላስቀረውም፡፡

ከሁሉም በላይ ብዙ ወጣቶች “እኔ ገና ጀማሪ ነኝ፤ እኔ ምንም አልጠቅምም፣ እኔ ለቤተ ክርስቲያን የምሆን ሰው አይደለሁም” ሲሉ ለሰውም ለራሳቸውም ኅሊናም እየነገሩ በትሕትና ሰበብ በቅድሚያ ከአገልጋይነት፣ እየቆዩም ከጾም ጸሎት ሸሽተው የጠፉ ብዙ ሰዎች ናቸው፡፡ ስለዚህ አንድ አገልጋይ “ሁል ጊዜም ስደክም ያን ጊዜ ኃይለኛ ነኝ” (፪ኛቆሮ. ፲፪፥፲) በማለት ሐዋርያው እንዳስተማረን እርሱም ለበለጠ ትጋት፣ ለበለጠ አገልግሎት መነሣሣት ይገባዋል፡፡ ምክንያቱም በእግዚአብሔር ቤት ታናሽና ታላቅ ኃላፊነት ያለበትና የሌለበት ሰው የለም፡፡ አምላካችን በሁላችንም ደጅ ቆሞ “እነሆ በደጅ ቁሜ አንኳኳለሁ፤ ማንም ድምጼን ቢሰማ ደጁንም ቢከፍትልኝ ወደ እርሱ እገባለሁ ከእርሱም ጋር ራት እበላለሁ፤ እርሱም ከእኔ ጋር ይበላል” (ራእ. ፫፥፳) እያለ ለበረከት ይጠራናል፡፡ ስለዚህ እያንዳንዳችን ይህን ጥሪ አክብረን የሚጠበቅብንን ተወጥተን የስሙ ቀዳሽ የመንግሥቱ ወራሽ እንድንሆን ልንተጋ ይገባል፡፡

. ተነሳሽነት ማጣትና ለነገ ማለት

የሰው ልጅ በአፍአ በሚታየው አካሉ ነገሮችን በትጋትና በብቃት ያከናውን ዘንድ አእምሮው ወይም መንፈሱ ለተግባር መነሳሳት ያስፈልገዋል፡፡ ተነሣሽነትን ከሚገድሉ ጉዳዮች አንዱና ዋነኛው ደግሞ ሥራን ወይም መንፈሳዊ አገልግሎትን ለነገ እያሉ በቁርጠኝነት አለመጀመር ነው፡፡ ቅዱስ መጽሐፍ “እነሆ የተመረጠችው ቀን ዛሬ ናት” (፪ኛቆሮ. ፮፥፪) እያለ ሲመክረን፤ በሌላው ክፍል ደግሞ ስለ ነገረ ምጽአቱ ሲያስተምረን “… የእግዚአብሔር ቀን ግን እንደ ሌባ ድንገት ትመጣለች” (፪ጴጥ. ፫፥፲) ማለቱ ነገሮችን ሁሉ ነገ አደርገዋለሁ፣ ነገ እፈጽመዋለሁ እያልን ወደ ኋላ ከማዝገም ይልቅ በቁርጠኝነት ወደፊት ልንገሰግስ እንደሚገባ የሚያስተምረን ነው፡፡

በዘመናችን ብዙ በክርስቶስ ክርስቲያን የተሰኙ ወጣቶችን ቀረብ ብለን ለምን በቅድስት ቤተ ክርስቲያን ደጀ ሰላም ተሳልመው ለመንፈሳዊ አገልግሎት እንደማይተጉ ብንጠይቃቸው የሚሰጡን አንድ ተደጋጋሚ ምላሽ አላቸው፡፡ እርሱም፡- “እያሰብከበት ነው፣ ትምህርቴን ልጨርስና፣ ይህን ላድርግና፣ ያንን ልፈጽምና፣ ወዘተ“ በማለት ይመልሳሉ፡፡ እንደዚህ ዓይነት የማይጨበጥ ምክንያት የሚፈጥሩት እንደ ነቢየ እግዚአብሔር ኢሳይያስ አገላለጽ ”እነሆኝ ጌታዬ፤ እኔን ላከኝ” (ኢሳ.፮፥፰) ማለት የማይችሉት ተነሳሽነት ከመንፈሳቸው ፈጽሞ ስለሚጠፋ ነው፡፡

በጥቅሉ በመንፈሳዊ አገልግሎት ብቻ ሳይሆን ወጣቶች በዘመናችን ለትምህርት፣ ለሥራ፣ ከፍ ሲልም ለግል እንክብካቤና ንጽሕናን ለመጠበቅ የሚሆን ተነሣሽነት ሲጎድላቸው ይስተዋላል፡፡ ይህ ተነሳሽነት ማጣት የብዙ ተወራራሽ መንስኤዎች ድምር ውጤት ነው፡፡ ከእነዚህም መካከል ለዘመናዊነት ያለን የተዛባ አመለካከት የወላጆች የልጅ አስተዳደግ ሁኔታ፣ በቴክኖሎጂ ከመበልጸግ ጋር ተያይዘው የመጡብን የማኅበራዊና ኤሌክትሮኒክስ ሚዲያ ሱሰኝነት ትልቁን ድርሻ ይስዳሉ፡፡ ከዚያ ባለፈ ግን የሰው ልጅ ለመኖር፣ ለመሥራት፣ ለመለወጥ፣ ብሎም ለዘለዓለማዊ ሕይወት የሚያበቃውን የጽድቅ ሥራ ለመሥራት ይተጋ ዘንድ ክርስቲያናዊ ዕሴት ሊኖረው ይገባል፡፡ ያም ሲሆን ነው “በሚያስችለኝ በክርስቶስ ሁሉን እችላለሁ” (ፊል. ፬፥፲፫) በማለት ፈተናና እንቅፋቱን ተራምደን ወደ ዘለዓለም ሕይወት የሚደረገውን መንፈሳዊ ሩጫ በቁርጠኝነት ጀምረን በድል የምናጠናቅቀው፡፡

. በቀላሉ ተስፋ መቁረጥ

ሌላውና በአራተኛነት የምናነሣው ወጣቶች ወደ ቤተ ክርስቲያን ቀርበው ለመንፈሳዊ አገልግሎት እንዳይተጉ እንቅፋት የሆናቸው ጉዳይ በቀላሉ ተስፋ የመቁረጥ አባዜ ነው፡፡ ብዙ ወጣቶች የሥላሴን ልጅነት በዐርባና በሰማኒያ ቀናቸው አግኝተው ስመ ክርስትናም ተሰይሞላቸው በስብከተ ወንጌል ተነቃቅተውና ልባቸው ተሰብሮ በታላቅ ተነሳሽነት ለአገልግሎት ወደ ቤተ ክርስቲያን ከመጡ በኋላ በቀላሉ በጥቃቅን ፈተናዎች ተዳክመው ተስፋ ይቆርጣሉ፡፡

እንደዚህ ዓይነት ወጣቶች የሀገራችን እናቶች በንግሥ ሰዓት በዝማሬአቸው ታቦተ ሕጉን ሲያጅቡ “አልጋ በአልጋ ነው መንገዱ” እንዲሉ መንፈሳዊ አገልግሎት ሁሌም በበረከት በድንቃ ድንቅ ተአምራት ብቻ የተሞላ፣ ሁሌም የዝማሬና የምስጋና በዓል፣ ሆሳዕና እንጂ ከሆሳዕና ማግሥት ሕማም፣ ድካም፣ መራብ፣ መጠማት፣ መገረፍ፣ መሰቀል ያለበት መሆኑን እጅግ አብዝተው ይዘነጉታል፡፡ ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በመዋዕለ ሥጋዌው የዚህ ዓለም ቆይታችን በፈተና የተሞላ እንደሆነ በቃልና በምሳሌ ከማስተማሩም ባሻገር በገዳመ ቆሮንቶስ ዐርባ መዓልትና ዐርባ ሌሊት ቆይቶ በተግባር ተፈትኖ አሳይቶናል፡፡ (ማቴ. ማቴ. ፬፥፩)፡፡ ለዚህም ነው “በብዙ ድካምና መከራ ወደ እግዚአብሔር መንግሥት እንገባ ዘንድ ይገባናል” (ሐዋ.  ፲፬፥፳፪)፡፡ ተብሎ የተጻፈው፡፡

የወይን ፍሬ ይሰበሰብ ዘንድ የሚሻ አንድ አትክልተኛ ያን ለዐይን ዕይታ እንኳ የሚያስጎመዥ ፍሬ ይለቅም ዘንድ የተከለውን ተክል ከለጋነት ወጥቶ አድጎና በልጽጎ ፍሬ የሚያፈራበትን ጊዜ በትዕግሥት እየጠበቀ ካልተንከባከበው ፍሬውን ይቀምስ ዘንድ እንዴት ይችላል? አንድ መንፈሳዊ አገልጋይም “በትዕግሥታችሁም ነፍሳችሁን ገንዘብ ታደርጓታላችሁ” (ሉቃ. ፳፩፥፲፱) እንደተባለ እንዲሁ አገልግሎቱ በእግዚአብሔር ፈቃድ ለፍሬ እስኪበቃ በትዕግሥትና በተስፋ መጠበቅ ይገባዋል፡፡ የቤተ ክርስቲያናችን ታላቁ ሊቅ ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ ለአንድ መንፈሳዊ አገልጋይ ሊኖረው ስለሚገባው ተስፋ ማድረግና ትዕግሥት ሲያስረዳ ይላሉ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ሺኖዳ በሦስተኛው መጽሐፋቸው “አንድ ፅንስ ምሉእ ሰው ሆኖ ይህችን ምድር ይቀላቀል ዘንድ ወራትን በእናቱ ማኅፀን መቆየት(መታገስ) ካስፈለገው፤ እንደዚሁም መንፈሳዊ ፅንሱ ሳይቋረጥ በአግባቡ ያድግ ዘንድ አንድ አገልጋይ በትዕግሥት ሊጠብቅ ይገባዋል፡፡’ ይላሉ (Spiritual Ministry: HH. Pope Shenoda III) ስለሆነም እግዚአብሔር በአንድም በሌላም መንገድ ወደ ደጀ ሰላሙ ጠርቶን አገልግሎት የጀመርን ወጣቶች ነገሮችን ሁሉ ከውጪ በርቀት ስንመለከታቸው እንደነበር ባይሆኑ እንኳን ድካማችን ለፍሬ ይበቃ ዘንድ ብዙ ዘመናትን ቢጠይቅም “መከራ በተቀበልሁ ጊዜ ወዲያውኑ እበረታለሁና” (፪ኛቆሮ. ፲፪፥፲) እንዲል ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ በእግዚአብሔር ኃይል ልንተጋ ይገባል እንጂ ተስፋችንን አቀዝቅዘን ለጠላት ዲያብሎስ እጅ መስጠት አይገባም፡፡

ይቆየን፡፡

የአሜሪካ ማእከል ያሠለጠናቸውን የግቢ ጉባኤ ተተኪ መምህራን አስመረቀ

በማኅበረ ቅዱሳን የአሜሪካ ማእከል የግቢ ጉባኤ ማስተባበሪያ በእንግሊዝኛ ቋንቋ የደረጃ ፩ የግቢ ጉባኤ ተተኪ መምህራንን አሠልጥኖ አስመረቀ፡፡

የማእከሉ የግቢ ጉባኤ ማስተባበሪያ ከአትላንታ ንዑስ ማእከል ጋር በመተባበር ከተለያዩ ግቢ ጉባኤያት ለተውጣጡና ተተኪውን ትውልድ የሚወክሉ ፲፭ የግቢ ጉባኤ ተማሪዎች የበጋ (Summer) የተተኪ መምህራን ሥልጠናን ለተከታታይ ፲፭ ቀናት በመስጠት አስመርቋል፡፡ ከሰኔ ፲፯ ቀን ፳፻፲፮ እስከ ሐምሌ ፩ ቀን 2016 ፳፻፲፮ ዓ. ም (June 24, 2024 – July 08, 2024) በአትላንታ ከተማ በእንግሊዝኛ ቋንቋ ለመጀመሪያ ጊዜ የተሰጠው ሥልጠናም በታቀደው መሠረት ውጤታማ እንደነበር ሥልጠናውን ያስተባበረው የአሜሪካ ማእከል የግቢ ጉባኤያት ማስተባበሪያ ገልጿል፡፡  

ሠልጣኞቹ የወሰዷቸው ፭ የትምህርት ዓይነቶች ሲሆኑ እነርሱም፡- ነገረ ሃይማኖት (Dogmatic Theology)፣ የቤተ ክርስቲያን ታሪክ (Church History)፣ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት (Bible Study)፣ ነገረ ቅዱሳን (Hagiology) እና ሐዋርያዊ ተልእኮና የስብከት ዘዴ (Apostolic service & Homiletics) ናቸው::

ሥልጠናው በነገረ መለኮት ትምህርት ከፍተኛ ልምድ ባላቸው መምህራን የተሰጠ ሲሆን ከእነዚህም መምህራን መካከል፡- ቀሲስ ዶ/ር አምሳሉ ተፈራ ፣ በኩረ ፍሥሐ ቀሲስ ዶ/ር ኃይለየሱስ አስናቀና ቀሲስ ዓለማየሁ ደስታ ይገኙበታል፡፡ ከሥልጠናው በተጨማሪም ማታ ማታ ሠልጣኞቹ ለሚያነሷቸው የተለያዩ ጥያቄዎች ከቅድስት ቤተ ክርስቲያናችን መምህራን መካከል ዲን ብርሃኑ አድማስ፣ ዶ/ር አማኑኤል አስፋው፣ ዲ/ን ዮሴፍና ሌሎችም ተጋባዥ መምህራን ምላሽ በመስጠት፤ እንዲሁም የሕይወት ተሞክሮዎቻቸውን በማካፈል ልምድ እንዲቀስሙ ተደርጓል፡፡

ተማሪዎቹ የተሰጣቸው ሥልጠና የነበራቸውን መጠነኛ ዕውቀትና ክህሎት እንዲያዳብሩ እንደረዳቸው፣ በዚህም መደሰታቸውንና ለማገልገልም ዝግጁ መሆናቸውን ገልጸዋል፡፡ በመጨረሻም የተሰጧቸውን ተከታታይ ትምህርቶች (Course) ካጠናቀቁ በኋላ የምስክር ወረቀትና የመጽሐፍ ቅዱስ ስጦታ ተበርክቶላቸዋል፡፡

ወጣትነትና ታማኝ አገልጋይነት

ክፍል አንድ

በዲ/ን ወልደ ቂርቆስ ደሳለኝ

የሰው ልጅ በዚህች ምድር ላይ በሚኖረው ቆይታ ብዙ ኃይልና መነሳሳት የተሞላበት ዘመኑ የወጣትነት ዘመን ነው፡፡ የሰው ልጅ ከሌላው ጊዜ በተለየ አዳዲስ ግኝቶችን ለማበርከት፣ እጅግ ከባድና ውስብስብ የሚመስሉ ጉዳዮችን በድፍረት ለመጀመርና ለመሞከር ታላቅ ወኔና ድፍረት የታጠቀበት ዘመን ቢኖር የወጣትነት ዘመን ነው፡፡ የመመራመር ጉጉት፣ የማወቅ፣ የማገልገል ልዩ ትጋትና ቁርጠኝነትን የተላበሰ ዘመንም የሚታየው በወጣትነት ዘመን ነው፡፡ አካላዊ ማኅበራዊ፣ መንፈሳዊ ብሎም ምጣኔ ሀብታዊ ለውጦች በስፋት የሚስተናገዱበት፣ ውስብስብ ፈተናዎች የሚገጥሙበት ዘመን ቢኖር የወጣትነት ዘመን ነው፡፡ ችኩልነት፣ እብሪተኝነት፣ አልታዘዝ ባይነት የሚፈታተኑት በወጣትነት ዘመን ነው፡፡ ለሉላዊነት አስተሳሰብ፣ ለረቀቀ የቴክኖሎጂ አቅርቦት፣ ለባህል ብረዛ፣ ለሥራ አጥነት፣ ለቤተሰብ ጫና የሚጋለጠውም በወጣትነት ዘመን ላይ ነው፡፡

ይህንን ወጣትነት ብዙዎች እንደተጠቀሙበት ሁሉ ብዙዎችም መልካም ፍሬ የማያፈራ ዛፍ ተብለው “እንግዲህስ ምድራችንን እንዳታቦዝን ቁረጣት” (ሉቃ. ፲፫፥፮) እንደተባለች እንደዚያች በለስ የመቆረጥ ፍርድ ተፈርዶባቸዋል፡፡ በዚህ የወጣትነት ዘመን አቤል የፈጣሪውን ንጽሐ ባህሪይነት ተረድቶ ቀንዱ ያልከረከረውን፣ ጥፍሩ ያልዘረዘረውን፣ ጸጉሩ ያላረረውን ንጹሕ የመሥዋዕት ጠቦት በንጽሕና አቅርቦ ከእግዚአብሔር ዘንድ አትርፏል፡፡ ወንድሙ ቃየልም በንዝህላልነትና ግድየለሽነት ከሕይወት መስመር ወጥቶ ተቅበዝባዥነትን ተከናንቧል፡፡ (ዘፍ.፬፥፫-፲፭)፡፡ በወጣትነት ዮሴፍ እንደ ወርቅ በእሳት ተፈትኖ ንጽሕናውን አሳይቶበታል፤ በዚህ በወጣትነት ራሱን ለታይታና ለይሰሙላ ባልሆነ ፍጹም ትሕትና ከወንድሞቹ ሁሉ በታች ራሱን ዝቅ አድርጎ በንግሥና ከፍ ከፍ ብሎበታል፡፡ (ዘፍ.፴፱፥፩)፡፡ በዚያም በምድርና በሰማይ ሠላሳ፣ ስድሳ፣ መቶም ያማረ ፍሬ አፍርቶ ዝገት የማይበላውን፣ ሌቦች የማይሰርቁትን መዝገብ አከማችቶበታል፡፡

በዚሁ የወጣትነት ዘመን እንደ ጢሞቴዎስ ያሉት ትጉሃን ደቀ መዛሙርት በትጋት የመምህራቸውን ፈለግ ተከትለው ለክርስቲያን ወገኖቻቸው ተርፈውበታል፤ በመምህራቸውም እንዲህ ተወድሰዋል”በአንተ ያለው ግብዝነት የሌለበትን እምነትህን አስባለሁ” (፪ጢሞ. ፩፥፲፭)፡፡ በወጣትነት ከሰማያዊው ክብር ይልቅ ወደ ምድራዊው ድሎት የመጡ እነዴማስም እንዲህ ተብለዋል”ዴማስ ይህንን የዛሬውን ዓለም ወድዶ እኔን ተወኝ፤ ወደ ተሰሎንቄም ሄደ” (፪ጢሞ.፬፥፲)፡፡ በዚሁ የወጣትነት ዘመን ነው እንደ ሊቀ ሰማዕታት ቅዱስ ጊዮርጊስ ያሉት መከራና ግፍን ሳይፈሩ በጥብአትና በእምነት ለታላቅ ድልና መንፈሳዊ አክሊል የበቁት፡፡ እንዲያው በጥቅሉ ይህንን የወጣትነት ዘመን ፈቃደ ሥጋን ለፈቃደ ነፍስ አስገዝተው ለክብር ሞት፣ ለዘለዓለም ሕይወት የበቁ ብዙዎች እንደሆኑ ቅዱሳት መጻሕፍት ይመሰክራሉ፤ አበው ሊቃውንትም ያስተምራሉ፡፡

በውኑ የእኛስ የወጣትነት ዘመን የትጋት ነውን? ከላይ እንደተጠቀሱት ደጋግ አበው ቅዱሳን የተሰጠንን መክሊት ሠርተን፣ ደክመን፣ ወጥተን ወርደን ለማትረፍ የጣርንበት ነው? ወይስ የተሰጠንን ጸጋና መክሊት ቀብረን ያው ያለን እንኳ ተወስዶብን ለቅሶና ጥርስ ማፋጨት ወዳለት ወደማይጠፋ እሳት ለመጣል እየጠበቅን ነው? በውኑ በወጣትነቱ ደግና ታማኝ አገልጋይ (ገብር ሔር) ማን ነው? ወጣቶች ወደ መንፈሳዊ አገልግሎት እንዳይቀርቡስ እንቅፋት የሆናቸው ምንድን ነው? ተግተው ለአገልግሎት የመጡት ወጣቶችስ እየገጠማቸው ያለው ፈተናና ተግዳሮት ምንድነው? በወጣትነት ታማኝ መንፈሳዊ አገልጋይ ለመሆንስ ምን ማድረግ አለባቸው? የሚሉትን ነጥቦች በዚህ ጽሑፍ ለመዳሰስ እንሞክራለን፡፡ በቅድሚያ ግን ወደ ቤተ ክርስቲያን እንዳንቀርብ፣ ለማገልገል ዝግጁ እንዳንሆን እንቅፋት የሆኑን ምክንያቶችን በጥቂቱ እንመልከት፡-

የመንፈሳዊ አገልግሎት እንቅፋቶች

በዘመናችን አብዛኛዎቹ ወጣቶች ከእግዚአብሔር ቤት እየሸሹ ውሎና አዳራቸው በመንፈሳዊ ሕይወታቸው ወደማይጠቀሙበት አቅጣጫ በማምራት ከዓላማቸው ተሰናክለው ለጤና መታወክ በሚያበቋቸው አልባሌ ቦታዎች ይሆናሉ፡፡ ድምጿን ከፍ አድርጋ ለምትጣራ ቤተ ክርስቲያን ልባቸውን ከመስጠት ይዘገያሉ፡፡ ወጣቶች ወደ አገልግሎት እንዳይገቡ እንቅፋት ከሚሆኑ ነገሮች መካከል የሚከተሉትን ጠቅለል አድርገን እንመልከት፡-

፩. ቤተ ክርስቲያንን አለማወቅ

፪. አልችልም/አይገባኝም ማለት

፫.ተነሳሽነት ማጣትና ለነገ ማለት

 ፬. በቀላሉ ተስፋ መቁረጥ

፩. ቤተ ክርስቲያንን አለማወቅ

ብዙ ወጣቶች ስብከተ ወንጌልን ልብ ሰጥቶ ከመታደም፣ ቅዱሳት መጻሕፍትን ጊዜ ሰጥቶ በተመስጦና በጥልቀት አንብቦ ከመረዳት፣ ሊቃውንትን፣ መምህራነ ወንጌልንና ካህናትን ቀርቦ ከመጠየቅ ይልቅ በተለያየ ሰበብና ምክንያት ራሳቸውን ስላሸሹ ቤተ ክርስቲያንን በውል ማወቅ፣ መረዳት ሲከብዳቸው ይስተዋላል፡፡ ቤተ ክርስቲያንን እናውቃለን ብለው የሚያስቡት እንኳን ዓለም ከምታቀርብላቸው ሥጋዊ ፍላጎትን ከሚያነሣሱ ከማኅበራዊ ትስስር ገጾች በለቃቀሟቸውና በቃረሟቸው የተቆራረጡና ምሉእ ያልሆኑ ሕጸጽና ግድፈት ያለባቸውን መረጃዎች በመሰብሰብ ቤተ ክርስቲያን ሐዋርያዊ ተልእኮዋን በውል ተረድተዋል ለማለት ይቸግራል፡፡

በዚህ ጽሑፍ ቤተ ክርስቲያንን አለማወቅ ስንል እግዚአብሔርንና የእግዚአብሔር ፈቃድ፣ የቤተ ክርስቲያንን ዶግማዊና ቀኖናዊ ድንጋጌዎች፣ አካሄዷንና አሠራሯን አለማወቅን ለመግለጽ ነው፡፡

ወጣቶች ቤተ ክርስቲያን ምንድን ናት? ተልእኮዋስ ምንደነው? ቤተ ክርሴቲያን ከእኔ ምን ትፈልጋለች? እኔስ ከቤተ ክርስቲያን የማገኘው ጥቅም ምንድነው? እነዚህን ለመሰሉ መሠረታዊ ጥያቄዎች ለኅሊናቸው በውል ምላሽ መስጠት ሲቸግራቸው ይስተዋላል፡፡ ለአንዳንድ ወጣቶች ቤተ ክርስቲያን የእነ አቡነ እገሌ፣ አባ እገሌ፣ ሰባኪ (ዘማሪ) እገሌ ናቸው፡፡ እነዚህ ዓይኑንና ተስፋውን የጣለባቸው ሰዎች ፈተና አድክሟቸው የዓለም አንጸባራቂ ውበት ስቦ አታሏቸው እንደ  ዴማስ (፪ጢሞ.፬፥፲) ወደ ኃላ መጓዝ፣ መሰናከል በጀመሩ ጊዜ ቀድሞውኑ ቤተ ክርስቲያንን በእነዚህ ሰዎች ትከሻ ላይ ወስነዋት ነበርና የእነርሱን ድካምና ጥፋት ከቤተ ክርሰቲያን ለይቶ ማየት ያቅታቸዋል፡፡ በዚህም ምክንያት ከሕወት መንገድ ተደናቅፈው ይወድቃሉ፡፡

ለዚህም ነው በየአድባራቱ፣ ማኅበራትና ሰንበት ትምህርት ቤቶች “የእገሌ መዝሙር ካልተዘመረ፣ እገሌ የተባለ ሰባኪ ካልመጣ፣ አባ እገሌ ካልተሾሙ፣ አቡነ እገሌ ካልተሻሩ አላገለግልም፣ አልመጣም …” ወዘተ በማለት ቀስ በቀስ ከቤተ ክርስቲያን እቅፍ የወጡና እየወጡ ያሉ ምእመናን ቁጥራቸው እየበዛ የመጣው፡፡ ነገር ግን ቤተ ክርስቲያን ከእነዚህ ነገሮች በላይ የሆነች አንዲት፣ ቅድስት፣ ሐዋርያዊትና ኩላዊት (ዓለም አቀፋዊት) ናት፡፡ (ሊቀ ጉባኤ አባ አበራ፤ ትምህርተ ሃይማኖትና ክርስቲያናዊ ሕይወት)፡፡ ለዚህም ነው አበው በሃይማኖት ጸሎት ደግመን ደጋግመን እንዘክረው ዘንድ “ከሁሉ በላይ በምትሆን ሐዋርያት በሰበሰቧት በአንዲት ቅድስት ቤተ ክርስቲያን እናምናለን” ብለው ያስቀመጡልን፡፡

 ቤተ ክርስቲያንን አለማወቅ በሦስት ክፍሎች ከፍለን ልናየው እንችላለን፡፡

የመጀመሪያው ስለ ቤተ ክርስቲያን ምንም ዓይነት ዕውቀትና ግንዛቤ አለመኖር ነው፡፡ አንዳንድ ወጣቶች ወላጆቻቸው በልጅነታቸው ካመላለሷቸው በኋላ እግሮቻቸው ደጀ ሰላምን አልረገጡም፡፡ ነገር ግን በአንገታቸው ማዕተብ አጥልቀው፣ በስማቸውም ክርስቲያን፣ የክርስቶስ ወገን ተሰኝተዋል፡፡ እንደነዚህ ዓይነት ሰዎች ቤተ ክርስቲያን ምን እንደሆነች፣ ተልእኮዋ ምን እንደሆነ፣ በዚህ ወቅት ቤተ ክርስቲያን ምን ሁኔታ ላይ እንደምትገኝ አያውቁም፤ የማወቅ ፍላጎታቸውም የደከመ ነው፡፡ እናም መቼም ቢሆን ውስጣቸው በቤቱ ቅናት ተቃጥሎ “እስመ ቅንዐተ ቤትከ በልዐኒ፤ የቤተህ ቅናት በልቶኛልና” (መዝ.፷፰፥፱) ብለው ለአገልግሎት ይነሡ ዘንድ፣ የሀገር፣ የቤተ ክርስቲያን መጥፋት አሳዝኗቸው ወደ መንፈሳዊ ቁጭት ውስጥ ይገቡ ዘንድ “ኢታርእየነ ሙስናሃ ለኢየሩሳሌም፤ የኢየሩሳሌምን ጥፋት አታሳየን” ሊሉ አይችሉም፡፡

በሁለተኛ ደረጃ የበቤተ ክርስቲያንን አስተምህሮዋን፣ ዶግማዋንና ቀኖናዋን በግል ምልከታቸው በሥጋዊ ድካማቸው ደረጃ ዝቅ አድርገው “ምን አለበት፣ ምን ችግር አለው፣ ብዙ ባናካብድ” በሚሉ ሰበቦች ታስረው ቤተ ክርስቲያንን ያወቁ የሚመስላቸው ነገር ግን ያላወቁ ወጣቶች ናቸው፡፡ ለእነዚህ ዓይነቶቹ ምእመናን ቤተ ክርስቲያን የምታስፈልጋቸው ሥጋዊ ፈተናዎች (ሥራ ማጣት፣ ከወዳጃቸው ጋር መጋጨት፣ ሥጋዊ ደዌ፣ የኑሮ መክበድ፣ የትምህርት ጉዳይ፣ …) ሲያስጨንቃቸው ብቻ ነው፡፡ የቤተ ክርስቲያን የሰማያዊና የዘለዓለማዊ ሕይወት ሰጪነት፣ የቤተ ክርስቲያን የነፍስ መጋቢነት አይታያቸውም፡፡

ሩጫቸው ምድራዊ ስኬት እስከ ማግኘትና መጎናጸፍ ድረስ ብቻ ነው፡፡ የቤተ ክርስቲያን ጉዳይ አሳስቧቸው ሳይሆን ለአገልግሎት የሚመጡት ለሥጋዊ ዓላማ ብቻ ነውና ጥያቄአቸው መልስ ሲያገኝ (ሥራ ወይም ትዳር ሲይዙ፣ …) ከቤተ ክርስቲያንም ይኮበልላሉ፡፡

በሦስተኛ ደረጃ ቤተ ክርስቲያንን ባልተረጋገጠና በተምታታ መረጃ በአላዋቂዎች ትምህርት ተመርኩዘው እናውቃለን የሚሉት ናቸው፡፡ በዚህኛው የዕውቀት ደረጃ ብዙ ወጣት ምእመናን ቤተ ክርስቲያን ለዘመናዊነት፣ ሠርቶ ለመለወጥ፣ ራስን ለማሳደግ ጠላት አድረገው ይስሏታል፡፡ መንፈሳዊነትንና ለቤተ ክርስቲያን አሳቢነትን ራስን ካለመንከባከብ፣ ንጽሕናን ካለመጠበቅ እና ሥራና ትምህርትን እርግፍ አድርጎ ትቶ የብህትውና ኑሮ ከመኖር ጋር የሚያዛምዱ ናቸው፡፡ እነዚህ ሰዎች በሕይወታቸው ውስጥ እግዚአብሔርን በፈራጅነቱ፣ በቀጪነቱ ፈርተው ያመልኩታል እንጂ ከፍቅር የመነጨ ፈሪሃ እግዚአብሔር አይኖራቸውም፡፡ የእንደዚህ ዓይነት ሰዎች ሌላው መለያ ባሕርያቸው በመንፈሳዊ መንገዳቸው ፊት ለፊት የሚታያቸው የክርስቶስ ሕይወት፣ አልያም የአበው ቅዱሳን ተጋድሎ አይደለም። ከዚያ ይልቅ በቅርብ የሚያገኙትን አገልጋይ የፍጹምነት ምሳሌ አድርገው ይስሉታል፡፡ እነዚህ ወጣቶች ከቤተ ክርስቲያን ይልቅ እነዚህን ሰዎች ከማምለክ ባልተናነሰ ሲያዳምጡ ይስተዋላል፡፡ በአጠቃላይ ሦስቱም ትክክለኛ መንገዶች አይደሉም፡፡

ይቆየን፡፡

ምንጭ፡- ሐመር መጽሔት ፳፯ ዓመት ቁጥር ፪ ሰኔ ፳፻፲፩ ዓ.ም

የእመቤታችን ትንሣኤ እና ዕርገት

“በጊዜውም ያለ ጊዜውም ጽና” (፪ኛጢሞ. ፬፥፪)

በእንዳለ ደምስስ

ጊዜ እግዚአብሔር ለሰው ልጆች ከሰጣቸው በረከቶች አንዱ ነው፡፡ ቀኑንም በሴኮንድ፣ በደቂቃ፣ በሰዓት፣ ሰዓቱንም በቀን ለክቶና ሰፍሮ እንጠቀምበት ዘንድ ሰጥቶናል፡፡ ነገር ግን የተሰጠንን ጊዜ በአግባቡ የምንጠቀም ስንቶቻችን ነን? ሁሉንም ነገር ለማከናወን ጊዜ አስፈላጊ መሆኑን ጠቢቡ ሰሎሞን ሲገልጽም “ለሁሉ ጊዜ አለው፤ ከፀሐይ በታችም ስለሆነ ነገር ሁሉ ጊዜ አለው …” በማለት ጊዜ ለፍጥረታት ሁሉ አስፈላጊ መሆኑን ይነግረናል፡፡

የጊዜን አስፈላጊነት ከተረዳን ማንኛውም ነገር በጊዜ ውስጥ የተለካና የተወሰነ እንደመሆኑ መጠን በሰው አእምሮ ወይም ፍላጎት አሁን ይከናወን ዘንድ የምንፈልገው ነገር በእግዚአብሔር ዘንድ ግን ገና ከሆነ የእግዚአብሔርን ጊዜ በጽናት መጠበቅ እንደሚያስፈልግ ሐዋርያው ይነግረናል፡፡ “በጊዜውም ያለ ጊዜውም ጽና” (፪ኛጢሞ. ፬፥፪) በማለት፡፡የእግዚአብሔርን ጊዜ መጠበቅ ደግሞ ዋጋ ያሰጣልና በጊዜውም ያለ ጊዜውም መጽናት ይገባል፡፡

እግዚአብሔር ጊዜን ለክቶ እንደሰጠን ሁሉ የሚያስፈልገንን ሁሉ ይሰጠን ዘንድም ጊዜ አለው፡፡ ነገር ግን የሰው ልጆች ደግሞ በተቃራኒው የምንሻውን ነገር ለማግኘት እንቸኩላለን፤ ሁሉንም ነገር አሁን ካልተደረገልን ብለን ከእግዚአብሔር ጋር ክርክር የምንገጥም፣ ባይደረግልን ደግሞ ከአምላካችን ጋር ለመጣላት የምንሞክር ብዙዎች ነን፡፡ ነገር ግን በእግዚአብሔር ላይ ከማጉረምረም ይልቅ ያላደረገልን ከእኛ አንድ ነገር የጎደለ ነገር እንዳለ በመረዳት በጸሎት በመትጋት የምንሻውን ነገር እስኪሰጠን ድረስ በትዕግሥት እግዚአብሔርን ደጅ መጽናት ያስፈልጋል፡፡

ለእኛ ጊዜው ነው፤ አሁን ሊሰጠን ወይም ሊያደርግልን ይገባል ብለን እንደምንለምነው ሁሉ እግዚአብሔር ፈቃዱ ሲሆን ባልታሰበ ጊዜና ሁኔታ ውስጥም ወደ እኛ ሊቀርብና ሊያከናውንልን ይችላል፡፡ ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ወደ ጌርጌሴኖን መንደር በደረሰ ጊዜ ሁለት አጋንንት ያደሩባቸው ሰዎች ከመቃብር ቦታ ወጥተው አገኛቸው፡፡ ክፉዎች ናቸውና በዚያ መንገድ ማንም ደፍሮ ማለፍ እስከማይችል ድረስ በእነዚህ አጋንንት ባደረባቸው ሁለት ሰዎች ቁጥጥር ሥር የነበረ ቦታ ነው፡፡ ነገር ግን ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ወደ እነርሱ ቀርቦ ባዩት ጊዜ እየራዱና እየተንቀጠቀጡ “የእግዚአብሔር ልጅ ኢየሱስ ሆይ ከአንተ ጋር ምን አለን? ጊዜው ሳይደርስ ልታሠቃየን ወደዚህ መጣህን?” እያሉ አጋንንቱ ጮኹ፡፡ በአቅራቢያቸው ወደሚገኙት እሪያዎች ይሰዳቸው ዘንድ ተማጸኑት፡፡ ጌታችንም እንደ ልመናቸው ይሄዱ ዘንድ ሰደዳቸው፡፡ አጋንነቱም በእሪያዎቹ ላይ እያደሩ ወደ ባሕሩ ወደቁ፡፡ (ማቴ. ፰፥፳፰-፳፱) እግዚአብሔር በራሱ ጊዜ ሁሉ ይቻለዋልና እንዲህም ያደርጋል፡፡

እኛ ያስፈልጉናል የምንላቸው ነገሮች ከእግዚአብሔር የሚለዩን፣ በሕይወታችን ውስጥ ትልቁን ጠባሳ ትተው የሚያልፉ ሆነው ሊገኙ ይችላሉና ስለምንለምነው ነገር ሁሉ በጸሎት የታገዘ ሕይወት ሊኖረን ይገባል፡፡ የምንሻው ነገር ሳይፈጸም ቢዘገይ የእግዚአብሔር ፈቃዱ አይደለምና ጊዜው ሲደርስ ያከናውንልን ዘንድ መጽናት ከእኛ ይጠበቃል፡፡ የምንሻውን መጠየቅ ብቻ ሳይሆን ለሕይወታችን እንደሚያስፈልግና እንደማያስፈልግ መለየት ከእኛ ይጠበቃል፡፡ የምንጠይቀው ነገር ከእግዚአብሔር ሊለየን፣ ከአምልኮት ሊያርቀን ይችላልና ስለምንጠይቀው ነገር ጥንቃቄ ልናደረግ ይገባል፡፡ እንደ ዘብድዎስ ልጆች ማለትም የዮሐንስ እና የያዕቆብ እናት “የምትለምኑትን አታውቁም” እስክንባል ራሳችንን ለተግሣጽ አሳልፈን እንዳንሰጥ ትዕግሥትን ገንዘብ ማድረግ ያስፈልጋል፡፡

የዮሐንስ እና የያዕቆብ እናት ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስን አንድ ጥያቄ ጠይቃዋለች፡፡ በሰው ሰውኛው አስተሳሳብ በዚህ ዓለም ላይ ሊነግሥ የመጣ መስሏታልና በመንግሥቱ አንዱን ልጇን በቀኛዝማችነት በቀኙ፣ ሁለተኛውንም ልጇን በግራዝማችነት በግራው በጋሻ ጃግሬነት እንዲያቆምላት ጠየቀችው፡፡ “እነዚህን ሁለቱን ልጆቼን በመንግሥትህ አንዱን በቀኝህ፣ አንዱንም በግራህ እንዲቀመጡ አድርግልኝ” አለችው፡፡ እርሱም “የምትለምኑትን አታውቁም፣ እኔ የምጠጣውን ጽዋ መጠጣት፣ ትችላላችሁን? …” ሲል ገስጿታል፡፡ ይህ ታሪክ ከሚያስፈልገን ነገር ውጪ ለእኛ ስለመሰለን ብቻ መጠየቅ እንደማይገባን ትልቅ ማሳያ ነው፡፡ አንዳንድ ጊዜ ሕይወትን የለመንን መስሎን ሞትን እንደነ ዮሐንስ እናት የምለምን እንኖራለን፡፡

እግዚአብሔር ሁሉንም በጊዜው የሚያከናውን አምላክ ነው፡፡ የምንለምነውን ባለማወቃችን፣ የራሳችንን ፍላጎት ብቻ በማስቀደማችን ከእግዚአብሔር አንድነት እንለያለን፡፡ “ለምንድነው እኔ በሚያስፈልገኝ ጊዜ እና ሰዓት የማያከናውንልኝ? እኔ አሁን ነው የምፈልገው!” እያልን ከእግዚአብሔር ጋር ሙግት የምንገጥም ብዙዎች ነን፡፡ ነገር ግን በጊዜውም ያለ ጊዜውም በመጽናት የእግዚአብሔርን ጊዜ መጠበቅ ያስፈልጋል፡፡ በራሳችን ፈቃድ ብቻ ተመሥርተን የምናከናውናቸው ተግባራት ሁሉ ለውድቀት የሚዳርጉን ናቸውና፡፡

ለመሆኑ የእግዚአብሔር ጊዜ መቼ ነው? እግዚአብሔር እያንዳንዱን ነገር ሲያከናውን በዕቅድ ነው፡፡ እግዚአብሔር እንደ ሰው አይደለም አይቸኩልም፣ አይዘገይምም፡፡ ዘግይቶ ወይም ቸኩሎ የፈጠረው አንዳች ነገር የለም፡፡ ሁሉንም በጊዜው ውብ አድርጎ ሠርቶታልና የሠራውም ሁሉ መልካም ነው፡፡ “ነገርን ሁሉ በጊዜው ውብ አድርጎ ሠራው” (መክ. ፫፥፲፩) እንዲል፡፡ በዕቅድና ሁሉን በጊዜው ባያከናውን ኖሮ በስድስቱ ቀናት እያንዳንዱን ፍጥረት ባልፈጠረ ነበር፡፡ ስለዚህ ከሰው ልጆች የሚፈለገው የእግዚእሔርን ጊዜ በትዕግሥት መጠበቅ ነው፡፡ “ … ቢዘገይም በእርግጥ ይመጣልና ታገሠው፤ እርሱ አይዘገይም” (ዕንባ. ፪፥፫) እንደተባለ፡፡

ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ ለሮሜ ሰዎች በላከው መልእክቱ “በበጎ ምግባር ጸንተው ለሚታገሡ ምስጋናና ክብርን፣ የማይጠፋ ሕይወትንም ለሚሹ እርሱ ለዘለዓለም ሕይወትን ይሰጣቸዋል” (ሮሜ. ፪፥፯) በማለት እንደገለጸው ለእግዚአብሔር የምንመች፣ እንደ ቃሉም የምንመላለስ ሆነን በመገኘት በጾምና በጸሎት በመትጋት እግዚአብሔር ሊያከናውንልን የምንሻውን ነገር በትዕግሥት ደጅ በመጥናት መጠበቅ ያስፈልጋል፡፡ ቅዱስ ጳውሎስ በዚህ ብቻ አያበቃም ለዕብራውያን ሰዎች በላከው መልእክቱም “ነገር ግን የእግዚአብሔርን ፈቃድ አድርጋችሁ የተሰጣችሁን ተስፋ ታገኙ ዘንድ መታገሥ ያስፈልጋችኋል” ሲል በመታገሥና በጽናት በሃይማኖት ቀንቶ፣ በምግባር ታንጾ መኖር ከሰው ልጆች ሁሉ ይፈለጋል፡፡ እግዚአብሔር እያንዳንዳችን የምንሻውን ብቻ ሳይሆን እርሱ ያዘጋጀልንን ሁሉ ይሰጠን ዘንድ ፈቃዱ ነውና በጊዜውም ያለ ጊዜውም ጸንተን እንቁም፡፡

ወስብሐት ለእግዚአብሔር

ጉባኤ-ቃና መጽሔት-ነሐሴ-2016-ዓ.ም

ጉባኤ-ቃና መጽሔት-ነሐሴ-2016-ዓ.ም

ጽንሰታ ለማርያም

ጽንሰታ ለማርያም

ነሐሴ ፯ ቀን እግዚአብሔር የመላእክት አለቃ ቅዱስ ገብርኤልን ወደ ከበረና ከፍ ከፍ ወዳለ ጻድቅ ኢያቄም ላከው፡፡ አምላክን የወለደች የእመቤታችን የድንግል ማርያምን ፅንሰቷንና ልደቷን በእርሱም ለዓለሙ ሁሉ ድኅነትና ተድላ ደስታ እንደሚሆን ነገረው፡፡

ይህ ጻድቅ ሰው ኢያቄምና የከበረች ሚስቱ ሐና ልጅ ሳይወልዱ ሸመገሉ፡፡ የከበረች ሐና መካን ሁናለችና ስለዚህም እጅግ ያዝኑ ነበር፤ የእስራኤል ልጆች ልጅ ያልወለደውን ከእግዚአብሔር በረከትን ያጣ ነው እያሉ ያቀልሉት ነበርና፡፡ እነርሱም ልጅ ይሰጣቸው ዘንድ ወደ እግዚአብሔር ዘወትር ፈጽሞ ይለምኑ ነበር፡፡ ከዚህም በኋላ ወንድ ልጅን ወይም ሴት ልጅን ቢወልዱ ለእግዚአብሔር ቤት አገልጋይ ሊያደርጉት ስዕለትን ተሳሉ፡፡ የልቡናቸውን መሻት የሆነውን ልጅ እንዲሰጣቸው እግዚአብሔርን ዘወትር በቤተ መቅደስ ተገኝተው ዕንባቸውን እያፈሰሱ መማጸናቸውን አላቋረጡም፡፡

ከዕለታት በአንድ ቀንም የከበረ ኢያቄምም በተራራ ላይ ሳለ ሲጸልይና ሲማልድ እነሆ እንቅልፍ እንቅልፍ ብሎት ተኛ፡፡ ያን ጊዜ የመላእክት አለቃ ቅዱስ ገብርኤል ተገለጸለት፡፡ እንዲህም አለው፡- “ሚስትህ ሐና ትፀንሳለች ዓለም ሁሉ ደስ የሚሰኝባትን የብዙዎችም ዐይነ ልቡናቸው በእርሷ የሚበራላቸውን በእርሷም ድኅነት የሚሆንባትን ሴት ልጅን ትወልድልሃለች” አለው፡፡

ሐናም በበኩሏ “አቤቱ ጌታዬ የአባቶቼ የእስራኤል አምላክ እኔ ባርያህ እለምንሃለሁ፤ ስማኝ ለዓይኔ ማረፊያ ለልቤ ተስፋ የምትሆነኝ የተባረከች ሴት ልጅ የማኅፀኔን ፍሬ ስጠኝ” ብላ ስትለምን ዋለች፡፡ ርግብ ከልጆቿ ጋር ስትጫወት ዓይታም በተሰበረ ልብ ውስጥ ሆና “አቤቱ ጌታዬ ለዚች ግእዛን ለሌላት እንስሳ ልጅ የሰጠህ አምላክ ምነው ለኔ ልጅ ነሳኸኝ?” ብላ ምርር ብላ አለቀሰች፡፡

ሐና እና ኢያቄም ከካህኑ ዘካርያስ ዘንድ ሄደው “አቤቱ ጌታችን ሆይ ወንድ ልጅ ብንወልድ ተምሮ ቤተ እግዚአብሔርን አገልግሎ እንዲኖር እንሰጣለን፤ ሴት ልጅም ብንወልድ ማይ(ውኃ) ቀድታ፣ መሶበ ወርቅ ሰፍታ፣ መጋረጃ ፈትላ፣ ካህናትን አገልግላ እንድትኖር እንሰጣለን” ብለው ስዕለት ገቡ፡፡ ካህኑ ዘካርያስም “እግዚአብሔር ጸሎታችሁን ይስማችሁ፤ ስዕለታችሁን ይቀበልላችሁ፤ የልቡናችሁን መሻት ይፈጽምላችሁ” ብሎ ቡራኬ ሰጥቶ ሸኛቸው።

ሐና እና ኢያቄም ዕለቱን ራእይ ዓይተው አደሩ፡፡ ራእዩም እንዴት ነው ቢሉ፡- ኢያቄም ፯ቱ ሰማያት እንደ መጋረጃ ተገልጠው ከላይኛው ሰማይ ነጭ ርግብ ወርዳ በሐና ራስ ላይ ስታርፍ፤ በጆሮዋም ገብታ በማኅፀኗ ስትተኛ አየ፡፡ ሐናም የኢያቄም መቋሚያ ለምልማ አፍርታ ፍጥረት ሁሉ ሲመገባት አየች፡፡ ከዚህም በኋላ ኢያቄም ያየውን ራእይ ለሐና፣ ሐና ያየችውን ራእይ ደግሞ ለኢያቄም በመንገር ራሳቸውን እግዚአብሔር ለገለጸላቸው ነገር ለማዘጋጀት ተስማሙ፡፡

ሁለቱም በአንድ ልብ ሆነው ዕለቱን በሩካቤ ሥጋ አልተገናኙም፤ ፈቃደ እግዚአብሔር ቢሆን ነው ብለው “አዳምንና ሔዋንን ብዙ ተባዙ ምድርንም ምሉአት ብሎ ያበሰረ አምላክ ለኛስ ይልክልን የለምን?” ብለው ዕለቱን መኝታ ለይተው እስከ ፯ ቀን ድረስ ሰነበቱ፡፡ ነሐሴ በባተ በሰባተኛው ቀን መልአኩ ቅዱስ ገብርኤል ከእግዚአብሔር ተልኮ “ከሰው የበለጠች፤ ከመላእክት የከበረች ደግ ፍጥረት ትወልዳላችሁ” ብሎ ለሐና ነገራት፡፡

በፈቃደ እግዚአብሔር፣ በብሥራተ መልአክ እመቤታችን እግዝእትነ ማርያም ነሐሴ ፯ ቀን ተፀነሰች፡:

ቅዱስ ያሬድ “ማርያምሰ ተኀቱ እምትካት ውስተ ከርሱ ለአዳም ከመ ባሕርይ ጸዓዳ፤ ማርያምስ ከጥንት ጀምሮ በአዳም ባሕርይ ውስጥ እንደ ነጭ ዕንቁ ታበራለች” በማለት እንደተናገረው እግዚአብሔር ቅድስት ድንግል ማርያምን ለአዳምና ለልጆቹ ሁሉ ድኅነት መሠረት እንዳደረጋት፣ ሊመረመር በማይችል ጥበቡም እንዳዘጋጃት ተናግሯል፡፡ አባ ሕርያቆስም በቅዳሴ ማርያም ድርሰቱ “ኦ ድንግል አኮ በፍትወተ ደነስ ዘተፀነስኪ አላ በሩካቤ ዘበሕግ እምሐና ወኢያቄም ተወለድኪ፤ ድንግል ሆይ በኃጢአት ፍትወት የተፀነስሽ አይደለም፤   በሕግ በሆነ ሩካቤ ከሐና ከኢያቄም ተወለድሽ እንጂ” ብሎ አመስግኗታል፡፡

ቅድስት ኦርቶዶክሳዊት ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያንም ይህንን መሠረት አድርጋ ዕለቱን በድምቀት ታከብረዋለች፡፡

የእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ምልጃዋ በረከቷ በሁላችን ላይ ይደር፡፡ አሜን፡፡

ምንጭ፡ ስንክሳር ነሐሴ  ቀን

“ሞት በጥር፤በነሐሴ መቃብር”

ሞት በጥር፤ በነሐሴ መቃብር”

እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም በ፷፬ ዓመቷ ጥር ፳፩ ቀን ፵፱ ዓ.ም ከዚህ ዓለም ድካም ማረፏን ነገረ ማርያም ያስረዳል፡፡ የእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም በሥጋ ማረፍን የተመለከቱት ቅዱሳን ሐዋርያትም ሊቀብሯት ወደ ጌቴሴማኒ ይዘዋት ሲሔዱ አይሁድ “እንደ ልጇ ተነሣች፤ ዐረገች እያሉ እንዳያውኩን በእሳት እናቃጥላት” ብለው በክፋት ተነሣሡ፡፡ ታውፋንያ የሚባል አይሁዳዊም አጎበሩን ይዞ ሊያወርዳት ሲል የእግዚአብሔር መልአክ ሁለት እጆቹን ቀሰፈው፡፡ የአይሁድን ክፋት የተመለከተው አምላካችን ቅዱስ እግዚአብሔር እመቤታችንን ሐዋርያው ቅዱስ ዮሐንስን አስከትሎ በደመና ነጥቆ በገነት ከዕፀ ሕይወት ሥር አስቀመጣት፡፡

ቅዱሳን ሐዋርያትም እመቤታችን ያለችበት ቦታ እንዲገለጥላቸው ባረፈች በስምንተኛው ወር ከነሐሴ ፩ ቀን ጀምረው ሱባዔ ገብተው እግዚአብሔርን በጸሎት መጠየቅ ጀመሩ፡፡ ከዚህ ላይ “ስምንት ወር ሙሉ ምን ይዘው ቆይተው ነሐሴ ላይ ሱባዔ ገቡ?” የሚል ጥያቄ ሊነሣ ይችላል፡፡ ቅዱሳን ሐዋርያት ከስብከተ ወንጌል፣ ከጾም፣ ከጸሎት፣ ከገቢረ ተአምራት፣ ተለይተው እንደማያውቁ መንፈሳዊ ሕይወታቸው ምስክር ነው፡፡

ከፊታቸው የዐቢይ ጾም፣ ከዚያም በዓለ ሃምሳ፣ ቀጥሎም የአገልግሎታቸው መጀመሪያ የሆነው የሐዋርያት ጾም ስለሚከተል ከሰው ተለይተው ሱባዔ ገብተው ጾም ጸሎት የጀመሩት ከነሐሴ ፩ ቀን ጀምሮ ነው፡፡ ለሁለት ሱባኤ በጾም ጸሎት ከቆዩ በኋላ እግዚአብሔር ጸሎታቸውን ሰምቶ ነሐሴ ፲፬ ቀን የእመቤታችንን ሥጋ ሰጥቷቸው በክብር ገንዘው በጌቴሴማኒ ቀብረዋታል፡፡ እሷም እንደ ልጇ እንደ ጌታችን መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ከሙታን ተለይታ ተነሥታለች፡፡ “ከመ ትንሣኤ ወልዳ፤ እንደ ልጇ ትንሣኤ” ያሰኘውም ይህ ታሪክ ነው፡፡

ሐዋርያው ቅዱስ ቶማስ ሲሰብክ ቆይቶ ደመና ጠቅሶ ከሀገረ ስብከቱ ወደ ኢየሩሳሌም ሲመጣ እመቤታችን ከሙታን ተለይታ ተነሥታ ወደ ሰማይ ስታርግ አገኛት፡፡ በዚህ ጊዜ “ቀድሞ የልጅሽን ትንሣኤ፤ ዛሬ ደግሞ ያንቺን ትንሣኤ ሳላይ ቀረሁን?” ብሎ ትንሣኤዋን ባለማየቱ ኀዘን ስለ ተሰማው ከደመናው ወደ መሬት ይወድቅ ዘንድ ወደደ፡፡ እመቤታችንም “አይዞህ አትዘን፤ ባልንጀሮችህ ሐዋርያት ያላዩትን ትንሣኤዬን አንተ አይተሃል” ብላ ከሙታን ተለይታ መነሣቷንና ማረጓን እንዲነግራቸው ካዘዘችው በኋላ የተገነዘችበትን ሰበን ሰጠችው፡፡

ሐዋርያው ቶማስም ትእዛዟን ተቀብሎ ወደ ሐዋርያት በመሄድ ምንም እንዳልሰማ እንዳላየ መስሎ “የእመቤታችን ነገር እንደምን ሆነ?” ሲል ጠየቃቸው፡፡ እነርሱም “ሥጋዋን አግኝተን ቀበርናት” አሉት፡፡ እርሱም “ሞት በጥር በነሐሴ መቃብር እንዴት ይሆናል?” አላቸው፡፡ ቅዱስ ጴጥሮስ ከዚህ በፊት የክርስቶስን ትንሣኤ መጠራጠሩን ጠቅሶ እየገሠፀ ስለ እመቤታችን መቀበር እነርሱ የሚነግሩትን ሁሉ መቀበል እንደሚገባው ለቅዱስ ቶማስ አስረዳው፡፡ በዚህ ብቻ ሳያበቃም ሐዋርያት የቅዱስ ቶማስን ጥርጣሬ ለማስወገድ ሲሉ የእመቤታችንን ክቡር ሥጋ ለቅዱስ ቶማስ ለማሳየት ወደ መቃብሯ ጌቴሴማኒ ሄደው መቃብሯን ቢከፍቱት የእመቤታችንን ሥጋ ማግኘት አልቻሉም፡፡

ቅዱስ ቶማስም “አታምኑኝም ብዬ ነው እንጂ እመቤታችንስ እንደ ልጇ ከሙታን ተለይታ ተነሥታ ስታርግ አግኝቻታለሁ” ብሎ የሰጠችውን ሰበን ለሐዋርያት ሰጥቷቸዋል፡፡ እነርሱም በእመቤታችን ትንሣኤና ዕርገት እየተደሰቱ ሰበኑን ለበረከት ተካፍለውታል፡፡ በቅዳሴ ጊዜ ሠራዒ ዲያቆኑ በሚይዘው መስቀል ላይ የሚታሠረው መቀነት መሰል ልብስ፤ እንዲሁም አባቶች ካህናት በእጅ መስቀላቸው ላይ የሚያስሩት ቀጭን ልብስና በራሳቸው የሚጠመጥሙት ነጭ ሻሽ የእመቤታችን ሰበን ምሳሌ ነው፡፡

በዓመቱ ቅዱሳን ሐዋርያት “ቶማስ የእመቤታችን ትንሣኤዋንና ዕርገቷን አይቶ እኛ እንዴት ሳናይ እንቀራለን?” ብለው ከየሀገረ ስብከታቸው ተሰባስበው ከነሐሴ ፩ ቀን ጀምረው ሱባዔ በመያዝ የእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያምን ሥጋ እንዲሰጣቸው እግዚአብሔርን ተማጸኑ፡፡ ጌታችንም ልመናቸውን ተቀብሎ ነሐሴ ፲፮ ቀን እመቤታችንን መንበር፤ ጴጥሮስን ተራዳኢ ካህን፤ እስጢፋኖስን ሠራዒ ዲያቆን አድርጎ ቀድሶ እመቤታችንንም ሐዋርያትንም አቍርቧቸዋል፡፡ እነርሱም እመቤታችንን በዓይናቸው ከማየት ባሻገር አብረው ሥጋውን ደሙን ተቀብለዋል (ትርጓሜ ውዳሴ ማርያም)፡፡

ይህንን ትምህርት መሠረት በማድረግ የቤተ ክርስቲያን ሊቃውንት ከነሐሴ ፩-፲፬ ያለውን ሁለት ሱባዔ ከሰባቱ አጽዋማት አንዱ ሆኖ በምእመናን ዘንድ መጾም እንደሚገባው ሥርዓት ሠርተውልናል (ፍት.ነገ.አን. ፲፭)፡፡ ይህ ጾምም “ጾመ ማርያም”  ወይም “ጾመ ፍልሰታ ለማርያም” እየተባለ ይጠራል፡፡ “ፍልሰት” የሚለው ቃልም “ፈለሰ ሔደ፤ ተሰደደ” ካለው የግእዝ ግስ የተገኘ ሲሆን ትርጕሙም ከአንድ ሀገር ወደ ሌላ ሀገር መሔድን ያመለክታል፡፡ “ፍልሰታ ለማርያም” ሲልም እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ካረፈች በኋላ ከጌቴሴማኒ ወደ ገነት መወሰዷን የሚያስረዳ ነው፡፡

በጾመ ፍልሰታ በቤተ ክርስቲያናችን በየቀኑ በማሕሌቱ፣ በሰዓታቱና በቅዳሴው በሚደርሰው ቃለ እግዚአብሔር ነገረ ማርያም ማለትም የእመቤታችን ከመፀነሷ ጀምሮ እስከ ዕርገቷ ድረስ ያለው ታሪኳ፣ ለአምላክ ማደሪያነት መመረጧ፣ ንጽሕናዋ፣ ቅድስናዋ፣ ክብሯ፣ ርኅርራኄዋ፣ ደግነቷ፣ አማላጅነቷ፣ ሰውን ወዳድነቷ በስፋት ይነገራል፡፡ እመቤታችንን ከሚያወድሱ ድርሳናት መካከልም በተለይ ምሥጢረ ሥላሴን፣ ምሥጢረ ሥጋዌንና ነገረ ድኅነትን ከነገረ ማርያም ጋር በማዛመድ የሚያትተው ቅዳሴ ማርያም፤ እንደዚሁም ነገረ ድኅነትን ከምሥጢረ ሥጋዌ (ከነገረ ክርስቶስ) እና ከነገረ ማርያም ጋር በማመሥጠር የሚያትተው ውዳሴ ማርያምም በስፋት ይጸለያል፤ ይቀደሳል፤ ይተረጐማል፡፡ በሰንበታት የሚዘመሩ መዝሙራት፤ በየዕለቱ በቅዳሴ ጊዜ የሚነበቡ የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍሎችም እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ለእናትነት  በእግዚአብሔር መመረጧን፣ ዘለዓለማዊ ድንግልናዋን፣ ክብሯን፣ ቅድስናዋን፣ ንጽሕናዋን የሚያወሱ ናቸው፡፡

የእግዚአብሔር ቸርነት፣ የእመቤታችን የቅድስት ድንግል ማርያም አማላጅነት፣ የቅዱሳን ሐዋርያት ጸጋና በረከት አይለየን፡፡

“የእግዚአብሔር መልአክ በሚፈሩት ሰዎች ዙሪያ ይሰፍራል፤ ያድናቸውማል”

(መዝ. ፴፬፥፯)

ሊቀ መላእክት ቅዱስ ገብርኤል በሐምሌ ዐሥራ ዘጠኝ ቀን ሕፃኑ ቂርቆስንና እናቱ ቅድስት ኢየሉጣን ከሚነደው እቶን እሳት ያዳነበት ዕለት ነው፡፡ ቅድስት ቤተ ክርስቲያናችንም በየዓመቱ ዕለቱን በድምቀት ታከብረዋለች፡፡ የእነዚህም ቅዱሳን ታሪክ በስንክሳር እንዲህ ይተረካል፡፡

በዚህችም ቀን ሕፃኑ ቂርቆስና እናቱ ኢየሉጣ በሰማዕትነት መከራን ተቀበሉ፡፡ ይህም ሕፃን ዕደሜው ሦስት ዓመት ሲሆነው ከሮሜ ሀገር ወደ ሌላ ሀገር እናቱ ይዛው ሸሸች፤ በዚያም የሸሸችውን መኮንን አገኘችው፡፡

ሰዎችም ነገር ሠሩባት፤ ወደ አርሱ አስቀረባትና ስለ አምልኮ ጠየቃት፤ እርሷም “መኰንን ሆይ ዕድሜው ሦስት ዓመት የሆነው ሕፃን አለ፤ አማልእክቶችህ ማምለክ መልካም እንደሆነ ወይም እንዳልሆነ ያስረዳን ዘንድ እርሱን ጠይቅ” አለችው፡፡

ሕፃኑም አለበት ጭፍራውን ልኮ ወደርሱ አስመጣው፤ ሕፃኑንም ፊቱ ብሩህና ደስተኛ እንደሆነ አየውና “አንተ ደስተኛ ሕፃን ሆይ እንዴት ነህ?” አለው፡፡ ሕፃኑም መልሶ “አዎ ለእኔ ደስታ ተጠብቆልኛል፤ ለአንተ ግን ኃዘንና ልቅሶ ጥርስ ማፋጨትም ነው፡፡ መጽሐፍ ለዝንጉዎች ተድላ ደስታ የላቸውም፤ ብሏልና” አለው፡፡ እግዚአብሔር ኃይልና ንግግርን ሰጥቶታልና ብዙ ተናገረ፡፡ በዚያም ያሉትን እስከ አስደነገጣቸው ድረስ ንጉሡን፣ መኳንንቱንና ጣዖታቱን ረገማቸው፤ ከብርታቱም የተነሣ አደነቁ፡፡

መኰንኑም በአፈረ ጊዜ በየዓይነቱ በሆነ ስቃይ ታላላቆች የማይችሉትን ታላቅና አስጨናቂ የሆነ ስቃይን አሰቃየው፡፡ እናቱንም ከርሱ ጋር እንደ እርሱ አሰቃያት፤ እግዚአብሔርም ያለ ምንም ጉዳት ያስነሣቸው ነበር፡፡ ብዙዎች አሕዛብም ይህን ዐይተው አደነቁ፤ ክብር ይግባውና በጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስም አምነው በሰማዕትነት ሞቱ፤ የሰማዕትነትም አክሊል ተቀበሉ፡፡

በሕፃኑ ላይም የመንፈስ ቅዱስ ጸጋ አደረበት፡፡ ታላላቅ ድንቆችና ተአምራቶችንም አደረገ፤ ብዙዎች በሽተኛቹንም አዳናቸው፡፡ ከዚህም በኋላ መኰንኑ በታላቅ የናስ ጋን ውስጥ ውኃ ጨምረው በእሳት ያፈሉት ዘንድ አዘዘ፡፡ የፍላቱም ድምጽ እንደ ክረምት ነጐድጓድ ሆነ፤ ያን ጊዜም ፍርሃትና የሃይማኖት ጉድለት በእናቱ ላይ ደረሰባት፤ ሕፃኑም ስለ እናቱ ወደ እግዚአብሔር ጸለየ፡፡

ያን ጊዜ ጌታችን ልቧን ወደ ሰማይ አሳርጎ ለቅዱሳን ሰማዕታት የተዘጋጁ የብርሃን ማደሪያዎችን አየች፤ ከዚህም በኋላ ጸናች፤ እግዚአብሔርንም አመሰገነችው፡፡ ልጅዋንም “ልጄ ሆይ ከእንግዲህ አንተ አባቴ ነህ፤ እኔም ልጅህ ነኝ” አለችው፡፡ “ያቺ ከእኔ የተወለድክባትም ቀን የተባረከች ናት” አለች፡፡ ወደዚያ ወደ ጋኑ ውስጥ በገቡ ጊዜም የውኃው ፍልሐት እንደ ንጋት ጊዜ ውርጭ ቀዘቀዘ፡፡ ከእግዚአብሔር የታዘዘ የመላእክት አለቃ ቅዱስ ገብርኤል ከሰማይ ወርዶ የእሳቱን ኃይል አቀዝቅዞታልና፡፡

ከዚህም በኋላ መኰንኑ ሥጋቸው ተቆራርጦ እስከሚወድቅ ድረስ በመቃጥን ውስጥ አድርገው እንዲጎትቷቸው አዘዘ፡፡ ከእግዚአብሔርም የታዘዘ መልአክ አዳናቸው፡፡ መኮንኑም በታላቅ ስቃይ ያሰቃያቸው ዘንድ አስቦ እስኪመክር ድረስ በወኅኒ ቤት ዘጋባቸው፡፡

ያን ጊዜም ክብር ይግባውና ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ወደ ሕፃኑ ቂርቆስ ወርዶ አጽናናው፣ አረጋጋውም፡፡ ስሙን ለሚጠራና መታሰቢያውን ለሚያደርግ ቃል ኪዳን ሰጠው፡፡

ለእግዚአብሔር ምስጋና ይሁን እኛንም በቅዱስ ቂርቆስና በኢየሉጣ ጸሎት ይማረን፤ በረከታቸውም ትድረሰን ለዘለዓለሙ አሜን፡፡  

ወስብሐት ለእግዚአብሔር

ምንጭ፡ ስንክሳር ዘወርኀ ሐምሌ ፲፱