መንፈሳዊ ተጋድሎ

መንፈሳዊ ተጋድሎ አንድ ሰው የሚያምንበትን እምነት፣ የሚመራበትን ሕግ፣ የሚያልመውን ተስፋ እና የሚወደውን ነገር ተከትሎ ከግቡ ለመድረስ ማድረግ ያለበትን በማድረግ፣ ማድረግ የሌለበትን በመተው በነጻ ፈቃዱ ወስኖ ሙሉ ኃይሉን አስተባብሮ የሚያከናውነው የመንፈሳዊ አገልግሎት፤ ጥረትና ትግል ነው።

ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ “መልካሙን ገድል ተጋድያለሁ ሩጫዬንም ጨርሻለሁ፤ ሃይማኖቴንም ጠብቄአለሁ፡፡ እንግዲህስ የጽድቅ አክሊል ይቆየኛል፤ ይህንም ጻድቅ ፈራጅ የሆነው እግዚአብሔር በዚያ ቀን ለእኔ ያስረክባል፤ ደግሞም መገለጡን ለሚወዱት ሁሉ እንጂ ለእኔ ብቻ አይደለም፡፡” (፪ኛ ጢሞ. ፬፥፯-፰) እንዲል፡፡

ቅዱስ ጳውሎስ በአገልግሎቱ መጨረሻ ላይ በአገልግሎት ለተከተለው ለመንፈስ ልጁ ጢሞቴዎስ ይህንን ቃል ሲጽፍ በተጋድሎው ይመስለው ዘንድ፣ በኋላም ለክብር አክሊል እንዲበቃ መንገዱን ለማሳየት ነው፡፡ “የእግዚአብሔርን ቃል የነገሩአችሁን መምህሮቻችሁን ዐስቡ፤ መልካም ጠባያቸውን አይታችሁ በእምነት ምሰሉአቸው” (ዕብ. ፲፫፥፯) በማለት፡፡  

ሐዋርያው የክርስቶስን መስቀል በመሸከም፣ መከራ በመቀበል ሕይወቱን በመንፈሳዊ ተጋድሎ ፈጽሞታል። ረጅም ሐዋርያዊ ጉዞ በማድረግ በታናሿ እስያና በምድረ አውሮፓ፣ በባሕርና በየብስ በመዘዋወር የክርስቶስን የምሥራች ዜና ለብዙዎች እንዲዳረስና በጨለማም ለሚኖሩት አሕዛብ ብርሃን የሆነውን የክርስቶስን ወንጌል ሰብኳል፣ አሳምኗል፤ ብዙዎችንም ከኃጢአት ወደ ጽድቅ መንገድ መልሷል፡፡ የእርሱን ፈለግ ለሚከተሉ ሁሉም የጽድቅ ዋጋ እንደሚያገኙ አስረድቷል።

መንፈሳዊ ተጋድሎ ከፈቃደ ሥጋ ጋር የሚደረግ ውጊያ ነው። ሰው በዚህ ዓለም በተሰጠው ዘመኑ ራሱን ለፈጣሪው ለማስገዛት ከራሱ ጋር ብርቱ ተጋድሎ ማድረግ ግድ ይለዋል። ቅዱስ ጳውሎስ “ሥጋ በመንፈስ ላይ፣ መንፈስም በሥጋ ላይ ይመኛል፤ ስለዚህም እርስ በእርሳቸው ይቀዋወማሉ፡፡ ስለዚህም የምትወዱትን ልታደርጉ አትችሉም“ ብሎ የገለጸው ይህንን በሰው ሕይወት ውስጥ ያለውን የማይቋረጥ ጦርነት ነው። (ገላ. ፭፥፲፪)

ታላቁ አባት ኢዮብም “ጥንቱን በምድር ላይ የሰው ሕይወት ጥላ አይደለምን? ኑሮውስ እንደ ቀን ምንደኛ አይደለምን?” (ኢዮ. ፯፥፩) በማለት ሰው ጽኑ ጦርነት የሚያካሄድበት የጦር ሜዳ መሆኑን ገልጿል። ይህም ጥንተ ጠላታችን ዲያብሎስ የሥጋ ፈቃዳችንን ብቻ ተከትለን እንድንጓዝ በማድረግ ከነፍስ ጋር የሚደረገው ጦርነት በተወሰነ ጊዜ ተነሥቶ የሚጠፋ ሳይሆን በሰው ዘመን ሁሉ የሚኖርና የዕድሜ ልክ ትግል ነው። ይህን የሥጋና የነፍስ ጦርነት በነፍስ አሸናፊነት ማጠናቀቅና ፈቃደ ሥጋን ድል አድርጎ ለፈቃደ ነፍስ ማስገዛት ይገባል ።ይህም ሲባል ሥጋ ርኵስ ነው፤ ሥጋ መጥፋትና መወገድ አለበት ማለት አይደለም፤ ሥጋ በራሱ የረከሰ አይደለምና። ምክንያቱም ሥጋ የተፈጠረው በራሱ በእግዚአብሔር ነውና፡፡ አምላካችን ደግሞ ርኵስ ነገር አይፈጥርም፡፡ ሰው የነፍስና የሥጋ ተዋሕዶ ውጤት በመሆኑም ፍጥረታትን ፈጥሮ ከጨረሰ በኋላ “እግዚአብሔርም የፈጠረውን ሁሉ እጅግ መልካም እንደሆነ አየ” እንዲል፡፡ (ዘፍ. ፩፥፴፩)

ስለዚህ ፈቃደ ሥጋን መዋጋት ማለት ተፈጥሮአዊና ንጹሕ የሆነውን ሥጋን ማጥፋት ወይም ደግሞ የሥጋን ፈቃድ ማስወገድ ማለት ሳይሆን፣ ኃጢአትን በማየት፣ በመስማት፣ በመለማመድ ያደገውን÷ ወደ ኃጢአት ያዘነበለውን ፈቃዳችንን መጐሰም /መግራት/ ማለት ነው፡፡ ይህ ፈቃድ (ኃጢአት) ሥጋን ከነፍስ ቁጥጥር ውጭ እንዲሆን ያደርገዋል፡፡የሰው ሥጋዊ ባሕርዩ ምግብ ሲያጣ ይራባል፣ ይደክማል፣ ሥራ መሥራት ይሳነዋል፡፡ ሲሰጡት ደግሞ ኃጢአትን ተለማምዷልና ሌላ ፈቃድ በማምጣት ጠላት ሆኖ ይፈትነዋል፡፡ “ያዕቆብ በላ፣ ጠገበ፣ ወፈረ፣ ደነደነ፣ ሰባ፣ የፈጠረውንም እግዚአብሔርን ተወ፣ የመድኃኒቱንም አምላክ ናቀ” ተብሎ እንደተጻፈ፡፡ (ዘዳ. ፴፪፥፲፭)

ሰውነት የሚፈልገውን ሁሉ እንደ ልቡ ካገኘና ያለ ገደብ የሚቀለብ ከሆነ ወደ ኃጢአት ለመገስገስ የተዘጋጀ መርከብ ነው፡፡ ሰውነት በተመቸውና ፈቃዱን ለመፈጸም ኃይል ባገኘ ጊዜ ነፍስ እየደከመች ትሄዳለች፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ ሰውነት ፈጽሞ ከደከመና ከዛለ ሥራ መሥራት ያስቸግራል፡፡ ስለዚህ ሐዋርያው “ሰውነቴን እየጎሰምሁ አስገዛዋለሁ” እንዳለ፡፡ (፩ኛ ቆሮ. ፱፥፳፯) በአግባቡ ሊያዝና ሊገራ ይገባዋል፡፡ በአጠቃላይ ቅዱስ ጳውሎስ “ወንድሞቻችን አሁንም በሥጋችን ሳለን በሥጋ ፈቃድ እንኖር ዘንድ አይገባም፡፡ እንደ ሥጋ ፈቃድ ብትኖሩ ትሞታላችሁ፤ ነገር ግን በመንፈሳዊ ሥራችሁ የሥጋችሁን ፈቃድ ብትገድሉ ለዘለዓለም በሕይወት ትኖራላችሁ፡፡” (ሮሜ ፰፥፲፫) እንዳለ ከፈቃደ ሥጋ ጋር በመጋደል ፈቃደ ሥጋችንን ለፈቃደ ነፍሳችን ማስገዛት ይገባናል፡፡

ስለዚህ እያንዳንዳችን በተሰጠን ጸጋ መሠረት የሐዋርያውን ትምህርትና አርአያ ተከትለን እንደ ስጦታችን እና እንደ ችሎታችን መንፈሳዊ ሩጫችንን ልንሮጥ ይገባናል፡፡ ቅዱሳን ሥጋቸውን ለነፍሳቸው በማስገዛት እስከ ዕለተ ሞታቸው ድረስ በተጋድሎ ዲያብሎስን ድል ነሥተውታልና እነርሱን አርአያ አድርገን መከራውን ሳንሰቀቅ በትዕግሥት መንግሥተ እግዚአብሔር የሚያስገባንን መንፈሳዊ ተጋድሎ እየፈጸምን እንሩጥ፡፡ ቅዱስ ጳውሎስ ለዕብራውያን ክርስቲያኖች ሲጽፍ እንዲህ ይላል፡- “እንግዲህ እነዚህ የሚያህሉ ምስክሮች እንደ ደመና በዙሪያችን ካሉልን እኛ ደግሞ ሸክምን ሁሉ የኃጢአትንም ጭንቀት ከእኛ አስወግደን ከፊታችን ያለውን ሩጫ በትዕግሥት እንሩጥ፡፡” (ዕብ. ፲፪፥፩-፪) ይህ ሩጫ ወደ ክብር አክሊል ያደርሰናል፡፡    

ወስብሐት ለእግዚአብሔር

የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ያወጣው መመሪያ ተቃውሞ አስነሣ

የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ሃይማኖታዊ ነፃነታችንን የሚጋፋ መመሪያ አውጥቷል ሲሉ ኦርቶዶክሳውያን ተማሪዎች ገለጹ፡፡ ተማሪዎቹ ይህንን ያሉት የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በ፳፻፲፯ዓ.ም ያወጣውን የሥነ ምግባርና ዲሲፕሊን መመሪያ ተከትሎ ነው፡፡

በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የሚገኙ ኦርቶዶክሳውያን ተማሪዎች ወደ መመገቢያ አዳራሽ ሲሄዱ ነጠላ እንዳይለብሱና ምግብ እንዳያወጡ ሃይማኖታዊ መብታቸውን የሚጋፋ የሥነ ምግባርና ዲሲፕሊን መመሪያ መውጣቱን አቶ አበበ በዳዳ የግቢ ጉባኤያት አገልግሎት ማስተባበሪያ ኃላፊ ለማኅበረ ቅዱሳን ቴሌቪዥን ገልጸዋል። አቶ አበበ በዳዳ ጠቅላይ ቤተ ክህነት ኦርቶዶክሳውያን የከፍተኛ ተቋማት ተማሪዎች ሃይማኖታዊ የመብት ጥሰት እንዳይፈጸምባቸው ከሚመለከታቸው አካላት ጋር መወያየት እንደሚገባም አሳስበዋል፡፡

ዩኒቨርሲቲው በ፳፻፲፯ ዓ.ም ባወጣው የሥነ ምግባር ዲስፕሊን መመሪያ “የተለያዩ እምነት ተከታይ ተማሪዎች በግቢው ስለሚያስተናገድ ከሃይማኖትና ከበዓላት ጋር የተያያዙ የአለባበስ ሥርዓቶች፣ የማንነትና የእምነት መገለጫዎች በመሆናቸው ሊከበሩ ይገባቸዋል” ይላል፡፡

በሌላ በኩል የኒቨርሲቲው ሃይማኖታዊ ነፃነታችንን የሚጋፋ መመሪያ አውጥቷል ሲሉ ኦርቶዶክሳውያን ተማሪዎች ገልጸዋል፡፡ በተጨማሪም “በምግብ ሰዓት የኅሊና ጸሎት ካልሆነ በቀር ጸሎት እንዳናደርግና ከዳቦ ውጭ ምግብ እንዳናወጣ እንዲሁም በመመግቢያ አዳራሽ ውስጥ ነጠላ እንዳንለብስ መመሪያ ወጥቷል” ብለዋል፡፡

ተማሪዎች አክለውም የወጣውን መመሪያ ምክንያት በማድረግ በአንዳንድ የጥበቃ አካላትና ግለሰቦች ጫና እየተደረገብን ነው ሲሉም ጠቁመዋል፡፡ ምግባችንን አውጥተን ለነዳያን መስጠትና መንፈሳዊ ጉዞ በምናከናውንበት ወቅት አውጥተን መጠቀም እንዳንችል ተደርጓልም ብለዋል፡፡

የግቢ ጉባኤያት አገልግሎት ማስተባበሪያ ኃላፊ አቶ አበበ በዳዳ ዩኒቨርሲቲው በመጀመሪያው ረቂቅ መመሪያ ያወጣቸው ሕጎች ለኦርቶዶክሳውያን ተማሪዎች በጣም አስቸጋሪ ነበሩም ብለዋል፡፡ ነገር ግን በተማሪዎች በተቋቋመ ኮሚቴ በመመሪያው አንዳንድ አንቀጾች ላይ ማሻሻያ እንዲደረግ በቀረበው አስተያየት መሠረት ከበፊቱ የተሻለ ቢሆንም አሁንም ግን የተማሪዎችን ሃይማኖታዊ መብት የሚጋፋ መመሪያ መሆኑን ጠቅሰዋል፡፡ የማስተባበሪያው ኃላፊ አክለውም በተለይም ነጠላን አላስፈላጊ ልብስ በማለት የተገለጸው መመሪያ አግባብነት የሌለው ነውም ብለዋል፡፡

በመጨረሻም ይህ አካሄድ ሀገርን የማይጠቅም በመሆኑ ሊታሰብበት እንደሚገባ አሳስበው ዩኒቨርሲቲው አሳማኝ ማስረጃ ማቅረብ የሚችሉ ሰዎች በልዩ ሁኔታ ሃይማኖቱ የሚፈቅደውን አለባበስ መልበስ ይችላሉ የሚል መመሪያ ስላለው የሚመለከታቸው አካላት ውይይትና ምክክር እንዲያደርጉ መልእክት አስተላልፈዋል፡፡

ምንጭ፡- በማኀበረ ቅዱሳን ብሮድካስት አገልግሎት

“ልጄን ከግብፅ ጠራሁት” (ማቴ. ፪፥፲፭)

ክረምቱ ለገበሬው ከባድ የሥራ ወቅት ነው፡፡ ማጡንና ድጡን፣ ዝናቡንና ጎርፉን ታግሦ በሬዎቹን ጠምዶ ሲያርስ፣ ሲጎለጉልና ምድሪቱ ዘር ታቀበል ዘንድ ሲያዘጋጅ ይቆያል፡፡ እግዚአብሔርም መልካም ፍሬ እንደሚሰጠው በማመን ዘሩን ወዳለሰለሰው መሬት ይበትናል፤ ይንከባከባል፣ አረሙንም እየነቀለ ለፍሬ ይበቃ ዘንድ ብርሃንን እየናፈቀ በተስፋ ይቆያል፤ ክረምቱ አልፎም የመጸው ወቅት ይተካል፡፡ ተራሮች፣ ሜዳና ሸንተረሩ ሁሉ ልምላሜን ይላበሳሉ፣ አበቦች ይፈካሉ፤ ገበሬው በክረምት ሲደክምበት የከረመውን እርሻ በልምላሜ ያጌጣል፣ ፍሬ ለመያዝም ደረስኩ ደረስኩ እያለ የገበሬውን ልብ በተስፋ ይሞላል፡፡

በቤተ ክርስቲያናችን በዚህ በልምላሜ ወቅት ከመስከረም ፳፮ ጀምሮ ያሉት ፵ ቀናት ዘመነ ጽጌ ተብሎ ይጠራል፡፡ ይህ ወቅት ቅድስት ቤተ ክርስቲያናችን እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ከልጇ ከጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ፣ ከአረጋዊው ዮሴፍና ሰሎሜ ጋር ወደ ግብፅ የተሰደደችበትን ጊዜ ታስባለች፡፡

በእነዚህ ሳምንታትም ዕለተ ሰንበት ከዋዜማው ጀምሮ ሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያን፣ ካህናትና ምእመናን ከምሽቱ ሦስት ሰዓት ጀምሮ የእመቤታችንን ስደት በማስመልከት በአባ ጽጌ ድንግል የተደረሰውን “ማኅሌተ ጽጌ” ፣ የተሰኘው ድርሰቱ፣ በቅዱስ ያሬድ መዝሙር እመቤታችንና ጌታችንን ወደ ግብፅ የተሰደዱበትን ወቅት በማስመልከት ያመሰገነበትን ጸሎት እንዲሁም በዝማሬ፣ በሽብሸባ፣ በእልልታና በጭብጨባ በድምቀት ያነጋሉ፡፡ እመቤታችንን በአበባ፣ ጌታችን መድኃኒታችን ኢያሱስ ክርስቶስን ደግሞ በፍሬ እየመሰሉ ሊቃውንቱ ያመሰግናሉ፡፡

አዳም የእግዚአብሔርን ትእዛዝ በመተላለፉ ምክንያት የዲብሎስ ባሪያ ሆነ፤ ፈጣሪውን አጥቷልና ተሸሸጎ የጸጸት ዕንባን አነባ፡፡ የአዳምን መጸጸት የተመለከተው እግዚአብሔርም “ከአምስት ቀንና ግማሽ ቀን በሃላ እምርሃለሁ፤ ይቅርታም አደርግልሃለሁ፤ በይቅርታ ብዛትና በምሕረቴ ብዛት ወደ አንተ ቤት እወርዳለሁ፤ በወገንህም ከርስ አድራለሁ፤ ይህ ሁሉ ስለ አንተ ደኅንነት ሆናል፡፡” (ቀሌ. ፫፥፲፱) በማለት ቃል ኪዳን ገባለት፡፡ ጊዜው ሲደርስም አዳምና ልጆቹን ከዲያብሎስ ባርነት ነፃ ያወጣ ዘንድ በቅዱስ ገብርኤል ብስራት ከእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ከሥጋዋ ሥጋን ከነፍሷ ነፍስን ተዋሕዶ በቤተልሔም በከብቶች ግርግም ተወለደ፡፡

ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርሰቶስ ከእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ሲወለድ ሰብአ ሰገል ከምሥራቅ ወደ ኢየሩሳሌም መጡ፡፡ እንዲህ ሲሉ፡- “ኮከቡን ከምሥራቅ አይተን እንሰግድለት ዘንድ መጥተናልና የተወለደው የአይሁድ ንጉሥ ወዴት ነው?” ሲሉ ጠየቁ፡፡ በይሁዳ፣ በገሊላና በሰማርያ የሮማውያን ተወካይ የነበረው ንጉሥ ሄሮድስ የጌታችን ንግሥና ምድራዊ ንግሥና መስሎት መንግሥቴን ሊቀማኝ ነው ብሎ ደነገጠ፡፡ ፊሪሳውያን መሲህ ተወልዶ ከሮማውያን አገዛዝ ነፃ ያወጣናል፡፡” ብለው ያምኑ እንደነበር ስለሚያውቅም ይህ የተፈጸመ መስሎት ጭንቀቱ በረታ፡፡ የተወለደውን ሕፃንም ለመግደል ተነሣ፡፡ (ማቴ. ፪፥፩-፫)

ሄሮድስም ሰብአ ሰገልን አስጠርቶ “ሄዳችሁ የዚህን ሕፃን ነገር ርግጡን መርምሩ፣ ያገኛችሁትም እንደሆነ እኔም መጥቼ እሰግድለት ዘንድ በእኔ በኩል ተመልሳችሁ ንገሩኝ” በማለት ተናገራቸው፡፡ (ማቴ. ፪፥፰) ሰብአ ሰገልም በኮከቡ እየተመሩ ጉዞአቸውን ቀጥለው ጌታችንን ከእናቱ ጋር አገኙት፤ ተንበርክከው ሰገዱለት፤ ወርቅ፣ ዕጣን፣ ከርቤ እጅ መንሻ አቀረቡለት፡፡ የእግዚአብሔር መልአክ ወደ ሄሮድስ እንዳይመለሱ፤ ነገር ግን መንገድ ቀይረው ወደ ሀገራቸው እንዲሄዱ በነገራቸው መሠረት በሌላ መንገድ ወደ መጡበት ተመለሱ፡፡

እነርሱም ከሄዱ በኋላ እነሆ የጌታ መልአክ በሕልም ለዮሴፍ ታይቶ “ሄሮድስ ሕፃኑን ሊገድለው ይፈልገዋልና ተነሥ፤ ሕፃኑንና እናቱን ይዘህ ወደ ግብጽ ሽሸ፤ እስክነግርህም በዚያ ተቀመጥ አለው፡፡” አረጋዊው ዮሴፍም ሳይጠራጠር እመቤታችንና ጌታችንን እንዲሁም ረዳት ትሆናቸው ዘንድ ሰሎሜን አስከትሎ “ልጄን ከግብፅ ጠራሁት” ተብሎ በነቢይ የተነገረው ፈጸም ዘንድ ወደ ግብፅ ወረደ፡፡ (ማቴ. ፪፥፲፫-፲፬) ሄሮድስም ሰብአ ሰገል እንዳታለሉት በተረዳ ጊዜ ጌታችን መድኃኒታችን ኢያሱስ ክርስቶስን ያገኘ መስሎት የቤተልሔምን አንድ መቶ አርባ አራት ሺህ ሕፃናትን በግፍ አስገደለ፡፡ ቤተልሔምና አውራጃዎቿም ሄሮድስ ባስገደላቸው ሕፃናት ደም ተጥለቀለቀች፡፡

ለሦስት ዓመት ከስድስት ወር በግብፅ ብዙ ጸዋትወ መከራዎችን እየተቀበሉ ከቆዩ በኋላ ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስን ይፈልገው የነበረው ሄሮድስ ሞተ፡፡ ሄሮድስም ከሞተ በኋላ እነሆ የጌታ መልአክ በግብፅ ለዮሴፍ በሕልም ታየው፡፡ እንዲህ ሲል፡- “የሕፃኑን ነፍስ የሚሹ ሙተዋልና ተነሥተህ ሕፃኑንና እናቱን ይዘህ ወደ እስራኤል ሀገር ሂድ” አለው፡፡ ኅዳር ፮ ቀንም ግብፅ ከምትገኘው ቁስቋም የምትባል ቦታ ደረሱ፡፡ በዚያም የእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ቤተ ክርስቲያን ቅዳሴ ቤት ተከበረ፡፡ አረጋዊው ዮሴፍም ሕፃኑንና እናቱን ይዞ ወደ እስራኤል ምድር ገባ፡፡” (ማቴ. ፪፥፲፱-፳፩)

ይህንን የእመቤታችን ከልጇ ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ጋር ወደ ግብፅ መሰደድን፣ በዚያም የደረሰባቸውን መከራ በማሰብ ኦርቶዶክሳውያን ምእመናን በረከት ያገኙ ዘንድ በጾም፣ በስግደት እንዲሁም ልዩ ልዩ የትሩፋት ተግባራትን በመፈጸም ወቅቱን ያስቡታል፡፡ ኅዳር ፮ ቀንም የእመቤታችንን ወደ ቁስቋም መድረስ ምክንያት በማድረግ በቁስቋም ማርያም ቤተ ክርስቲያን ከዋዜማው ጀምሮ በሰዓታቱ፣ በዝማሬ በማሳለፍ፣ ታቦት ወጥቶም በሥርዓተ ንግሥ ይጠናቀቃል፡፡

ወስብሐት ለእግዚአብሔር

“በሚሞት ሰውነታችሁ ኃጢአትን አታንግሡአት” (ሮሜ. ፮፥፮)

በእንዳለ ደምስስ

ኃጢአት የሚለው ቃል “ኃጥአ” ከሚለው የግእዝ ቃል የወጣ ሲሆን ትርጉሙም፡- አጣ፣ መገፈፍ፣ መነጠቅ ማለት ነው፡፡ አዳም አባታችን ለሰባት ዓመታት በገነት ፍጥረታትን እየገዛና እያዘዘ በተድላና ደስታ ሲኖር በምክረ ከይሲ ተታሎ አትብላ የተባለውን ዕፀ በለስ በላ፣ ኃጢአትንም በራሱ ላይ አነገሣት፣ የእግዚአብሔርንም ትእዛዝ ተላለፈ፡፡ በዚህም ምክንያት ክብሩን አጣ፣ ጸጋውም ተገፈፈ፣ በእግዚአብሔር የተሰጠውንም የገዢነት ሥልጣን ተነጠቀ፣ እስከ መረገምም አደረሰው፡፡ “ከእርሱ እንዳትበላ ከአዘዝኩህ ከዚያ ዛፍም በልተሃልና ምድር በሥራህ የተረገመች ትሁን፤ በሕይወት ዘመንህም ሁሉ በድካም ከእርስዋ ትበላለህ፤ እሾህና አሜከላ ታበቅልብሃለች፣ የምድርንም ቡቃያ ትበላለህ፤ ወደ ወጣህበት ምድር እስክትመለስ ድረስ በፊትህ ወዝ ትበላለህ፣ አፈር ነህና ወደ አፈርም ትመለሳለህና” ተብሎ እግዚአብሔርን ያህል ጌታ፣ ገነትን ያህል ቦታ አጣ፤ወደ ምድረ ፋይድም ተባረረ፡፡ ዘለዓለማዊ ሆኖ የተፈጠረው የሰው ልጅ በራሱ ላይ ኃጢአትን አንግሧልና ዘለዓለማዊነትን አጣ፤  ይህ ፍርድ የኃጢአት ሥራ ያስከተለው ውጤት እንደሆነ እንረዳለን፡፡  

አዳም የእግዚአብሔርን ትእዛዝ መተላለፉን በተረዳ ጊዜ ኃፍረቱን ይሸፍን ዘንድ ቅጠልን አገለደመ፣ ተሸሽጎም በደሉ ዕረፍት ነስቶት በጸጸት አለቀሰ፡፡ (ዘፍ. ፲፯-፲፱) እግዚአብሔር ፍርዱ እውነተኛ ነውና ሞት በምድር ላይ ነገሠ፡፡ አዳምም ከነበረው ክብር ወረደ፤ “የኃጢአት ትርፍዋ (ደመወዝዋ) ሞት ነውና” (ሮሜ. ፮፥፳፫) ተብሎ እንደተጻፈ በወዙና በላቡ ይበላ ዘንድ እሾህና አሜኬላውን እየመነጠረ ምድርንም እየቆፈረ ሕይወቱን ለማቆየት ታገለ፡፡ ነገር ግን እግዚአብሔር ፍጹም ቸር ነውና የአዳምን ንስሓ ተመልክቶ “አምስት ቀን ተኩል ሲሆን ከልጅ ልጅህ ተወልጄ አድንሃለሁ” (ቀሌ. ፫፥፱) ባለው አምላካዊ ቃሉ መሠረት አምስት ሺህ አምስት መቶ ዘመን ሲፈጸም ከእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ከሥጋዋ ሥጋ ከነፍሷ ነፍስ ነስቶ ይህንን ዓለም ያድን ዘንድ ተወለደ፡፡ 

መጥምቀ መለኮት ቅዱስ ዮሐንስም “እነሆ የዓለሙን ኃጢአት የሚያስወግድ የእግዚአብሔር በግ፡፡ ከእኔ በፊት የነበረ ሰው ከእኔ በኋላ ይመጣል ብዬ ስለ እርሱ የነገርኋችሁ ይህ ነው፤ እርሱ ከእኔ አስቀድሞ ነበርና፡፡ ነገር ግን እስራኤል እንዲያውቁት ስለዚህ እኔ በውኃ ላጠምቅ መጣሁ፡፡” (ዮሐ. ፩፥፳፱-፴፩) ሲል የመሠከረለት ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በገባው ቃል መሠረት በዚህ ምድር ላይ ተመላለሰ፡፡ ወንጌልን አስተማረ፣ ድውያንን ፈወሰ፣ በቀራንዮ አደባባይ በመስቀል ላይ ተሰቀለ፣ ሞተ፣ ተቀበረ፣ በትንሣኤውም ትንሣኤያችንን አወጀ፡፡ አዳምና ልጆቹንም ወደ ቀደመ ክብራቸው መለሰ፡፡

እግዚአብሔር ኃጢአትን እንጂ ኃጢአተኛን አይጠላምና የተከፈለልንን ዋጋ አስበን እንደ ቃሉም ተጉዘን፣ የተሰጠንን ክብር ጠብቀን መገኘት ከእኛ ከኦርቶዶክሳውያን ይጠበቃል፡፡ ለዚህም ነው ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ ለሮሜ ሰዎች በላከው መልእክቱ “በሚሞት ሰውነታችሁ ኃጢአትን አታንግሡአት” (ሮሜ ፮፥፮) ሲል የሚያሳስበን፡፡

ኃጢአት ከእግዚአብሔር አንድነት ይለያል፣ ሥጋንና ነፍስን ያጎሳቁላል፣ በመጨረሻም ወደ ሞት ያደርሳል፡፡ በተለይም በርካታ ወጣቶች ይጉዳቸው ወይም ይጥቀማቸው ሳያመዛዝኑ ሁሉንም የመሞከር ችግር በከፍተኛ ደረጃ ስለሚታይባቸው በቀላሉ ኃጢአትን ለመለማመድ ይፈጥናሉ፡፡ በቅድስት ቤተ ክርስቲያናችን ወጣትነትን የእሳትነት ዘመን መሆኑን ታስተምራለች፡፡ ይህንን የእሳትነት ዘመንን በመንፈሳዊነት ማረቅ፣ መግራት ካልተቻለ ጥፋቱ ከራስ አልፎ ቤተሰብን፣ ማኅበረሰብንና ሀገርን እንዲሁም ቅድስት ቤተ ክርስቲያንን ይጎዳል፡፡ ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ ለመንፈስ ልጁ ጢሞቴዎስ “አንተ ግን በተማርህበትና በተረዳህበት ጸንተህ ኑር፤ ከማን እንደተማርኸው ታውቃለህና” (፪ጢሞ. ፫፥፲፬) እንዲል ከእግሩ ሥር ቁጭ ብሎ በመማሩ፣ የሚያከናውናቸውን መንፈሳዊ ተግባራት ሁሉ በማገዝና በመሳተፍ መንፈሳዊነትን ገንዘብ አድርጓልና ወጣትነቱን ተጠቅሞበታል፡፡ ከእግሩ ሥር ቁጭ ብሎ ሲማርና ሲያገለግለው የነበረው ደቀ መዝሙሩ ዴማስ ግን የወጣትነት ስሜቶች ተገዢ ሆኖ ለዓለም እጁን በመስጠት፣ ብልጭልጯ የተሰሎንቄ ከተማ ማርካው ከአገልግሎቱ አሰናክላ ጥላዋለች፤ ኃጢአትንም በራሱ ላይ አነገሣት፡፡ “ዴማስ ይህንን የዛሬውን ዓለም ወድዶ እኔን ተወኝ፤ ወደ ተሰሎንቄም ሄደ” (፪ጢሞ. ፬፥፲) እንዲል ፡፡

የግቢ ጉባኤያት ተማሪዎቻችንም በወጣትነት ዕድሜ ላይ የሚገኙ በመሆኑ ከቤተሰብ የሚርቁበት፣ በራስ መተማመን የሚያዳብሩበት፣ ለዓለሙም ሆነ ለመንፈሳዊው ዓለም ራሳቸውን አጋልጠው የሚሰጡበት ጊዜ ላይ በመሆናቸው በማስተዋል ራሳቸውን ሊመሩ ይገባል፡፡ ሥጋዊ ፍላጎትና የጓደኛ ግፊት ሳይበግራቸው ወደ እግዚአብሔር በመቅረብ የሚታገላቸውን የኃጢአት ቀንበር አሽቀንጥረው በመጣል በመንፈሳዊ ሕይወት መታነጽ ይጠበቅባቸዋል፡፡ ዲያብሎስ ዙሪያቸውን አጥሮ ከመንገዳቸው ሊያስወጣቸው እንቅልፍ እንደሌለው በመረዳት ከምን ጊዜውም በላይ በጾም፣ በጸሎት፣ በስግደትና በአገልግሎት በመትጋት ድል ሊነሡት ይገባል፡፡ “እንግዲህ ዐዋቂዎች ሁኑ፣ ትጉም፣ ጠላታችሁ ጋኔን የሚውጠውን ፈልጎ እንደሚያገሳ አንበሳ ይዞራልና፡፡ እርሱንም በእምነት ጸንታችሁ ተቃወሙት” በማለት ቅዱሰ ጳውሎስ እንዳስተማረው፡፡ (፩ጴጥ. ፭፥፰-፱)

በሁለቱም ወገን ማለትም ዓለማዊውን ጥበብ በመንፈሳዊ ጥበብና ዕውቀት በመግራት ሀገርንና ቅድስት ቤተ ክርስቲያንን ለመጥቀም ትክክለኛ ጊዜው የወጣትነት ጊዜ ነው፡፡ ይህን ጊዜ በዋዛ ፈዛዛ ማሳለፍ ስለማይገባ ከእግዚአብሔር የተሰጠንን የወጣትነት የዕድሜ በረከት ልንጠቀምበት ያስፈልጋል፡፡ “በሚሞት ሰውነታችሁ ኃጢአትን አታንግሡአት” (ሮሜ. ፮፥፮) ተብለን እንደተማርን መንፈሳዊነትን ለጽድቅ አገልግሎት በማዋል ዓለም ከዘረጋችውና ካጠመደችው የኃጢአት ወጥመድ ልንርቅ ይገባል፡፡

ወስብሐት ለእግዚአብሔር 

የጥያቄዎቻችሁ መልስ:- ከሱስ መላቀቅ አቃተኝ

ክፍል ሁለት

የሁለተኛ ዓመት የከፍተኛ ትምህርት ተቋም ተማሪ ነኝ፤ ተወልጄ ያደግሁት በአነስተኛ የገጠር ከተማ ነው፡፡ በመንደራችን ጫት የሚቅም ሰው አይደለም ጫት ምን እንደሆነ በተግባር አይታወቅም ማለት ይቻላል፡፡ ወደ ከፍተኛ ትምህርት ተቋም በገባሁ አንድ ዓመት ባልሞላ ጊዜ ውስጥ በጓደኞቼ ግፊት ጫት መቃም ለንባብ ይረዳል በሚል ሰበብ የጫት ተጠቃሚ ሆንኩ፡፡ አሁን ከጫት ቃሚነት አልፌ በተለያዩ ሱሶች ተይዣለሁ፡፡ ከእነዚህ ሱሰሶች ለመላቀቅ በተለያዩ ጊዜያት ሞክሬአለሁ፤ ነገር ግን አልተሳካልኝም፡፡ ይህ የሁል ጊዜ ጭንቀቴ ነውና ምን ትመክሩኛላችሁ?

ገብሬ (ከሐዋሳ ዩኒቨርሲቲ ግቢ ጉባኤ)

“ከሱስ መላቀቅ አቃተኝ” በሚል ገብሬ (ከሐዋሳ ዩኒቨርሲቲ ግቢ ጉባኤ) ልኮልን በክፍል አንድ ዝግጅታችን ከተያዘባቸው ልዩ ልዩ ሱሶች በቁርጠኝነት መውጣት እንዲችል መ/ር ፍቃዱ ሳህሌ ሁለት መሠረታዊ ነጥቦችን አንስተዋል፡፡ እነዚህም፡- ምክንያቱን በሚገባ መመርመር እና የሚያስከትለውን ጉዳት ማጤን የሚሉ ንዑስ ርእሶችን አንስተው አብራርተውልናል፡፡ በክፍል ሁለት ዝግጅታችን ደግሞ ሊወሰዱ የሚገባቸው ርምጃዎች ላይ በማተኮር ያቀርቡልናል፡፡

ሀ. መወሰን

ይህ የመጀመሪያው መሠረታዊ ርምጃ ነው፡፡ አንድ ሰው ሳይወስን ምንም ነገር ማድረግ አይችልም፡፡ ከጥያቄህ እንደተዳነው ከሱሶች ለመላቀቅ ፍላጎት አለህ፤ ይህ ደግሞ ለመወሰንህ በቂ መነሻ ነው፡፡ ፍላጎትና ውሳኔ ግን ተመጋጋቢነት እንጂ አንድነት የላቸውም፡፡ ብዙ ሰዎች ፍላጎት ይኖራቸውና ውሳኔ የመወሰን ዐቅም ያጣሉ፡፡ ውሳኔ የመወሰን ዐቅም ምክንያቱንና ውጤቱን በሚገባ በማወቅ ላይ ተመሥርቶ በቁርጠኝነት የሚረጋገጥ የድርጊት እርሾ ነው፡፡ ለመወሰን ስንነሳም ልንጋፈጣቸው የሚገቡ ልዩ ልዩ ተግዳሮቶች መኖራቸውን መገንዘብ ይገባል፡፡ ከእነዚህም መካካል፡-

ጊዜያዊ ሕመሞች፡- በራችንን ከፍተን ያስገባናቸው ክፉ ነገሮች ወደ ሱስነት ከተቀየሩ በኋላ ዳግም በራችንን ከፍተን ውጡልን ብንላቸው በቀላሉ አይወጡም፡፡ በገቡበት ወቅት ቀስ በቀስ የተቆጣጠሯቸውን ቦታዎች በዋዛ የሚለቁ አይሆኑም፡፡ ወንበዴ የተቆጣጠራቸውን ሥፍራዎች መንግሥት አስገድዶና አስፈላጊውን መሥዋዕትነት ከፍሎ እንደሚያስለቅቅ ሁሉ እነዚህም በቆራጥ ውሳኔ ተገደው እንዲወጡ ማድረግ ያስፈልጋል፡፡ ወንበዴ ለጊዜው የተቆጣጠረውን አካባቢ አጠፋፍቶና አውድሞ እንደሚሄድ ሁሉ ሱሶችም የተቆጣጠሩትን ሰውነት አካላዊና ኅሊናዊ ጉዳት ስለሚያደርሱበት በለቀቁትም ጊዜ ክፍተቱን መልካም ነገሮች ተቆጣጥረው እስኪሞሉትና ሰውነት እስኪያገግም ድረስ መጠነኛና ጊዜያዊ ሕመሞችና ድብርት እንደሚኖር መረዳት ይገባል፡፡

ተአማኒነት ማጣት፡- በክፉ የሱሰሰኝነት ሕይወቱ ያውቁትና ይሸሹት የነበሩት የትምህርት ቤት ወይም የሥራ ጓደኞች፣ ቤተሰቦችና ልዩ ልዩ የማኅበረሰቡ አባላት ወደ ቀደመ ማንነቱ የተመለሰውን ሰው ፈጥነው ላያምኑት ይችላሉ፡፡ እንደ አንዳንድ ክፉ ጓደኛ ቀርቦ ሊያጠምዳቸው መስሏቸው ሊሸሹትም ይችላሉ፡፡ ይህ ችግር ጊዜያዊ ስለሆነ ሳትቀየምና ተስፋ ሳትቆርጥ የጀመርከውን ከሱስ የመላቀቅ ጉዞ በፍጥነት ወደፊት መገስገስ ይኖርብሃል፡፡ ቅዱስ ጴጥሮስ ይህን በማስመልከት ሲያጽናናን “በቅንነትና እግዚአብሔርን በመፍራት ግብራችሁን አሳምሩ፤ ሥራችሁን ክፉ አስመስለው የሚያሙአችሁ ሰዎች ቢኖሩ ስለ ክርስቶስ ከምትሠሩት ከሥራችሁ ደግነት የተነሣ የሚያሙአችሁ ሰዎች ያፍሩ ዘንድ፡፡” (፩ኛጴጥ. ፫፥፲፮) እንዳለው፡፡

የክፉ ጓደኞች ተቃውሞ፡- በክፉ ምክራቸው ሰዎችን እየጎተቱ ወደ ጥፋት የሚከቱ ሰዎችና በእነርሱም ላይ አድሮ ይህን የሚያሠራቸው ሠይጣን አንድ ሰው ወደ መልካምና ክርስቲያናዊ ሕይወቱ ሲመለስ ዝም ብሎ የማየት ትዕግሥት አይኖራቸውም፡፡ ስለዚህም ያ ሰው ፍላጎቱንና ውሳኔውን እንዳያሳካ ለማድረግ የቻሉትን ሁሉ ይፈጽማሉ፡፡ ቢችሉ መጀመሪያውኑ እንዳይወጣ፣ አለበለዚያም ከወጣ በኋላ ተልፈስፍሶ ወደ እነርሱ እንዲመለስ ለማድረግ የማይፈነቅሉት ድንጋይ. የማቆፍሩት ጉድጓድ አይኖርም፡፡ አሁንም ቅዱስ ጴጥሮስ ይህን በማስመልከት እንዲህ ይለናል፡፡ “የአሕዛብን ፈቃድ ያደረጋችሁበት ያለፈው ዘመን ይበቃችኋልና ዝሙትን፣ ምኞትን፣ ስካርን ወድቆ ማደርን፣ ያለ ልክ መጠጣትን፣ ጣዖት ማምለክን፡፡ እንግዲህ ዕወቁ ወደዚህ ሥራ አትሩጡ፤ ከዚህ ጎዳና ልክ መጠን ከሌለው ከዚያ ሥራም ተለዩ፤ እነሆ ከእነርሱም መካከል ሰዎች ስለ እናንተ ያደንቃሉ፤ በዚያ በቀድሞው ሥራ ሳትተባበሩዋቸው ሲያዩአችሁም ይሰድቡአችኋል፡፡” (፩ጴጥ. ፫፥፬) ይህን በማወቅ አንተም ምንም ዓይነት መከራ ቢያመጡብህ ወደ ኋላ ላለመመለስ መወሰን አለብህ፡፡

ለ. ሳያቅማሙ መፈጸም

ውሳኔ ብቻውን ምንም ያህል የተጠናና ያማረ ቢሆንም እንኳ ምንም ፋዳ አይኖረውም፡፡ የብዙዎቻችን ችግር የመወሰን ሳይሆን የመተግበር ሆኖ ነው የሚገኘው፡፡ ውሳኔህን ወደ ተግባር ለመለወጥ ሳትነሣሣም በቀጥታ የታሰርክባቸውን የሱስ ገመዶች ሁሉ በጣጥሰህ መጣል እንዳለብህ አትዘንጋ፡፡ ከሱስ እንዳትወጣ የሚፈልጉ አዛኝ የሚመስሉ ክፉ ጓደኞች “በአንድ ጊዜ ስለሚከብድህ ቀስ በቀስ እያስታመምክ ለመተው ሞክር“ ሊሉህ ይችላሉ፡፡ ይህ ግን የማዘናጊያ መንገድ እንጂ ሁነኛ መፍትሄ ኤደለም፡፡ የሚከተሉትን ነጥቦች በወጉ በመረዳትና በመጽናናት የተያዝክበትን የሱስ መረብ መበጣጠስ ብቻ ሳይሆን ወደዚያ የሚወስዱ የተለያዩ መንገዶችን ሁሉ መዝጋት ይኖርብሃል፡፡

ሰው ክቡር ፍጡር መሆኑን መረዳት፡- ሰው በትነት ተፈጥሮ በእግዚአብሔር መልክና ምሳሌ የተፈጠረ፣ በበደሉ ክብሩን ቢያጣም ወልደ እግዚአብሔር ሰው ሆኖ ወደ ቀደመ ክብሩ የመለሰው የፍጥረታት ቁንጮ ነው፡፡ ለባዊት፣ ነባቢትና ሕያዊት ነፍስ ስላለችውም በባሕርይው ዐዋቂ ሆኖ የተፈጠረ፣ የልጅነትን ጸጋ በጥምቀት በተቀበለ ጊዜም ሁሉ ኃጢአትን የሚቃወምበት ኃይልና ጸጋ የተጨመረለት ክቡር ፍጡር ነው፡፡ በዚህም የተነሣ ከመጀመሪያዋ ጀምሮ ለርኩሰት ሳይሆን ለቅድስና ጠርቶናል፡፡ (፩ኛተሰ. ፬፥፯) ሁሉ ቢፈቀድልንም ሁሉ እንደማይጠቅመንና አንዳች ሊሰለጥንብን እንደማይገባ አስተምሮናል፡፡ (፩ኛ ቆሮ. ፮፥፲፪፤ ፲፥፳፫) ቅዱስ ዳዊትም “ሰውስ ክቡር ሆኖ ሳለ አላወቀም፣ ልብ (ማስተዋል) እንደሌላቸው እንስሶች ሆነ፣ መሰላቸውም፡፡” (መዝ. ፵፰፥፳) እንዲል፡፡

እግዚአብሔርን ማወቅ፡- ይህን ስንል በባሕርይው ሳይሆን በገለጠልን መጠን ከቅዱሳት መጻሕፍትና ከሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያን ቀርቦ ዐቅም በፈቀደ መረዳት ማለታችን ነው፡፡ ፈቃዱን፣ ሀልዎቱን ምሉዕነቱን፣ከሀሊነቱ፣ ሁሉን ቻይነቱን፣ ፍቅሩን፣ ወዘተ ባወቅን ቁጥር ወደ እርሱ የምንቀርብ እንሆናለን፡፡ ከዚያም የሚገዛን፣ የሚያዘንና የሚቆጣጠረን ሱስ ሳይሆን አምላካችን ቅዱስ እግዚአብሔር ይሆናል፡፡ በሃይማኖት መኖራችንን ዓለማ የምናስተውለውና አምነን የምንታመነው ያኔ ነው፡፡ እንዲህ ከሆነም ከእግዚአብሔር ከአንተ ጋር ስለሚሠራ የሚያሸንህፍ ምንም ዓይነት ቁሳዊ፣ ምናባዊና መንፈሳዊ ጠላት ሊኖር እንደማይችል እርግጠኛ ሁን፡፡

ምክንያተኝነትን ማራቅ፡- ምንም እንኳን ለገጠሙን ችግሮች ልዩ ልዩ ምክንያቶችን መደርደር ብንችልም ዋነኛው ተጠያቂዎቹ ግን እኛው ራሳችን ነን፡፡ ለመውጣትም በምናደርገው ትግል ዋነኞቹ ተጋዳዮች እኛው ነን፡፡ በራሳችን ጣፋት ለገጠሙን ለሚገጥሙን ችግሮች ክሳችን ውጪ ሌሎችን ተጠያቂ ለማድረግ መሞከር ከኅሊና ወቀሳም ሆነ ከእግዚአብሔር ፍርድ እንደማድን ማወቅ ዐዋቂነት ነው፡፡ በተጨማሪም ተሸናፊነትን አርቆ እችላለሁ፤ እግዚአብሔር ይረዳኛል፣ ብሎ ችግሩን መጋፈጥ ራስን በመግዛት ወደ እግዚአብሔር ለመቅረብ ያስችላል፡፡

ስለዚህ ውድ ወንድማችን የሕያው እግዚአብሔር ማደሪያ መሆንህ (፩ቆሮ. ፫፥፲፮) ኃልን በሚሰጥ በክርስቶስ ሁሉን እንምችል እና በእርሱ ከአሸናፊዎች እንደምትበልጥ ማመን ይኖርብሃል፡፡ (ፊል. ፬፥፲፫፤ ሮሜ ፰፥፴፯-፴፱) ከሱሶች ስትለያይ ከሱሰኛ ጓደኞችህም መለያየት እንደሚኖርብህ አትርሳ፡፡ በእነርሱ ምትክ መንፈሳውን ጓደኞች በመተካት፣ ጸበል በመጠመቅ፣ ወደ ቤተ ክርስቲያን በመገስገስና ንስሓ አባት ይዘህ ንስሓ በመግባት፣ ራስህን ለመንግሥተ ሰማያት ማዘጋጀት ይኖርብሃል፡፡ ከቃለ እግዚአብሔር ባለመራቅ እና ወደ ቅዱሳት መካናት ከክተርስቲያን ወንድሞችና እኅቶችህ ጋር በመጓዝ የቅዱሳንን በረከት ለማግኘት መትጋት አለብህ፡፡ ቅዱስ ጳውሎስ ይህን በተመለከተ “ብልቶቻችሁ ዓመፃ ሊያደርጉ ለርኩሰትና ለዓመፃ ባሪያዎች አድርጋችሁ እንዳቀረባችሁ እንደዚሁ ብልቶቻችሁ ሊቀደሱ ለጽድቅ ባሪያዎች አድርጋችሁ አሁን አቅርቡ፡፡” (ሮሜ፮፥፲፱) በማለት ያስተማረን ቃል የሕይወትህ መመሪ\ በማድረግ እንድትመላለስ እንመክርሃለን፡፡

ወስብሐት ለእግዚአብሔር

የጥያቄዎቻችሁ መልስ:- ከሱስ መላቀቅ አቃተኝ

የሁለተኛ ዓመት የከፍተኛ ትምህርት ተቋም ተማሪ ነኝ፤ ተወልጄ ያደግሁት በአነስተኛ የገጠር ከተማ ነው፡፡ በመንደራችን ጫት የሚቅም ሰው አይደለም ጫት ምን እንደሆነ በተግባር አይታወቅም ማለት ይቻላል፡፡ ወደ ከፍተኛ ትምህርት ተቋም በገባሁ አንድ ዓመት ባልሞላ ጊዜ ውስጥ በጓደኞቼ ግፊት ጫት መቃም ለንባብ ይረዳል በሚል ሰበብ የጫት ተጠቃሚ ሆንኩ፡፡ አሁን ከጫት ቃሚነት አልፌ በተለያዩ ሱሶች ተይዣለሁ፡፡ ከእነዚህ ሱሰሶች ለመላቀቅ በተለያዩ ጊዜያት ሞክሬአለሁ፤ ነገር ግን አልተሳካልኝም፡፡ ይህ የሁል ጊዜ ጭንቀቴ ነውና ምን ትመክሩኛላችሁ?

ገብሬ (ከሐዋሳ ዩኒቨርሲቲ ግቢ ጉባኤ)

የወንድማችን ጥያቄ ብዙዎች እየተቸገሩበት ከሚገኙ ጉዳዮች አንዱ መሆኑን በተለያዩ ጊዜያት ለዝግጅት ክፍላችን በሚደርሱን መልእክቶች ተረድተናል፡፡ በዚህም መሠረት ለጥያቄው ምላሽ ይሰጡን ዘንድ መ/ር ፍቃዱ ሳህሌን ጋብዘናል፣ እነሆ ምላሹ፡፡

በቅድሚያ የዘወትር ጭንቀትህ ገልጸህ መልስ እንድንሰጥህ በመጠየቅህ ልናመሰግንህ እንወዳለን፡፡ ይህ በመንፈሳዊ ሕይወት መስመር ለመጓዝና ከእግዚአብሔር ጋር ለመኖር ያለህን ጉጉት ያሳየናል፡፡ የችግሩን አደገኛነትና ነውርነት ከመገንዘብም በተጨማሪ ለመላቀቅ ያደረግሃቸው ተደጋጋሚ ሙከራዎች የጭንቀትህን ደረጃዎችና ከሱስ ለመውጣት ያለህን የመሻት ጥልቀት ያመለክታል፡፡

ሱስ ክፉ ልማድ ነው፡፡ ብዙ ሰዎች እንደ ቀልድ (ጨዋታ) እየጀመሩት በደጋገሙት ቁጥር ኅሊናቸው እየተቆጣጠራቸው ከሕዋሳቶቻቸው ጋር ክፉኛ የሚቆራኝ የሕይወት እንቅፋት ነው፡፡ ከዚያም ራስን የመግዛት ኃይልን ከሰዎች በመቀማት በልጓምነት ሸብቦ ወደፈለገው የጥፋት አቅጣጫ የሚወስድ የክርስቲያናዊ ሕይወት ብቻ ሳይሆን የሰብአዊነትም ጠንቅ ነው፡፡ ሰይጣን ሰዎችን እንዳሻው የሚጋልብበትና የወደደውን የሚሠራበት ፈረስ ነው፡፡

በምድራችን ላይ ብዙ ዓይነት ሱሶች አሉ፡፡ ለምሳሌ ያህል፡- የወሬ ሱስ፣ የአልኮል መጠጦች፣ የሲጋራ፣ የቡና፣ አንተ እንደተቀስከው የጫት፣ የተለያዩ አደንዛዥ ዕፆችና ልዩ ልዩ የሱስ ዓይነቶችን መዘርዘር ይቻላል፡፡ አብዛኞቹ ሌሎች የሱስ ተጠቂዎችን በማየት እስቲ እኔም ልሞክረው ተብለው እንደ ቀልድ የተጀመሩ ቀስ በቀስ አእምሮን የተቆጣጠሩና መሽገው የቀሩ ናቸው፡፡ ጥቂቶቹ ደግሞ በብስጭትና በሌሎች አስገዳጅ ሁኔታዎች ተጀምረው የሰውን ኅሊና አሥረው የተቀመጡ ናቸው፡፡ ከዚህም በተጨማሪ አንዱ የሱስ ዓይነት ብቻውን የሚኖር ሳይሆን ሌላውን እየጋበዘ በአንድ ሰው ሕይወት ተደብለው መውጫ መግቢያ እያሳጡ ነው የሚኖሩት፡፡ እንዲህ እየተጠራሩ ኅሊናውንና ሕዋሳቱን ሁሉ በመቆጣጠር ወደ ቀደመ ሕይወቱና ማንነቱ እንዳይመለከትና እንዳይመለስ ለማድረግ ያለ ምንም ዕረፍት በኅብረት የሰውን አእምሮ ይቆጣጠራሉ፡፡

ውድ ወንድማችን ከተያዝክባቸው ልዩ ልዩ ሱሶች በቁርጠኝነት መውጣት እንድትችል የሚከተሉትን መሠረታዊ ነጥቦች ማስተዋልና መተግበር ይጠበቅብሃል፡፡

፩. ምክንያቱን በሚገባ መመርመር

ሰዎች በእነዚህና መሰል ሱሶች የሚጠመዱበትን ምክንያት ውስጣዊና ውጫዊ በማለት መከፋፈል ይቻላል፡፡ እንደ አጠቃላይ ሲዘረዘሩ ግን የግል ፍላጎትና ተነሣሽነት፣ የቤተሰብ አኗኗርና አስተዳደግ፣ ማኅበረሰባዊ የባህል ተጽእኖ አጉል ጓደኛ፣ ሥራ ፈትነት፣ ብስጭትና ሌሎችም እንደ መነሻዎች ማየት ይቻላል፡፡ አንተም “ለንባብና ለትምህርት ውጤታማነት ጫት መቃም ጥሩ ነው” የሚል የጓደኞችህ አሉታዊ ግፊት ለዚህ እንዳበቃህ ገልጸህልናል፡፡ ብዙ ወንድሞቻችንና እኅቶቻችን እንዳንተው ተታለው በሱስ የተያዙና መውጣት አቅቷቸው የተቸገሩ ሆነው ይታያሉ፡፡ ምንም እንኳ ብዙ ምክንያቶች ቢኖሩትም የአንበሳውን ድርሻ የሚወስደው የራሳችን ስንፍና መሆኑን መዘንጋት የለብህም፡፡

፪. የሚያስከትለውን ጉዳት ማጤን

በጠቀስናቸውና በመሳሰሉት ሱሶች መያዝ ምንም ዓይነት ጥቅም የሌላቸው ከመሆኑም በላይ ልዩ ልዩ ጉዳቶችን በሰዎች ላይ በማድረስ ይታወቃሉ፡፡ አካላዊ ጉዳትን ለምሳሌ ያህል ብንመለከት፡- የጥርስና የንግግር አካላት በሽታን፣ የካንሰር በሽታን፣ በግብረ ሥጋ ግንኙነት የሚተላለፉ ኤች አይ ቪ እና የመሳሰሉት ተላላፊ በሽታዎችን የመሳሰሉትን መጥቀስ ይቻላል፡፡ የሥነ ልቡናዊ አለመረጋጋትና ራስን መጣል፣ ራስን ከሌሎች ማግለልና ራስንም ወደ ማጥፋት መድረስ፣ በማኅበረሰቡ መገለል፣ ሱስን ለማርካት ሲባል የገንዘብ ፍለጋ ልዩ ልዩ ወንጀሎችን መፈጸምና በወንጀሉ የመጠየቅ አደጋዎች ሁሉ ሊታሰቡ የሚገባቸው  ከሱስ ጋር የሚያያዙ ችግሮች ናቸው፡፡ ውጤታቸውም ክቡር የሆነውን የሰው ልጅ የሁለት ዓለም ስደተኛ ማድረግ ነው፡፡ ውድ ወንድማችን የአንተም ጥያቄ ከእነዚህ ሱሶች ጉዳትና ውጤት ለመዳን በመሆኑ ከዚህ በመቀጠል ደግሞ ልትወስዳቸው የሚገቡ ርምጃዎችን በአጭሩ እናቀርብ፡፡

ይቆየን

Y

በሰሜን አሜሪካ አዲስ ግቢ ጉባኤ ተመሠረተ

በውጪ ዓለም ላለችው ቤተ ክርስቲያን ተረካቢ ለማፍራት እንዲሁም የከፍተኛ ትምህርት ተቋም ተማሪዎች መንፈሳዊ ሕይወታቸውንና ክርስትናቸውን ጠብቀው እንዲቆዩ ግቢ ጉባኤያትን ማጠናከር አስፈላጊ በመሆኑ በሰሜን አሜሪካ ማኅበረ ቅዱሳን የሳን ሆዜ ንዑስ ማእከል የቤይ ኤሪያ ግቢ ጉባኤ ምሥረታ ተካሂዷል፡፡

ግቢ ጉባኤው ጠንካራ ሆኖ እንዲቀጥልም ውይይት የተካሄደ ሲሆን በግቢ ጉባኤ ለመሳተፍ በተማሪዎቹ ዘንድ ከፍተኛ ፍላጎት መኖሩን በመግለጽ ለተግባራዊነቱ የሁሉም ኦርቶዶክሳውያን ድርሻ መሆኑም ተጠቁሟል፡፡

በውይይት መርሐ ግብሩም “ግቢ ጉባኤያት ለቤተ ክርስቲያን የሚጠቅሙ፣ ነገ በአገልግሎት የሚተጉ፣ በምድረ አሜሪካ ቁልፍና ታዋቂ ካምፓኒዎች ውስጥ ተቀጥረው ቤተ ክርስቲያንን የሚደግፉ በሥነ ምግባር የታነጹ ኦርቶዶክስ ባለሙያዎችን የሚያፈራ ኦርቶዶክሳዊ ተቋም ነው” ተብሏል፡፡

በተለይም በቤይ ኤርያ እና አካባቢው የሚኖሩ ወላጆች ለከፍተኛ ትምህርት ተቋም ተማሪዎቻቸው ጊዜ ሰጥተው በግቢ ጉባኤያት አገልግሎት ላይ ንቁ ተሳትፎ እንዲያደርጉ እና በቀጣይነትም ከዚህ በተሻለ ትጋት እንዲሳተፉ መምህራኑ አደራ ብለዋል፡፡

ምንጭ፡- መረጃው የማኅበረ ቅዱሳን አሜሪካ ማእከል ሚዲያ ክፍል ነው፡፡

“ትዕግሥትን ልበሱት” (ቆላ. ፫፥፲፪)

ጥቅምት ፲፱ ቀን ፳፻፲፯ ዓ.ም

በእንዳለ ደምስስ                                            

ትዕግሥት በክርስትና ሕይወት ውስጥ ሰፊ ድርሻ አለው፡፡ መታገሥን ገንዘብ ማድረግ ከክርስቲያን የሚጠበቅና የበጎ ምግባር መገለጫ ከሆኑት የመንፈስ ፍሬዎች አንዱ ነው፡፡ “የመንፈስ ፍሬ ግን ፍቅር፣ ደስታ፣ ሰላም፣ ትዕግሥት፣ ምጽዋት፣ ቸርነት፣ እምነት፣ ገርነት፣ ንጽሕና ነው፡፡” እንዲል (ገላ. ፭፥፳፪) ትዕግሥት በማድረግ ውስጥ መከራ እንዳለ መረዳት ያስፈልጋል፡፡ መከራ ያስተምርሃል፣ መከራ ይመክርሃል፣ መከራ ያንጽሃል፤ በዚህ ደግሞ ትዕግሥትን ትማራለህ፡፡ “መከራ በእኛ ላይ ትዕግሥትን እንደሚያመጣ እናውቃለንና፡፡ ትዕግሥትም መከራ ነው፤ በመከራም ተስፋ ይገናል፡፡” (ሮሜ. ፭፥፫-፭) በማለት ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ እንዳስተማረን፡፡

በተለይ በወጣትነት ዕድሜ የእሳትነት ሕይወት የሚያይልበት ጊዜ በመሆኑ ወጣቶች ብዙ መሥራት፣ እግዚአብሔርን በትጋት ማገልግል በሚችሉበት ዕድሜ ለስሜታቸው ተገዥ በመሆን ለሱስና ለተለያዩ ክፉ ምግባራት ሲጋለጡ እንመለከታለን፡፡ ለውሳኔ መቸኮል፣ ክፉ ወይም ደጉን ሳይለዩ ሌሎች ስላደረጉ ብቻ ማድረግን፣ ሁሉንም ነገር ለመሞከር መጣደፍ፣ … በወጣትነት ዘመን ጎልተው የሚታዩ ጸባያት ናቸው፡፡ ነገር ግን ጠቢቡ ሰሎሞን “የጭንቀት ቀን ሳይመጣ በጉብዝናህ ወራት ፈጣሪህን ዐስብ” እንዳለው (መክ. ፲፪፥፩) ወጣትነትን ለአገልግሎት በመስጠት ከእግዚአብሔር ጋር ያላቸውን አንድነት ሊያጠነክሩ ይገባል፡፡

በዚህ ጉዞ ውስጥ ሲያልፉም በርካታ ውጣ ውረዶች ሊገጥሟቸው እንደሚችሉ በማሰብ ራሳቸውን በማጽናት በትዕግሥትና በጥበብ መሻገር ያስፈልጋል፡፡ መንገዱ እንቅፋት የሚበዛበት፣ መውጣት መውረድ ያለበት ቢሆንም እግዚአብሔርን ተስፋ በማድረግና ትዕግሥትን በመላበስ ወደ አሰቡበት ለመድረስ መትጋት ይገባል፡፡ ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ ለቆላስይስ ሰዎች በላከው መልእክቱ ይህንን አስመልክቶ ሲገልጥ እንዲህ ይላል፡- “እንግዲህ እግዚአብሔር እንደመረጣቸው ቅዱሳንና ወዳጆች ምሕረትንና ርኅራኄን፣ ቸርነትና ትሕትና፣ የውሃትንና ትዕግሥትን ልበሱት” እንዳለ (ቆላ. ፫፥፲፪)፡፡

ወጣቶች ያሰቡበት ለመድረስ በትዕግሥት ካልተጓዙ ዓለም ጉዞአቸውን ለማደናቀፍ በሯን ከፍታ፣ እጆቿን ዘርግታ ለመስተናገድ ትጠብቃቸዋለች፡፡ አንዱን አለፍኩ ሲሉ ሌላው እየተተካ ቢቸገሩ እንኳ የዓለምን ወጥመድ ሰባብረው ማለፍ የሚችሉት ትዕግሥትን በመላበስ ነው፡፡ ብዙ ጊዜ የሚታየው ግን እኔ ባሰብኩት ጊዜና ሰዓት ለምን አልተፈጸመልኝም በማለት የእግዚአብሔርን ጊዜ ከመጠበቅ ይልቅ በቀላሉ ተሸንፈው ሲወድቁ ማየት ነው፡፡ ለዚህም ነው ሐዋርያው “ዳተኞች እንዳትሆኑ በሃማኖትና በትዕግሥት ተስፋቸውን የወረሱትን ሰዎች ምሰሉአቸው” እያለ የሚመክረን፡፡ (ዕብ. ፮፥፲፩-፲፪)

ቅዱስ ዮሴፍ ወደ ምድረ ግብፅ በወንድሞቹ ከተሸጠ በኋላ በትዕግሥት እግዚአብሔርን ተስፋ በማድረግ ተጓዘ፡፡ በግብፅ በፈርዖን ሚስት ጲጥፋራ በተፈተነ ሰዓትም በእግዚአብሔር ፊት ኃጢአትን እንዳይሠራ ታገሰ፤ መታገሱም በፈርዖን ቤት በአለቅነት እስከ መሾም አደረሰው፡፡ ሊቀ ነቢያት ሙሴም በፈርዖን ቤት የፈርዖን ልጅ ከመባል ይልቅ ከወገኖቹ ጋር መከራ መቀበልን መርጧል፡፡ በኋላም እስራኤላውያን ወገኖቹን ከግብፅ ምድር ወደ ተስፋይቱ ምድር ማርና ወተት ወደምታፈልቀው ምድረ ርስት ይመራ ዘንድ በእግዚአብሔር እስከ መመረጥ አደረሰው፡፡ ይህም በትዕግሥት የተገኘ በረከት ነውና ወጣቶች ትዕግሥትን ገንዘብ በማድረግ እግዚአብሔርን በመመካትና እንደ ቃሉም በመጓዝ መንገዳቸውን ሊያቀኑ ይገባል፡፡ “ትዕግሥት መራራ ናት፤ ፍሬዋ ግን ጣፋጭ ናት” እንዲሉ፡፡ (

ወስብሐት ለእግዚአብሔር

መልእክተ_ቅዱስ_ፓትርያርክ

፳፻፲፯ ዓ.ም የጥቅምቱ የቅዱስ ሲኖዶስ ምልአተ ጉባኤ ተጀመረ፡፡ ምልአተ ጉባኤው ጥቅምት ፲፩ ፳፻፲፯ ዓ.ም በዋዜማው በጸሎት የተጀመረ ሲሆን ጥቅምት ፲፪ ቀን ፳፻፲፯ ዓ.ም ቅዱስ ፓትርያርኩ ባስተላለፉት መልእክት ቀጥሏል፡፡ ቅዱስነታቸው ያስተላለፉትን መልእክት ቀጥለን አቅርበነዋል፡፡   

መልእክተ_ቅዱስ_ፓትርያርክ

በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን!

ብፁዕ አቡነ አብርሃም የመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ቤተ ክህነት ዋና ሥራ አስኪያጅ፣ የባሕር ዳርና የሰሜን ጐጃም አህጉረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ፤

ብፁዕ አቡነ ሄኖክ የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ፤

ብፁዓን አበው ሊቃነ ጳጳሳት የቅዱስ ሲኖዶስ አባላት፤

ዓመቱን ጠብቆ ስለ አጠቃላይ ተልእኮአችን ለመወያየት በዚህ ጉባኤ የሰበሰበን አምላካችን ስሙ የተመሰገነ ይሁን፤

“ወይእዜኒ ግብኡ ኀበ ኖላዊሃ ወዓቃቢሃ ለነፍስክሙ፤ አሁንም ወደ እረኛችሁና ወደ ነፍሳችሁ ጠባቂ ተመለሱ” (1 ጴጥ 2÷!5)

ሁሉን የሚችል አምላካችን እግዚአብሔር በፍቅሩና በፍቅሩ መነሻነት ብቻ ፍጥረታትን በሙሉ እንደፈጠረ ቅዱስ መጽሐፍ ያስተምረናል፤ ከፈጠረም በኋላ የክብሩ ተሳታፊ እንዲሆኑ ወዶ ክብሩን አድሎአቸዋል፡፡ እግዚአብሔር ለፍጡራኑ ካደላቸው ነገሮች አንዱ በየዓይነታቸው ጠባቂና መሪ እያደረገ በፍጡራን ላይ ፍጡራንን መሾሙ ነው፤ ይህ ስጦታ በሰማይም ሆነ በምድር ላሉ ፍጥረታት የተሰጠ የሱታፌ መለኮት ስጦታ ነው፡፡

ይህም በመሆኑ ሁሉም ፍጡራን አራዊትም ሆኑ እንስሳት ይብዛም ይነስ ጠባቂና መሪ እንዳላቸው እናስተውላለን፤ በተለይም የፍጥረታት ቁንጮ የሆኑ መላእክትና ሰዎች መሪና ሹም እንዳሏቸው የማንክደው ሐቅ ነው፡፡ ቅዱስ መጽሐፍም ይህንን ደጋግሞ ያስረዳል፤ የእነዚህ ሁሉ ላዕላዊ ጠባቂና መሪ ደግሞ እግዚአብሔር ነው፤ እግዚአብሔር በፍጡራን ላይ ፍጡራንን ጠባቂዎች አድርጎ ሲሾም ፍጡራንን የክብሩ ተሳታፊ ለማድረግ እንጂ የእሱ ጥበቃ አንሶ ወይም ድጋፍ ሽቶ አይደለም፡፡ ስለሆነም ፍጹምና ላዕላዊ የሆነ ጥበቃው ሁሉንም ያካለለ ነውና ከእሱ ቊጥጥርና ጥበቃ ውጭ አንድም ነገር እንደሌለ የምንስተው አይደለም፡፡

ብፁዓን አበው ሊቃነ ጳጳሳት

የቅዱስ ሲኖዶስ አባላት!

በአምሳለ እግዚአብሔር በተፈጠረውና በክብር መልዕልተ ፍጡራን በሆነው ሰው ላይ በዚህ ዓለም የተሾሙ ሁለት አካላት አሉ፤ እነሱም የመንፈስና የዓለም መሪዎች ናቸው፡፡ በተለይም የመንፈስ መሪዎችና ጠባቂዎች የተባሉት በመንፈስ ቅዱስ ተሹመን በዚህ ክርስቶሳዊ ጉባኤ የተሰበሰብነው እኛ የቅዱስ ሲኖዶስ አባላት ነን፡፡

ይህ ጉባኤ በሀገር ውስጥና በውጭ ለሚገኙና በሚሊዮኖች ለሚቆጠሩ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ምእመናን መሪና ጠባቂ ነው፤ ከዚያም ባሻገር እንደ ቃሉ እስከ ዓለም ዳርቻ ድረስ ቃሉን በመስበክ ፍጥረተ ሰብእን በሙሉ የመጥራት ተልእኮ ለእኛ የተሰጠ የቤት ሥራ ነው፡፡ ከዚህ አኳያ የተሰጠን ኃላፊነት እጅግ በጣም ታላቅ እንደመሆኑ የሚጠበቅብን ውጤትም በዚያው ልክ ትልቅ ነው፤ ብዙ ከተሰጠው ብዙ ይፈለግበታል ያለው የጌታችን አስተምህሮም ይህንን ያስታውሰናል፡፡

ሁላችን እንደምንገነዘበው አሁን የምንገኝበት ዘመን የጸላኤ ሠናያት መንፈስ በእግዚአብሔር ሕዝብ ላይ ከምንም ጊዜ በበለጠ ጦሩን ሰብቆ የተነሣበት ጊዜ ነው፤ አሁን ያለው ዓለም በሀገራችንም ሆነ በሌላው ክፍለ ዓለም ላሉ ኦርቶዶክሳውያን ከባድ ፈተና ደቅኖብናል፡፡ ክፉው መንፈስ የሰውን አእምሮ በማዛባት ምእመናንን በቅዱስ መጽሐፍና በሕገ ተፈጥሮ ከተመደበላቸው የጋብቻ ሕግ በማስወጣት እንስሳት እንኳ የማይፈጽሙት ነውረ ኃጢአት እንዲፈጽሙ በመገፋፋት ላይ ይገኛል፡፡ በአማንያን ልጆቻችን ላይም በረቀቀ ስልት ግድያ፣ እገታ፣ አፈና፣ የመብት ተጽዕኖ እና አድልዎ በማድረግ እንደዚሁም በአስመሳይ ስብከትና አምልኮ ጣዖትን በማለማመድ ሕዝቡ ሳይገባውና ሳይጠነቀቅ ከእግዚአብሔር መንግሥት እንዲወጣ እያደረገ ነው፡፡

ብፁዓን አበው ሊቃነ ጳጳሳት

የቅዱስ ሲኖዶስ አባላት!

ክፉው መንፈስ በተራቀቀና በተራዘመ ስልት ሊውጠን በተነሣ ልክ እኛም ከእሱ እጥፍ በሆነ መለኮታዊ ኃይል ልንመክተው ካልቻልን በፈጣሪም ሆነ በትውልድ እንደዚሁም በታሪክ ፊት በኃላፊነት መጠየቃችን አይቀርም፡፡ መከላከል የምንችለውም ችግሩን በውል ከመረዳት አንሥቶ ሕዝቡን በደምብ በማስተማርና በመጠበቅ እንደዚሁም ለመሪነታችን ዕንቅፋት ከሚሆኑን ዓለማዊ ነገሮች ራሳችንን በማራቅ ነው፡፡ ሕዝቡም በዚህ ዙሪያ ሊያደምጠንና ሊከተለን የሚችለው መስለን ሳይሆን ሆነን ስንገኝለት ነው፡፡ ሕዝቡ ሊከተለን የሚችለው እሱን በብቃት ለመጠበቅ ዓቅሙም ተነሣሽነቱም ቁርጠኝነቱም እንዳለን ሲመለከት፣ እንደዚሁም ከዕለት ተዕለት ተግባራችንና አኗኗራችን የሚያየው ተጨባጭ እውነታ ኅሊናውን ሲረታ እንደሆነ አንርሳ፡፡

የምናስተምረው ሌላ የምንሠራው ሌላ ከሆነ ግን ከሕዝቡ አእምሮ መውጣታችን እንደማይቀር መገንዘብ አለብን፤ በመሆኑም በሰብእናችን፣ በአስተዳደራችን፣ በአመራራችንና በጥበቃችን ሁሉ እንደቃሉና እንደቃሉ ብቻ ለመፈጸም መትጋትና በቁርጥ መነሣት ጊዜው አሁን ነው እንላለን፡፡ ይህ ሲሆን በምእመናንና በእኛ መካከል ያለው ግንኙነት አስተማማኝና እንከን የለሽ ይሆናል፤ ይህ ከሆነ እውነትም የመሪነት፣ የእረኝነትና የመልካም ተምሳሌነት ኃላፊነታችንን በትክክል ተወጥተናል ማለት እንችላለን፡፡

ብፁዓን አበው ሊቃነ ጳጳሳት

የቅዱስ ሲኖዶስ አባላት!

የሰው ልጆች በዚህ ዓለም ሲኖሩ የተሟላ ሰላምና ጣዕመ ሕይወት ሊኖራቸው የሚችለው በመንፈሳዊ ኑሮአቸው የተሻለ ነገር ስላገኙ ብቻ አይደለም፡፡ ሰዎች ከሥጋዊ ክዋኔም ጭምር የተፈጠሩ እንጂ እንደ መላእክት ሥጋ የሌላቸው መንፈስ ስላይደሉ ለኑሮአቸውና ለሥጋዊ ክዋኔአቸው የሚሆን ነገር ያስፈልጋቸዋል፡፡ በዚህም ዓለማዊው አስተዳደር የተመቻቸ መደላድል ሊፈጥርላቸው ግድ ነው፤ ዓለማዊው አስተዳደርም የመለኮትን ተልእኮ ለመፈጸም የተሾመ ሹመኛ እንደመሆኑ የእግዚአብሔርን ሕዝብ በትክልል መምራት ይጠበቅበታል፡፡ ምንም ቢሆን የተቀበለው ኃላፊነት የእግዚአብሔር ነውና በሚሠራው ሁሉ በሿሚው አምላክ ከመጠየቅ አያመልጥም፡፡

እኛም በዚህ ዓለም የእግዚአብሔር ወኪሎች ስለሆንን ቢሰሙንም ባይሰሙንም ዓለማውያን ሹማምንትን የማስተማርና የመምከር ኃላፊነት አለብን፡፡ ይህ የሁለታችን ኃላፊነት እንደ እግዚብሔር ፈቃድ ስንፈጽም የሕዝብ ሰላምና በረከት፣ ፍቅና አንድነት፣ ዕድገትና ልማት በአስተማማኝ ሁኔታ ይረጋገጣል፡፡ ነገር ግን በአሁኑ ጊዜ በሀገራችንም ሆነ በአካባቢያችን እየሆነ ያለው ይህ አይደለም፤ አለመግባባት በዝቶአል፣ ማኵረፍና መቀያየም ሰፍቶአል፤ ነገሩ ሁሉ ግራ የሚያጋባና የተመሰቃቀለ ሆኖ ይታያል፡፡ ችግሩ ከሕዝብ አልፎ የአምልኮ ስፍራዎችንና የአምልኮው ፈጻሚዎችን ዒላማ ያደረገ እግዚአብሔርን መዳፈር እየተለመደ መጥቶአል፤ ይህ ለአንድ ሀገር ወይም ሕዝብ የውድቀት ምክንያት ከሚሆን በቀር ከቶውኑም የዕድገት ምልክት ሊሆን አይችልም፡፡

ከሁሉም በላይ የሚያሳዝነው ደግሞ ይህ ክፉ ድርጊት እየተፈጸመ ያለው በእኛው ልጆች በኢትዮጵያውያን መሆኑ ነው፤ ስለሆነም በከተማም፣ በጫካም፣ በገጠርም በየትኛውም ስፍራ የምትገኙ ልጆቻችን ምንም ይሁን ምን ሀገርንና ሕዝብን ከመጉዳት ተቆጠቡ፡፡ በተለይም ከቤተ ክርስቲያንና ከሀገር እንደዚሁም ሕዝቡን ከሚያገለግሉ ካህናትና ሲቪል ሰራተኞች እባካችሁ እጃችሁን አንሡ፤ ቤተ ክርስቲያን እኮ የእናንተና የሕዝቡ ሁሉ እናት ናት፤ በእናታችሁ ላይ መጨከንን እንዴት ተለማመዳችሁት? አሁንም ንስሓ ግቡ ያለፈው ይበቃል፡፡ ልብ በሉ ከእግዚአብሔር ጋር መጣላት አይበጅም፤ ሰውን መጉዳትና እግዚአብሔርን መዳፈር አቁሙ፤ የእግዚአብሔር ገንዘብ የሆነውን ሥርዓተ አምልኮም ያለቦታው አታውሉ፤ ጥያቄአችሁን በሰላማዊ መንገድ ለመፍታት ዕድል ስጡ፡፡ በእግዚአብሔር ስም ለመላው ኢትዮጵያውያን ወገኖቻችንና ልጆቻችን የምናስተላፈው ወቅታዊ መልእክታችን ይህ ነው፡፡

በመጨረሻም

በቅድስት ቤተ ክርስቲያናችን ሁለንተናዊ አገልግሎትና የሥራ አፈጻጸም ላይ ለመምከርና ለመወሰን ኃላፊነት ያለው ቅዱስ ሲኖዶስ በዛሬው ዕለት መደበኛና ዓመታዊ ጉባኤውን የጀመረ መሆኑን ለሕዝበ ክርስቲያኑ እናበሥራለን፡፡

እግዚአብሔር ጉባኤያችንን ይባርክ!

እግዚአብሔር አምላክ ኢትዮጵያንና ሕዝቦቿን ይባርክ!

ወስብሐት ለእግዚአብሔር አሜን፡፡

አባ ማትያስ ቀዳማዊ

ፓትርያርክ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ

ሊቀ ጳጳስ ዘአኵስም

ወዕጨጌ ዘመንበረ ተክለ ሃይማኖት

ጥቅምት ፲፪ ቀን ፳፻፲፯ ..

አዲስ አበባ፣ ኢትዮጵያ

የብፁዕ ወቅዱስነታቸው በረከት አይለየን!

የ፳፻፲፯ ዓ.ም ፵፫ኛው አጠቃላይ የሰበካ መንፈሳዊ ዓለም አቀፍ መደበኛ ጉባኤ የአቋም መግለጫ በማውጣት ተጠናቀቀ

የ፳፻፲፯ ዓ.ም ፵፫ኛው አጠቃላይ የሰበካ መንፈሳዊ ዓለም አቀፍ መደበኛ ጉባኤ የአቋም መግለጫ በማውጣት ተጠናቀቀ

፵፫ኛው አጠቃላይ የሰበካ መንፈሳዊ ዓለም አቀፍ መደበኛ ጉባኤ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ጠቅላይ ቤተ ከህነት አዲሱ አዳራሽ ከጥቅምት ፮ – ፲ ቀን ፳፻፲፯ ዓ.ም በማካሄድ ፳ ዋና ዋና ነጥቦችን ያካተተ የአቋም መግለጫ በማውጣት ተጠናቀቀ፡፡ የአቋም መግለጫውን እንደሚከተለው አቅርበነዋል፡፡

በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የ፵፫ኛው አጠቃላይ የሰበካ መንፈሳዊ ዓለም አቀፍ መደበኛ ጉባኤ የአቋም መግለጫ

“ትውልደ ትውልድ ይንእዱ ምግባሪከ ወይዜንዉ ኃይለከ፤ የልጅ ልጅ ሥራህን ይናገራሉ፤ ያመሰግናሉ፣ ከሃሊነትህን ይናገራሉ ያስተምራሉ፡፡” (መዝ. ፻፵፬፥፬)

፩. በጉባኤው መክፈቻ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ቀዳማዊ ፓትርያርክ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም ወእጨጌ ዘመንበረ ተክለ ሃይማኖት ያስተላለፉፉልንን ቃለ ምዕዳንና ቃለ ቡራኬ ጉባኤው በሙሉ ድምጽ ተቀብሎታል፣ ለተግባራዊነቱ ቃል ይገባል፡፡

፪. ብፁዕ አቡነ አብርሃም የጠቅላይ ቤተ ክህነት ዋና ሥራ አስኪያጅ፣ የባሕር ዳርና የሰሜን ጎጃም አህጉረ ሰብከት ሊቀ ጳጳስ ያስተላለፉልንን አባታዊ መልእክት ጉባኤው በሙሉ ድምጽ ተቀብሎ ተግባራዊ ለማድረግ ቃል እንገባለን፡፡

፫. በብዙ የሀገራችን ክፍል ባለው የሰላም እጦት የተፈጠሩት ዘርፈ ብዙ ችግሮች ምክንያት የካህናት፣ የመነኮሳትና የምእመናን ሞትና ስደት በጥብቅ እያወገዝን በዚህ ታሪክ የማይረሳው በምድር ወንጀል፣ በመንፈሳዊው ዓለምና በሰማይ ኃጥያት የሆነ እኩይ ተግባር የተሰማራችሁ ሁሉ ወደ ርኃራኄ ልብ እንድተመለሱ ጉባኤው በአጽንኦት ጥሪውን ያስተላልፋል፡፡

፬. የሰላም ዕጦት ጉዳይ ምንም እንኳ ዓለም አቀፍ ቢሆንም ሀገራችንም በተከሰተው ግጭትና ጦርነት ምክንያት ሰላም ካጣች ሰንብታለች፣ ስለሆነም ቅዱስ ሲኖዶስ በዓለም የሚደነቅ፣ ለሀገር ተገን የሚሆን አስደነቂ ውሳኔ እንደሚወስን ተስፋችን ጽኑ ነው፣ ጸሎታችንም ነው፤ የአገልጋዮች እንባ የሚታበስበት፣ ለነገ ታሪክ የትውልድ ተወቃሽ ከመሆን ይልቅ፤ የሰላምና እርቅ ምሳሌ የምንሆንበት ከፍተኛ የሰላም ሥራ ልዩ የሆነ የሰላም ኮሚቴ ተቋቁሞ ዘላቂ ሰላምን ለሀገርና ለቤተ ክርስቲያን የሚያመጣ ሥራ እንዲሠራ ጉባኤው ያሳስባል፡፡

፭. የዚህን ዓለም ተድላ ንቀው፣ ዳዋ ለብሰው ጤዛ ልሰው በገዳም ተወስነው ድምጸ አራዊቱን ግርማ ሌሊቱን ታግሰው ለመላው የሰው ዘር የሚጸልዩ ይህን ይደግፋሉ ያንን ይቃወማሉ የማይባሉ ገዳማውያን መነኮሳት ከየበዓታቸው ተጎትተው ወጥተው የተገደሉበት ሁኔታ በሀገራችን መከሰቱ ጉባኤውን እጅግ አሳዝኖታል፤ ይህ ጉዳይ ቀጣይነቱ እየታየ ስለሆነ የሚመለከታቸው ሁሉ ተገቢውን የሕግ ሥራ በመሥራት የሰው ልጅ ከአምላክ የተሰጠውን የመኖር መብት፣ የእምነት ነፃነት፣ የመዘዋር ተፈጥሯዊና ሰብዓዊ መብት በሀገራች እንዲከበር ያሳስባል፡፡

፮. በታሪካችን ያላየነው ከአባቶቻችን ያልሰማነው በመጻሕፍት ያላነበብነው ከኢትዮጵያ ባሕልና ሥነ ልቡና ውጪ በሆነ መንገድ ሰዎችን ለገንዘብ ሲባል ማገት በተለይም ፊትና ኋላ፣ ግራና ቀኝ፣ እሳትና ውኃ ያለዩ ሕጻናት በአሰቃቂ ሁኔታ መገደላቸው፣ ወጣቶችና አረጋውያን ሳይቀር እያተገቱ የሚሰቃዩበትና የሚደፈሩበት ሁኔታ የገጠመንን ፈተና ክብደቱን የሚያሳይ መሆኑ ይህ ጉዳይ ልዩ ትኩረት ተሰጥቶት መፍትሔ እንዲበጅለት ጉባኤው ጥሪውን ያቀርባል፡፡

፯. ጥላቻና የጥፋት ቅስቀሳዎች፣ በዜጎች መካከል አለመተማመንና መለያየት፣ ለሀገር አንድነትና የሕዝብ አብሮነት ጠንቅ፣ ለወደፊቱ አስጊ የሆኑ እንቅስቃሴዎች የበዙበት፣ የትውልዱ የወደፊት በሰላምና በተረጋጋ ሁኔታ የመኖር ዋስትና እየጠፋ፣ በርካታ ወጣቶች በስደትና በመፈናቀል ላይ ያሉበት ሁኔታ በመኖሩ የጥላች ንግግር፣ ዘለፋና ያልተገባ ትችትና መናናቅ ማንንም የማያንጽ ክፉ ትምህርት፣ ለሀገርም፣ ለሕዝብም የማይጠቅም ሁሉንም የሚያጠፋ ስለሆነ በእንዲህ ያለ ተግባር መገናኛ ብዙኃን በመጠቀም የተሰማራችሁ፣ ሁሉ በሚያፋቅርና በሚያዋድድ ተግባር እንድትሰማሩ ጉባኤው ጥሪውን ያቀርባል፣ ቅዱስ ሲኖዶስም ለዚሁ ትኩረት ሰጥቶ መመሪያና ውሳኔ ያወጣ ዘንድ በአጽንኦት እንጠይቃለን፡፡

፰. በፍትሕ መንፈሳዊ አንቀጽ ፳ በእንተ ሰማዕታት የጌታችንን ትምህርት መሠረት በማድረግ በተሠራው ቀኖና ካህናትና ምእመናን ሰማዕትነትን የተቀበሉበትን ቀን መዘከርና ማክበር፣ የከበረ አጽማቸውን በቅጽረ ቤተ ክርስቲያን በክብር ማስቀመጥ፣ ቤተሰቦቻቸውንና በእነሱ ሥራ ይተዳደሩ የነበሩ የሰማዕታት ቤተሰብ በሚል መርዳት የተደነገገ ቀኖና ነው፤ ይህን በማድረግ የሰማዕትነት ዋጋን እናገኛለን፣ ቤተ ክርስቲያነን እናጸናለን፤ በዚህ ቀኖና መሠረትና ከሰብዓዊ ርኅራሄ በመነሣት በሰማዕትነት የተለዩን ወገኖች መታሰቢያቸው እንዲደረግ፣ ቤተሰቦቻቸውና ጉዳተኞችን ወላጆቻውን ያጡ የካህነትና የምእመንና ጨቅላ ሕጻናትና ያልደረሱ ልጆች፣ ያለጧሪ የቀሩ አረጋውያን የቤተ ክርስቲያንን እንክብካቤ በጥብቅ ይፈልጋሉ፤ ለዚህ መፍትሔ እንዲሆን በውጭና በሀገር ውስጥ ያሉ አህጉረ ሰብከት ያካተተ አስቸኳይ ዓለም አቀፍ ግብረ ኃይል እንዲቋቋም ቅዱስ ሲኖዶስ ውሳኔ እንዲሰጥበት እያሳሰብን ለተግባራዊነቱም ሁላችንም ቃል እንገባለን፡፡

፱. በአንዳንድ አካባቢዎች ሕግንና የአምልኮ ነፃነት ሰብዓዊ መብትን በመጣስ የመስቀል ደመራና የባሕረ ጥምቀት ቦታ መወሰድ ሃይማኖታዊ አለባበስና መስቀል መያዝን በመከልከል የአንገት ማዕተብን መበጠስ፣ በኦርቶዶክሳውያን ላይ እንግልትና ወከባ መፍጠር አሳዛኝ በመሆኑ ድገርጊቱን አጥብቀን እየተቃወመን በቅዱስ ሲኖዶስ ቀርቦ ውይይት እንዲደረግበት ጉባኤው ያሳስባል፡፡

፲. ቤተ ክርስቲያን እንኳንስ ተናግራ ሰማች ሲባል የሚያስደነግጥ ግርማና መታፈር፣ መከበርና መወደድ የነበራት በመሠረተችው ሀገር የምትሳደድበት፣ የመሪዎቿ አባቶች ጥሪ የማይከበርበት፣ የሰላም ጥሪ ድምጽዋ የማይሰመባት፣ ምክንያቱ ምን እንደሆነ በመፈተሸ ክብርና ልዕልናዋ እንዲመለስ በቅዱስ ሲኖዶስ ቀርቦ ውይይትና ጥልቅ ምክክር እንዲደረግ መፍትሔም እንዲፈለግለት ጉባኤ ያሳስባል፡፡

፲፩. ሙስና፣ ዘረኝነት፣ ጎሠኝነት፣ ቡድነኝነት፣ አድሎዓዊነትና ግለኝት በተመለከተ በጋራ በአንድ ድምጽ በመነሣት ይህንን ክብረ ነክና አጋላጭ፣ ለቤተ ክርስቲያን እድገትና ለሐዋርያዊ ተልእኮ እንቅፋት፣ የቤተ ክርስቲያን ማንነት ለሌላቸው ግለሰቦች መደበቂያ፣ በጥቂት ግለሰቦች በደልና ጥፋት በንጽሕና በቅድስና የሚያገለግሉ፣ ካህናትንና ሠራተኞችን የሚያሳፍሩ፣ ምእመናንን የሚያሸማቅቁ በመሆናቸው እነዚህን ክፉ ደዌያት ስም አጠራራቸውን ከቤተ ክርስቲያን አስተዳደር ለማስወገድ ቅዱስ ሲኖዶስ፣ በጥናትና በቁርጠኝነት ላይ የተመሠረተ፣ የጥፋት በራቸውን በዘላቂነት የሚዘጋ ሥልት እንዲቀይስ ጉባኤው ያሳስባል፡፡

፲፪. በአዲስ አበባ የኮሪደር ልማት እስከ አሁን ቤተ ክርስቲያን በፈረሱባት ሕንፃዎችና ቤቶች ምትክ ቦታ በመስጠት ጉዳቷን ለመቀነሰ የተደረገውን ጥረት ጉባኤው እያደነቀ፤ በተሰጡት ይዞታዎች ላይ በአጭር ጊዜ ግንባታውን በማካሄድ የአባቶችቻንን አሻራ መልሶ በመትከል፣ ይዞታውን ማስከበርና የተቋረጠውን ገቢ ማስቀጠል እንዲቻል ብርቱ ጥረት እንዲደረግ ጉባኤው እያሳሰበ፤ የኮሪደር ልማት የተባለው ጉዳይ በሌሎች የክልል ከተሞችም እየተስፋፋ ስለሆነ በቀጣይ ለሚነሡ የይዞታ ጥያቄዎች ለሚከሰቱ ችግሮች ከወዲሁ ዝግጅት እንዲደረግ፡፡

፲፫. አዳዲስ አማኞችን አሳምኖ ለሥላሴ ልጅነት ማብቃት፣ የአዳዲስ አብያተ ክርስቲያናት መተከል፣ መታነጽና መባረክ የታየው ስብከተ ወንጌልና ሐዋርያዊ ተልእኮ እመርታ ሁሉን ያስደሰተ በመሆኑ ከዚህ በበለጠ አጠናክረን ለመሥራት ቃል እንገባን፡፡

፲፬. የቅዱስ ባኮስ የቅድስና ዕውቅና ቤተ ክርስቲያን በታሪኳ ስትዘግበው የቆየ ቢሆንም ጽላት ተቀርፆ እንዲከበር መደረጉ አስደሳች ሲሆን ለሀገር በረከት፣ ለትውልድ የመንፈሳዊ ሕይወት አርአያ፣ ለቅድስና ፍኖት የሆኑ ነገርግን የማይታወቁ የሌሎች ኢትዮጵያውያንን ቅዱሳን ታሪክና ገድል በማጥናት እንዲዘከሩ እንዲደረግ ጉባኤው ያሳስባል፡፡

፲፭. በቅዱስ ሲኖዶስ ውሳኔ የተከፈቱ መንፈሳውያን ኮሌጆችና የካህናት ማሠልጠኛዎችም በአጥጋቢ ሁኔታ ሥራ መጀመራቸው፣ በዚህ ዘርፍ በእጥፍ እየጨመረ የመጣው ዕድገትና ውጤት ጉባኤው ያደነቀ ሲሆን ወደ ሥራ ለመግባት በሂደት ላይ ያሉት በርካታ መንፈሳዊ ኮሌጆች እየተስፋፉ ያሉ የአብነት ትምህርት ቤቶች፣ ዘመናዊ የትምህርት ተቋማት በአጠቃላይ ሁሉም ትምህርትን የሚመለከት ጉዳይ በትምህርት ኮሚሽን ተቋቁሞ ጥናት በማድረግ እንዲስፋፉ ጉባኤው ያሳስባል፡፡

፲፮. በሰላም መታጣትና በቀኖና ጥሰት ምክንያት መላው ወለጋ አህጉረ ስብከት ለበርካታ ወራት ከማእከሉ ጋር ያለው ግንኙነት ተቋርጦ ከቆየ በኋላ በቅርቡ በሀገረ ሰብከቱ ሊቀ ጳጳስ ወደ መዋቅር መመለሳቸው ጉባኤውን በእጅጉ አስደስቷል፤ ስለሆነም ቀሪ ሥራዎች ተጠናቀው የቤተ ክርስቲያን መዋቅር እንዲጠበቅ፣ በሌሎችም አካባቢዎች ለተፈጠሩት የመዋቅር ጥሰቶች ቀኖናዊ መፍትሔ እንዲበጅለት ጉባኤ ያሳስባል፡፡

፲፯. ሐዋርያዊትና የክርስቶስ አገልጋይ የሆነች ቤተ ክርስቲያን ቋንቋን በማክበር ታገለግልበታለች እንጅ በቋንቋም አትገደብም፤ ስለዚህ በልዩ ልዩ ቋንቋዎች ሐዋርያዊ ተልእኮ መፈጸሟ እንደተጠበቀ ሆኖ ለወደፊት የሁሉም መዓረገ ክህነት ሢመት፣ በየደረጃው ያሉ የአስተዳደር ሥራ የኀላፊነት ምደባዎች፣ መሠረት እምነትን፣ ቀኖና ቤተክርስቲያንን፣ ዕውቀትና ሙያዊ ብቃትን ብቻ መሠረት ያደረገ ይሆን ዘንድ ጉባኤው በጥብቅ ያሳስባል፡፡

፲፰. ሰበካ ጉባኤን ማጠናከር፣ ሰንበት ትምህርት ቤትን ማደራጀት፣ አብነት ትምህርት ቤቶች ማጎልበትና ማስፋፋት፣ ሕጎችና ደንቦችን በማዘጋጀት የተደረገውን ጥረት የሚያስመሰግን ሆኖ አሁን ወቅቱን የጠበቁ ሕጎችና ደንቦችን በማውጣት ሁሉም እንዲሠራበት ማድረግን፣ መልካም አስተዳደርን ማስፈን፣ የራስ አገዝ ልማትን ማሳደግና በገቢ ራስን መቻል፣ በጸደቀው የዐሥር ዓመቱ መሪ ዕቅድ መሥራት የቤተ ክርስቲያናችን ዓይነተኛ ተልእኮ በመሆኑ በሚሰጠው መመሪያ መሠረት ለመፈጸም ቃል እንገባለን፡፡

፲፱. የቤተ ክርስቲያናችን የውጭ ሀገር አገልግሎት እየሰፋና እያደገ መምጣቱ በጉልህ የሚታይ ሲሆን ይህ እድገትና አደረጃጀት እንዲጠናከር፤ በተጨማሪም ቤተ ክርስቲያን በዓለም አቀፍ ደረጃ ያላት ተሳትፎ የበለጠ እንዲያድግ ትኩረት ተሰጥቶት እንዲሠራ ጉባኤው ያሳስባል፡፡

፳. ከውይይትና ከብፁዓን አበው መልእክቶች እንደተሰጠው መመሪያ የቤተ ክርስቲያንን ልዕልና ለመመለስ፣ ለሀገራንችን ሰላምና ደኅንነት ለሰው ልጆች ሁሉ መልካም ግንኙነት የጋራ ጸሎት በኅብረት ይደረግ ዘንድ ቅዱስ ሲኖዶስ መመሪያ እንዲሰጥበት ጉባኤ በአክብሮት ይጠይቃል፡፡

በመጨረሻም እስከ ዛሬ ስንሰበሰብበት ከነበረው መቃረቢያ አዳራሽ ወጥተን ይህ ዛሬ የተገኘንበት አዳራሽ በአጭር ጊዜ አሁን ባለበት ደረጃ እንዲህ ጸድቶና ተውቦ የ፵፫ኛውን አጠቃላይ ጉበኤ እንዲከናወንበት ብፁዕ ጠቅላይ ሥራ አስኪያጁ አመራር መስጠታቸው ቁርጠኝነት ካለ ብዙ መሥራት እንደሚቻል ያሳየ፣ የሥራ ክትትልና አፈጻጸም አድናቆታችንን በመግለጽ ሐዋርያው እግዚአብሔር ቢፈቅድና ብንኖርና እንዳለው የአዳራሹ ቀሪው ሥራ ተጠናቆ በቅርቡ እንደሚመረቅ ተስፋችንን እንገልጻለን፡፡

ይህ ጉባኤ በተሳካ ሁኔታ እንዲፈጸም ያደረጉ በቅዱስነታቸው አባታዊ ርእሰ መንበርነት፣ በብፁዕ ጠቅላይ ሥራ አስኪያጁ በሳልና የተረጋጋ አመራር ሁሉም መርሐ ግብሮች በተያዘላቸው ሰዓትና ጊዜ ተጠናቀው እንዲፈጸሙ የመሩንን አባቶች በረከታችሁ ይድረሰን እያልን፡፡

የጉባኤው ዋና አዘጋጅ የሰበካ ጉባኤ ማደራጃ መምሪያ ዋና ኀላፊና መላው ሠራተኞች፣ ሁሉም ተባባሪ አካላት በገንዘብም በጉልበትም ትብብር ያደረጉ ሁሉ በአጠቃላይ ጉባኤው አመስግኗል፡፡

ከሁሉም በላይ ለዚህ ለ፵፫ኛው አጠቃላይ የሰበካ መንፈሳዊ ዓለም አቀፍ መደበኛ ጉባኤ ያደረሰንና ያስፈጸመን የአባቶቻችን አምላክ ልዑል እግዚአሔር ምስጋና ይግባው አሜን፡፡ ሎቱ ስብሐት ወባርኰት ወጥበብ፣ ወአኰቴት፣ ወኃይል ወጽንዕ ለአምላክነ ለዓለመ ዓለም፤ አሜን!